Dedicated to Ato Girma Alemayehu
የድርጅቱ መልእክት
የድጋጋፍ ድርጅታችን እያገረገ ያለውን መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በተጠናከረ ሁኔታ እየቀጠለ ሲሆን ይህንንም እንቅስቃሴ በተለያየ የአለም ክፍሎች ተበትነው ያሉ ደጋፊዎቹ እንዲሁም በኖርዌይ ያሉ አባላቱ በቀላሉ እንዲከታተሉ የራሱ የሆነ የድህረ ገጽ ከኦገስት፣ 2012 ጀምሮ አገልግሎት ላይ መዋሉ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም የድጋፍ ድርጅታችንን ይህንን የመረጃ መለዋወጫ መረብ በማስተወሻነት ለድርጅት ወይም ለግለሰብ ለመስጠት በፕሮጀክትነት ይዞት እየተንቀሳቀሰ ይገኝ ነበር፣ በማያያዝም ለዚህ ቦታ ከተመረጡ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በተለያየ መስፈርት ሲፈተሽ ከቆየ በዄላ በኖርዌይ ማህበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል የማይረሳ ውለታም ጥለው አልፈዋል ያላቸውንና ለዚህም ቦታ ይመጥናሉ ተብሎ የታመነበት አቶ ግርማ አለማየሁ ማስታወሻነት ይህ ድህረ ገጽ ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመሆኑም ያበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁም የህይወት ታሪካቸው የተለያዩ መረጃዎችን በማጣቀስ እንዲሁም የሚያውቋቸውን ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸውን በማማከር ከዚህ በታች ያለው አጭር የህይወት ታሪካቸው በጥንቃቄ ሊዘጋጅ ችሏል፣ በማያያዝም በዚህ ስራ ውስጥ በመሳተፍ መረጃ በመስጠት በማቀናበር ለረዳችሁ ወገኖች ሁሉ የድጋፍ ድርጅታችን ከፍ ያለ ምስጋናውን እያቀረበ ለቀጣይን ድርጅታችን ለአገራቸው እና ለማህበረሰባችን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ወገኖቻችንን ስራዎቻቸውን እና ትውፊታቸውን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የምናስበው እና ዋጋ የምንሰጥ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
አንበሳው ግርማ አለማየሁ
በቀድሞዋ የወሎ ጠቅላይ ግዛት ደሴ አካባቢ አንድ እጅግ ውብ የሆነ ፣ አንድ ደቦል ወጣት ተወለደ ፡፡ ወላጅ እናትና አባቱ ገበየሁ ይመር ብለው ስም አወጡለት ፡፡ ይህ ወጣት በወሎ ክፍለሃገር የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደቀጠለ ፣ በወቅቱ የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ፣ መሬት ላራሹ የሚለውን መሪ መፈክር አንግቦ ሲንቀሳቀስ ፣ ደውሉ የገበየሁ ጆሮ ላይ አቃጨለ ፡፡
በወቅቱ የነበረውን የፊውዳል አስተዳደርና ፣ የፈላጭ ቆራጭ ንጉሳዊ አስተዳደርን በመፈንቅለ መንግሥት የገለበጠው ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ፣በተማሪዎች ፊት-አውራሪነት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ፣ በጉልበቱ ነጥቆ በምትኩ ፍጹም አምባገነን ወታደራዊ መንግሥት በመመስረቱ ፣ ጥቃትን በፍጹም የማይቀበለው አንበሳው ገበየሁ ይመር፣ ወታደራዊውን መንግሥት ለመፋለም የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲን ሠራዊት -የኢህአፓን ሠራዊት ኢህአሠን ገና በለጋ እድሜው በ14 ዓመቱ ተቀላቀለ ፡፡
በአካሉ ደንዳናና ፍርሃት የምትባል ነገር ፈጣሪ ያልፈጠረበት ገበየሁ ይመር ትግራይ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ወደ ሚገኘው አሲምባ ተራራ ለትግል ሲወጣ፣ እናት አባቱ ያወጡለትን የተጸውዖ ስሙን – ግርማ ዓለማየሁ በሚል የትግል ስም ለውጦ ፣ የአሲምባን ተራራና ምሽግ መትረየሱን እንደቀላል ቋጠሮ በመሸከም ላመነበት ዓላማ የወታደራዊውን መንግሥት ያናውጥ የነበረ ጀግና ነበር ፡፡
ኢህአሠ አሲምባ ላይ በትግራይ አገር ገንጣይና አስገንጣይ ቡድኖች ከተመታና ፣ በዘረኞች ጥቂት የባንዳ ልጆች፣ የአባይ ኢትዮጵያ ልጆች የትግራይን መሬት አይርመሰመሱባትም በሚል የዘረኛ ፍልስፍና የውጊያ ቦታቸውን በጦርነት ካስለቀቋቸው በኋላ ወደ ቀድሞዋ የኤርትራ ክፍለሃገር በመሰደድ ፣ እዚያም ለሁለት ወራት ጉርጓድ ውስጥ ታስሮ ከከረመ በኋላ ፣ ከኤርትራ እስር ቤት በመውጣት ፣ ለአንድ ዓመት ያህል በሱዳንና በቻድ የስደት ጽዋን ተጎንጭቷል ፡፡
እንደፈረንጆች አቆጣጠር በ1979 ዓ.ም ከቻድ እንደገና ወደ ኬንያ በመሰደድ ፣ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን በስደተኝነት በመመዝገብ ፣ ኑሮውን በስደት ናይሮቢ ውስጥ ቀጥሎ እያለ ፣የትምህርት እድል በዚያው ኬንያ ናይሮቢ በማግኘቱ፣Nirobi college of Arts በመግባት ለሁለት ዓመት እንደተከታተለ ፣ በአጋጣሚ ናይሮቢ ከተማ በተዋወቃቸው ኖርዌጅያኖች አማካኝነት እንደፈረንጆች አቆጣጠር በ1981 አጋማሽ ላይ ወደ ኖርዌይ መጥቶ መኖር ሲጀምር ፣ በቀጥታ ወደ ትምህርት ቤት በመግባት ለሶስት አመት የሚሰጠውን የመኪና መካኒክነት ትምህርት በመከታተል ትምህርቱን ከፍጻሜ አድርሷል፡፡
ግርማ ዓለማየሁ ከራሱ በፊት ዘወትር የእናት አገር ፍቅሩን የሚያስቀድም ፣ ጓደኞቹ ቤተሰብ መስርት እባክህ ሲሉት ፣ አገር የሌለው ልጅ ወልጄ ፣ ራሴ ከስደት ሳልወጣ ልጄን የስደት ሰለባ አላደርገውም በማለት ፣ ወያኔን ለመፋለም ሌት ተቀን ሲያስብና ለዚያም ትግል የሚሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ እንቅስቃሴ የሚባል የትግል ድርጅት በመመስረት በሊቀመንበርነት በማገልገል እስከ ህይወቱ ፍጻሜ ድረስ አገልግሏል ፡፡
ግርማ ዓለማየሁ ምንም እንኳ ትልሙ እውን ሳይሆን በሞት ቢነጠቅም ፣ ለትግል ጓዶቹ ህይወቱ ከማለፉ በፊት የተናዘዘውን ከዚህ ላይ ማንሳቱ እጅግ ጠቃሚ ነው ፡፡ በአጋጣሚ ህይወቱ ልታልፍ ሶስት ሳምንታት ሲቀሯት ፣ በኖርዌይ በየአምስት ዓመቱ ዘወትር የሚደረገው የመንግሥት ምርጫ ይካሄድ ነበር ፡፡ በዚያ ምርጫ ወቅት -የሴንትራል ፓርቲ መሪ የነበረቸው ሴት-በወያኔ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ወቀሳና ተቃውሞ በማሰማቷ ፣የትግል ጓዶቹን ሰብስቦ ፣ እባካችሁ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ አስተባብሩና ይህች ሴት እንድትመረጥ አድርጉ ፡፡ ለሃገራችን ቋሚ ጠበቃ ሆናለችና ድምጻችን ሁሉ ለርስዋ ይሁን በማለት ፣ አስከፊው የካንሰር ህመም እያንገላታው የርሱን የሟች ድምጽ ለመጣል ከዘራውን ተደግፎ እያቃሰተ የምርጫው ጣቢያ ደርሶ ድምጹን ከሰጠ በኋላ ሲመለስ ፣ አጥወልውሎት በመውደቅ ዳግም ወደ ሆስፒታል እንዲትኛ ተደረገ ፡፡
አንበሳው ግርማ አለማየሁ ከዚያ በኋላ በህይወት አልተመለሰም ፡፡ ግርማ ዓለማየሁ ጎምለል-ጎምለል እያለ በኦስሎ ከተማ ሲንቀሳቀስ መውጫ መግቢያ የሚጠፋቸው የወያኔ ፍጡሮች ፣ አንገታቸውን ቀና አደረጉ ፡፡ አዎ ! ዛሬ ግርማ አለማየሁ በህይወት ቢኖር ኖሮ 52 ዓመት እድሜ ይኖረው ነበር ፡፡ የትግል አርማውን የተረከቡት ጓዶቹ የግርማን የሙት መንፈስ ላለማስቀየም ሲሉ አሁንም በጸረ ወያኔ ትግላቸው ቀጥለውበታል ፡፡ አገራችን ከዘረኞች አገዛዝ አንድ ቀን ነጻ መውጣቷ ስለማይቀር ፣ የትግል ጓዶቹ ያችን ቀን ደሴ አብረው በጋራ በምሄድ በቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ባረፈው መካነ መቃብሩ ላይ የፍቅራቸውን ለቅሶ ያለቅሱለታል ፡፡ ግርማ አለማየሁ በስጋ ሞተ እንጂ በመንፈስ ከትግል ጓዶቹ ጋር ነው ፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar