በብጹዕ አቡነ መቃሪዮስ ስም የሲኖዶሶች ድርድር
አስመላሽ ገበየሁ
ከደቡብ አፍሪካ
ከውጭው ሲኖዶስ በቁጥር 2087/2012 በ 10/19/2012 ለአዲስ አበባው ሲኖዶስ አቃቤ መንበር ለአቡነ ናትናኤል የተጻፍውን ደብዳቤ አስመልክቶ የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘንና ብስጭት ለመግለጽ ቃላቶች ያጥሩኛል። አባቶቻችን ሰላምታ መለዋወጣቸው ባልከፋ ነበር ሆኖም ወንድማቸውን ብጹዕ አቡነ መቃሪዎስን መስዋዕት ለማድረግ የተላከውን ደብዳቤ በተለይም “…..ይህንን ከባድ ስራ በምናካሂድበት ጊዜ የአፍራሽነት ተልዕኮ ያላቸው መስለው የሚታዩ ቢኖሩ እርምጃችንን የሚያሰናክሉ ሊሆን አይገባም። ለምሳሌ እንደ ብጽዕ አቡነ መቃሪዮስ ያሉ የሚናገሩትና የሚሰሩት በራሳቸው ፈቃድ እንጅ ሲኖዶሳችንን ወክለው እንዳይደለ ……እኛም የማንደግፈው መሆኑ እንዲታወቅልን…..” ይላል። በጣም ያሳዝናል። ለነገሩ ለዚችው ሆዴ በሬውን አረድኩት የሆነ ነገር ነው።ማለትም በአገራችን ብሂል
“በሬ ሆይ፤ በሬ ሆይ ሞኙ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገድሉን ሳታይ
እልም ካለው ገደል ገብተህ ወደቅህ ወይ?”
ዓይነት የሆነ ደብዳቤ ነው። ያሳዝናል። ዳሩ ግን በስብሃት ነጋና በአባይ ጸሐዬ የሚመራው የአዲስ አበባው ሲኖዶስ መቼ ዋዛ ሆነና በውጭ ያሉትና “ዕርቅ ሰላም” በሚሉት አባቶች ላይ የስቅላት የሞት ብይን አስተላለፈባቸውና 6ኛ ፓትርያርክ ሾመና አቆብቅበው የነበሩትን ሁሉ አስተነፈሳቸው። እንደ ዮሴፍ ወንድማችውን ለመሸጥ (ለመደራደር) የተፈተለው የድብዳቤ ፈትል ውሃ በላው።
የውጭው ሲኖዶስ አራተኛው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ትክክለኛው ፓትርያርክ ናቸው። የቤተክርስቲያን ህግ አንድ ፓትርያርክ በህይወት እያለ አሱን አስወግዶ ሌላ ፓትርያርክ መሾም ህገውጥነት ነው ብሎ ጸንቶ በመቆም ለወደፊቱ እንዳይደገም መሠረት የሆኑ ጉዳዮችን ማንሳትና ለጥንታዊቷ ተውህዶ ቤተክርስቲያናችን የነገረ መለኮትና ቀኖና ቤተክርስቲያን መቆም ሲገባው የኋሊት በመሄድ በብጹዕ አቡነ መቃሪዮስ ማመካኘት ምን ይሉታል? ወይንስ ውስጡን እንደምናውቀው በተሞከረው ድርድር ላይ አባ ጳውሎስ ብጹዕ አቡነ መርቆሪዎስን “ከሥልጣን የለቀቁት በህመም ምክንያት ወደው ነው” ብለው እንደዋሹና እንዲያስዋሹ በጋሻ ጃግሬዎቻችው የተቀነባበረ የስብሐት ነጋና የአባይ ጸሃዬ ሴራ ዓይነት ይሆን? ይህ ደብዳቤ እውነቱን የሳተ ያንቀላፋና ዓላማውን የሳተ ነው።
አቡነ መቃሪዎስን የወነጀለው ዶሴ ማብሪያሪያና ማስተባበያ ያስፈልገዋል። ዛሬ የተዋህዶን ትምህርት ያፋለሱ፣ ታሪክ ያቃወሱ ሰዎችንና መጻህፍቶቻቸውን እንዳንቀበል ሰርቶ ከማሰራትና በውስጣቸው በቤተ ምኩራብ የገበትን የሸቀጥ ሰዎች በክርስቶስ ጅራፍ ከመገሰጽ ይልቅ ብጹዕ አቡነ መቃሪዎስ እውነትን በመናገር በጽድቅ የጀመሩትን ህይወት “አፍራሽ” ብሎ መደራደር ምን አመጣው? ከዮሴፍ የወንድሞች ሽያጭ በምንስ ይለያል? እንደዚህ ዓይነቱ ከንቱ የማሳጣት ቀላጤ በቤተክርስቲያን ጠንክራ እንድትነሳ ህዝባችንም ነጻ እንዲወጣ የሚያደርግ መንገድ አይደለምና እራሳችንን ከዕርም እናውጣ። ጨካኝ አለቃም አንሁን። “.. ዘይትሃጸብ እምድኃረ ገሠሠ በድነ ወካዕበ ይደግም ገሢሠ ምንተ ይበቁ አዖ….” ሲራክ 31፡30
ማለትም እሬሳ የነካውን ሰው መልሶ ለመንካት እጁን ቢታጠብ መታጠቡ ምን ይጠቅማል? እንዳለው ከገባንበት እርም ሳንወጣ እንደገና ሌላ እርም ውስጥ ለመግባት አንሞክር። ብጹዕ አቡነ መቃሪዎስን እርም ያልተጫናቸው ከተገፋው ህዝብ ጋር እንዳይቆሙ፣ እንዳያጽናኑ፤ እንዳይሰሩ፣ ለአገራቸውና ለህዝባቸው መከራ በአደባባይ እንዳይጮሁ እንቅፋት ከመሆን ያላለፈ ሚዛን የሌለው ማኒፌስቶ በስብሃት ነጋ መሆኑን አለማስተዋላችን ለዚችው ሆዴ በሬዬን አረድኩት እንደተባለ እውነተኛ አባቶቻችንን በጠላት መሸንገያ አንረድ።
ከዚህ አስጸያፊ አድራጎታችንም እንታቀብ። ይልቁንስ እርሙን ፈልጋችሁ አውጡና ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችንንም ለትውልዱም ፈውስ የሚሆነው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው “…አዕትቱ እምላዕእሌክሙ እኩየ…” ክፉን ከመካከላችሁ አውጡት 1ቆሮ 5፡13 ይላል እንጅ እውነትን የሚናገሩትን ከመካከላቸሁ አውጡና መደራደሪያ አድርጉ ወይም ሽጡ አይልም። የዚህ ዓይነቱ ወንድምን አሳልፎ የመስጠት ከውድቀትና ከዕንቅፋት በስተቀር ምንም ሊፈይድ አይችልምና እንጠንቀቅ። መከራው ቢበዛም ለተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትንሳዔ በመፈቃቀር፣ በአንድነት ከህዝባችን ጋር እንቁም። እራሳችንን በአስታራቂዎች ስም ከሥልጣን ናፋቂዎች ጉያና ከዕርምና ከተዋህዶ አሳዳጆች አናውጣ።
ብጽዕ አቡነ መቃሪዮስ በየአህጉራቱ ለምንገኝ ምዕመናን ኢትዮጵያዊያን በዚህ ምድር ተልኳችን ፈጽመን ፈጣሪ ወዳዘጋጀልን ቦታ እስክንሄድ የተጉ የእውነተኛ የእረና ምሳሌያችን ናቸውና በግፍ ለታሰሩ ይጮሃሉ፣ እንደበግ ለታረዱት ክርስቲያኖች ይጮሃሉ፣ በመንገላታት ላይ ላሉ ይጮሃሉ፣ ለስደተኞች ይጮሃሉ፣ በተለያየ መከራ ላሉ ይጮሃሉ፣ ለተቆራረጠችውና ወደብ አልባ ለሆነችው ኢትዮጵያይጮሃሉ። መስቀላቸውን ከፍ አድርገው በወገናቸውና በህዝባቸው ላይ ለሚደርሰው ማለቂያ ለሌለው ደባና የተደራረበ ግፍ ይጮሃሉ፣ ያዝናሉም። ለወገን ፍቅር ለቤተክርስቲያን አንድነትና ክብር ቆመው ለተሰው በዓለም ዙሪያ አጽማቸው ለተበተነው በረሃና ከተማ ሳይሉ ጸሎት ያደርጋሉ።
ብጽዕ አቡነ መቃሪዮስ ከተበተነው ስደተኛ ጋር የቆሙ የተወደዱ የቤተክርስቲያናችንና የአገራችን ተወዳጅ ብጹዕ አባት ናቸው። እኝህ አባት ከመንደርተኝነትና ከጎሰኝነት የራቁ ሁሉንም በእኩል አይን የሚያዩና የሚባርኩ ደገኛ አባት ናቸው። ፊታቸው ላይ የሚያዩት የህዝባቸው ሃዘን ያንገበግባቸዋል። በጥቅሉ የእውነተኛ ተዋህዶ አባት የታማኝ ኢትዮጵያዊ ዜግነት መምህር ምሳሌ ናቸው። ዛሬ አገር ማለት ጎጥ፤ ቤተክርስቲያን ማለት ጎጥ፣ ሐይማኖት ማለት ጎጥ፣ ወገን ማለት ጎጥ በሆነበትና ይኽው በሚሰበክበት የሕዝብን ሀብት የግሌ ነው በሚሉ ከንቱ ጎጠኞችና የሥልጣን ጥመኞች የሰነዘሩት ቀላጤ ባዶና መሠረት የሌለው እራሱ በራሱ የቀበረ ተቀባይነት የሌለው ደብዳቤ ነውና ከእንደዚህ አይነቱ የመጠላለፍ ውድቀት እንውጣ።ልብ ያለው ልብ ይበል!
|
torsdag 7. mars 2013
በብጹዕ አቡነ መቃሪዮስ ስም የሲኖዶሶች ድርድር
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar