‹‹ለልጄ ወተት መግዣ ብቻ አንድ ሺሕ ብር ይሰጥልኝ›› የበምጫ ትራንዚት ባለቤት
በተጠረጠሩባቸው የተለያዩ የሙስና ወንጀሎች ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙት በሚኒስትርነት ማዕረግ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ መታመማቸውን ጠበቃቸው ግንቦት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው አስታወቁ፡፡
ጠበቃው አቶ መላኩ በአስቸኳይ ሕክምና እንዲደረግላቸው ጠይቀው፣ “እኚህ ሰው በጠና ስለታመሙ የታሪክ ተወቃሽ እንዳንሆን፤” ብለዋል፡፡
የአቶ መላኩን ጤንነት በሚመለከት ጠበቃው በዝርዝር ጠይቀው የሕመማቸው ዓይነትና ደረጃ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ባይረዱም፣ መልካቸው ቢጫ ሆኖ እንዳዩዋቸው ገልጸዋል፡፡ ለምን እንዳላነጋገሩዋቸው ሲጠየቁ በቂ ጊዜ እንዳልነበራቸው የገለጹት ጠበቃው ከእሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸውን፣ ነገር ግን ሆስፒታል ይሂዱ ወይም አይሂዱ አለማወቃቸውንም አስረድተዋል፡፡
በአጃቢ ሆነው ሕክምና እንዲያገኙ ጠበቃው ላነሱት ጥያቄ፣ ስለመታመማቸው የሚገልጽ ማስረጃ ከክሊኒክ ወይም ከሆስፒታል እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ያለማስረጃ ትዕዛዝ መስጠት እንደማይቻል ፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
አቶ መላኩ መንግሥት የሚያውቀውና በአገር ውስጥ ሕክምና የማይድን ሕመም እንዳለባቸውና በውጭ አገር እየታከሙ እንደነበር፣ ለፍርድ ቤቱ ራሳቸውና ጠበቃቸው ማስረዳታቸው የሚታወስ ነው፡፡
በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ቀጥሮት የነበረውን የእነ አምባውሰገድ አብርሃ የምርመራ መዝገብን ተመልክቷል፡፡ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የናዝሬትና ሚሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆችን ጨምሮ 11 ተጠርጣሪዎች ቀረጥ በማጭበርበር፣ ክስ በማቋረጥ፣ የኮንትሮባንድ ዕቃ ሳይፈተሽ እንዲያልፍ በማድረግና ተገቢ ያልሆነ ሀብት በማከማቸት የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ወንጀል ችሎትና ለተጠርጣሪዎቹ አስረድቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችለውን የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን መሰብሰቡንና ቃል መቀበል መጀመሩን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ ቀሪ ሰነድ ማሰባሰብ፣ የምስክሮችን ቃል መቀበልና የተሰበሰቡ ሰነዶችን የመለየት ሥራ እንደሚቀረው በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
አቶ አምባውሰገድ የልብ ሕመምተኛ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት፣ መርማሪ ቡድኑ በብርበራ የሚፈልገውን ማስረጃ በመውሰዱና እሳቸውም ሊያጠፉት የሚችሉት ማስረጃ ስለሌለ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ቃለአብ ዘርአብሩክም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ የናዝሬት ጉምሩክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያዴሳ ሚደቅሳ ሥራ ከማስተባበር ውጭ ጣልቃ ገብተው የተጠረጠሩበትን ወንጀል እንዳልፈጸሙና ከተያዙ ሰባት ቀናት እንዳለፋቸው በማሳወቅ፣ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜን ተቃውመው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡
በሕገወጥ መንገድ በሕገወጦች ተይዞ የነበረን 46 ኪሎ ግራም ወርቅ በመያዝ ከመንግሥት ምስጋናና 100 ሺሕ ብር ሽልማት ማግኘታቸውን የገለጹት የባለሥልጣኑ ባልደረባ አቶ እሸቱ ግረፍ ናቸው፡፡ በተመሰገኑበት ሥራ ሌላ ነገር ሊሠሩ እንደማይችሉ፣ መርማሪዎችም አሉ የተባሉ ሰነዶችን በብርበራ የወሰዱ በመሆናቸውና የሚቀር ነገር የሌለ በመሆኑ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
አቶ ጌታሁን ቱጂ፣ አቶ መላኩ ግርማ፣ አቶ አስፋው ሥዩም፣ አቶ ጌታነህ ግደይና አቶ ዮሴፍ አዳዊ የተባሉ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች የተጠረጠሩበት ጉዳይ መርማሪ ቡድኑ ካለው ጋር የማይገናኝና የሥራ ድርሻቸውም የማይገናኝ መሆኑን በማስረዳት፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
አርክቴክት በእግዚአብሔር አለበል መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው የመጠርጠሪያ ድርጊት ከእሳቸው ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ገልጸው፣ የመንግሥትና የግል የሆኑ ከ60 በላይ ፕሮጀክቶች እንዳሏቸው በማስረዳት፣ ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸው በመሆኑ ዋስትና እንዲከበርላቸው ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡
የባህር ዳርና የጎንደር ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችን እንደሚያማክሩ የተናገሩት አቶ በእግዚአብሔር፣ ከ131 በላይ ደረጃ አንድ ተቋራጮችን ከማማከራቸውም በተጨማሪ፣ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው እሳቸው የሥራውን ጥራት ማረጋገጥ ስላለባቸው ሥራ እየቆመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ መንግሥትም ሆነ ሠራተኞች እንደሚበደሉ የገለጹት አርክቴክቱ፣ ሰነዶችን በሚመለከት ሁሉም ሰነዶች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ በመሆናቸው ሊሰውሩና ሊያጠፉ የሚችሉበት አጋጣሚ ስለሌለ፣ እሳቸውን አስሮ ማቆየቱ ምንም ጥቅም እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
ሥራ ከሚበላሽና ሠራተኛ ከሚበተን ፍርድ ቤቱ ውክልና ለሌላ ሰው የሚሰጡበትን መንገድ እንዲያመቻችላቸው የጠየቁት አቶ በእግዚአብሔር፣ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰነዶች እንደተያዙባቸው በመግለጽ እንዲለቀቁላቸው ጠይቀዋል፡፡ ክፍያ የሚፈጽሙት በየዕለቱ ቢሆንም ማህተምና ቼክ ስለተወሰደባቸው የሠራተኞች ደመወዝ፣ የገቢ ግብርና የጡረታ ክፍያ መክፈል አለመቻላቸውንም አስረድተዋል፡፡ አገር እያለሙ መሆኑን በመናገር በዋስ ሆነው ሥራቸውን እየሠሩ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የጠየቁት አቶ በእግዚአብሔር፣ በመርማሪዎች እንደተነገራቸው ‹‹ሰው ታውቃለህ›› በሚል ብቻ መታሰራቸውን አስረድተዋል፡፡
የችሎቱን ታዳሚዎች ያሳዘነና ከንፈር ከማስመጠጥ አልፎ እንባ እስከ ማፍሰስ ያደረሳቸው የበምጫ ትራንዚት ባለቤት አቶ ዘለቀ ልየው ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ ነው፡፡ አቶ ዘለቀ የጉምሩክ አስተላላፊ ትራንዚተር መሆናቸውን በጠበቃቸው በኩል ገልጸው፣ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ስድስት ቀናት ቢሆናቸውም እስከ ግንቦት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ቃላቸውን አለመስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 (4) መሠረት አንድ በቁጥጥር ሥር የዋለ ዜጋ ቃሉን እንዴት መስጠት እንዳለበት የተቀመጠው ድንጋጌም መጣሱን አመልክተዋል፡፡
ቢሯቸው መታሸጉንና በቢሯቸው ውስጥ ያለው ሰነድ ሳይለይ የሚያስፈልገውም ሆነ የማያስፈልገው ሰነድ አንድ ላይ በመታሸጉ፣ በእሳቸውም ላይ ሆነ በመንግሥት ላይ ጉዳት እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡ ኤልሲ የተከፈተባቸው፣ ሥራ የተጀመረላቸውና ያልተጀመረላቸው ነጋዴዎች ብሔራዊ ባንክ ሄደው እንዳይጠይቁ መቸገራቸውን፣ ወደ አገር ውስጥ ያልገቡ ዕቃዎች ሰነዶች በሙሉ ስለተቆለፈባቸው ለወደብ የሚከፈለው በዶላር መሆኑንና ተጎጂው አገር ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የታሸገባቸው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመሆኑ ድርጊቱ ሕገወጥ መሆኑን በመጠቆም እንዲከፈትላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠበቃቸው ጠይቀዋል፡፡
ሕፃን ልጃቸው እሳቸው ሲያዙ ተመልክቶ እስካሁን በመሳቀቅ ላይ በመሆኑ እንዲያገኛቸው እንዲታዘዝላቸውም አመልክተዋል፡፡ ተጠርጣሪው እንዲናገሩ ጠይቀው ሲፈቀድላቸው እምባ እየተናነቃቸው፣ ‹‹እቤቴ አንድም ብር እንኳን ሳይተው መርማሪዎቹ ሁሉንም ገንዘብ ወስደውታል፡፡ የምጠይቀው ለልጄ ወተት መግዣ ብቻ አንድ ሺሕ ብር እንዲሰጡልኝ ነው፤›› ካሉ በኋላ መናገር አልቻሉም፡፡ የችሎቱ ታዳሚዎችም በተጠርጣሪው ንግግር የተወሰኑት ሲያለቅሱ የተወሰኑት ተክዘው ተስተውሏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከተናገሩ በኋላ ምላሽ እንዲሰጥ በፍርድ ቤቱ የታዘዘው መርማሪ ቡድኑ፣ አንዳንድ ጥያቄዎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች በመሆናቸው በቢሮ በኩል እንደሚፈቱ ተናግሯል፡፡ የዋስትና መብት ጥያቄን በሚመለከት ጉዳዩ ውስብስብ መሆኑን በመጥቀስ ቢለቀቁ ሰነድ፣ ምስክርና ሌሎች ማስረጃዎችን ሊያጠፉበት እንደሚችሉ በመግለጽ፣ ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግና የ14 ቀናት ጊዜ ምርመራ እንደፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡
ሌላው ፍርድ ቤቱ ችሎቱ ከመጀመሩ በፊት ለመርማሪ ቡድኑ ያነሳው ጥያቄ፣ ተጠርጣሪዎች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበር ያዘዘውን ትዕዛዝ ኮሚሽኑ ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ቢታዘዝም፣ ለምን ሳይፈጽም እንደቀረ እንዲያብራራ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ የተጠርጣሪዎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት መከበር አለመከበር የመከታተል ግዴታ እንዳለበትም ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጠው ተጠርጣሪዎች በስድስት መዝገብ ተከፋፍለው የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ሥራው ውስብስብ በመሆኑና ለብርበራ ተጠርጣሪው ጭምር የሚወጣበት ጊዜ በመኖሩ፣ ከሕግ አማካሪ ጋር የሚገናኙበትን ጊዜ ረቡዕና ዓርብ መደረጉን፣ የጊዜ ቀጠሮ ያላቸውንም በመለየት ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር እያገናኘ መሆኑን ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መርማሪ ቡድኑ እንዳብራራው ጉዳዩ ውስብስብ መሆኑን ፍርድ ቤቱ መገንዘቡን ገልጾ፣ የተመርማሪዎች ዋስትና ጥያቄን ውድቅ ማድረጉን በማስረዳት ለመርማሪ ቡድኑ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በመፍቀድ ለግንቦት 26 ቀን 2005 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ማለትም በቤተሰብ፣ በሕግ አማካሪና በሐኪም የመጎብኘትና የማግኘት መብታቸውን በሚመለከት የማዕከላዊ እስረኛ ኃላፊ ኮማንደር ብርሃኑ አበበ ቀርበው እንዲያስረዱ በታዘዘው መሠረት ኮማንደሩ ግንቦት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. አስረድተዋል፡፡
ኮማንደር ብርሃኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ሁሉም የሕግ አማካሪዎች ደንበኞቻቸውን አግኝተዋል፡፡ በችሎት የተገኙም የሕግ አማካሪዎች ከአቶ ከተማ ከበደ ጠበቃ በስተቀር ሁሉም መገኘታቸውን መስክረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪዎችና የሕግ አማካሪዎች የተገናኙበት ቀን ሪፖርት እንዲደረግና አቶ ከተማ ከበደን በሚመለከትም ጥብቅ ትዕዛዝ በማስተላለፍ ለግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ሪፖርት እንዲያደርጉ በድጋሚ አዟል፡፡
Source: ethiopianreporter
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar