onsdag 3. juli 2013

ጄ/ል ክንፈ ተመለሱ፤ መከላከያ ውጥረት ነግሷል


(ከኢየሩሳሌም አርአያ)
የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ብ/ጄነራል ክንፈ ዳኘው ላለፉት ሶስት ወራት ገደማ ከስልጣናቸው ታግደው ከቆዩ
በኋላ በዚህ ሳምንት ወደ ሃላፊነት መመለሳቸውን የቅርብ ምንጮች ገለፁ። በጄ/ል ሳሞራ የኑስ ትእዛዝ ታግደው ከቆዩት ከፍተኛ ጄነራሎች
መካከል አንዱ ጄ/ል ክንፈ እንደሚገኙበት የጠቆሙት ምንጮቹ ስልካቸውን በመጥለፍ በእንቅስቃሴያቸው ዙሪያ ክትትል ይደረግባቸው
እንደነበር አስታውቀዋል። ጄ/ል ክንፈ በሳሞራ ታግደው የቆዩት የነአዜብ/በረከትን ቡድን በመቃወም ከነስብሃት ቡድን ጋር በመሰለፋቸው
እንደሆነ ምንጮቹ አመልክተዋል። የጠ/ሚ/ር መለስን ሕልፈት ተከትሎ በመከላከያ ከፍተኛ ጄነራሎች መካከል የተፈጠረው ያለመግባባት
ስር እየሰደደ መሄዱንና የልዩነቱ መንስኤም በሕወሐት የተፈጠረው ቀውስ - ጄነራሎቹ ጎራ እንዲለዩ ጫና ማሳደሩን ያመለከቱት ምንጮች፣
አክለውም ልዩነቱ በአገር ጉዳይ ዙሪያ ሳይሆን አንዱ ሌላኛውን በማስወገድ የራስን ጥቅም አስጠብቆ በስልጣን ለመቆየት የሚደረግ የሙስና
መጠላለፍ ነው ብለዋል።

ጄ/ል ክንፈ የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት በሟቹ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ እንደሆነ ያስታወሱት ምንጮቹ
ከስልጣን ሊያግዳቸውም ሆነ ሊያወርዳቸው የሚችለው በህግ ስልጣን የተሰጠው ጠ/ሚኒስትሩ መሆኑን ያስረዳሉ። በዚሁ መሰረት
ስልጣኑ በአዋጅ የተቀመጠው ለጠ/ሚ/ር ሃ/ማሪይም ቢሆንም - በግልፅ የሚታየው ግን ከህግ ውጭ የጄ/ል ሳሞራ ፈላጭ ቆራጭ ውሳኔ
ከመሆኑ በተጨማሪ የታገደውን ጄ/ል ወደ ቦታው የሚመልሰው በተቃራኒው የቆመውና በሕወሐት ውስጥ ያለው የነስብሃት ቡድን
መሆኑን ምንጮቹ ያመለክታሉ። አቶ መለስ ይዘውት የቆዩትና “በሕገ-መንግስቱ ተሰጠ” ከተባለው ስልጣን በአብዛኛው ለጠ/ሚ/ር
ሃ/ማሪያም ሊሰጥና ሊተላለፍ አልቻለም ሲሉ የጠቆሙት ምንጮቹ ቁልፍ የሆነው የጦር ሃይሎች ጠ/አዛዥነትን ጨምሮ በርካታዎቹ ሕገ-
ወጥ በሆነ ሁኔታ በሕወሐት ሰዎች ቁጥጥር ስር መውደቃቸውን አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ- ጄ/ል ሳሞራ የሚመሩት ስብሰባ በመከላከያ ከፍተኛ ጄነራሎች ተሳታፊነት በዚህ ሳምንት ሲካሄድ መሰንበቱን
ምንጮች ጠቆሙ። ውጥረትና ያለመረጋጋት በተስተዋለበት የሳሞራ ንግግር በዋና አጀንዳነት የቀረበው የግንቦት ሰባት ጉዳይ ሲሆን በዚህም
፥ « ግንቦት ሰባት በመንግስትና በሕገ-መንግስቱ ዙሪያ መጠነሰፊ አደጋ ጋርጦብናል፤ በግንቦት ሰባት የሚደገፉ በአገር ውስጥ ያሉ
ተቃዋሚዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ ልንወስድ ይገባል፤» ማለታቸውን የገለፁት ምንጮቹ፣ ሳሞራ «ለምሳሌ.» ሲሉ ሰማያዊ ፓርቲን
እንዲሁም « አንዳንድ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች» በማለት መፈረጃቸውን አስታውቀዋል። በተጨማሪ የሙስሊሙ ማህበረሰብ እያነሳ
ያለውን ፍትሃዊ የመብት ጥያቄ፣ ሳሞራ ከግንቦት ሰባት ጋር ለማያያዝ መሞከራቸውን ምንጮቹ አያይዘው ገልፀዋል።
በሌላም በኩል የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ሃላፊ ብ/ጄነራል ተክለብርሃን ወ/አረጋይ በበኩላቸው፥ ከእንግሊዝ አገር
ረቀቅ ያለ መሳሪያ በማስመጣት በስካይፕ ተቃዋሚዎች የሚያደርጉትን ግንኙነቶች በመጥለፍና ተዛማች የስለላ ተግባራትን እያከናወነ
መሆኑን ከገለፁ በኋላ « ግንቦት ሰባት ከግብፅ ጋር ግንኙነት እንዳለው ለህዝቡ ከነገርነው ከጎናችን ይቆማል፣ ግንቦት ሰባትን በማውገዝ
የእንቅስቃሴው ተባባሪ አይሆንም፣ በአገር ውስጥ ያሉትም ተቃዋሚዎች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ህዝቡ አይቃወምም፤ እንዳውም
ለመንግስት ድጋፍ ይሰጣል፤» በማለት በተሰብሳቢ መኮንኖች ጭምር ገረሜታን የፈጠረ ንግግር ማድረጋቸውን ምንጮቹ አስታውቀዋል።
በዚህም ለሕዝብ ያላቸውን ግምትና የግንዛቤ ደረጃ ያመላከተ ነው ያሉት ምንጮቹ የጄ/ል ተክለብርሃን የእውቀት ደረጃ ምን ድረስ
እንደሆነ ያሳየ ነው ብለዋል። የኤንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በአቶ ደብረፂዮን ጭምር በበላይነት እንደሚመራና አቶ ሃ/ማሪያም
የሚያውቁት እንደሌለ ምንጮቹ አያይዘው ጠቁመዋል። በሕገ - መንግስቱ መከላከያ ከየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ እንደሆነ
ቢደነግግም፣ ከወረቀት በዘለለ ተግባር ላይ ሲውል እንደማይታይና የነሳሞራና ተከታዮቻቸው ተደጋጋሚ አቋምና ተግባር በቂ ማስረጃና
ማሳያ መሆኑን ምንጮቹ በሰጡት አስተያየት አስረድተዋል።
በመጨረሻም፥ የታገዱ ሌሎች ጄኔራሎችን ጉዳይ እንዲሁም ባለፈው ወር በሳሞራ ትእዛዝ የተባረሩ የሕወሐት ጄነራሎች ወደ ከፍተኛ
ንግድ መሰማራት በተመለከተ ዝርዝር መረጃውን ይዘን እንመለሳለን።
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.comhttp://www.ethiomedia.com/abc_text/esat_questions.pdf

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar