ኢህአዴግ ደብሮታል!
ባለፈው ጊዜ ግንቦት 17 ሰማያዊ ፓርቲ በአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ አቅርቦ መነግስት እንደተለመደው ዝም ብሎ ደብዳቤ አንቀበልም በማለት አላየንም አልሰማንም ብሎ የአራዳ ሰፈር ልጆች (ባላየ ባልሰማ ሙድ) እንደሚሉት አይነት ሊያልፈው ነበር፡፡ ነገር ግን ሰማያዊዎቹ ፈቃድ አንጠይቅም ካሳወቅናችሁ ይበቃችኋል ሰልፉን ባልነው ሰዓት እና ቦታ ከማድረግ አንቦዝንም እና አስቡበት ብለው ለበላይ አቤት አሉ፡፡ ያኔም የበላዩ የኦቦ ኩማ ደመቅሳ ቢሮ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ አጉል ግርግር ከሚፈጠር መደራደር ይሻላል ብሎ ዘየደ፡፡ ተደራደረ ለግንቦት 25ም ሰልፉ እውቅና ተሰጠው፡፡ እኛም የሰማያዊን አስጨናቂነት፤ የከንቲባውንም ተጨናቂነት አደነቅን፡፡
ሳስበው ሳስበው ኢህአዴግ የዛን ጊዜ አጣብቂኝ ውስጥ ሆኖ ለሰልፉ እውቅና ከሰጠ በኋላ ደብሮታል፡፡ እንደውም ቀፈፈኝ ብሎ እውቅናውን ቢያነሳ ራሱ ደስ የሚለው ይመስለኛል፡፡ በተለያየ ማህበራዊ ድረ ገጾች ሰልፉ እንዲደነቃቀፍ ስልታዊ እንቅስቃሴ የሚያደረጉ ምልምሎችን እየተመለከትን ነው፡፡ እነዚህ ምልምሎች አንድ ጊዜ “የሰልፉ ቀን ተቀይሯል” ሲሉ ሌላ ጊዜ ደግሞ “ቦታው ተለውጧል” እያሉ የተለያዩ የሚያምታቱ መረጃዎችን እያቀበሉን ነው፡፡ እነዚህ መረጃዎች ከሚያበጁት የሚያፈርሱት ይበልጣልና መረጃ ሳሆኑ “መራጃ” ናቸው ብያቸዋለሁ፡፡ (በቅንፍም የግንበኛ ልጅ መሆን ጥቅሟ ይቺ ናትኮ በእውኑ፤ “መራጃ” ማለት ምን እንደሆነ ከእኛ ውጪ የሚያውቁ ጥቂቶች አይደሉምን… “መራጃ” ድንጋ ለመፈረካከስ የሚያገለግል አንዳች ብረት ነው)
ለማንኛውም አስከ አሁን ድረስ እንደሰማነው ሰላማዊ ሰልፉ በዕለቱ እና በሰዓቱ ይከናወናል፡፡ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በሰልፉ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ኢህአዴግ ደብሮታል፡፡ ኢህአዴግ ቀፎታል፡፡ ኢህአዴግ ሙዱ “ተከንቷል”!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar