የወያኔ ልማት ሰዋዊ ሽታ የለውም
ሀገራችንን አንቆ የሚገዛው ወያኔ ራሱን የልማት መንግስት ነኝ በሚል ራሱን በሚጠፋ ስእል ላይ አስቀምጦል። በየአመቱ የተጋነነ እና የሌለ ነጠላ የስታቲስቲክ ዜማ እየለቀቀ ያቀርባል። በዴሞክራሲያዊ መንገድ ህጋዊ መሰረት ማግኘት ስለተሳነው በልማታዊ መዝገብ ስም ለመገኘት አይን የአወጣ ሙከራ ያደርጋል።
የወያኔ ልማት ሰዋዊ ሽታ የለውም። ለዘረኛው መንግስት ልማት ማለት ብልጭልጫዊ ነገር ማሳየት እንጂ የሰውን፣ የህዝቡን ጉስቁል ኑሮ መቀየር ማሻሻል መሆኑን አያውቅም። አንድ ሺ አፈናቅሎ አንድ የስርአቱን አገልጋይ ቱጃር ያከብርና አገር ለማ ይለናል። የጋምቤላን አኙዋኮች ከአያት ቅድመ አያት መሬት አፈናቅሎ በርሃብ እየቆላ፣ የአረብና ህንድ የሩዝ ሁዳድ ስላደረገው ብቻ አገር ለማ ከበሮ ደልቁ ይለናል።
ወያኔ ልማት ለሰው መሆኑን ወይ አያውቀውም አሊያም ረስቶታል። በአዲስ አበባና በብዙ አካባቢዎች መንደርን እያፈረሰ የሚበትናቸው ዜጎች፤ ከእነሱ ጋር እድራቸው፣ ሰንበቴያቸው፣ ማህበራቸው፣ ማህበራዊ ህይወታቸው አብሮ እንደሚፈርስ ቢያውቅም ግድ የለውም። የወያኔ ልማት ሰውን ወደተራ እንስሳነት የሚያወርድ የወሮበላ ስራ ነው።
ህወሃት እንደ መንግስት ሱፍ ለብሶ፣ በሌላ በኩል እንደ ኢፈርት ባለቤትነቱ ወዛደር መስሎ ውል ይፈራረማል። ኢፈርት የሚገጣጥመውን መኪና ለመከላከያ ሚኒስተር ይሸጣል፤ እንደ መንግስት በህዝብ ስም እርዳታ ይቀበላል፣ እንደ ወሮበላ ዘራፊ ስማቸውን ቀይረው ወዲያውኑ ዘረፋውን ይጀምራል። ይህን የመሰለ የዘቀጠ ውንብድና በህዝብ ንብረት ላይ እየሰሩ ሌሎችን የወያኔ ግልገሎች ደግሞ ሌቦች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች እያሉ ሲሳደቡ አይናቸውን አያሹም።
የወያኔ አለቆች ድሃ ገበሬዎችን ከመኖሪያቸው ሲያፈናቅሉ ደን ስለጨፈጨፉ ነው የሚል የፈጠራ ክስ ይፈጥሩና የኤፈርት ኩባንያዎች ኢሉ አባቦር ውስጥ የያዩን ደን እየጨፈጨፉና እያጋዩ የሚሰሩትን የዝርፊያ ማእድን ቁፈራ ልማት ነው ይሉናል።
ወያኔ በሚገዛት ኢትዮጵያ ባለሀብት መሆንና ሀገር አልምቶ ራስን መጥቀም ገደብና መስመር አለው። ብዙ ኢንቨስተሮች የወያኔ ባለስልጣንን በአጋርነት፣ በሸሪክነት እንዲያስገቡ ይገደዳሉ። አሊያም ሀብቱን ላለመነጠቅ የፈለገ ሀብታም ልሁን ባይ የዳጎሰ ገንዘብ ለባለስልጣናቱ እጅ መንሻ ለኪስ ተጠይቀው ይሰጣሉ። በአንጻሩ የወያኔን የሀብታምነትን ቀይ መስመር ዘለው እምቢ ያሉ እስር ቤት የተጣሉ፣ የተሰደዱ በተለይ ወያኔ ከሚጠላው የጎሳ ወገን የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ፣ የልማት ተስፈኞቹ በቃሊቲና በዝዋይ እስር ቤቶች ተጨናንቀዋል።
ዛሬ ዛሬ ጤፍ ጠፋ ተወደደ፣ ስኳር ጠፋ ምን እንሁን፣ መብራትና ውሃ ጠፋ ፈረቃው በዛብን ሲባሉ፤ መልሳቸው አስገራሚ እና አሳዛኝ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የጠፋው፣ የምትራቡት አገሪቱ እያደገች ስለሆነ ነው የሚል የማላገጥ መልስ ይሰጣሉ። የሚሉት እድገት ቁልቁል እንደካሮት እየጨመረ ያለውን ድህነት መሆኑን ማለታቸው ነው።
በኢትዮጵያ የነገሰው ደህነት፣ ከድህነቱ ጋር የተያያዘው መጠነ ሰፊ ተስፋ መቁረጥና ስደት ለወያኔ ምኑም አይደለም። ምናልባትም የአገሪቱን እድገት ያመጣው ነገር ነው በሚል መላምት የሆነ፣ የይሆናል ግምታቸውን ይሰጡናል።
የአደገችና የበለጸገችን ኢትዮጵያ ከመፍጠር ይልቅ በልማት ስም የግል ምቾታቸውንና ድሎቶቻቸውን ለማስጠበቅ፣ ብሎም የስልጣን ጊዚያቸውን ለማራዘም ሲሉ፤ ህዝብን ከቀዪው በማፈናቀል ለርሃብና ለስቃይ ለስደት እየዳረጉት ይገኛሉ።
ህወሃቶች የሀብት ክፍፍል በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሚል የአካባቢውን ነዋሪ በማንነቱ ምክንያት አፈናቅለው የህወሃት አባላትንና ደጋፊዎችን የመጥቀም ስትራቴጂዎችን ቀርጸው ሰፊውን የህዝብ ጉልበት እንደ መዥገር መጠው፣ በቀዪው ያፈራውን ንብረትና ገንዘብ እንኳ ሳይሰበስብ ያፈናቅሉታል። ታዲያ የትኛው የልማት ስትራቴጂ ይሆን ህዝብን ማእከል ያደረገው?
የተማሩ ዜጎች በተማሩበት ሙያ ሰርተው በልማቱ ሂደት ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዳይጠቅሙ አድረገው ራእያቸው በማጨለም በጨፍን የስርአቱ ባሪያ አገልጋይ አሊያም አጨብጫቢ እንዲሆኑ ሆነው ይቀረጻሉ፤ አሊያ ግን መጽዋት ጠባቂ ወይም ከሀገር እንዲሰደዱ ይደረጋሉ።
የወያኔ ልማት ህዝብ ህዝብም፣ ሰው ሰውም አይሸትም! ስለዚህም በአገር አልሚነት ስም ማንንም ማታለል አይችልም። ይህ የዝርፊያና የፈንጋይ የወያኔ ኢኮኖሚ ከራሳቸውና ከጉጅሌዎች ባለፈ ውጭ የሚጠቅመው ኢትዮጵያዊ አይኖርም።
ኢትዮጵያ ለሁሉም ልጆቿ የሚሆን የተፈጥሮ ጸጋ አላት። ምቹ የአየር ንብረት፣ ለም አፍርና በተስተካከለ መልከዓ ምድር የተቸረች ሀገር ነች። ልጆቿ ሁሉ የዚህ ጸጋ ባለቤት እንዳይሆኑ እና ዜጎቿ በእኩልነት ተጠቃሚ ሳይሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሆነው እንዲሰደዱ እያደረገ ያለው ወያኔ ነው። ወያኔ አልሚ ሳይሆን የልማት ፀርና የአንድነት ቀበኛ ነው።
በኢትዮጵያ ልማትም፣ እድገትም፣ እኩልነትም፣ ሰብአዊ ክብርም፣ ተስፋም፣ በሀገር መኩራትም እንዲኖር ወያኔ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለበት። ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለነዚህና ለእውነተኛ የሰበአዊ መብት መከበር፣ ሁሉም ዜጎች በሀገራቸው የትኛውም ቦታ በእኩልነት ሰርቶ የማደግ መሰረታዊ መብቶች፤ ህዝብን ማእከል ላደረገ እውነተኛ ልማት እና ሀገራችንን ከመፈራረስ አደጋ ለመታደግ ረጅሙን የትግል ጉዞ በአንድ ርምጃ ጀምሮአል፡፡ እርሰዎስ? ኑ! ተቀላቀሉን፡፡ ድህነት፣ ውርደት፣ ስደት እስከመቼ?
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar