ከቤንሻንጉል ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች
ወደነበሩበት እንዲመለሱ ተወሰነ
“ስህተት ተፈፅሟል”
አቶ አህመድ ናስር
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር
በዘሪሁን ሙሉጌታ
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ከቤንሻንጉል ክልል ተፈናቅለው በጎጃም ፍኖተሰላም አካባቢ እንዲሰፍሩ የተደረገው በስህተት መሆኑን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለፁ። የተፈናቀሉት በሙሉ ቀደም ሲል ወደነበሩበት እንዲመለሱ መወሰኑንም አስታወቁ።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አህመድ ናስር በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ሰሞኑን ከክልሉ እንዲፈናቀሉ የተደረጉ የአማራ ተወላጆች በሙሉ እንዲመለሱ መወሰኑን ገልፀዋል።
በክልሉ ከአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ከኦሮምያ ከመሬት ጥበት፣ ከአፈር ምርታማነት ማጣት ጋር በተያያዘ የተሻለ መሬት ፍለጋ ሰዎች ወደ ክልሉ እንደሚገቡ የገለፁት አቶ አህመድ ነገር ግን ሰፈራው በሕገ-ወጥ መንገድ ሲፈፀም መቆየቱን አስታውሰዋል።
ወደነበሩበት እንዲመለሱ ተወሰነ
“ስህተት ተፈፅሟል”
አቶ አህመድ ናስር
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር
በዘሪሁን ሙሉጌታ
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ከቤንሻንጉል ክልል ተፈናቅለው በጎጃም ፍኖተሰላም አካባቢ እንዲሰፍሩ የተደረገው በስህተት መሆኑን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለፁ። የተፈናቀሉት በሙሉ ቀደም ሲል ወደነበሩበት እንዲመለሱ መወሰኑንም አስታወቁ።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አህመድ ናስር በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ሰሞኑን ከክልሉ እንዲፈናቀሉ የተደረጉ የአማራ ተወላጆች በሙሉ እንዲመለሱ መወሰኑን ገልፀዋል።
በክልሉ ከአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ከኦሮምያ ከመሬት ጥበት፣ ከአፈር ምርታማነት ማጣት ጋር በተያያዘ የተሻለ መሬት ፍለጋ ሰዎች ወደ ክልሉ እንደሚገቡ የገለፁት አቶ አህመድ ነገር ግን ሰፈራው በሕገ-ወጥ መንገድ ሲፈፀም መቆየቱን አስታውሰዋል።
“እኛ የምንቃወመው በሕገ-ወጥ መንገድ በደን ውስጥ እየገቡ ደን እየመነጠሩ ሰፈራ ማስፋፋቱን ነው። ይህ ደግሞ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም አደጋ አለው” ያሉት አቶ አህመድ“በሕገ-መንግስታችን መሠረት ማንኛውም ሰው ለስራ ቢዘዋወር ችግር የለውም” ብለዋል።
ነገር ግን አሁን ከክልሉ እንዲፈናቀሉ የተደረጉት ለምን እንደሆነ ርዕሰ መስተዳደሩ ተጠይቀው ከታች ያለው አስተዳደር ስህተት በመፈፀሙ ነው ሲሉ አምነዋል። አስተዳዳሪዎቹ ሕዝቡን ያፈናቀሉት ሕገ-ወጥ ሰፈራውን ከነባሩ የመለየት ስራ ላይ ተናቦ የመስራት ችግር በማጋጠሙ ነው ብለዋል።
“አስተዳደራችን አካባቢ ስህተት ተፈፅሟል። መፈፀም ግን አልነበረበትም። ነገር ግን እንደ ክልል መንግስት በሕገ-ወጥ መንገድ የሰፈሩትን መቆጣጠር አለብን። ኅብረተሰቡ በፈለገው ጊዜና ወቅት እየተነሳ ደን እየመነጠረ መስፈር አስቸጋሪ ስለሆነ ስርዓት መያዝ አለበት የሚል አቋም አለን” ያሉት አቶ አህመድ ስህተት የፈፀሙ የአስተደደር አካላት ላይም ግምገማ በማካሄድ ማስተካከያ እናደርጋለን ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ ከአማራ ክልል ባለስልጣናት ጋር ምክክር መደረጉንም ያስታወሱት አቶ አህመድ ችግሩ በድጋሚ ሊፈጠር የማይችልባቸውን ቀዳዳዎች ለመድፈን ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ወደ 1 ሺህ 346 አባወራዎች ከ3ሺህ ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲፈናቀሉ መደረጉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ችግሩ ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ጋር የተያያዘ መሆኑንም አስረድተዋል።
“በክልላችን አንዳንድ ቦታዎች ሰዎቹን ወደ አካባቢው ካስገቡአቸው በኋላ የሚታይ ችግር አለ። በተለይ ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ችግር አለብን። በየጊዜው እናጣራለን፤ እንጠርጋለን፣ እንገመግማለን ችግሩን ግን ሙሉ በሙሉ ማፅዳት አልተቻለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ክልሉ መግባትና መውጣት የሚያስችል ሕገ-መንግስታዊ መብቱ የተከበረ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ከአማራ ክልል ወደ ክልላችን ለስራ በሚገቡበት ሁኔታ ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል። ይሁን እንጂ የክልሉ ደን እንዳይወድምና ጥበቃ እንዲደረግ ከአማራ ክልል ጋር ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
በትናንትናው ዕለት በፍኖተ ሰላም ከተማ ተፈናቃዮችን ወደመጡበት አካባቢ ለመመለስ 11 መኪኖች መዘጋጀታቸውንና ተፈናቃዮቹን የሚያጅቡ የፌዴራል ልዩ የፖሊስ ኃይል መታጀባቸውን የዓይን ምስክሮች ገልፀዋል።
መንግስት በመለስ ፋውንዴሽን ውስጥ ጣልቃ መግባቱን የአቶ መለስ ልጅ ተቃወመች
የአቶ መለስ ዜናዊን ምስል ያለፈቃድ መጠቀም ሊከለከል ነው
በዘሪሁን ሙሉጌታ
የቀድሞ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የበኩር ልጅ ወጣት ሰምሀል መለስ ባለፈው ቅዳሜ በተቋቋመው “የመለስ ፋውንዴሽን” ውስጥ መንግስት ጣልቃ መግባቱን ተቃወመች።
ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2005 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው የፋውንዴሽኑ የማቋቋሚያ መስራች ጉባኤ ላይ ወጣት ሰምሀል ፋውንዴሽኑ የመለስ አስተሳሰብ ምንጭ መሆን ሲገባው መንግስት በፋውንዴሽኑ ላይ ሚናው መጉላቱ ተገቢ አለመሆኑን ተናግራለች።
ወጣት ሰምሀል በፋውንዴሽኑ ምስረታ ወቅት “አሰራሩ እኔ አልገባኝም። ከዚህ በፊትም ቤተሰብ አንስቶ ነበር። በአዋጁ ላይ የመንግስት ሚና መጉላቱ ስህተት ነው ብለናል” ስትል ተቃውሞዋን አሰምታለች።
ሰምሀል የመንግስትን በፋውንዴሽኑ ጣልቃ መግባትን ብትቃወም ከፋውንዴሽኑ 13 የቦርድ አባላት አራቱ ከቤተሰባቸው ዘጠኝ ደግሞ የመንግስት አካላት ሆነው የተመረጡ ሲሆን ወደፊት አዋጁን በማሻሻል ሌሎች አካላትን ለማሳተፍ ከመታሰቡ ባለፈ በዕለቱ የሰማህል ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
በተያያዘ ዜና የቀድሞ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ምስል ያለቤተሰቦቻቸውም ወይም በስማቸው ከተቋቋመው ፋውንዴሽን ፈቃድ ውጪ በማንኛውም ቦታ መለጠፍም ሆነ ምስላቸውን ቀርፆ መጠቀም ሊከለከል ነው።
የአቶ መለስን ምስል ያለፈቃድ መጠቀምን የሚከለክለው ረቂቅ መመሪያ የተዘጋጀው በአዋጅ ቁጥር 781/2005 አንቀፅ ዘጠኝ ንዑስ አንቀፅ 2(ሰ) መሰረት ነው።
ረቂቅ መመሪያው ባለፈው ቅዳሜ የመለስ ፋውንዴሽን ይፋ በተደረገበት ወቅት ለውይይት ተበትኗል። በረቂቅ መመሪያው ስለ ምስላቸው አጠቃቀም በሚያወሳው አንቀፅ 8 ንዑስ አንቀፅ (1) ላይ ማንኛውም ሰው ለክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ያለውን ፍቅርና ክብር ለመግለፅ ምስሉን በመኖሪያ ቤቱ ግድግዳ ላይ ሊሰቅል፣ በአልበም ውስጥ፣ በቦርሳው፣ በኪሱ፣ በተሽከርካሪው ወይም በሌላ የግል መጠቀሚያው ሊይዘው ከሚችለው በስተቀር ምስላቸውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ፣ ለሽያጭ፣ ለባዛር፣ ለጨረታ ወይም ለማንኛውም የንግድ ድርጅት ወይም ሌላ ተቋም ማስታወቂያ፣ የንግድ ምልክት፣ ለመታሰቢያነት ወይም ለማንኛውም ጥቅም ማስገኛነት ሊሰቅል ወይም ሊቀርፅ ወይም በማንኛውም ሁኔታ ሊያስቀምጥ እንደማይችል አስቀምጧል።
ከዚህ በተጨማሪ የአቶ መለስን ምስል በተለየ ሁኔታ ለህዝባዊ አላማና ጥቅም ለመጠቀም የፈለገ አካል ከቤተሰባቸው ወይም ከፋውንዴሽኑ ቦርድ ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት መመሪያው ያስገድዳል።
በተያያዘም ከፋውንዴሽኑ ፈቃድ ውጪ በአቶ መለስ ዜናዊ ስም ማንኛውንም አይነት ግንባታ ለመገንባት በማሰብ የእሳቸውን ስም፣ ምስል ወይም ስራዎች በመጠቀም ገንዘብ ወይም ቁሳቁስ መሰብሰብን ረቂቅ መመሪያው ከልክሏል።¾
የኢትዮጵያ መንግስት የግራዚያኒ መታሰቢያ ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያወግዘው በይፋ ጥሪ አቀረበ
በፋኑኤል ክንፉ
የዓለም ዓቀፍ ሕብረተሰብ እና የአፍሪካ ሕብረት የፋሺስት ጄነራል ሩዶልፉ ግራዚያኒ መታሰቢያ እንዲሆን በጣሊያን ሀገር መናፈሻና ሙዚየም መሰራቱን እንዲያወግዙ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በይፋ ጥሪ አቀረቡ።
በሩዋንዳ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ መጋቢት 29 ቀን 2005ዓ.ም ለ19ኛ ጊዜ በተደረገው የመታሰቢያ በዓል ላይ የተገኙት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ “ፋሺስት ጄነራል ሩዶልፉ ግራዚያኒ ለመታወስ የሚበቃ ተግባር የለውም። ለመታወስም አይመጥንም። ከዚህ ይልቅ፤ በሰራቸው የጦር ወንጀል፣ የዘር ማጥፋት ተግባሮች እና በሰው ፍጥረት ላይ በፈጸመው ወንጀል ሊወገዝ የሚገባው ፋሺስት ነው” ሲሉ ገልፀውታል።
አያይዘውም ዶክተር ቴዎድሮስ እንዳሉት “ፋሺስት ጄነራል ሩዶልፉ ግራዚያኒ በኢትዮጵያ እና በጣሊያን ንፁሃ ዜጎች ላይ ለደረሰው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ቀጥታ ተጠያቂ ነው ሲሉ በይፋ ወንጅለው ድርጊቱን አውግዘዋል።
ይህን መሰል ድርጊት በአፍሪካ ውስጥ እንዳይስፋፋ የአፍሪካ ሕብረት የሚያደርገውን ጥረትንም አመስግነዋል። ዶክተር ቴዎድሮስ በሥነሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር፤ አፍሪካ ሕብረት በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚፈጠሩትን ግጭቶች ለመፍታትና ለመከላከል እያደረገ ያለውን ተነሳሽነት የሚደነቅ ነው ብለዋል። በተለይ አግባብ ካልሆነ ቅጣትና ጉዳት እንዲሁም ተደጋጋሚ ከሆኑ ከፍተኛ ወንጀሎች አህጉሩን ለመከላከል ሕብረቱ የሚያደርገውን ጥረት ቦታ የሚሰጠው ነው ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
በአፍሪካ ሕብረት ሰነድ ላይ እንደሰፈረው ከፍተኛ የሆኑ ወንጀሎች ሲፈፀሙ ሕብረቱ ጣልቃ እንደሚገባ መደንገጉ ይታወቃል።
በጣሊያን አገር የፋሽስት ጄኔራል ሩዶልፍ የመታሰቢያ ሐውልት መሠራቱን በመቃወም በአዲስ አበባ መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም ሰልፍ የወጡ ወገኖች በዕለቱ መታሰራቸው ይታወሳል። በሰልፈኞቹ በኩል የታሰሩት ሰልፍ በመውጣታቸው መሆኑን በወቅቱ ለመገናኛ ብዙሃን የገለፁ ሲሆን፤ በመንግሥት በኩል ግን ያልተፈቀደ ሰልፍ በመውጣታቸው መታሰራቸው መነገሩም አይዘነጋም።¾
ኢዴፓ የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ በገለልተኛ
አካል እንዲጣራ ጠየቀ
*ሰማያዊ ፓርቲ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ጠይቋል
በመስከረም አያሌው
ከየክልሉ በተለያየ ምክንያት ቀዬ እና ሀብት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱ እና የተፈናቀሉ ዜጐች ጉዳይ ነፃና ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲጣራ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)ጠየቀ።
ፓርቲው ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ከአንድ አመት በፊት ጀምሮ ከደቡብ ህዝቦች ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ፣ ከሶማሌ ህዝቦች ክልል ጅጅጋ ከተማ እንዲሁም ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ያሶ ወረዳ የተፈናቀሉ የአማራዎች ጉዳይ፤ እንዲሁም ከኦሮሚያ፣ ከጋምቤላ፣ ሶማሌና ሌሎች ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጐች ጉዳይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመሆኑ እና በየክልሉ በሚኖሩ ቀሪ ዜጐች ላይም ስጋት እየፈጠረ ስለሆነ ገለልተኛ በሆነ አካል ሊታይ ይገባል። ዜጐችን ለማፈናቀል አስገዳጅ ሁኔታው ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ በበቂ ቅድመ ዝግጅት ላይ ተመስርቶ መከናወን አለበት ያለው ፓርቲው፤ ጉዳዩን የሚያጣራ ራሱን የቻለ አካል አቋቁሞ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ህጋዊ ማጣራት ማድረግ እና ህጋዊ መፍትሄ ማበጀት የመንግስት ኃላፊነት ነው ብሏል።
በዜጐች ላይ በብሔርተኝነትና ፖለቲካ ምክንያት በዜጐች ላይ እየተከሰተ ያለው የማፈናቀል ድርጊት በየክልሉ የሚኖሩ ዜጐች በሰላም ሰርቶ የመኖር ፍላጐታቸውና ሀብት ባፈሩበት ቀዬ የመሰንበት ጥያቄ ላይ ስጋት እያጫረ በመሆኑ የሚሰጠው የመፍትሄ ሀሳብም እነዚህ ዜጐች ህይወታቸውን በተረጋጋ መንገድ እንዲቀጥሉ አቅጣጫ ጠቋሚ መሆን አለበት ብሏል። ከጥቂት አመታት በፊት ጋብ ብሎ የነበረው የዜጐች መፈናቀል ከሃያ አንድ ዓመት የብሔርተኝነት ፖለቲካ እና የገዥ መደብ መዳከም በኋላ ዳግም ማገርሸቱ በህገ-መንግስቱ ላይ የሰፈሩትን የእኩልነት እና ሌሎች መሰረታዊ መብቶችን የሚነፍግ ነው ሲልም ፓርቲው ገልጿል።
በተያያዘ ዜናም ሰማያዊ ፓርቲ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እየተፈናቀሉ ስላሉ ዜጐች አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል። ፓርቲው እንደገለፀው በርካታ ሺህ ዜጐች በጉራፈርዳ ወረዳ እንዲፈናቀሉ በተደረገበት ማግስት ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልም ዜጐች እንዲፈናቀሉ በማድረጉ ለደረሰው ጉዳት መንግስት ለህዝብ አስቸኳይ ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባዋል። ዜጐች በሚናገሩት ቋንቋ ላይ ተመስርቶ እንዲፈናቀሉ መደረጉ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በማፈናቀል ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ላይ የተቃጣ አደጋ መሆኑን መንግስት ተገንዝቦ፤ በእነዚህ ዜጐች ላይ ለደረሰው የህይወት፣ የንብረትና የስነ ልቦና ጉዳት ጥፋተኞች በህግ እንዲጠየቁም ፓርቲው ጠይቋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለተፈናቀሉ ዜጐች ጊዜያዊ መጠለያ እና አልባሳትን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች እና ጥቃቱ እንዲቆም ከሚመለከተው አካል ጋር ተወያይቶ ለህዝቡ ይፋ እንዲያደርግ የጠየቀው መግለጫው፤ ትልቁ የስልጣን አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይህን ህገ-መንግስት የጣሰና ሀገር የሚጐዳ ተግባር ፈፃሚዎች በህግ እንዲቀጡ ማድረግ አለበት ብሏል።n
ከኮንደሚኒየም ዕድለኞች 30 በመቶ ያህሉ
በዕድላቸው አይጠቀሙም
በፀጋው መላኩ
የቤቶች የኮንስትራክሽን አጠቃላይ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየናረ ከመሄዱ ጋር በተገናኘ በርካታ የኮንዶሚኒየም ቤት ባለእድለኞች የእድላቸው ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ የከተማና የኮንስትራክሽን ሜኒስተር አቶ መኩሪያ ሃይሌ ገለፁ። ከካይዘን የአሰራር ፍልስፍና ጋር በተያያዘ ባለፈው ሀሙስ በከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማብራሪያ የሰጡት አቶ መኩሪያ ሃይሌ የኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የከተማ ነዋሪዎች ዲዛይን የተደረገ ቢሆንም ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ ንሮ ስለሚገኝ ነዋሪዎች የእድላቸው ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
በአጠቃላይ ከኮንደሚኒየም ዕድለኞች መካከል ሰላሳ በመቶ የሚሆኑት እድለኞች እጣው ከደረሳቸው በኋላ በእድላቸው የማይጠቀሙ መሆናቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ ባለእድለኞች የእድላቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የቤቶች ዋጋ ውድነት መሆኑን አመልክተዋል። እንደ አቶ መኩሪያ ገለፃ ፕሮጀክቶቹ ሲጀመሩ የጠጠር፣ የአሸዋ፣ የሲሚንቶ እና የጉልበት ዋጋ በቁርጥ ዋጋ የሚሰላበት ሁኔታ ቢኖርም በመጨረሻ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ግን ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት የሚታይ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህም ተመልሶ በቤት ተረካቢው ላይ የሚጫን መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ በቀጣይ ግን መንግስት የሚገነቡት የጋራ መኖሪያቤቶች ፕሮጀክቶቻቸው ሲጀመር ሳይሆን ሳያልቅም ጭምር ዋጋቸው መቀነስ መቻል ያለበት መሆኑን ገልጸዋል። በሀገሪቱ ባለው ኋላቀር የኮንስትራክሽን ከፍተኛ የሆነ የግብዓት የሚታይ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን አሁን ያለው 20 በመቶ ብክነት ለቀጣይ ወደ 10 በመቶ ለማውረድ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
በቅርቡ እጣቸው በወጣው አስር ሺ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለስቱዲዮ ቤቶች አማካይ ዋጋ በካሬ 1 ሺ 865 ብር ሲሆን ለቅድመ ክፍያም 13 ሺ717 ብር ይጠበቃል። ለባለአንድ መኝታ ቤት ደግሞ አንድ ባለእድለኛ በካሬ 2ሺ491 ብር መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን 27ሺ 388 ብር ደግሞ ቅድመ ክፍያው ነው። የባለ ሁለት መኝታ ቤቶች እድለኞች በካሬ 3ሺ426 ብር መክፈል የሚገባቸው ሲሆን ቅድመ ክፍያው 54ሺ63 ብር ነው። ባለሶስት የመኝታ ክፍሎች ዕጣ እድለኞች በአንፃሩ በካሬ 3ሺ 580 ብር እንዲከፍሉ ይደረጋል። ቅድመ ክፍያው ደግሞ 75ሺ 545 ብር ነው። ነዋሪው የመሬት ሊዝ ዋጋ ጨምሮ የተለያዩ ዋጋዎች ተቀንሰውለት ቀጥተኛ የግንባታ ወጪውን ብቻ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ክፍያ እንዲፈፅም ቢደረግም ከህዝቡ የኑሮ አቅም አንፃር ግን ለበርካቶች ውድ መሆኑ የሚነገረው በተለይ ቅድመ ክፍያው ሁኔታ የብዙዎችን የመክፈል አቅም የተፈታተነ መሆኑ ነው የሚነገረው።¾
የሞባይል ዝርፊያ የፈፀሙ ወጣቶች እስከ ሰባት
ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ
በአሸናፊ ደምሴ
የፌዴራሉ አቃቤ ህግ የማይገባቸውን ብልፅግና ለማግኘት በማሰብ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተሳታፊ በመሆን ከግል ተበዳይ ላይ ግምቱ 2ሺ 300 ብር የሚደርስ ሞባይል ዘርፈው ለመሰወር ሲሞክሩ ደርሼባቸዋለሁ ሲል ክስ የመሰረተባቸውን ሁለት ተከሳሾች በሰባት እና በስድስት አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ከትላንት በስቲያ ወሰነ።
ተከሳሾቹ የካቲት 6 ቀን 2005 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ5፡30 ሲሆን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 10/11/12 ልዩ ቦታው ውሃጋን አስቴር ግሮሰሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የግል ተበዳይን ኖኪያ ሞባይል ሞዴል ኤን-73 (N-73) የገበያ ግምቱ 2ሺህ 300 ብር የሆነን መንትፈው ለመሰወር አስበው ተንቀሳቅሰዋል ይላል።
በወቅቱም ተበዳይ ይነጋገሩበት የነበረውን ሞባይል 1ኛ ተከሳሽ ከኋላ በመምጣት መንትፎ ለመሮጥ ሲሞክር የግል ተበዳይ በሁለት እጁ የያዘው በመሆኑ፤ ድንገት 2ኛ ተከሳሽ በመምጣትና በድንጋይም ቀኝ ሽንጡን በመምታት ስቃይ በማድረስ ጥለውት ያመለጡ በመሆኑ በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል ተከሷል።
ተከሳሾቹ የዐቃቤ ህግን ክስ በአግባቡ መከላከል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን፤ ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎትም 1ኛ ተከሳሽ ሰባት አመት ፅኑ እስራት ሲፈረድበት፤2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ6 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።n
በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሁለት የከተማ
እርሻ ኔትወርኮች ተቋቋሙ
በመስከረም አያሌው
የአለም የምግብ ድርጅት (ፋኦ) ከሀዋሳ እና ባህርዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ተጨማሪ ሁለት የከተማ እርሻ ኔትወርኮችን አቋቋመ።
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ተቋቁሞ የነበረው እና ተጨማሪ የስራ እድልን ለመፍጠር የሚረዳው እንዲሁም ስነ-ምግብን የሚያሻሽለው የከተማ እርሻ ኔትወርክ በሁለቱ ከተማዎች መቋቋማቸው በተለያዩ ሴክተሮች መካከል ያለውን የመረጃ ቅብብሎሽ ያሻሽለዋል። ኔትወርኮቹ ሲቋቋሙ ዋናው አላማቸው የተለያዩ የከተማ እርሻ ባለድርሻዎች በከተማ እርሻ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ከተሰማሩ የመንግስት፣ የምርምር ተቋማት፣ የልማት አጋሮች እና ከግል ዘርፍ ጋር በማገናኘት ተጨማሪ የስራ እድልን፣ ምርትና ምርታነትን እንዲሁም የትኩስ እና የተመጣጠነ ምግብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ነው።
የባህርዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ስማቸው ወንድማገኝ እንደገለፁት ኔትወርኮቹ መቋቋማቸው በከተማዋ ያለውን የምግብ ዋስትና ለማሻሻል የነዋሪውን ገቢ ለማሳደግ እንዲሁም የህዝቡን የምግብ ማምረት አቅም ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
እነዚህ በተጨማሪ የተቋቋሙት ኔትወርኮች ባለፈው አመት የተቋቋመውን አዲስ አበባው ኔት ወርክ በመቀላቀል በዜጐች ምርታማነት ላይ መሻሻልን ለማምጣት እንደሚሰሩ ተገልጿል።n
የሳዑዲው ንጉስ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በስደተኞች ላይ የሚካሄደው
አሰሳ ለጊዜው እንዲቆም አዘዙ
በፀጋው መላኩ
የሳዑዲው ንጉስ አብደላ ቢን አብድልአዚዝ ባለፉት ሳምንታት በመላ ሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ ሲካሄድ የነበረው ህገወጥ ነዋሪዎችን የማሰስና የማደን ሥራ እንዲቆም አዘዙ። ትዕዛዙ ያለፈቃድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያለፈቃድ ነዋሪዎችን ጭምር የሚመለከት ሲሆን ንጉሱ ለሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርና ለሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያቤቶች ባስተላለፉት ትዕዛዝ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ነዋሪዎች የእፎይታ ጊዜ ተጠቅመው ከመኖሪያና ከስራ ፈቃድ ጋር የተያያዘ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ አስታውቀዋል። የንጉሱ መግለጫ የምህረት ጊዜውን ተጠቅመው ተገቢውን ማስተካከያ የማያደርጉ ፈቃድ አልባ ነዋሪዎች ህጋዊ እርምጃ የሚወስድባቸው መሆኑን ዜናውን ያሰራጨው አረብ ኒውስ አስታውቋል።
ለተወሰኑ ቀናት በተከታታይ በሀገር ውስጥ ጉዳይና በሰራተኞች ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች የጋራ ትብብር አማካኝነት በህገወጥ ነዋሪዎች ላይ አሰሳ ሲደረግ የቆየ ሲሆን በርካታ ቀጣሪዎችም ከፍተኛ ስቃይ ሲደርስባቸው የቆየ መሆኑ ተመለክቷል። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ባደረገው ማጣራት በርካታ ህገወጥ ነዋሪዎች ፎርጅድ መኖሪያ ይዘው ተገኝተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ 34 የወንጀል አይነቶችንም የተለዩ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ አስታውቋል። ከህገወጥ ነዋሪዎች የተለያዩ የህጋዊ ሽፋን መረጃዎች ጋር በተያያዘ 1ሺ እስከ 5ሺ ሪያል ቅጣት የሚጥል መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጨምሮ ገልጿል። ከፎርጅድ መኖሪያ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ለህገወጥ ነዋሪዎች እገዛ የሚያደርጉ የራሷ የሳዑዲ ዜጐች ስማቸው በመገናኛ ብዙኃን እንዲገለፅ የሚደረግ ሲሆን እስከ 30ሺ የሚደርስ ሪያል ቅጣት እንዲከፍሉ ይደረጋል ተብሏል።n
በአሰቃቂ ሁኔታ የግድያ ሙከራ የፈፀመው ግለሰብ የዋስትና መከበር አነጋጋሪ ሆኗል
· አምስት የወንጀል ሪከርዶች አሉበት ተብሏል
በአሸናፊ ደምሴ
በቀድሞ ባለቤቱ ላይ በቂም በቀል ተነሳስቶ በስለት የታገዘ የግድያ ሙከራ ፈፅሟል በሚል ዐቃቤ ህግ ክስ የመሰረተበት ግለሰብ በ15 ሺህ ብር የዋስትና መብቱ እንዲከበር መፈቀዱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ዐቃቤ ሕግ በመሰረተው የክስ ዝርዝር ውስጥ እንዳስረዳው ተከሳሽ ነጂብ አብደላ ሰውን ለመግደል አስቦ በመጋቢት 11 ቀን 2005 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 9፡30 ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3ክልል ልዩ ቦታው ቦሌ መድሃኒአለም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ሬድዋን ህንፃ 1ኛ ፎቅ ውስጥ፤ የግል ተበዳይና የቀድሞ ባለቤቱ የነበረችውን ማሪያ የኑስ በመካከላቸው በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በሃይማኖታቸው መሰረት በስምምነት የተፋቱ ሆኖ ሳለ፤ ለመግደል አስቦ ቢለዋ እና አርቴፊሻል ሽጉጥ በማዘጋጀት በተበዳይ ስም የተዘጋጀ ቼክ መኖሩን በመግለፅ ቢሮው ድረስ መጥታ እንድትወስድ በማግባባት ወንጀሉን ለመፈፀም ስለመሰናዳቱ ያትታል።
ወንጀሉ በተፈፀመበት እለትም ከተከሳሽ ጋር አብራ ትሰራ የነበረች ፀሐፊ “ዛሬ የቤተሰብ ጉዳይ አለ” በሚል ሰበብ ወደቤቷ እንድትሄድ በማድረግ፤ የግል ተበዳይ ወደቢሮው ስትገባ በሩን በመቆለፍ እና በሲጃራ መተርኮሻ ሁለት ጊዜ ጭንቅላቷን በመምታት እንዲሁም በአርቴፊሻሉ ሽጉጥ በማስፈራራት “የኔን ህይወት አበላሽተሸ አትኖሪም”የሚል ሀይለ ቃል መናገሩ በክስ ዝርዝር ውስጥ ሰፍሯል።
በወቅቱም የተበዳይን አይን ለማጥፋት አዘጋጅቶት የነበረውን ስለት ወደአይኗ ቢሰነዝርም ራሷን ለመከላከል ባደረገችው ጥረት የፊት ቆዳ መሰንጠቅና አራት ቦታዎች ላይ በመውጋት ደም እንዲፈሳት ቢያደርግም፤ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች የፖሊስ ሃይል ጠርተው በሩን በጉልበት በመክፈት ህይወቷ የተረፈ ሲሆን፤ ተከሳሹም በከባድ የግድያ ሙከራ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት መሆኑን ይገልፃል።
ዐቃቤ ህግ በፖሊስ የምርመራ ስብስብ ላይ በመንተራስ ክስ የመሰረተ ቢሆንም ሂደት ላይ እያለ ተከሳሽ ያቀረበውን የዋስትና መብት ጥያቄ የተመለከተው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት የተከሳሹን የዋስትና ጥያቄ በመቀበል በ15ሺ ብር ዋስትና ከማረሚያ ቤት ወጥቶ ጉዳዩን እንዲከታተል ሰሞኑን ወስኗል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት እና በቦሌ ፍትህ ጽ/ቤት የፌዴራል አቃቤ ህግ የሆኑት አቶ እምሽታው ተሰማ ተከሳሹ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አምስት ወንጀሎች ሪከርድ ያለበት በመሆኑ በዋስ ቢለቀቅ ወደፍርድ ቤት ቀርቦ ይከራከራል የሚል እምነት የለኝም በማለት አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሹ ለፖሊስ በሰጠው ቃል ተበዳይን አጥፍቶ እራሱንም የመግደል ሀሳብ የነበረው መሆኑን በመጥቀስ ምናልባትም ከማረሚያ ቤት ከወጣ የከፋ ወንጀል ሊፈፅም ይችላል ብለዋል።
ይህንና መሰል ስጋቶችን በመዘርዘር ቅሬታ እንዳላቸው የጠቀሱት ዐቃቤ ህጉ በተሰጠው የዋስትና መብት ላይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቃቸውንም አስታውቀዋል።
(ምንጭ ፡-ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 396 ረቡዕ ሚያዝያ02/2005)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar