በጎንደር ቅስቀሳ ላይ የነበሩ የአንድነት አባላት መታሰራቸው ቁጣን ቀሰቀሰ -አንድነት በየትኛውም የመንግስት ህገወጥ ጫና ሰልፉን እንደማይሰርዝ ይፋ አድርጓል
-
በጎንደር ቅስቀሳ ላይ የነበሩ 4 የአንድነት አባላት በፖሊስ መታሰራቸው በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ቁጣን ቀሰቀሰ፡፡ አንድነት ምንም አይነት ህገወጥ እስር በጎንደር የተዘጋጀውን የተቃውሞ ሰልፍ እንደማያስቆመው አሳውቋል፡፡
ዛሬ ሰኔ 22 ቀን 2005 ዓ.ም በሰሜን ጎንደር ምዕራብ አርማጨሆ በጎንደር ሰኔ 30 የሚደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ የሚመለከት በራሪ ወረቀት በማሰራጨት ላይ የነበሩት አለልኝ አቧይ፣ ዋኘው፣አብርሀም ልጅ አለም፣አንጋው ተገኝ የተባሉት የአንድነት አባላት ህገወጥ በሆነ መንገድ በአካባቢው ፖሊሶች መታሰራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችን እንዳስቆጣ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመላክቷል፡፡ ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ወረቀት በመበተናቸው ብቻ የታሰሩት ግለሰቦች ሁኔታ የስርአቱን አምባገነንነት አመላካች ነው፡፡
የዞኑ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች “እስር ለጎንደር ነዋሪ በተለይም ለአንድነት አባላት አዲስ አይደለም” ካሉ በኋላ “የታሰሩት አባሎቻችንን ለማስፈታት ከምናደርገው ጥረት ጎን ለጎን የቅስቀሳ ስራው እንዳይስተጓጎል ተጨማሪ አባላት የቅስቀሳ ስራውን እንዲቀጥሉ ወደ ስፍራው ልከናል፡፡” ብለዋል፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሙላት ጣሰው ለሰሜን ጎንደር አስተዳዳሪ ለአቶ ግዛቴ አብዩ ስልክ በመደወል የታሰሩት የአንድነት አባላት በአፋጣኝ መፈታት እንዳለባቸው ተናግረው ገዢው ፓርቲ የሚያደርገው አፈና ከህዝባዊ ንቅናቄ እንቅስቃሴያችን አያስቆመንም በማለት አሳስበዋል፡፡
አንድነት ፓርቲ የሚጠበቅበትን ስለሰልፉ የማሳወቅ ተግባር አጠናቆ ቅስቀሳ የጀመረ ቢሆንም በበጎንደር ምዕራብ አርማጨሆ የተቃውሞ ሰልፉን አላማ የሚያብራራ በራሪ ወረቀት በማሰራጨት ላይ የነበሩ አባላቱ በህገወጥ መንገድ ከመታሰራቸውም በላይ በተለያዩ አካባቢዎች የአንድነት ፓርቲ የቅስቀሳ ቡድን አባላት የሚደርስባቸውን ማስፈራሪያ ወደ ጎን ብለው ቅስቀሳውን አጠናክረው መቀጠላቸውንና የአከባቢው ነዋሪም በራሱ ተነሳሽነት በራሪ ወረቀቶችንና መረጃዎችን በማስተላለፍ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ የአንድነት ፓርቲ የሰሜን ጎንደር ዞን አመራሮች ለፍኖተ ነፃነት አስታውቀዋል፡፡
አንድነት ፓርቲ በጎንደር ለሚደረገው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የጎንደር ከተማና አከባቢው ነዋሪዎች በስፋት እንዲሳተፉ በቀየሰው ስትራቴጂ መሰረት ስኬታማ ቅስቀሳ እያደረገ ሲሆን ሁለተኛው የቅስቀሳ ቡድንም ዛሬ ወደ ጎንገር መንቀሳቀሱ ታውቋል፡፡
ምንጭ፡ ፍኖተ ነፃነት
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar