ኢሳት ዜና:-ባለፈው ሳምንት ከአፋር ጋድሌ ወታደራዊ ንቅናቄ ጋር በተያያዘ 14 ሰዎች መታሰራቸውን፣ ከታሰሩት መካከልም፣ የቀበሌው ሊቀመንበር፣ የወረዳ ምክር ቤት አባል፣ አንድ ፖሊስ እና ሽማግሌዎች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሎአል።
አብዛኞቹ የተያዙት በፌደራል ፖሊሶች ሲሆን በቅርቡ 70 የሚሆኑ የአፋር ወጣቶች አፋር ጋድሌ የሚባለውን የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ የሚገኘውን ድርጅቶች መቀላቀላቸውን ተከትሎ ነው።
ከታሰሩት መካከል የሩማይቶ ቀበሌ ሊቀመንበር ፣አቶ አብዱሊ ሞሚን፣ አፈጉባኤው ኖር አሊ፣ የፖሊስ አዛዡን ያዮ አሊ ፣ አብዱጀሊል አንፈሬ፣ ሙሀመድ አሊ፣ ሙሀመድ ኢሴይ፣ ሙሀመድ ዩሱፍ፣ አቦ አብዱ፣ ፎካ ሀሌ፣ ሀቢብ መሀመድ፣ አብዱል ሁሴን፣ የ70 አመቱ የሱፍ አህመድ፣ እና አብዱ ኑር ይገኙበታል።
በጉዳዩ ዙሪያ የአፋር ጋዲሌ ወታደራዊ አዛዥ የሆኑትን ኮሎኔል መሀመድ አህመድን አነጋገርናቸው፣ ኮሎኔልም የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውንና አብዛዦቹ ከእርሳቸው ጋር ዝምድና ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል። አንዳንዶች የት እንደገቡም እንደማያውቁ ኮሎኔሉ ገልጸዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ በአፋርና በሶማሊ ሀውያ ጎሳዎች መካከል ትናንት በአዋሽ አርባ አካባቢ በተደረገ ከፍተኛ ውጊያ 5 አፋሮች ሲገደሉ 15 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል። ግጭት ከወር በፊት ከተካሄደው ግጭት ጋር የተያያዘ ነው። በሶማሊ ሀውያ ጎሳዎች በኩል የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልታወቀም።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስትን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የሶማሊ ክልል ሚሊሺያዎች ከክልላቸው አልፈው በአፋር ክልል ስለሚፈጽሙት ጥቃት የሚሊሺያ አዛዡን የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ አብዲን ለማግኘት ሙከራ ብናደርግም አዲስ አበባ ለስብሰባ መሄዳቸውን ጸሀፊያቸው በመግለጽ ሳይሳካ ቀርቷል።
በቤይሩት በቤት ሰራኝነት ተቀጥራ የምታገለግል አንዲት ኢትዮጵያዊ ወጣት፣ አሰሪዋን ሆን ብላ በፈላ ውሃና በእሳት አቃጥላለች በሚል በቁጥጥር ስር መዋሏን ደይሊ ስታር የተሰኘው ድረ ገጽ ዘገበ።
ኢሳት ዜና:-በዚሁ የዜና ዘገባ መሰረት በሰሜን ቤይሩት ግዛት ማስቲታ ጀቢል በተሰኘ ስፍራ የምትኖረው የ70 ዓመቷ አረጋዊት ወ/ሮ ሳሚያ፣ ድንቅነሽ የተሰኘች የ24 ዓመት ዕድሜ ያላት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛዋ፣ ከነሃስ በተሰራ ቅርፃ ቅርጽ ጭንቅላቷን ከመታቻት በኋላ የፈላ ውሃ ፊቷ ላይና ደረቷ ላይ በማፍሰስ ጉዳት አድርሳባታለች።
አደጋ የደረሰባት ግለሰብ ለህክምና በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል እንደተወሰደች የሚያትተው ይኸው ዘገባ፣ ፖሊስ የወንጀሉን መንስዔ ለማጣራት ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል። በቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እሕቶቻችን በአሰሪዎቻቸውና በደላሎች እጅግ አስከፊ ግፍና በደል እንደሚፈፀምባቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ በተለያየ መንገድ ለሞትና ለአካል ጉዳት፤ እንዲሁም ለአዕምሮ ሕመም የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን እህቶች ቁጥራቸው እጅግ በርካታ እንደሆነ ይታወቃል።
እንግሊዝ አገር የሚታተመው ዘጋርዲያን የተሰኘው ጋዜጣ ከአንድ ዓመት በፊት እንደዘገበው ከሆነ በሊባኖስ ውስጥ ከ60-80ሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያዉያን በቤት ሰራተኝነትና በተመሳሳይ የስራ መስክ ተቀጥረው እንደሚያገለግሉ የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ ህጋዊ የሆኑት 43ሺህ ያህሉ ብቻ ናቸዉ።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar