- የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደለት
- ሁለት ተጠርጣሪዎች በምርመራ ወቅት መደብደባቸውን ተናገሩ
‹‹ተያዘ የተባለው ሰነድ ሁሉ በሀብት ምዝገባ ያስመዘገብኩት ነው›› አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ
የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ ቡድን፣ በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉ ተጠርጣሪዎች እንዲቋረጡ ከተደረጉት 60 የክስ መዝገቦች ውስጥ 28 ያህሉን መሰብሰቡን ግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡
መርማሪ ቡድኑ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ እንዳስረዳው፣ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ባለፉት 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ላይ የሠራውን የምርመራ ሥራ እንዳብራራው፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥራዎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ሰብስቧል፡፡ ከተለያዩ ባንኮች በተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ላይ ከአራጣ ብድር ጋር የተያያዙ ማስረጃዎችን፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ (መኒ ላውንድሪንግ) መጠቀምን የሚያሳዩ ሰነዶችን መሰብሰቡን ገልጿል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ጨምሮ እንደገለጸው፣ ተጠርጣሪዎቹ በአራጣ ብድር የተከሰሱ ሰዎችን ክስ ያቋረጡባቸውን የክርክር መዝገቦችን መሰብሰቡንና በኮንትሮባንዲስቶች ላይ በፍርድ ቤት ተጀምረው ከነበሩትና በሕገወጥ ጥቅም ከተቋረጡት 60 የክስ መዝገቦች ውስጥ 28 የሚሆኑት መሰብሰቡንም ገልጿል፡፡
በአንድ የንግድ ድርጅት ላይ ተወስኖ የነበረን ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ግብር ወደ ሦስት ሚሊዮን ብር የተቀነሰበትን ሰነድ፣ እንዲሁም 87 ሚሊዮን ብር ግብር እንዲከፍል ተወስኖበት የነበረን ድርጅት፣ በሕገወጥ መንገድ ወደ ስምንት ሚሊዮን ብር ዝቅ የተደረገበትን ሰነድም መሰብሰቡን ቡድኑ ለችሎቱ ተናግሯል፡፡
ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኦዲት ሊያደርጋቸው የሚገቡ ስምንት ኩባንያዎች መኖራቸውን ማረጋገጡን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ ኦዲት የሚደረጉትን ለይቶ መጨረሱንና ለመሥሪያ ቤቱ ደብዳቤ መጻፉን አሳውቋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የምስክሮችን ቃል በከፊል መቀበሉንና የንብረት ጥናትም በከፊል መሥራቱን ገልጾ፣ የቀሩትንም የምርመራ ሥራዎች ጠቁሟል፡፡
ያላግባብ ክሳቸው የተቋረጡ 40 የክስ መዝገቦችን መሰብሰብ፣ በሕገወጥ መንገድ ግብር እንዲቀነስ የተደረገባቸውን ሰነዶች፣ ሕጋዊ በማስመሰል ሕገወጥ ገንዘብን ለመጠቀም የተዘጋጁ ሰነዶችን መሰብሰብ፣ የስምንት ኩባንያዎችን ግብር ማጣራት፣ የኦዲተሮችን ቃልና የቀሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው በመግለጽ፣ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ላለፉት 14 ቀናት በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሠራቸውንና የሚቀሩትን ሥራዎች ለችሎቱ ካሳወቀ በኋላ፣ በጠየቀው ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜን በሚመለከት አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በችሎቱ የተፈቀደላቸው፣ በኢትዮጵያ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የሕግ ማስከበር ኃላፊ የምርመራ መዝገብ ሥር ያሉ 12 ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡
መርማሪ ቡድኑ በጥቅል ከመግለጽ ባለፈ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ምን እንደሠራ፣ ተጠርጣሪው ከሠራው ወይም ካጠፋው ነገር አንድም እንኳን እንዳልተነገረው፣ ምን ሠርቶ ምን እንደቀረው እስካሁን የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት፣ የአቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር ጠበቃ ናቸው፡፡ ደንበኛቸው ተጠርጥረው የታሰሩት ክስ በማቋረጥና ባልተፈቀደ የፍራንኮቫሉታ ፈቃድ ሲሚንቶ ማስገባት እንደነበር ያስታወሱት ጠበቃው፣ መርማሪ ቡድኑ 14 ቀናት የምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ሲጠይቅ ያልተናገራቸውና ለደንበኛቸው ያልተገለጹላቸው ሰነዶችን ማሸሽ፣ ንብረት ከተገቢው በላይ ማፍራትና ከባለሥልጣናት ጋር መመሳጠር፣ ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም፣ አራጣ ማበደርና ግብር ያላግባብ መቀነስ የሚሉት የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥስና ያላግባብ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት ስለተጠረጠሩበት ወንጀል በተያዙበት ወቅት ሊነገራቸው ይገባ እንደነበር የገለጹት ጠበቃው፣ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ መርማሪ ቡድኑ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ሲጠይቅ ያስመዘገባቸው፣ ‹‹የሲሚንቶው ጉዳይ ምን ሆነ? ሰነድ ጠፋ ወይስ ምን ሆነ? ሊገለጽልን ይገባል፤›› ካሉ በኋላ፣ በወቅቱ ያልተገለጹና እንደ አዲስ ክስ የቀረቡት ጉዳዮች ተገቢ ጥያቄዎች ባለመሆናቸው የ14 ቀናት ተጨማሪው የጊዜ ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
አቶ ገብረ እግዚአብሔር እንዲናገሩ ችሎቱን ጠይቀው ሲፈቀድላቸው እንደተናገሩት፣ በምን ተጠርጥረው እንደታሰሩ አያውቁም፡፡ ለምርመራ ሲቀርቡ በተደጋጋሚ የሚቀርብላቸው ጥያቄ ስለንብረታቸው ነው፡፡ የልብ ሕመምተኛ መሆናቸውንና ንብረታቸውም የተመዘገበ መሆኑን በመግለጽ፣ ማወቅ የሚፈልገው አካል በፈለገ ጊዜ ሊያውቅ እንደሚችል ገልጸው፣ እሳቸው ግን በአንድ በተዘጋ ክፍል ውስጥ መሆናቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
እምባና ሳግ እየተናነቃቸው ዝቅ ባለ ድምፅ መናገር የቀጠሉት አቶ ነጋ፣ በታሰሩበት ክፍል ውስጥ ሁለት ጊዜ ራሳቸውን ስተው ወድቀው እንደነበርና መደብደባቸውንም ገልጸዋል፡፡
ነጋዴ በመሆናቸው ሀብት ማፍራት እንደሚችሉ የተናገሩት ተጠርጣሪው፣ ምርጥ ታክስ ከፋይ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ መሆናቸውን፣ ለአገራቸው 33 ሚሊዮን ብር መድበው በ23 ሚሊዮን ብር ያስገነቧቸውን ፖሊ ቴክኒክ ትምህርት ቤቶችን ለሕዝብና ለመንግሥት ማስረከባቸውን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡
‹‹አገሬን ያወቅኋት አሁን ነው፤ ዜጋ ነኝ ለማለት አይቻልም፤›› ያሉት አቶ ነጋ፣ ሲደበደቡ ራሳቸውን ስተው እንደሚወድቁ አስታውቀው፣ ኢሰብዓዊ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ጠቁመዋል፡፡ የደም ግፊትና የስኳር ሕመምተኛ መሆናቸውንና የልብ ቱቦ ተገጥሞላቸው ያሉ ታማሚ በመሆናቸው ክትትል ካልተደረገላቸው ለሕይወታቸው አስጊ መሆኑን ጠበቃቸው አክለዋል፡፡
የመርማሪ ቡድኑን በጥቅል የመግለጽ ሁኔታ እንደ አቶ ነጋ እሳቸውም እንደሚቃወሙት የተናገሩት የባለሥልጣኑ ሠራተኛ አቶ ጥሩነህ በርታ ሲሆኑ፣ መርማሪዎች ወደ ምርመራ ክፍል በመውሰድ የሚጠይቋቸው ከሥራቸው ጋር የማይገናኝ፣ መረጃ እንደሚያውቁ ተደጋጋሚ ጥያቄ እንደሚቀርብላቸውና በማያውቁት ጉዳይ ላይ መረጃ ሰብስበው ክስ ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው ተጠርጥረዋል በተባሉበት ክስ የማቋረጥ ወንጀል መጠየቅ ያለባቸው እሳቸው ሳይሆኑ ከእሳቸው በላይ ያሉ ኃላፊዎች እንደሆኑ የተናገሩት ተጠርጣሪው፣ እነሱ ሳይጠረጠሩ እሳቸውን አስሮ ማሰቃየት ኢሰብዓዊ ድርጊት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሱሪያቸውን ከፍ በማድረግ እግራቸውን ለችሎቱ እያሳዩ መደብደባቸውን የገለጹት ተጠርጣሪው፣ ውኃ እየተደፋባቸው እንደተገረፉ ለበላይ ኃላፊ ቢያመለክቱም፣ መርማሪዎቹ በድጋሚ ሲያገኟቸው ‹‹እንኳን ለኃላፊ ለማንም ብትናገር አንተውህም›› እንዳሏቸው ሲገልጹ መርማሪ ቡድኑ አቤቱታቸውን ተቃውሟል፡፡ የተቃወመበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ፍር ቤቱ ሲፈቅድለት፣ ተጠርጠሪው የሚያነሱት ጉዳይ አስተዳደራዊ መሆኑን በመጠቆም፣ ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደማይገባ አመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹አስተያየታቸው ሊደመጥ ይገባል፡፡ ኮሚሽኑ ከሰብዓዊ መብቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ አቤቱታዎችን እንዲያስተካክል በተደጋጋሚ ቢታዘዝም ሊታረም አልቻለም፤›› በማለት ተጠርጣሪው አቤቱታቸውን እንዲቀጥሉ አዟል፡፡
ተጠርጣሪው ቃላቸውን እስካሁን የተቀበላቸው እንደሌለ በመግለጽ፣ ቢሮአቸውንም ሆነ ቤታቸውን ቡድኑ በርብሮ ምንም አለማግኘቱን፣ እያንገላታቸው ያለው አዲስ ማስረጃ ለማሰባሰብ እንጂ በእሳቸው ላይ ምንም ዓይነት ጭብጥ እንደሌለው ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብላቸው አመልክተዋል፡፡
የባለሥልጣኑ ኦዲተር መሆናቸውንና ደመወዛቸው ከአሥር ሺሕ ብር በላይ መሆኑን፣ የተጣራ 5,600 ብር አካባቢ እንደሚያገኙና ሥራ የሌላቸውን ባለቤታቸውን ጨምሮ፣ ልጆቻቸውንና የእህታቸውን ልጅ ጭምር የሚያስተዳድሩት እሳቸው መሆኑን የተናገሩት አቶ በላቸው በየነ ሲሆኑ፣ መርማሪ ቡድኑ የልጃቸው ላፕቶፕ ጨምሮ በመሥሪያ ቤታቸውና በቤታቸው ያለውን ሁሉንም ሰነድ ስለወሰደ በዋስ እንዲለቃቸው ጠይቀዋል፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በጥቅሉ ሳይሆን እያንዳንዱ ተጠርጣሪ የተጠረጠረበትን ወንጀል ለይቶ ማቅረብ እንደሚገባው የገለጹት ተጠርጣሪው፣ መንግሥት በመደባቸው በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ለ27 ዓመታት መሥራታቸውን፣ አብዛኛው ሥራዎቻቸውን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጭምር ያውቁት እንደነበር፣ ቤተሰብንም ሆነ ሌላ አካል ወይም ማንንም ለመጥቀም በሚል ሕገወጥ ሥራ ሠርተው እንደማያውቁ አስረድተዋል፡፡
በቅርቡ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ሥልጠና ለመስጠት እሳቸውና ሌላ አንድ ሰው ተመርጠው እንደነበር የተናገሩት ተጠርጣሪው፣ መርማሪ ቡድኑ ኩባንያዎችን ኦዲት እንዲያደርጉለት ለዋና ኦዲተሩ ደብዳቤ መጻፉን አስታውሰው፣ ‹‹ኦዲት የሚያደርጉት ሠልጥነው ነው ወይስ?›› ሲሉ ፍርድ ቤቱ ‹‹ይኼ በማስረጃ ጊዜ የሚታይ ነው፤›› በማለት አስቁሟቸዋል፡፡
አቶ ገብረ ዋህድ ወልደጊዮርጊስ ሁለት ሕፃናት ልጆቻቸው እስካሁን ድረስ የት እንዳሉ እንደማያውቁ፣ የሚረዳቸው ወይም የሚቀልባቸው ሰው ባለመኖሩ ሥጋት ላይ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት፣ ባለቤታቸው ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይና እህታቸው ወ/ሮ ንግስቲ ተስፋይ፣ እንዲሁም በውጭ አገር ለሰባት ዓመታት ቆይቶ ከመጣ አራት ወራት ብቻ የሆነው የወ/ሮ ንግስቲ ልጅ አቶ ሀብቶም ገብረመድኅን በዋስ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
እሳቸው የተጠረጠሩበትን የወንጀል ሰነድ አሽሽተዋል በሚል ቤተሰቦቻቸው መታሰራቸው አግባብ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ገብረ ዋህድ፣ ሸሽቷል የተባለው ሰነድ ኮሚሽኑ ባወጣው የሀብት ማስመዝገብ አዋጅ የተመዘገበና ኮሚሽኑ የሚያውቀው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የባለቤታቸው እህት የ60 ዓመታት አዛውንት መሆናቸውን፣ ከአቅም በላይ በሆነ ውፍረት ክብደታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ዕርዳታ እንደሚፈልጉና የደም ብዛትና የስኳር ሕመምተኛም ስለሆኑ ከተቻለ በነፃ ካልሆነም በዋስ አንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ኮሚሽኑ የቀረው መደበኛ ሥራው መሆኑን የገለጹት አቶ ገብረ ዋህድ፣ ከእሳቸውና ከቤተሰባቸው ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ በዋስ እንዲለቀቁ ወይም የምርመራ ጊዜው አንዲያጥር አመልክተዋል፡፡
የአቶ ስዬ አብርሃ ወንድም አቶ ምሕረተ አብ አብርሃ ባቀረቡት አቤቱታ እንደገለጹት፣ የሚተዳደሩት በንግድ ነው፡፡ ከ1993 ዓ.ም. እስከ 1999 ዓ.ም. ድረስ በታሰሩበት ወቅት ንብረታቸውን ያስተዳድር የነበረው ኮሜት የሚባል ድርጅት ነበር፡፡ ንብረታቸውን በሚመለከት ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር አለመግባባት ላይ ደርሰው፣ መብታቸውን ያስከበሩት በፍርድ ቤት ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ‹‹ተጠርጥረሃል›› ከተባሉበት ክስ ማቋረጥ፣ ኮንትሮባንድ፣ አራጣና ሌሎች ጉዳዮች ጋር እንደማይገናኙ ተናግረዋል፡፡ ከነበሯቸው ከ15 በላይ ተሽከርካሪዎች ልጆቻቸውን እያስተዳደሩ ያሉት በሁለት ተሽከርካሪዎች በሚያገኙት ገቢ ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ምህረተ አብ፣ ባለሥልጣኑ ከፍተኛ ግብር ጭኖባቸው ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ በፍርድ ቤት ባደረጉት ክርክር መብታቸውን ማስከበራቸውን ገልጸው፣ አሁን የተጠረጠሩበትን ምክንያት ስለማያውቁት ዋስትና እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡
ሁሉም ተጠርጣሪዎች በአጠቃላይ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው የምርመራ ውጤት ወንጀሉ ጥቅል መሆኑን፣ በተያዙበት ወቅት ያልተነገራቸው የወንጀል ክስተት እየቀረበባቸው መሆኑን፣ ማስረጃ ተሰብስቦ ቢያልቅም መብታቸው አለመከበሩን፣ ጥርጣሬዎቹ ከሰነድ ጋር የተገናኙ በመሆናቸው ታስረው ሊቆዩ እንደማይገባና ዋስትና ሊፈቀድላቸው እንደሚገባ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደማያስፈልግ የሚሉትን ሐሳቦች ሁሉም ያነሱ ሲሆን፣ በተናጠል ደግሞ የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን፣ የጤና ችግር እንዳለባቸው፣ የመብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው መሆኑን፣ ከተያዙ ጀምሮ ቃላቸውን አለመስጠታቸውን ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ በምርመራ መዝገቡ የቀረቡት 12 ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ተጠርጣሪዎቹ ላነሷቸው ጥያቄዎች በሰጠው ምላሽ፣ የተጠረጠሩበት ወንጀል የተፈጸመው በተናጠል ሳይሆን በቡድንና ውስብስብ በሆነ መንገድ መሆኑን ገልጿል፡፡ ጉዳዩ አገራዊ በመሆኑ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑንም አስገንዝቧል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች መሆናቸውን በመጠቆም፣ ሥልጣንንና ገንዘብን ተገን በማድረግ ውስብስብ በሆነና በጥቅም በመመሳጠር በአገር ገቢ ላይና በሌሎች የሕዝብ ጥቅሞች ላይ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን አስረድቷል፡፡ ክስ እንዲቋረጥና ከውጭ የሚገቡ የንግድ ዕቃዎች ቀረጥ እንዳይከፈልባቸው ሲደረግ፣ ለጠቋሚዎች የሚከፈል አበል ለራስ ጥቅም ሲደረግ፣ አንድ ተጠርጣሪ ብቻ የሚሠራው ሳይሆን በቡድንና በመመሳጠር የሚሠራ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ ድርጊቱ በአጠቃላይ በትብብር የተሠራ መሆኑንና ለቀሪ የምርመራ ጊዜ ተጨማሪ 14 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ አመልክቷል፡፡
ቃል አልሰጠንም ያሉት ተጠርጣሪዎች ቃላቸውን መስጠታቸውን በተለያየ መንገድ መግለጻቸውን፣ ሰብዓዊ የመብት ረገጣ ደርሶብናል ያሉት ተጠርጣሪዎችም በማስረጃ የቀረበ ባለመሆኑ ሊታመን እንደማይችል መርማሪ ቡድኑ ገልጾ፣ ዋስትና ቢፈቀድ የሰነድና የምስክሮች ቃል ሊያጠፉበት እንደሚችሉ በመናገር ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ በማን ላይ ምን እንደተሠራ፣ በማን ላይ ምን እንደቀረው በግልጽ አለማስቀመጡን፣ ይኼም ለክርክር በር መክፈቱን፣ በርካታ ምስክሮች የቀሩት በማን ላይ እንደሆነና ሰነድም ሆነ ሌላ መረጃ ለማጣራት የተፈለገው በማን ላይ እንደሆነ ግልጽ አለመደረጉ አግባብ አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ በቀጣይ ቀጠሮ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ በተናጠል የተሠራው ተዘርዝሮ እንዲቀርብ አዟል፡፡
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ከድርጊቱ ውስብስብነት አንፃር የተጠርጣሪዎች ዋስትና ጥያቄን አለመቀበሉን፣ የመርማሪ ቡድኑን 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜያት መፍቀዱን አስታውቆ፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን አቤቱታ ኮሚሽኑ አጣርቶ እንዲያቀርብ በማዘዝ ለሰኔ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በዕለቱ መቅረብ የነበረበት የእነ አቶ መላኩ ፈንታ የምርመራ መዝገብና የእነ አቶ መሐመድ ኢሳ የምርመራ መዝገብ በመሆኑ፣ መዝገቡ የቀረበ ቢሆንም ቀኑ በመምሸቱ ለግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. በይደር ተቀጥሯል፡፡ በእነ መሐመድ ኢሳ የምርመራ መዝገብ ፍሬሕይወት ጌታቸው የተባሉ ተጠርጣሪ በመካተታቸው ጠቅላላ የተጠርጣሪዎች ቁጥር 55 ደርሷል፡፡
ግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሹማምንት፣ ታዋቂ ነጋዴዎችና ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ችሎት ለመታደም በፍርድ ቤት የተገኙ ታዳሚዎች ከችሎቱ አቅም በላይ ስለነበሩ በርካቶች ችሎቱን መከታተል አልቻሉም፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar