søndag 17. mars 2013

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ - መልክአ ኢትዮጵያ ፩



ጽዮን ግርማ Tsion Girmaጽዮን ግርማ
የሚሳሳሙት ደንበኞቻቸው ወንድ እና ሴት ብቻ አይደሉም። አንዳንዴ ወንድና ወንድ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሴትና ሴት ሊሆኑ ይችላሉ። በዲሲ፣ በሳንፍራንሲስኮ፣ በቺካጐ እና በአትላንታ ጉብኝቴ ወንድ ለወንድ እና ሴት ለሴት ሲሳሳሙ በዐይኔ ተመልክቻለሁ። ድርጊቱን ማየት እንደመስማት እና ማውራቱ ቀላል አይደለም። ለእንደኔ ዓይነቷ ሊብራል ነኝ ባይ እንኳን መሣቀቁ ነፍስን ከሥጋ ያላቅቃል። ግን ደግሞ ያየሁትን ጽፌ ለማስነበብ ጓጉቼ ስለምጓዝ እየተሳቀቅኹም ቢሆን እንዲህ ያሉትን ቦታዎች ጐብኝቻለሁ። ...


ከከተማ ወጣ ካልኩ ጥሬ ሥጋ አሊያም ጥብስ መብላት ያስደስተኛል። ይኸው ዛሬ ከአዲስ አበባ ወጥቼ የሚያስጐመዥ ምርጥ ሥጋ እያወረድኩ ነው። ብቻዬን ግን አይደለሁም፤ ሶምሶን ከተባለው ዘመዴ እና መላኩ ከሚባለው ጓደኛው ጋር ነኝ። ጥሬ ሥጋ ደስ የሚለው ከሰው ጋር ስብስብ ብለው ሲበሉት ነው። ሳሚ የሥጋ ቤቱ ደንበኛ ስለሆነ ለዘመድ የሚሆን ምርጥ ሥጋ ነው ያስቆረጠልን። ሥጋው ለስላሳ ነው፤ ጣዕሙ ደግሞ የጉድ ነው። መላኩ ቶሎ በልተን እንድንነሳ ስለፈለገ ደጋግሜ ጨዋታ ለመጀመር ያደረኩትን ሙከራ አከሸፈብኝ። "ቶሎ ቶሎ ብሉ እንጂ" ይላል - እየደጋገመ ጦርነት የመጣ ይመስል።

ከፊት ለፊታችን በትልቅ ረከቦት የቡና ስኒ ተደርድሮ፣ ሣሣ ባለ የዕጣን ጢስ ታጅቧል። የፈላ ቡና መዓዛ አካባቢውን አውዶታል። የሀገር ባህል ልብስ የለበሰችው የጠይም ቆንጆ ቡናው ተንተክትኮ እስኪወጣለት ትጠባበቃለች። ከዚህ ጀበና ላይ አንድ ስኒ ቡና ለመጠጣት ጐምዥቼ ነበር። መላኩ ግን ትዕግሥት አልነበረውም። የደንቡን ለማድረስ እንደተጣደፈ አልጠፋኝም።


"በቃ፣ ቡናውን እዚያው ታመጣልናለች እንግባ" አለ። "ቡናችን ከመጣ ምን ቸገረኝ" ብዬ አብሬው ተነሳሁ። ሳሚም ተከተለን። ከነበርንበት ክፍል ወጥተን በስተግራ በኩል ባለው ኮሪደር ዘወር እንዳልን በርካታ ክፍሎች ተደርድረው ተመለከትኩ። በስተቀኝ በኩል መሀል በሩ ወለል ብሎ የተከፈተ መጸዳጃ ቤት አየሁ። በመጸዳጃ ቤቱ ወለል ላይ አገልግሎት የሰጠ የመጸዳጃ ቤት ወረቀት በግዴለሽነት ተጥሏል። የመፀዳጃ ክፍሉ ሽታ ቆይቶም ቢሆን መረበሹ አይቀርም በሚል ያዝ አድርጌ ለመዝጋት ሞከርኩ። መዝጊያው የተገጠመ መስሎ ተመልሶ ተከፈተ። ሳይበላሽ አልቀረም።

መላኩ ከተደረደሩት ክፍሎች የአንደኛውን መዝጊያ ገፋ አድርጎ ዘው አለ። ሳሚም ተከተለው። እኔም እያመነታሁ ገባሁ። ክፍሉ ጢቅ ብሎ ሞልቷል። መጅሊስ ላይ የተቀመጡት በሙሉ አፈጠጡብን። እንግዳ በመሆኔ ብዙ ዓይኖች ያረፉት እኔ ላይ ነበር። ከእነዚያ ዓይኖች ለመሸሽ ቀረብ ያለኝ ቦታ አረፍ አልኩ። ጥቂት ከተረጋጋሁ በኋላ ቀስ ብዬ ዙሪያ ገባውን ማማተር ያዝኩ። ሳሚ እንደ መላኩ ቤተኛ አለመሆኑ ያስታውቃል። መላኩ ግን ከሁሉም ጋር ያወራል።

ከፊት ለፊቴ በመጋረጃ የተከለለ ክፍት በር ይታየኛል። ከመጋረጃው ጀርባ ሌላ ክፍል እንዳለ ገባኝ። ከበሩ በስተኋላ ፊታቸውን ለእኛ የሰጡ ወጣቶች ተቀምጠዋል። ነፍሷን በጨርቅ ያንጠለጠለች የምትመስል ቀጭን ልጅ ጉልበቷን ከደረቷ ጋር ገጥማ ተጣጥፋ ተቀምጣለች። በመልክም በአለባበስም የሚመሳሰሉ ሴትና ወንዶች በመጅሊሱ ላይ ተሰይመዋል። ከሴቶች ይልቅ የወንዶች ቁጥር በርከት ይላል።

በክፍሉ በስተግራ ጥግ ላይ 42 ኢንች የሚጠጋ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን ከመሬት ትንሽ ከፍ በምትል ማስቀመጫ ላይ ጉብ ብሏል። አጠገቡ ከተቀመጠ ተለቅ ያለ የሲዲ ማጫወቻ የአብዱ ኪያርን "እቴ ሜቴ የሎሚ ሽታ" ዘፈን በቀስታ ያጫውታል፤ ቤቱ ውስጥ ጐልቶ የሚሰማው ግን ዘፈኑ ሳይሆን ሌላ ድምፅ ነው።

"... ዱቅ ... ዱቅ ... ዱቅ" ያደርጋሉ የቤቱ ታዳሚዎች - በየተራ። አንዱ ሲያቋርጥ ሌላው ይቀጥላል። ከአፋቸው የሚወጣው ወፍራም ጭስ ቤቱን በከፊል አዳምኖታል። ሁሉም ሺሻ እያጨሰ ነው። በየሰዉ ፊት ባለው ጠረጴዛ ላይ የኮካ ጠርሙሶች እና ውኃ የያዙ ፕላስቲኮች ተቀምጠዋል። ነጭ የሻይ ሲኒዎች ከማንኪያ ጋርም ይታያሉ፤ ሻይ መስሎኝ ነበር። ግን አይደለም። ምን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉቼአለሁ።

ቀጠን ያለች ጠይም አስተናጋጅ ሁለት የሺሻ ጠርሙሶች አምጥታ አጠገባችን አኖረች። "ሙአሰል" ተሞልተው ፎይል የተጠቀለሉ ቡሪዎች (የሚጨሰው ነገር ተሞልቶ አናታቸው ከተበሳ በኋላ ከጠርሙሱ ላይ የሚቀመጡ ሸክላዎች) አምጥታ አስቀመጠችበት። ያመጣችውን እሳት በቀጭን መቆንጠጫ እያነሣች ቡሪው ላይ አደረገች። ሺሻውን አዘጋጅታ ከጨረሰች በኋላ ፊት ለፊታችን ተቀምጣ ትምገው ጀመር። በአጫሾች ቋንቋ ማቀጣጠል (ማፈንዳት) ይባላል። አንዱን ሺሻ ልቧ እስኪጠፋ ስባ ጭስ ማውጣት ሲጀምር፣ ለአንዱ አጫሽ አቀበለችው እና ሁለተኛውን ተያያዘችው።

እኛ በተቀመጥንበት መደዳ በስተግራ በኩል ካለው የኋላ በር ቀጭን፣ ፀጉሩን ወደ ላይ ያቆመ ወጣት እሷ ያመጣችው ዐይነት የእሳት ማቀጣጠያ ፍም ከመሰለ እሳት ጋር ይዞ ወጣ። ፊቱ ላይ አመድ ቦኖበታል። እሳት ሲያቀጣጥል እንደነበር መገመት አላቃተኝም። ሳሚ እና መላኩ ሺሻቸውን እየሳቡ ጨዋታ ይዘዋል።

እስካሁን የነገርኳችሁ ሁሉ የተከሰተው ኢትዮጵያ ውስጥ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ አካባቢ ሊመስላችሁ ይችላል። ነገር ግን አሜሪካ ነው። ሺሻ ቤቱም ያለው ቁርጥ ሥጋ ካወራርድንበት ቤት በስተኋላ። በጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ ውስጥ ነው።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar