ጳጉሜን 200ደሀነት በብዙ መልኩ የኢትዮጵያን ሕዝብ (ባለሥልጣኖቹንና ሀብታሞቹን ጨምሮ) እንደሚያሰቃየው ዓለም በሙሉ የሚያውቀው እውነት ነው፤ በአለፉት ዓርባ ዓመታት ውስጥ በደም ውስጥ እየዋኙ በተከታታይ የመጡት አገዛዞች የኢትዮጵያን ሕዝብ ማታለያ ያደረጉት ዘዴ ደሀነትን ማጥፋት ነው፤ መማር ለሚፈልግና መማር ለሚችል ሀብታሙን ማደህየት ብቻ ደሀውን እንደማይጠቅመው ደርግ አሳይቶአል፤ አሁን ደግሞ ሀብታሙን ማድለብ ብቻ ደሀውን እንደማይጠቅመው እያየን ነው፤ በአጼ ዘመን ደሀው ተረስቶ ነበር ለማለት ይቻላል፤ በደርግ ዘመን ደሀው የፖሊቲካ ሞተር ነው ተባለና ሀብታሙ የደሀው ኢላማ ሆነ፤ ደሀውና ሀብታሙ በቅራኔ ተጣመዱ፤ ደርግ በሀብት ልዩነት ላይ በተመሠረተ ፖሊቲካ ላይ ዙፋኑን ተክሎ ደሀውን ከሀብታሙ ጋር እያጋጨ ሥልጣኑን ለማጠናከርና ለማደላደል ሞከረ፤ ደርግ ከሶቭየት ኅብረት ጋር ስለገጠመ የምዕራቡን ዓለም፣ በተለይ አሜሪካን አስደነገጠ፤ የደነገጠው አሜሪካ ኢትዮጵያን በሱዳን በኩልም በሶማልያ በኩልም አቆሰለ፤ ወያኔንና ሻቢያንም አፈረጠመ፤ ደርግ በአንድ በኩል ከሶማልያጋር፤ በሌላ በኩል ከሻቢያና ከወያኔ ጋር፤ በአንድ በኩል ከኢሕአፓና ከመኤሶን ጋር፣ በሌላ በኩል ከኢዴኅ (የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት) ጋር ሲፋለም የአገሪቱን ሀብት አፈሰሰ፤ ጠላቱ ያደረገው ሀብታም ጨርሶ ሳይጠፋና ወዳጁ ያደረገው ደሀው ጉልበት ሳያገኝ ጦረኛ ነኝ ባዩ ደርግ በጦር ሜዳ ተሰናበተ፤ ደሀነትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ኑሮ እያመነመነ ቀጠለ።
ሻቢያና ወያኔ በአሜሪካ ድጋፍ ደርግን አወረዱት፤ ወያኔ በአሜሪካ ድጋፍ ኤርትራን አስገነጠለ፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ አዲስ ዓላማ ነደፈና ወያኔን የዓላማው ዋና መሣሪያ ለማድረግ አሠለጠነው፤ በዚህም ምክንያት ለደሀዎች የቆመና ግራ-ዘመም መስሎ የጀመረው ወያኔ ሀብታሙን የፖሊቲካ ሞተር አደረገው፤ ሀብት ማጋበስንም ዋናው ዓላማ አደረገ፤ወያኔ እንኳን በጠቅላላ የኢትዮጵያን ደሀ ሕዝብ፣ አንኳን በጠቅላላ የትግራይን ደሀ፣ ተራ የወያኔ አባሎቹንም ከደሀነት አላወጣቸውም፤ በእርግጥ ነባር የወያኔ አመራር አባል ሁሉ የናጠጡ ሀበታሞች ሆነዋል፤ በዚህም ምክንያት በአሜሪካ እርዳታ ወያኔ ሀብት የማይጠግቡ ሀብታሞች አለኝታ ሆነ፤ በዚህም ምክንያት በሙስና ውስጥ ተዘፈቀ፤ በዚህም ምክንያት ነቀዘ፤ በዚህም ምክንያት ተሰምቶ የማይታወቅ የአገር ሀብት ተዘረፈ፤ ወዘተ. … የኢትዮጵያ ደሀ ሕዝብ ይበልጥ እየመነመነ በመቀጠል ላይ ነው፤ ዝርፊያ የባለሥልጣኖች አመል በሆነ መጠን ደሀነት ይስፋፋል፤ ደሀነት በተስፋፋ መጠን ሥጋውን ግጦ ጨርሶ ከአጥንት ጋር እንደሚታገል ውሻ ባለሥልጣኖች ይበልጥ ይበልጥ በጭካኔ የደሀውን አጥንት ይግጣሉ።
ወያኔ በአሜሪካ ድጋፍ የጎሣ ልዩነትን እንደፖሊቲካ መሣሪያ ይዞ ተነሣ፤ በጎሣ ላይ የተመሠረተ አገዛዝ ላይ ዙፋኑን ተከለ፤ ደርግ በማርክሳዊ-ሌኒናዊ ፖሊቲካ በከፋፍለህ-ግዛ አመራር ለመጠቀም እንደሞከረ ወያኔም ያንኑ የከፋፍለህ-ግዛ አመራር በጎሣ ልዩነት ላይ መሥርቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስበርሱ እያጋጨ ሥልጣኑን ለማጠናከርና ለመደላደል በመሞከር ላይ ነው፤ ኮሚዩኒስቶች ካፒታሊዝም የሚባል ጭራቅ ስላላቸው ነፍጠኛው ወያኔም ‹‹ነፍጠኛ›› የሚባል ግዙፍ ጭራቅን ፈጠረና ጎሣዎችን ሁሉ የሚያስፈራራበት መሣሪያ ፈጠረ፤ በተለያዩ መንገዶች ጭራቁ የመራባት ኃይሉን ቀንሶ ቁጥሩ እያነሰ ሄደ ቢባልም ማስፈራሪያነቱ አልቀረም፤ ከሌሎች ታሪክና አስተሳሰብ የተገኘውን ካፒታሊዝም የሚባለውን የመተዳደሪያ ሥርዓት ሰው-በላ ከማለት ተነሥቶ የወያኔ የጎሣ ሥርዓት ተመሳሳይ የሚሆን ቃል ፈለገ፤ ጭራቅ ነፍጠኛ ተገኘ፤ የማሰብ ችጋር ሰውን ያውም ወገንን ወደጭራቅነት በመለወጥ የግል ቁስልን ማኅበራዊ አስመስሎ ለትውልድ ማስተላለፍ ነው፤ ከዚያም በላይ የማሰብ ችጋሩ የራሱን ነፍጠኛነት እንዳይገነዘብ ጋርዶበታል።
የጠና የማሰብ ችጋር የተውሶ ሱሰኛና ጥገኛ ያደርጋል፤ በኋላም ለኢትዮጵያ ሕዝብ አገራዊ መርሆዎች ሆነው የተወረወሩለት ‹‹ትራንስፎርሜሽን››፣ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚሉ ለሕዝቡ ባዕድ የሆኑ ማወናበጃዎች ናቸው፤ በአለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ውስጥ ካየናቸው የማሰብ ችጋር ምልክቶች ውስጥ የሽብርተኛነት ልምድ ያላቸው ሰዎች ስለሽብርተኛነት ምንም የማያውቁትን ሰዎች በአሸባሪነት በመወንጀልና በማሰር አዲስ አሜሪካንን የማታለያ ዘዴ መፍጠራቸው ነው፤ አገዛዙ የማሰብ ችጋር እንዳለበት ብዙ ሰዎች ለመቀበል ያዳግታቸው ነበር፤ የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል ድምጥማጡን ማጥፋት በኢትዮጵያ ደኅንነትም ሆነ በኢኮኖሚ ላይ ያለውን ከፍተኛ ተጽእኖ መገመት የሚችል ሰው አልተገኘም፤ ከሃምሳ ዓመታት በላይ የፈጀውን የኢትዮጵያን ዓየር ኃይል አፈራርሶ በጥቂት ወራት እንደገና በአጭር ጊዜና በአቋራጭ ለመገንባት የተሞከረው የጅል ሥራ የማሰብ ችጋርን በተጨባጭ አሳይቶአል፤ ዛሬ ደሞ አደባባይ የወጣ የማሰብ ችጋር ግዙፍ ማስረጃው በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ እየታየ ነው፤ ትናንት በብዙ ሚልዮን ብር ወጪ የተሠሩ መንገዶች ዛሬ እየተቆፈሩ ናቸው፤ ማፍረሱ ትርፍ አለው፤ አፍርሶ መሥራቱም ትርፍ አለው፤ ትርፉን የሚበላው ማን ነው? በትርፉ ሰማይ-ጠቀስ ሕንጻዎች ይሠራሉ፤ በውጭ አገር ባንኮች ዳጎስ ያለ ቅሪት ይከማቻል፤ ኪሳራውን የሚሸከመው ያለጥርጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ የቤትና የመንገድ ማፍረስ-መሥራት-ማፍረስ-መሥራት ጉዳይ ግዙፍና የማይደበቅ፣ ለሁሉም የሚታይ በመሆኑ በአገዛዙ አመራር ውስጥ ለሃያ አንድ ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ያደኸየውን የማሰብ ችጋር ከተደበቀበት አወጣና አጋለጠው፤ ስለዚህም ዛሬ ስለማሰብ ችጋር ማታለል አይቻልም፤ የማሰብ ችጋር ደሀነትን ያበቅላል።
ደርግ ወዝ-አደር ለሚባል አንድ የደሀ መደብ ቆሞ ያላገኘውን የምዕራባውያን ድጋፍ ወያኔ ‹‹ጭራቁን›› ለማጥቃት በብዙ ጎሣዎች ላይ የቆመ ስለሆነ የምዕራባውያን ድጋፍ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ፈሰሰ፤ ጭራቁን ‹‹አከርካሪቱን ሰብሮ ሁለተኛ እንዳያንሰራራ›› ለማድረግ በወያኔ አቀነባባሪነት ብዙ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስና ለመቀራመት ሲሻሙ ደሀና ደሀነት ዳር ወጡ፤ እንዲያውም ይባስ ብለው ደሀና ደሀነትን ለጉልበተኞች ጠያቂ የሌለበት የብዝበዛ መስክ አደረጉት፤ ደሀነት ተስፋፍቶ የደሀው አጥንት ተግጦ፣ ተግጦ ተቆርጥሞ የሚጋጥ እየጠፋ ነው፤ ስለዚህም እርስበርስ የሚያባላ ተላላፊ በሽታ እየጣላቸው ነው።
በወያኔ ዘመን በተግባር ደሀውን እያደኸዩ ደሀነትን ስለመቀነስ ማውራት የፖሊቲካ ፈሊጥ ሆነ፤ የደሀዎችን ቁጥር በመጨመር ደሀነትን ማስፋፋት እንጂ ደሀነትን ማጥፋት እንደማይቻል ለመረዳት ሃያ አንድ ዓመት ፈጀብን፤ በነዚህ ዓመታት ውስጥ ሚልየኔሮች እንደደሀ ተቆጥረው ሀብታም የሚባሉት ቢሊየነሮች ብቻ ሆኑ፤ ለደሀው ግን አሥር ብርም ራቀው፤ የደሀነት መዘዙ ብዙ ነው፤ ዱሮ ለዓመት በዓል ለአንድ ሰው አሥር ብር ቢሰጡት አንድ ዶሮ ይገዛበት ነበር፤ ዛሬ አራት እንቁላል ቢገዛለት ነው! ስለዚህም በመስጠትና ባለመስጠት መሀከል ያለው ልዩነት በጣም ተቀራረበ፤ መስጠት ሰጪውን የሚጎዳ ሆኖ ተቀባዩን እምብዛም የማይረዳው ከሆነ አለመስጠት አማራጭ እየሆነ ነው፤ ስለዚህም በደሀው ላይ ደሀነቱ እየበረታ ነው፤ ደሀው እየጫጨ ነው፤ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በጠኔ ይወድቃሉ ሲባል እየሰማን ነው፤ መፍትሔ ተገኘ ሲባል ግን ሰምተን አናውቅም፤ ከማሰብ ችጋር ሳንወጣ ከደሀነት ለመውጣት መመኘት ቀዠት ብቻ ነው፤ የሥላሴዎች እርግማን!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar