torsdag 8. august 2013
የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ እና የመቀሌያችን መታፈን ከነመፍትሄው!
ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)
ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. (August 5, 2013)
የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ ወደፊት በመገስገስ ላይ ይገኛል። አንድነቶች የኢትዮጵያን ጸረ-ሽብር ህግ
ለማሰረዝ የዜጎች ፊርማ በማሰባሰብ ዘመቻ ላይ ናቸው። የቀድሞውን የግብጽ ፕሬዘዳንት ሞርሲን ከስልጣን
የማውረድ እንቅስቃሴ ያስጀመረው ከአስራ አምስት ሚሊዮን በላይ የሚገመተው የግብጾች ፊርማ ከተለያዩ
ከተሞች የተሰበሰበው በሶስት ወሮች ነበር። በግብጾች አይን ሲታይ አንድነቶች በሶስት ወሮች አንድ ሚሊዮን ፊርማ
ማሰባሰብ አይችሉም ብለን መገመት ያዳግተናል። እርግጥ ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ ትግል ባህል እና ክህሎት
እንደ ግብጾች ብዙ አልዘለቅንም። ይሁን እንጂ ካሰብነው ቁጥር እንደምንደርስ ጥርጥር የለኝም። የአንድነት
መሪዎች መታሰር ቢደርስባቸውም የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት የመጀመሪያው ዘመቻ በጎንደር እና በደሴ ከተሞች
ሐምሌ 7 ቀን በስኬት ተፈጽሟል። በጎንደር እና በደሴ ከተሞች የዜጎች ፊርማዎች ተሰብስበዋል።
ባለፈው ሳምንት ደግሞ አንድነቶች የየከተሞች አስተዳዳሪዎች እና የጸጥታ ኃይሎች የሚፈጽሙባቸውን የወከባ፣
የመኪና ጎማ በማስተንፈስ መጓጓዣ የማሳጣት፣ የቢሮክራሲ ጫና፣ የአካል ድብደባ እና እስር የተለመደ ጽዋቸውን
በቻይነት እና በሆደ ሰፊነት በመቀበል እሁድ ሐምሌ 28 ቀን ከመቀሌ በስተቀር በወላይታ፣ በጂንካ፣ በአርባምንጭ
እና በባህርዳር ሁለተኛውን ዘመቻ በስኬት አጠናቀዋል። ይኽን በውጣ ውረድ የተሞላ ዘመቻ አንድነቶች
ሳይታክቱ፣ በትዕግስት፣ በፅናት፣ በአርቆ አስተዋይነት እና በድስፕሊን በታነጸ አኪያሄድ ፈጽመዋል። አንድነቶች
“አንድነት ፓርቲ ሳይገድል እየሞተ ህገ-መንግስቱን የማስከበር ትግሉን አጠንክሮ ዛሬም ወደፊትም ይቀጥላል፡፡”
የሚሉትን መርሃቸውን ምንም ሳይሸራረፍ በተግባር እየፈጸሙት ነው። ከህዝባቸው ጋር ታግለው ህዝባቸውን
የመብቱ ባለቤት ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኛነት እያሳያዩን ነው። ሊመሰገኑ ይገባል። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ
እንደሚባለው በአንድ ወገን ፀር-ሽብር ህጉን ለማሰረዝ ሰላማዊ ትግል ዘመቻ ስታደርጉ በሌላ በኩል ደግሞ
ከቀድሞው የመገዳደል የፖለቲካ ትግል ባህላችን ወደ ሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ባህል ልታሸጋግሩን ታሪክ እየሰራችሁ
ነው። ይኽን ሁሉ የምታደርጉት በአስጨናቂ እና በተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ህዝባችሁ ይረዳዋል።
የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስበው በአገር ውስጥ እና ካገር ውጭ የሚኖረው ህዝባችሁ ስራችሁን በአክብሮት፣
በአድናቆት እና በኩራት እያስተዋለ ነው። በስራችሁ እና በስኬታችሁ ልትደሰቱ ይገባል። ታሪክ እየሰራችሁ ነው።
በጅንካ፣ በባህርዳር፣ በአርባምንጭ የምትኖሩ ዜጎቻችም ሐምሌ 28 ቀን ባደባባይ ወጥታችሁ፥ “የታሰሩ የፖለቲካ
እና የነፃ ጋዜጣ እስረኞች ይፈቱ! መንግስት ህገ-መንግስቱን ያክብር! መንግስት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን
ያቁም! ውሸት ሰልችቶናል! ይቁም!!! የጸረ – ሽብር ህጉ ባስቸኳይ ይሰረዝ! ዘርን መሰረት ያደረገ ማፈናቀል
ባስቸኳይ ይቁም!! የዜጎች ሰብአዊ መብቶች ይከበር!! መብት መጠየቅን ከጸጥታ እና ከልማት ጋር ማያያዝ
በአስቸኳይ ይቁም! የፓርቲ አባልነት በፍላጎት መሆን አለበት!!” በማለት የሰብዓዊ መብት ይከበር መልዕክቶች
አሰምታችኋል። እነዚህ መልዕክቶቻችሁ እና ጥያቄዎቻችሁ የጅንካ ወይንም የአርባምንጭ ወይንም የባህርዳር ብቻ
አይደሉም። የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎች ናቸው። የአለም ህዝብ ጥያቄዎች ናቸው። የተባበሩት መንግስታትም
እንዲከበሩ የሚታገልላቸው መሰረታዊ መብቶች ናቸው። በትናትናው ዕለት በወላይታ የሚኖሩ ዜጎቻችንም
ስለአገራቸው አሳሳቢ ጉዳዮች በአደባባይ ተሰባስበው ተወያይተዋል። ሰላማዊ ትግላቸውን አጠናክረው
እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። ስለዚህ በጅንካ፣ በአርባምንጭ፣ በባህርዳር እና በወላይታ የምትኖሩ ወንድሞች እና
እህቶች በሙሉ ሐምሌ 28 ቀን ባደረጋችሁት የጥሩ ዜጎች ስራ ልትደሰቱ እና ልትኮሩ ይገባል።
በዚሁ ባለፈው ሳምንት ህውሃት በመቀሌ ድምጽ ማጉያ እንዳይሰማ በማድረግ እና አንድነቶችን በማሰር የታቀደው
የመቀሌ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ እንዳይሳካ አድርጓል። አምባገነኖች ከጠብመንጃ ይልቅ ነፃ ፕሬስ
እንደሚፈሩ እናውቃለን። ባለፈው ሳምንት ግን በመቀሌ አምባገነኑ ህውሃት የድምጽ ማጉያ ሲያፍን አስተዋልን።
ድምጽ ማጉያ አይገድልም። ህውሃት ግን ለምን ድምጽ ማጉያ ይፈራል? ድምጽ ማጉያ እንደ ነፃ ፕሬስ ከአንድ ሰው
የሚተላለፍን መልዕክት ለብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ እንዲደርስ ያደርጋል። አምባገነን ህውሃት የፈራውም እሱን ነው።
ስለዚህ የሰብዓዊ መብት መከበርን አስፈላጊነት የሚቀሰቅስ የድምጽ ማጉያ ከሐምሌ 25 ቀን ጀምሮ በመቀሌ ስራ
ላይ እንዳይውል ተደረገ በህውሃት። በተጨማሪ የአንድነቶችን የቅስቀሳ ቁሳቁሶች ህውሃት በአደባባይ በፖሊስ
አስነጠቀ። በቅስቀሳ ላይ የነበሩትን የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አባል አቶ እንግዳ ወ/ፃዲቅ እንዲሁም
የትግራይ ዞን የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል የሆኑትን አቶ ክብሮም ብርሃነ እና አቶ አርአያ ፀጋይን አሰረ።
የመቀሌ ህውሃት አስተዳዳሪ እና የጸጥታ ኃይሎች እነዚኽን እና ሌሎች ማለቂያ የሌላቸው መሰናክሎችን በመፍጠር
የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ በመቀሌ እንዳይሳካ አድርጓል። ህውሃት የመቀሌን ህዝብ አሳብ በነፃነት
የመግለጽ ህገ-መንግስታዊ መብት ጥሷል። ወንጀል ፈጽሟል።እንግዲህ ህውሃት እና ሰብዓዊ መብት የሚሰብኩ ድምጽ ማጉያዎች፣ ህውሃት እና ሰብዓዊ መብት የሚሰብኩ
መኪናዎች፣ ህውሃት እና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚጠይቁ በራሪ ወረቀቶች እሳት እና ጭድ መሆናቸውን
ባለፈው ሳምንት በመቀሌ ህውሃት ወለል አድርጎ እንዲታየን አድርጓል። ህውሃት እና ሰብአዊ መብት እሳት እና
ጭድ ናቸው። ግን ለምን? ከፍ ብለን እንዳነበብነው ደግሞ አንድነቶች በአንድ ወገን ፀረ-ሽብር ህግ ለማሰረዝ
ሰላማዊ ትግል ዘመቻ ሲያደርጉ እግረመንገዳቸውን በኢትዮጵያ ከቀድሞው የመገዳደል የፖለቲካ ትግል ባህል ወደ
ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ባህል ሽግግር መሰረት እየጣሉ ነው። በዚህስ ረገድ ምን ይደረግ? ስለሆነም የዚኽ ጽሑፍ
ግብ (1ኛ) ህውሃት እና ሰብዓዊ መብት ለምን እሳት እና ጭድ ሆኑ? እና (2ኛ) የፖለቲካ ትግል ባህል ሽግግሩ
ሳያቋርጥ እንዲዳብር እና በህዝባችን ዘንድ እንዲሰርጽ ምን እናድርግ? ለሚሉትን ሁለት መሰረታዊ (መርህ ነክ)
ጥያቄዎች መልስ መስጠት ነው።
(1ኛ) ለምን ህውሃት እና ሰብዓዊ መብት እሳት እና ጭድ ሆኑ? የመግደል አቅም የሌላቸውን እንደ ድምጽ ማጉያ
አይነት ቁሳቁሶችን ህውሃት ለምን ሊፈራ ቻለ? ለሚለው ጥያቄ መልስ እንስጥ።
የመንግስት ስልጣን ከምርጫ ሳጥን ይመነጫል የሚለው የፖለቲካ ትግል ባህል በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል
የሚፈጸም ነው። ህውሃት ይኼን የፖለቲካ ባህል ከወሬ ባሻገር አያውቀውም። ባህሉም የለውም። በነፃ ምርጫ
እመረጣለሁ ብሎም አያምንም። የመንግስት ስልጣን ከጠብመንጃ አፈሙዝ ይመነጫል የሚለው እርስ በርስ
መጨራረስን በይፋ የሚሰብከው ፍልስፍና ነው የህውሃት የፖለቲካ እምነት። ህውሃት ተወልዶ ያደገው ይህን
የፖለቲካ እምነት በመከተል እና በመፈጸም ነው። ይኽ የፖለቲካ ፍልስፍና ደግሞ ለስልጣን እንጂ ለሰብዓዊ መብት
ዋጋ እንደማይሰጥ ግልጽ ነው። ትጥቅ ትግል እና ሰብዓዊ መብት የተባሉት ሁለት ነገሮች እሳት እና ጭድ ናቸው።
ባጭሩ ትጥቅ ትግል እየሰብክ እና እያራመድክ ሰብዓዊ መብት አክባሪ ነኝ አትበለኝ ነው የምልኽ!!!
ህውሃት ሳያቋርጥ ለአስራ ሰባት አመቶች በእርስ በርስ ጦርነት ህዝብ አጫርሶ፣ መንደሮች አፍርሶ እና ህዝብን
ለስደት ዳርጎ ለስልጣን የበቃ ድርጅት ነው። እንደሚታወቀው ህውሃት ቲ.አል.ኤፎችን በተኙበት አርዶ፣
ኢ.ዲዩ.ዎችን፣ ኢህአፖችን እና የደርግን ወታደሮች ፈጅቶ ነው እዚህ የደረሰው። በትግራይም ህውሃትን ከተቀላቀሉ
ወጣቶች ውስጥ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ የፈለጉን በአረመኔነት ገድሎ፣ በውስጡም ቢሆን ከአምባገነኖቹ
መሪዎቹ የተለየ አሳብ የነበሩዋቸውን አባላቱን እየፈጀ፣ ገበሬውን ስደተኛ እያደረገ፣ የውጭ እርዳታ ለማግኘት
ድርቅ እልቂት በአረመኒነት እንዲባባስ እያደረገ ነው ለስልጣን የበቃው። ይህ ሁሉ ተግባሩ ህውሃትን የሰብዓዊ
መብት አፍራሽነት የሻምዮንነት ማዕረግ ያስገኝለታል። ህውሃት እና ሰብዓዊ መብት እሳት እና ጭድ ናቸው።
ህውሃት ስልጣን ላይ ከወጣም ወዲህ አገር አፈረሰ። የባህር በር አሳጣን። የአልቢኒያ እና የሶቪየት ህብረት
አምባገነኖች የጻፉትን ቃል በቃል ቀድቶ ኢትዮጵያን ሊያስተዳድር ሞከረ። አልሰራ ሲለው በሽብር በማስተዳደር
ላይ ይገኛል። የአገሩን ህዝብ ታሪክ ጠንቅቆ አውቆ፣ ቀደም ብለው የተፈጸሙ ስህተቶችን አስተካክሎ እና
እንዳይደገሙ አድርጎ ህዝቡን አቀራርቦ አገር በመምራት ላይ የሚገኝ ቡድን አይደለም።
ስለዚህ ባለፈው ሳምንት ህውሃት በመቀሌ እና በሌሎች ከተሞች የፈጸማቸውን እንቅፋቶች እና ወደፊት ሰላማዊ
ትግላችንን ለማራማድ በምናደርገው ጥረቶች ከህውሃት በኩል የሚገጥሙን ፈተናዎች ምንጫቸው ይህ የህውሃት
ከሰብዓዊ መብት ማክበር ባህል ጋር እሳት እና ጭድ መሆኑ እንደሆነ መዘንጋት የለበንም። በህገ-መንግስቱ ውስጥ
የተዘረዘሩት ሰብዓዊ መብቶችም ቢሆኑ የምዕራቡን አለም ለማጭበርበር እና የገንዘብ እርዳታ ለማግኛ እንጂ
አምባገነኑ መለስም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው የመኪና ጎማ አስተንፋሽ ወሮበላ ህውሃት ፍጽም
አያምንባቸውም። ህውሃት የፖለቲካ ባህሉ መግደል ነው። ስብዕናው የተሟጠጠ ነው። ታሪኩ ደም ነው። ስለዚህ
ህውሃት በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ስርዓት መገንባት የሚያስችለው ባህል ፍጹም የለውም። በዚህ ሁሉ ምክንያት
ሰብዓዊ መብት የሚቀሰቅስን የድምጽ ማጉያ ህውሃት ቢፈራ ሊገርመን አይገባም።
(2ኛ) የፖለቲካ ትግል ባህል ሽግግሩ ሳያቋርጥ እንዲዳብር እና በህዝባችን ዘንድ እንዲሰርጽ እንዴት እንርዳ?
ህውሃት አምባገነን ነው። አምባገነን ይፈራል። ህውሃት በህዝብ ይሁንታ ስልጣን ላይ አልወጣም። ህጋዊነት
እንደሌላቸው ህውሃቶች ብልቦናቸው ያውቁታል። ስለዚህ ከጠበንጃ ይልቅ ህዝባዊ ነፃ መሰባሰብን፣ ህዝባዊ ነፃ
ውይይትን እና ህዝባዊ ተሳትፎን ይፈራሉ። ህዝቡ በነፃነት የሚያደርጋቸው ነገሮች አምባገነኖችን ያስደነግጧቸዋል።
ያስበረግጓቸዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላማዊ ትግል ወታደሮች ነን የምንል ሁሉ እነዚህን የአምባገነኖች ሁሉ መለያ
መሰረታዊ ጸባዮች ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል። የፖለቲካ ትግል ባህል ሽግግር ቀላል እንደማይሆንም በቅድሚያ
ልንገነዘብ እና ልንዘጋጅ ይገባል። የሰላም ትግል ሰራዊት ትግባሮች ድርብርብ ናቸው። ለምሳሌ የሚሊዮኖች ድምጽለነፃነት ዘመቻ ለማኪያሄድ እንኳን አንድነቶች የሰላማዊ ትግልን ባህል ለህዝብ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ
በየከተማው የሚገኙ የህውሃት አስተዳዳሪዎች እና የፀጥታ ኃይሎችን ሲያግባቡ፣ ሲቻል ሲያላምዱ፣ እንዳይፈሩ እና
በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንዲያምኑዋቸው ሲጥሩ፣ ወደ ድርድር እንዲመጡ ሲያበረታቱ እና የመሳሰሉትን
ሲያደርጉ አይተናል። እንደ አስፈላጊነቱም የተመጠነ ‘የጀግኖች’ መውጫ በር መስጠት ሊያስፈልግ ይችላል። ይኽ
ሁሉ መቼ መደረግ እንዳለበት እና እንደሌለበት እና የትኛው መቅደም እንዳለበት ማወቅ ያስፈልጋል።
የፖለቲካ ትግላችንን ባህል ሽግግር ለማፋጠን ህውሃትን የተጀመረው የፖለቲካ ባህል ሽግግር አካል ማድረግ
ለሁላችንም ይጠቅማል። ይኽን ለማድረግ ሰለአምባገነኖች ፀባይ ከፍ ብለን የዘረዘርናቸውን ማወቅ እና ተገቢውን
ስራ መስራት ይጠቅማል። የሰላማዊ ትግላችን ግብ ህውሃትን ለመበቀል አይደለም። በፍጹም። የሰላም ትግል
ወታደር ግቦች ህዝባችንን ወደ ነፃነት፣ ዲሞክራሲ እና ልማት ማሸጋገር ነው። ይኽን ከስኬት ለማድረስ እራስን
በዘመናዊ ሰላማዊ ትግል ንድፈ አሳብ እና አፈጻጸም መቃኘት ያስፈልጋል። እንደትናንቱ በሰላማዊ ትግል መዝገበ-
ቃላት ትርጉሙ ብቻ መወሰን በቂ አይደለም። የሰላማዊ ትግል ክህሎታችንን ማዳበር አለብን።
ስለዚህ የመቀሌ አንድነቶች የወሰናችሁት የማፈግፈግ ውሳኔ የሚያመለክተው ብስለታችሁን እንጂ መሸነፋችሁን
አይደለም። በማፈግፈግ የሰላም ትግል ሰራዊትን ለነገ ማቆየት ጠቃሚ ነው። ይኽን አይነቱ ማፈግፈግ መፍራት
አይደለም። የሰላም ትግል ሰራዊት በመቀሌ ያላጠናቀቀው ተጨማሪ ስራ መኖሩን ተገንዝቦ ሰልፉን ወደፊት
ማስተላለፉ አኩሪ እርምጃ ነው። አንድነቶች በመቀሌ የደረሰባችሁ ጠንካራ እንቅፋት እና ያደረጋችሁት አይነት
ማፈግፈግ እነ ጋንዲም በዘመናቸው ትግላቸውን ወደ አዳዲስ ከተሞች ለማሰራጨት ጥረት ሲያደርጉ
ደርሶባቸዋል። አፈግፍገዋልም። አንድነቶች ሰላማዊ ትግላቸውን በመቀሌ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እና መስከረም
2006 ዓ. ም. ከመግባቱ በፊት ስኪታማ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ጥርጥር የለኝም። ካለፈው ሳምንት አንድ
ነገር ተምረናል። በመቀሌ የተሳካ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንደ ጅንካ፣ አርባምንጭ ወይንም ባህርዳር የአንድ እና
ሁለት ቀን ቅስቀሳ እንዲሁም የጥቂት አንድነቶች ስምሪት ብቻ በቂ አይደለም። መፍትሄው ዘመቻውን ማጠናከር
ነው። ተጠባባቂ ኃይል መመደብ ሊያስፈልግም ይችል ይሆናል። የስለማዊ ትግሉ ነፋስ ከመቀሌ ተነስቶ ወደ
አክሱም እና አዲግራትም እንዲነፍስ ማድረግ ይጠቅማል። በመቀሌ የተከማቸውን የህውሃት ኃይል ለመበተን።
በአንድ ወገን የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ በመቀሌና በቀሩት ከተሞች እንዲቀጥል ስንታገል በሌላ በኩል
ህውሃት አንድነት ፓርቲን ለመወንጀል እና ክትግል ሜዳ ለማስወጣት የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖርም
ከወዲሁ መገመት እና መከላከያውን ማዘጋጀት ይኖርብናል። ይኽን ምኞቱን ለማሳካት ህውሃት የተቻለውን
በማድረግ ላይ ስለመሆኑ ባለፈው ሳምንት በወላይታ የአንድነት ፓርቲ የዞን አመራር አባል በሆነችውን በወ/ሮ
ሀድያ መሀመድ ላይ የፈጸመው ተቋሚ መረጃ ነው። ህውሃት ካለ ምንም ምክንያት ወ/ሮ ሀድያ መሀመድን ካሰረ
በኋላ የአንድነት ፓርቲ ህዝበ ሙስሊሙን ለአመፅ ያነሳሳል የሚል ሰነድ እንድትፈርም አግባባት። እምቢ አለች።
ከዚያ ህውሃት ሊያስገድዳት ሞከረ። በኢንቢታዋ ጸናች። እስሩ ቀጥሏል። አንድነቶች ህውሃት ሊቀድማችሁ
አይገባም። ለምሳሌ በወ/ሮ ሀድያ መሀመድ ላይ የተፈጸመውን በአገር ቤት እና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች እንዲሁም
ዲፕሎማቶች እንዲያውቁት ሰፊ ዘመቻ ማድረግ ይጠቅማል። ህውሃትን ተአማኒነት ለማሳጣት። ሌላም ይደረግ።
ይኽ ፍራቻ አይደለም። ጀግኖች የሚያደርጉት ጥንቃቄ ነው። አንድነቶች በርቱ!!!
አንባቢዎች ሆይ! አንድነቶች ፀረ-ሽብር ህግን ለማፍረስ እና የፖለቲካ ትግል ባህላችንን ለመቀየር የጀመሩትን ዘመቻ
እንቀላቀል። እንርዳቸው! የተጀመረው አዲስ ታሪክ አካል እንሁን!!! የሚከተሉትን በማድረግም በመሰራት ላይ ባለው ታሪክ
ማህተማችንን ማስቀመጥ እንችላለን።
እርዳታ፥ በገንዘብ!
እርዳታ፥ በአሳብ!
እርዳታ፥ መረጃዎች በፍጥነት በማሰራጨት!
እርዳታ፥ ፊርማዎች በማሰባሰብ!
እርዳታ፥ እንደገና በገንዘብ!
ድረ ገጻቸው፥ www.andinet.org
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar