“ግብረሰዶማዊነት ወደፊት!”
J
በድጋሚ ከተመረጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካን እየጎበኙ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሴኔጋል ጉብኝት ባደረጉት ወቅት የግብረሰዶማውያን መብት ሊከበር እንደሚገባው አስታወቁ፡፡ የአገራቸው ጠቅላይ ፍርድቤት ሰዶማውያንን የሚደግፍ ውሳኔ ሰሞኑን በማሳለፉ ደስታቸውን ገለጹ፡፡ የሴኔጋሉ አቻቸው ግብረሰዶማውያን እንዳይወነጀሉ ለማድረግ አገራቸው ዝግጁ አለመሆኗን ተናገሩ፡፡
ሰሞኑን በአፍሪካ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝታቸውን በጀመሩባት ሴኔጋል የግብረሰዶማውያንን መብት በተመለከተ ለአፍሪካውያንና ለመሪዎቻቸው ማብራሪያና “ትምህርት” ሰጥተዋል፡፡ “መንግሥታት ዜጎቻቸውን እንዴት ሊያስተናገዷቸው ይገባል፤ ሕጉስ እንዴት ሊያያቸው ይገባል ለሚለው ጥያቄ መልሱ ሁሉም ሰው በእኩልነት ሊስተናገድ ይገባዋል” በማለት “ግብረሰዶማዊነት ወደፊት” የሚያስብል ንግግር አድርገዋል፡፡
አፍሪካን እየጎበኙ የሚገኙት ኦባማ የአገራቸው ጠቅላይ ፍርድቤት የግብረሰዶማውያንን መብት ሊያስከብር የሚችል ውሳኔ ማስተላለፉ እንዳስደሰታቸው በጉብኝታቸው ወቅት ጠቁመዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ ለጋብቻ መጠበቅ ከለላ የሚያደርገውን Defense of Marriage Act (DOMA) የተባለው ሕግ ለወንድና ሴት ተጋቢዎች ብቻ በማለት ያስቀመጠው ከለላ የግብረሰዶማውያንን መብት ይጻረራል በማለት ነበር፡፡ ስለሆነም በፍርድቤቱ ውሳኔ መሠረት በተመሳሳይ ጾታዎች መካከል የተፈጸመ “ጋብቻ” ከፌዴራል መንግሥት የሚሰጡ ጥቅማጥቅሞችን ሊያስከለክል አይገባም በማለት ወንድ ሚስትም ሆነ ሴት ባል ያላቸው ሁሉ የጥቅሙ ተካፋይ እንዲሆኑ ፈቅዶላቸዋል፡፡ እንዲሁም በካሊፎርኒያ ጠቅላይ ግዛት የሰዶማውያን ጋብቻ እንዲቀጥል ፈቃድ የሚሰጥ ውሳኔ ጠቅላይ ፍርድቤቱ አስተላልፏል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ግብረሰዶማዊነት በህግ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል በበኩላቸው ግብረሰዶማውያን እንዳይከሰሱ ለማድረግ አገራቸው ዝግጁ አለመሆኗን ተናግረዋል፡፡ “በጣም በመቻቻል” የምንኖር ነን ያሉት የሴኔጋሉ መሪ አገራት ውስብስብ የሆኑ ሕጎችን በራሳቸው ጊዜ በተግባር ላይ እንደሚያውሉ በመጥቀስ የኦባማን ሃሳብ ተግሳጽ በተሞላበት ምላሽ አስተናግደውታል፡፡
በመቀጠልም አገራቸው ሴኔጋል ወንጀለኞችን በሞት መቅጣት ያቆመች መሆኗን በመናገር አሜሪካ ግን ይህንን እስካሁን ተግባራዊ አለማድረጓን በመጥቀስ ኦባማን ተሳልቀውባቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ወንጀለኞችን በሞት የመቅጣት ህግ ከ30 በላይ ግዛቶች ውስጥ ተግባራዊ ሲሆን በተለይም በቴክሳስ በሰፊው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ወንጀለኞችን በሞት መቅጣት እንደገና ከተጀመረ ከ1974ዓም በኋላ የቴክሳስ ጠቅላይግዛት 500ኛዋን ወንጀለኛ ሰሞኑን በመግደል የቀዳሚነቱን ስፍራ ይዞ ይገኛል፡፡
“ዴሞክራሲ ከራባችሁ ኬክ ብሉ”
በፈረንሣይ አብዮት አካባቢ ህዝቡ መራቡን በተለይም የፈረንሣይ ጭሰኞች መቸገራቸውና በረሃብ እየተንገላቱ መሆናቸውን የተነገራት ልዕልት ማሪ አንቷኔ (“Qu’ils mangent de la brioche”) “ከራባቸው ኬክ ይብሉ” ብላ መልሳለች እየተባለ ለዘመናት ሲዘበትባት ኖሯል፡፡ ልዕልቲቱ ይህንን ለማለትዋ የተረጋገጠ ነገር ባይሆንም ነጻነት፣ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ … ለጠማው የአፍሪካ ሕዝብ ባራክ ኦባማ “የግብረሰዶማውያን መብት ሊከበር ይገባል” በማለት መሠረታዊውን የህዝብ ጥያቄ ችላ ማለታቸው “ዴሞክራሲ ከራባችሁ ኬክ ብሉ” የማለት ያህል እንደሆነ ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ ጠቁመዋል፡፡
በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት “ለውጥ” እና “ተስፋ” ቀዳሚ ዓላማቸው አድርገው የበርካታዎችን ቀልብ የሳቡት ባራክ ኦባማ፤ ለአፍሪካ መሠረታዊ ችግር እስካሁን ጆሮ አለመስጠታቸው ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ሰሞኑን በአሜሪካ ምክርቤት “ኢትዮጵያ፤ ድኅረ መለስ” በሚል ርዕስ በተደረገው ምክክር የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ የተናገሩትን በድጋሚ ያስታወሱም አሉ፡፡ በወቅቱ አቶ ኦባንግ ያሉት “ኦባማ ለምርጫ በተወዳደረ ጊዜ ጥቂት ደመወዝ የሚከፈላቸው ኢትዮጵያውያን የምርጫ ዘመቻውን ደግፈው ነበር፤ እስካሁን ከኦባማ የሰሙት ነገር የለም” በማለት ነበር፡፡
ከምዕራባውያን የሚመነጨውን ማንኛውንም ነገር – ከፖለቲካ እስከ ማኅበራዊ አመለካከት – ትክክለኛ አድርገው ለሚቀበሉ ግብረሰዶማዊነት ሥልጣኔ ይመስላቸዋል በማለት ለጎልጉል አስተያየት የሰጡ የሃይማኖትና የማኅበረሰብ ሳይንስ ጉዳዮች ምሁር “ጋብቻ” የሚለውን ቃል ለሁለት ወንዶች መጠቀም እርስበራሱ የሚጋጭ ጉዳይ ነው በማለት ተመሳሳይ ጾታ ብሎ ጋብቻ ማለት የተሳከረ አነጋገር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “ይህ የሰዶማውያን መብት ይከበር የሚለው ጉዳይ በሕግ እየጸደቀ ሲሄድ ድርጊቱን ከሃይማኖታቸው አኳያ የሚቃወሙ ሰባኪያን የሃይማኖት ትምህርታቸውን በሚያስተምሩበት ቤ/ክ ይሁን መስጊድ ወይም ምኩራብ ግብረሰዶማዊነትን እየተቃወሙ ሰበካ ማድረግ በህግ የሚያስጠይቃቸው ይሆናል” በማለት ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን የማኅበረሰብ ቀውስ ጠቁመዋል፡፡
በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ዳግም የመመረጥ ፈተና የሌለባቸው የአሜሪካ መሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን የአፍሪካን የዱር እንስሳት እየጎበኙ ወደፊት ለሚሠሩት ፕሬዚዳንታዊ ቤተመጻህፍት (ፋውንዴሽን) ፎቶ እንደሚሰበስቡ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው፡፡ የባራክ ኦባማም ጉብኝት ከዚህ የተለየ አለመሆኑ ግልጽ ሲሆን “የአፍሪካ ልጅ” እየተባሉ ሲሞካሹ የኖሩት ፕሬዚዳንት ዛሬ ደቡብ አፍሪካ ሲገቡ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ገጥሟቸዋል፡፡ ቅዳሜ የክብር ዶክትሬት በሚቀበሉበት የዮሐንስበርግ ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ ተቃውሞ ይጠብቃቸዋል፡፡
ዛሬ ተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ደቡብ አፍሪካውያን “ይቻላል” (Yes! We can!) ለሚለው የኦባማ የምርጫ መፈክር “አትችልም!” (“No, You Can’t Obama,”) የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ “ኦባማ የመጣው አፍሪካንና ደቡብ አፍሪካን ለመዝረፍ ነው” በማለት ጠንካራ ተቃውሞውን የገለጸው አንዱ ተሰላፊ “አፍሪካውያን በብዙ መልኩ እየተሰቃዩ እያለ እርሱ ግን የአፍሪካን ሐብት፤ ወርቅ፣ አልማዝ፣ … ለመዝረፍ ነው የመጣው” ብሏል፡፡
የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ፣ … ዕጦት ላንገላታውና በአምባገነኖች መዳፍ ሥር ለሚሰቃየው የአፍሪካ ሕዝብ በቃላት እንኳን ድጋፋቸውን ከመስጠት እስካሁን የተቆጠቡት ኦባማ አሜሪካ በአፍሪካም ሆነ በሌሎች አገሮች ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ፍላጎቱ እንደሌላት በማያወላውል መልኩ ያረጋገጠ መሆኑ የብዙዎች ግንዛቤ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፕሬዚዳንቱን የሥልጣን ኃይል ጥያቄ ውስጥ የሚጥልም ነው፡፡
በአውሮጳ የፖለቲካ ምጣኔሃብት ተመራማሪ የሆኑ እንደሚሉት “አሜሪካኖች እንደ ህወሃት/ኢህአዴግ ዓይነቱን አምባገነናዊ አገዛዝ እስኪያስመልሰው ድረስ በዕርዳታ ገንዘብ ካሽሞነሞኑ በኋላ “ኢህአዴግን ምን እናድርገው” በማለት “ምክር ስጡን” እያሉ በሕዝብ ሰቆቃ ላይ ያላግጣሉ፡፡ ሲሻቸውም ደግሞ አፍሪካ ድረስ በመሄድ “ዴሞክራሲ ከራባችሁ ኬክ ብሉ” በማለት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አፍሪካውያን ችግር ያልሆነውን የግብረሰዶማውያን መብት መከበር ይሰብኩናል፡፡ ታዲያ ለዚህ ልግጫ መልሳችን መሆን የሚገባው “ራሳችንን ነጻ እናወጣለን፤ ነጻነታችንን አንለምንም፤ አሜሪካ ግን በነጻነት መንገዳችን ላይ ዕንቅፋት እንድትሆንብን አንፈልግም” በማለት አቶ ኦባንግ ሜቶ ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ምክርቤት በተካሄደው ምክክር የተናገሩትን ዓይነት ቁርጠኝነት ነው በማለት አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡
100ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣው የኦባማ የአፍሪካ ጉብኝት በአሁኑ ጊዜ በበጀት ቀውስ ምክንያት በርካታ ሠራተኞች ደመወዛቸው እየተቆረጠ ባለባት አሜሪካ አነጋጋሪ መሆኑን ዋሺንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡ የደኅንነት ሰዎችን እንዲሁም 14ሊሞዚን፣ 56 ጥይት የማይበሳቸው ድጋፍ ሰጪ መኪናዎች፣ ሙሉ የህክምና ባለሙያዎችን የያዘና ጀቶችን የጫነ መርከብ … ለፕሬዚዳንቱና ለቤተሰባቸው ጥበቃ በማድረግ ሥራ ላይ እንደሚውሉ ጋዜጣው ያብራራል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ በደቡብ አፍሪካ የሁለት ቀን ቆይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሰኞ ወደ ታንዛኒያ ያመራሉ፡፡ የአባታቸው የትውልድ አገር ነው የሚባለውን ኬኒያ ሳይረግጡ በዚያው ወደ አገራቸው እንደሚያቀኑ የጉዞ መርሃግብራቸው ያስረዳል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ(link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar