June 26, 2013
Print PDFቀን፡ 18/06/2013
በUKእና በመላው ዓለም በስደት ላይ የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችና መላው ነጻነት ወዳድ ኢትዮጵያውያን።
ከሃገሩ ርቆ በስደት ዓላም የሚገኘው ኢትዮጵያዊ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ በፈጣሪው ተራዳዒነት ጥሮና ግሮ ላለፉት 40 ዓመታት ያቆማትና ያሳደጋት ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያስተዳድሩና መንፈሳዊ አባት እንዲሆኑት መርጦ የሾማቸው አባ ግርማ ከበደ በገንዘቡም ሆነ በማንኛቸውም ነገር ላይ አዛዥና ፈራጭ ቆራጩ እኔ ካልሆንኩ በማለት ሆነ ብለው ያስነሱት ውዝግብ አልሰምር ሲላቸው እነሆ አሁን ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗን ከነ ሃብትና ንብረቷ ከስደተኛው ህብረተሰብ ወስጄ በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ቀጥተኛ ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ትሆናለች በሚል አስባብ በአውሮፓ ውስጥ በስደተኛው የተቋቋሙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናትን በቀጥታ ለመቆጣጠር ሲባል ለተቋቋመው ሃገረ ስብከት አስረክቤ ጥቅሜን አስረክባለሁ በማለት ተከታዮቻቸውን ይዘው በሚያደርጉት ትግል ትንቅንቁ ቀጥሎ ይገኛል።
ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በሃገር፤ በሕዝብና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚከተለውን የዘረኛ ፖሊሲና አሠራር ባለመቀበል የዚህም ዘረኛ አገዛዝ ተዋናኝ ለነበሩት ለአባ ጳውሎስ ሳትበገር ለ22 ዓመታት የመንግሥትም ሆነ የፓለቲካ ተጽዕኖ ሳይኖርባት በነፃነት ቆማ የኖረችና ነጻ በመሆኗም ለከፍተኛ የዕድገት ደረጃ የበቃች በአውሮፓ አንጋፋዋ ቤተ ክርስቲያን ነች።
ይህንን በመሰለ አኩሪ የነጻነት ታሪክ የምትታወቀውን ቤተክርስቲያን ነው ዛሬ አባ ግርማ ከበደና ተከታዮቻቸው ለንዋይና ለሥልጣን ሲሉ የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ላቋቋመው ሃገረ ስብከት ለማስረከብ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ የሚገኙት።
ይህ የእነ አባ ግርማ የክህደት ሥራ ተግባራዊ ሆነ ማለት ደግሞ በስደት ላይ የሚገኘው ሕዝብ ሳይተርፈው ከራሱና ከልጆቹ አፍ በመነጠል ከ1.7 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ገንዘብ በማውጣት ጥሮና ግሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ የምትተላለፍልኝ የሃይማኖቴና የኢትዮጵያውነቴ ቅርስ ትሆነኛለች ብሎ ህንፃ ገዝቶ ያቆማትን ቤተ ክርስቲያን ሃገር አይል ኤምባሲ ከመሸጥ ወደ ኋላ የማይለው ወያኔ ተረክቦ ህዝበ ክርስቲያኑን በመበታተን ቢያሻው ሊሸጣት ካልሆነም ደግሞ የራሱ ሰዎች መገልገያ ብቻ እንዲያደርጋት እድሉን አገኘ ማለት ነው።
በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያኗን የዘረኛው ወያኔ አገዛዝ ተሿሚዎች ተቆጣጠሯት ማለት ደግሞ ነፃነትና ፍትሕ በሰፈነበት ሃገር የወያኔ አገዛዝ ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚካሄደው ሁሉ የቤተ ክርስቲያኗ አባላት የሆኑ ስደተኞችን ከPersonal Data ጀምሮ ሥራቸው፤ ግንኙነታቸው፤ የፓለቲካ አመለካከታቸውና በአጠቃላይ እንቅስቃሴአቸውን ሁሉ በአገዛዙ የስለላ መነጽር ውስጥ በስገባት መብትና ነጻነታቸውን ሁሉ መቆጣጠር ተቻለው ማለት ነው ።
ከዚሁ ጋርም የወያኔ አገዛዝ ሹመኞች አንድ እግራቸው ቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ገባ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ገቢ ያላቸውንና ቁልፍ ሚና አላቸው የሚባሉትን አብያተ ክርስቲያናት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ወያኔ በሚጠቀመው ስልት መሠረት የአገዛዙን የጎሳ አባላትና ደጋፊዎች በብዛት የቤተ ክርስቲያኗ አባል በማድረግና under cover ካህናትን አስርጎ በማስገባት በቤተክርስቲያኗ የሥራና የኃላፊነት ዘርፉ ሁሉ የራሱን ሰዎች በመሰግሰግ የቤተ ክርስቲያኗን ሃብትና ንዋይ በቁጥጥር ሥር ማዋልና አባላቷ የወያኔ አገዛዝ የሚሰራውንና የሚለውን ከመደገፍና ከመቀበል ሌላ በነፃነት ማሰብም ሆነ በነፃነት መወሰን የሚባል ነገር እንዳይኖራቸው በማድረግ ለወያኔ ሹመኞች ሰጥ ረጥ ብለው የሚገዙበትን ሁኔታ ማመቻቸ ቻሉ ማለት ነው።
ይህም ብቻ አይደለም ሌላው ቤተ ክርስቲያኗ በሃገር ስብከቱ ሥር እስከ ሆነች ድረሥ ከምታገኘው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ ለሃገረ ስብከቱ ፈሰስ በሚልና በሌላ ሰበብ አስባብ በተ ክርስቲያኗን የውጪ ምንዛሪ ገቢ ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም ነው። ይህ ማለት ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ቤተ ክርስቲያኗ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ በደልና ግፍ ሁሉ በፋይናንስ የምታጠናክር ተቋም ሆነች ማለት ነው።
አባ ግርማ ከበደ ትላንትና ቤተ ክርስቲያኗ በአባ ጳውሎስ ላይ እና በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ላይ የወሰደችውን አቋም መደገፍ ብቻ ሳይሆን ከዛም አልፈው የወያኔን አገዛዝ በሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በመገኘትና የተቃዋሚ ፓለቲካ ድርጅቶችንና የኮሚኒቲ አመራሮችን በመቅረብ ሃገርና ሕዝብን የሚወዱና የወያኔን አገዛዝ የሚቃወሙ እውነተኛ መነኩሴ ተደርገው ለመታየት ይሞክሩ ነበር።
እሳቸው ግን ይህን ሁሉ ያደርጉ የነበረው ሥልጣናቸውን ለማደላደል እንዲችሉ የስደተኛውን ስነ ልቦና ለመግዛት እንጂ የእውነት ስላልነበር በአሁኑ ወቅት ስደተኛው ህብረተሰብ ከቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት የዘለለ የጵጵስናም ሆነ የሃገረ ስብከት ሹመት ስለማይሰጣቸው አምኖና አክብሮ፤ አቅፎና ደግፎ ያኖራቸውን ስደተኛ ህብረተሰብ ጀርባችውን በመስጠት 180 ዲግሪ ከዞሩ ውለው አድረዋል። በዚህም መሠረት ከጥቂት ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን ለወያኔ ኤምባሲና ሃገረ ስብከት በማደር ቤተ ክርስቲያኗን ከስደተኛው መዳፍ ፈልቅቀው ለማስረከብ ከመማጸን አልፈው ከኢትዮጵያ ድረስ ጳጳሳትን በማስመጣት፤ የሳቸው ደጋፊ ከሆኑ ጥቂቶች በስተቀር በሺህ የሚቁጠሩት በገንዘብና ጉልበታቸው የቤተ ክርስቲያኑን ህንፃ ገዝተው ያቆሙ የቤተ ክርስቲያኗን አባላት በመካድ እነሱ በሌሉበትና ባልተጠየቁበት ሁኔታ የሌሎች ቤተ ክርስቲያናት አባላትን በመሰብሰብ በጳጳሳቱ ፊት ቤተ ክርስቲያኗ ሙሉ በሙሉ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በጎሳ መርጦ ባቋቋመው ሃገረ ስብከት ሥር ነች በማለት ቤተ ክርስቲያኗን በጠራራ ፀሐይ ሸጠዋል።
አባ ግርማ ከበደና ተከታዮቻቸው በሺህ የሚቆጠረውን የቤተ ክርስቲያኗን አባላት እንደሌለ ቆጥረው ይህንን የመሰለ የክህደት ተግባር ከፈጸሙ በኋላ፡
1) በ26/05/2013 በዕለተ እሑድ ቤተ ክርስቲያኑ ተዘግቶበት ለራሱም ሆነ ለልጆቹ መጸለያና ማቁረቢያ አጥቶ፤ ወንጌልን ተጠምቶ በከፍተኛ ሃዘንና ትካዜ ውስጥ የሚገኘው ሕዝበ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኑን ግንብ ተጠግቶ የዕለት ጸሎቱን በሚያደርስበት ወቅት አባ ግርማ ከበደ ግን ቤተ ክርስቲያኑን የዘጉበትና ሊከፍቱም የሚችሉበት የቤተ ክርስቲያኑ መዝጊያ ቁልፍ በኪሳቸው እንደያዙ፤ ከዚህም ሌላ የስላሴን ቤተ ክርስቲያን አማራጭ አድርገው ሲያገለግሉና ሲገለገሉ እንዳልሰነበቱ ልክ እንደ ሕዝቡ ተበዳይ መስለው ለመታየት እቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመግባት በሚሞክሩበት ወቅት በድርጊታቸው የተቆጣው ሕዝብ የቤተ ክርስቲያኑን ቁልፍ ስጡን በማለት በሩን አላስገባም በማለቱ፤ በተነሳው ሁከት አባ ግርማ ከበደ እግዚአብብሄርን ሳይፈሩና ሰውንም ሳያፍሩ ቤተ ክርስቲያኗ የግል ንብረቴ ነች (This is my Property) ባማለት ለፖለስ አቤቱታ በማቅረብ የባለቤትነት መብታቸው ተጠብቆላቸው ፓሊስ አጅቦ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ግቢ እንዲያስገባቸው ጠየቁ።(ይህን ያሉበት ምክንያት ሕዝቡ የገዛውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና የቪካሬጅ ህንፃ አደራ ጠባቂ (Holding Trustee) ሆነው እንዲጠብቁ አምኖ አደራ ከጣለባቸው ሁለት ካህናትና ሁለት ምእመናን መካከል አንዱ በመሆናቸው ነው) ሕዝብ ከሌሎች ሦስት ሰዎች ጋር ሆነህ ንብረቴን ጠብቅልኝ ብሎ የሰጠውን አደራ እዛው አደራ የሰጠው ሕዝብ ፊት ቆሞ ይህ የግል ንብረቴ ነው በማለት አይን ያወጣ ክህደት የሚፈጽምን ሰው ከቶ ማን ይሉታል? እግዚአብሔርን ለማገልገል ለዚህ ዓለም ሞቻለሁ ያለ መነኩሴ ወይስ አይን ያወጣ፤ ተራ ሌባ?
2) በ02/06/2013 በዕለተ እሑድ እንደተለመደው አባ ግርማ ከበደ ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ሄደው የመገልገልና የማገልገል አማራጩ እያላቸው አማራጭ አጥተው በሃዘንና በቁጭት የቤተ ክርስቲያናቸውን ግንብ ተጠግተው ጸሎታቸውን የሚያደርሱትን የቤተ ክርስቲያኗን አባላት ለመምሰል በሚሞክሩበት ወቅት ከሕዝቡ በተነሳው ቁጣ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ መግባት ያልቻሉ ሲሆን አባ ግርማ ከበደ ግን የሚፈልጉት በእሳቸው ምክንያት በሕዝቡ መካከል ጸብና እረብሻ ተነስቶ በሕዝብ መካከል ከፍተኛ መጎዳዳት እንዲደርስ ቢሆንም ሕዝቡ ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር በመሆን ሁከቱ እንዳይስፋፋና ጉዳት እንዳይከሰት በማድረግ አባ ግርማ ከበደን ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሳይገቡ ከውጪ እንዲመለሱ አድርጓቸዋል።
3) በ09/06/2013 በዕለተ እሑድ የአባ ግርማ ከበደ ደጋፊ የሆኑ የሰንበት ት/ቤተ ወጣቶች የነበሩና አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኗ አባላትም ሆኑ ያልሆኑ ጭምር ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ሲገቡ አንዳችም ነገር ሳይፈጠር ከቆየ በኋላ ሕዝበ ክርስቲያኑ የዕለት ጸሎቱን ጨርሶ ባለበት ወቅት አባ ግርማ ከበደ የፓሊስ ኃይልን በማስጠራት መግቢያ በሩ በፓሊስ መጠበቁን ካረጋገጡ በኋላ ረፋዱ ላይ ከወደ ደቡብ በኩል ብቅ እንዳሉ ሰው ሁሉ ዓይኑን ወደ እሳቸው ሲወረውር ይባስ ብለው መሰቀል መያዝ ባለበት እጃቸው የቪዲዮ ምስል መቅረጫ ሞባይል ፍታቸው ላይ ደቅነው በመያዝ ግራና ቀኝ በትዕቢት እያዘዋወሩ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያለውን ምእመን በቪዲዮ ሲቀርጹ በሳቸው ምክንያትና በሳቸው አማካኝነት ቤተ ክርስቲያኑ ተዘግቶበት በጠዋት ቁር በቤተ ክርስቲያን አጥር ጥግ ጥግ ተኮራምቶ የቆመውን ሕዝበ ክርስቲያ ሃዘንና እሮሮ እግዚአብሔር አይቶ ከሰማይ ቁጣ ያወረደ በሚመስል ሁኔታ ከየት እንደሚዘንብ የማይታወቅ ያልበሰለ እንቁላል መዓት በአባ ግርማ አናት ላይ መፍረጥ ጀመረ።
አባ ግርማ ከበደ የምስል ቀረጻቸው በዚህ የእንቁላል አደጋ ከተቋረጠባቸው በኋላ በር ላይ የነበሩትን የጸጥታ አስከባሪዎች መከታ አድርገው በጉልበት ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ካልገባሁ በማለት ትግልና ግብ ግብ በገጠሙበት ወቅት ራሳቸው ላይ ያለው ቆብ በእንቁላሉ ተሙለጭልጮ ወልቆ ሊወድቅባቸው ችሏል። ይህ በተፈጠረበት ወቅት አባ ግርማ ይበልጥ በመበሳጨታቸው ሊሆን ይችላል ሰውን ለመማታት ሲወራጩ በአካባቢያቸው ሆኖ ሁኔታውን በቪድዮ ይቀርጽ የነበረን ጋዜጠኛ በቅርብ አግኝተው እሱን ለመደባደብ እጃቸውን ሲሰነዝሩ በፓሊስ ገላጋይነት ቪዲዎ ቀራጩ ከመመታት ሊተርፍ ችሏል።
አባ ግርማ ከበደ ይህንን ሁሉ የሚያደርጉበት ምክንያት እንደምንም ብለው ቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመግባት እውስጥ በሚገኘው የእሳቸው ደጋፊና ተቃዋሚ በማለት የተፈረጀው አንድ ሕዝብ መካከል ጸብ እንዲነሳና ሕዝቡን እርስ በእርሱ በማጎዳዳት ጸቡ ጥላቻውና በደሉ ሁሉ በዝቡ መካከል ሆኖላቸው ሕዝቡ ሲፋጅ እሳቸው ከጎን ቆመው ለማየትና ችግሩ የእሳቸው እንዳልሆነ አድርገው ለማሳየት ነበር።
ሆኖም ግን ውርደቱ ሁሉ በሳቸው ላይ እንጂ በሕዝብ መካከል አልነበረምና ዕቅዳቸው ባለመሳካቱ የተበሳጩት አባ ግርማ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ካልገባሁ የሚለው ትንቅንቃቸውን ማቆም ስላልቻሉ በመጨረሻ በጸጥታ ኃይሎቹ አማካኝነት ከአካባቢው እንዲርቁ ተደርገው በሕዝቡ መካከል እንዲከሰት ፈልገውት የነበረው ጸብና መጎዳዳት ሳይከሰት ቀርቷል።
4) በሦስቱ ተከታታይ ሳምንታት የሕዝቡ ተቃውሞው እሳቸው እንደተመኙት ክራሳቸው አልፎ ሕዝብን ከሕዝብ ወደ ማጎዳዳት አልሸጋገር ያላቸው አባ ግርማ ከበደ በ16/06/2013 በዕለተ እሑድ ከጠዋቱ 0730 ሰዓት ጀምር በቁጥር ወደ 20 የሚጠጉ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ያልሆኑና በቤተ ክርስቲያንም አካባቢ ታይተው የማይታወቁ ወጣቶችን እቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ በማሰማራት የፀብና የአምባ ጓሮ አሰላለፍ እንዲይዙ አስደረጉ።
ቤተ ክርስቲያኗን ከስደተኛው ሕዝብ እጅ ወስዶ ለዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ሹመኞች ለማስረከብ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካትና የአባ ግርማን ሃጢአትና በደል ሽፋንና ከለላ ለመሥጠት የተሰማሩት ወጣቶች እነዚህ ነበሩ።
ቀጥሎም የቤተ ክርስቲያኑ አካባቢ ጸጥታ ያሰጋቸው የፓሊስ ኃይሎች ወደ ቤተ ክርስቲያኗ አካባቢ እንደደረሱ አባ ግርማ ከበደ በቤተ ክርስቲያኑ አጥር መግቢያ ግራና ቀኝ ባሰለፏቸው ወጣቶች ተከልለው ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ሲገቡ ሕዝበ ከርስቲያኑ በሰለጠነ መንገድ ለሥራቸው የሚመጥን የተቃሞ ድምጽ ካሰማ በኋላ በዚህ ዕለትም አባ ግርማ የሚመኙት በሕዝብና በሕዝብ መካከል ምንም ግጭትና አንባጓሮ ሳይነሳ ነገሩ በሰላም ሊያልፍ ቻለ።
በዚህ ዕለት ሕዝበ ክርስቲያኑ የታዘበው ነገር ቢኖር ከአሁን በፊት አባ ግርማ ከበደ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን በመቀስቀስና በማደራጀት በ10/02/2013 በዕለተ እሑድ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወጣቶቹ አባ ግርማን አይደግፉም ያሏቸውን አባትና አያቶቻቸው የሚሆኑትን አዛውንቶችን ሳይቀር እጅግ የሚያጸይፍ ስድብ እንዲሰድቧቸውና እንዲያዋርዷቸው በማስደረግ ይህ ድርጊታቸውም በቪዲዮ ተቀርጾ በዩ ትዩብ ዓለም እንዲያየው ሆነ።
ነገሩ ከተፈጸመ በኋላም ወጣቶቹ ንሰሃ ገብተው ሕዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ ጉዳዩ መክሰም ሲችል የወጣቶቹን ከሕዝብ ጋር መጋጨት የኃይል ማጠናከሪያቸው አድርገው የሚጠቀሙበት አባ ግርማ ከበደ ቅራኔው የባሰ ሰፍቶ ሄዶ ቤተ ክርስቲያኗ በሁከትና በብጥብጥ ዓለም የሚያውቃት አስደረጓት።
አሁንም እንደገና አባ ግርማ ከበደ ከወያኔ የስለላና የደህንነት አካል ጋር ቁርኝት በመፍጠር የቤተ ክርስቲያኑን ችግርም ሆነ የሃገሪቱን Criminal Law ጠንቅቀው ያውቃሉ ሊባሉ የማይችሉ፤ በቤተ ክርስቲያኗ እና በአባላቷ ዘንድ ጨርሶ የማይታወቁ እንግዳ ሰዎችን ሆነ ብለው በማሰማራት በቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ ብጥብጥና ረብሻ ተነስቶ ሕዝብ እርስ በእርሱ የሚጎዳዳበት ሁኔታ ሊያመቻቹ ችለዋል።
የእነዚህ በቁጥር ከ20 የማይበልጡ ወጣቶች ትክክለኛ ማንነትም ሆነ በምን ምክንያትና ለምን ዓላማ በዛን ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ እንደመጡ በሚመለከተው አካል ክትትልና ጥናት እየተደረገበት ሲሆን አባ ግርማና ደጋፊዎቻቸው ግን ራሳቸው መሸፈንና መከለል ያቃታቸውን አሳፋሪ የክህደት ተግባራቸውን ወጣቶቹ እንዲሸፍኑላቸውና እንዲከልሏቸው በመሣሪያነት ለመጠቀም መሞከራቸው ወጣቶቹ ገና በለጋ ዕድሜአቸው በማያውቁት ነገር ውስጥ ገብተው ከሕዝብ ጋር በመጣላትና በመጋጨት ያልተገባ ነገር ፈጽመው በወንጀለኝነት መዝገብ (Criminal record) ውስጥ እንዲገቡና ወደ ፊት የሚጠብቃቸው የብሩህ የተስፋ ህይወታቸው ሁሉ ጨልሞ ዕድሜአቸውን በሃዘንና በፀፀት እንዲያልፍ የሚያደርግ በመሆኑ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።
ሕዝቡ ግን የአባ ግርማንና የተከታዮቻቸውን የተንኮል ተግባር አስቀድሞ ተረድቶ ሥለነበር የዕለቱ ሂደት በሰላም እንዲያልፍ አስቀድሞ አቅዶ የመጣ ስለነበር በዕቅዱ መሠረት ዕለቱ በሰላም ሊያልፍ ችሏል።
ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ፡ አሁንም ቢሆን አባ ግርማ ከበደና ተከታዮቻቸው የቤተ ክርስቲያኗን አባላት ክደውና ንቀው በሕገ ወጥ መንገድ ቤተ ክርስቲያኗን ባለንብረት ከሆነው ስደተኛ ሕዝብ ነጥቀው ለወያኔ አገዛዝ ሹመኞች ለማስረከብ የሚያደርጉት ጥረት እንደቀጠለ ሲሆን ይህ የሚቆመው አባላቱ መብታቸውን ተጠቅመው በሚያደርጉት ትግልና የምንኖርበት ሃገር ሕግ ለጉዳዩ እልባት በሚሰጥበት ወቅት ነው። እስከዛው ድረሥ ግን የቤተ ክርስቲያኗ አባላትና መላው በስደት ላይ የሚገኝ ነጻነት ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህቺን በእግዚአብሔር ተራዳኢነትና በስደተኛው ሕዝብ ሃብትና ጉልበት የቆመችን ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ከማይፈሩና ሕዝብን ከማያከብሩ የሥልጣንና የንዋይ ጥመኞች ለመከላከልና ለማዳን ገንዘቡንና ጉልበቱን አስተባብሮ በአንድነት በመቆም በቁርጠኝነት በመታገል ደባና ተንኮላቸውን ሁሉ በጣጥሶ ጥሎ ለአንዴና ለመጨራሻ በአሸናፊነት መወጣት ይኖርበታል።
አባ ግርማ ከበደ ዛሬ አሉ ነገ አላፊ ናቸው ሕዝብ ግን ትውልድ ትውልድን እየተካ ለዘለዓለም ኗሪ ነውና የነገሩ ሁሉ ቀንደኛ ተዋናኝ፤ የችግሩ ሁሉ ዋንኛ መሠረት፤ ሰላማዊ መፍትሄዎችን ሁሉ አምካኝና በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር ሁሉ በአንደኛ ደረጃ ተጠያቂ አባ ግርማ ከበደ እንጂ ሕዝብ ስላልሆነ በተለይ በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ችግር ቀሰቀሰ የተባለው ነገር ቀርቶ የሲኖዶስንና የሃገረ ስብከትን አጀንዳ በማንሳት ሕዝብን የበለጠ ለመከፋፈልና እርስ በእርሱ ለማጋጨት የሚደረገው ሙከራ ዋንኛ ተዋናኝ አባ ግርማ ከበደ ስለሆኑ ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ ወዳጅና ጠላቱንም ሆነ ክፉና ደጉን በሚገባ በመለየት ከሁሉም በላይ የስደት ቅርሱና ትንሿ ኢትዮጵያው የሆነችውን ቤተ ክርስቲያኑን ተነጠቀ ማለት በነፃነት ሃገር ነጻነቱን፤ ክብሩንና ህልውናውን አሳልፎ ሰጠ ማለት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያኑንም ሆነ ነጻነቱን እና ክብሩን ማስከበር ሰብዓዊ ግዴታው መሆኑን አውቆ ትግሉ በሚጠይቀው መስክ ሁሉ በመገኘት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ሁሉ እንዲፈጽም በእመቤታችን ቅድስት ድግል ማርያም ሥም ጥሪ ተላልፎለታል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን!!
2 Responses to ስለ ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ መረጃ