mandag 25. februar 2013

ድንቄም ምርጫ!


ድንቄም ምርጫ!

የካቲት 21 2013
ላንዲት ሀገር መሰረታዊ የእድገት ሃይል ያላት የተፈጥሮ ሃብትና የሕዝቦቿ ሁለንተናዊ ብቃት ናቸው። የሕዝቦቿን ሁለንተናዊ ብቃት ለመገንባት ደግሞ ካሏት የትምህርት ተቋማትና
Ethiopian election 2013የትምህርቱ ስርአት በተጨማሪ በሕዝቦቿ መካከል  ያለው የባህል፣ የሃይማኖትና የአኗኗር መስተጋብር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦና በዚሁ ሳቢያም የሚገኘው ቀጥተኛ ያልሆነ የእውቀትና የልምድ አቅምና ዝውውሩ የሚናቅ አይሆንም። የተረጋጋና በመከባበር የሚመራ የሃይማኖት ስርአት፣ የአንደኛው እንቅስቃሴ ሌላኛውን በመደገፍ ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ እንቅስቃሴ፣ ጎጂ የሆኑ ብህሎችን በማስቀረት ላይ ያተኮረና የሁሉም ብህላዊ ዕሴቶቻችን አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ የማያነሳ ማሕበረሰብ ከሁሉም በላይ ለአንዲት ሀገር እድገት አስፈላጊዎች ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳ የተፈጥሮ ሃብትና ብቃት ያለው የሰው ህይል የእድገት መሰረቶች ናቸው ቢባልም እነዚህን ሃብቶች ስርአት ባለው መልክ አቀናጅቶና አስተባብሮ መምራት የሚችል የሕዝብ አስተዳደርም ወሳኝ መሆኑ አሌ ልባል አይገባም። ያሉንን ሃብቶች ወደ ውጤት የመቀየሩ ሂደት ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል ደግሞ ሀገሪቱ የህግን የበላይነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚቀበል ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና የሕዝብን የበላይነት የሚያምን ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሊኖራት ይገባል። ይህም ሲጠቃለል ለአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ቀጣይነት ዴሞክራሲና ዴሞክራሲአዊ ስርአት ወሳኝ ግብአት ነቸው ማለት ነው።
አንዳንድ ሰዎች ከዴሞክራሲ ውጭ እድገት ሊመጣ እንደሚችል አንዳንድ ሀገሮችን እየጠቀሱ ቢሞግቱም በቅርብ ጊዜያት እየወጡ ያሉ ስለ እድገት የሚያወሩ ከሂዎት ልምድ የተገኙ ተሞክሮዎችና ትንተናዎች ግን የእድገት መሰረት የሆነው ማሕበረሰብ ነፃነትና ሁሉንም ያማከለ የሃብት ክፍፍል ወሳኝ እንደሆኑ ያረጋግጣሉ። ነጻነትና የተማከለ የሃብት ክፍፍል ደግሞ ከዴሞክራሲ ፍሬዎች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ልብ ይሏል።
በሀገራችን ኢትዮጵያም ለእድገት ዋና ግብአት የሆነውን ዴሞክራሲን በወረቀት ላይ ለተመልካች እንዲመች በማስቀመጥና የነጻነትን አስፈላጊነትም በሚዲያ በመልፈፍ  ወያኔ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም። የዴሞክራሲ ውጤት የሆነው ነፃ ምርጫም ለወያኔ የፕሮፓጋንዳ አንዱ ጭራ እንጅ  የህግ የበላይነት የሚታይበት፣ የሕዝብ አሸናፊነት የሚታወጅበት፣ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛነት የሚገለጽበትና የምርጫ ታዛቢዎች ሳይሸማቀቁ ያዩትን የህሊና ፍርድ የሚሰጡበት መድረክ አይደለም። ይልቅስ ወያኔ ሲመቸው  እየታገለ ሳይመቸው እያጭበረበረ የሚጋልብበት ነጻ የግሉ ሜዳ እንጅ።
የወያኔ ምርጫ ተሳታፊዎች የተወሰኑት ከምርጫ በፊት በሰበብ አስባቡ የሚገፉ ውድድር ተብየው ውስጥ የገቡትም ቢሆኑ ወያኔ የፈቀደውን ያህል የምርጫ ድምጽ የሚሰጡ እንጅ የሕዝባቸውን እውነተኛ ድምጽ የሚያገኙ እይደሉም አልነበሩምም። ይህን ለማረጋገጥ ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም በቅርቡ የወያኔው አፈ ቀላጤ የምርጫ ህጉ ይከበር ብለው ጥያቄ ስላነሱት 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተናገረውን ብቻ መጥቀስ በቂ ይሆናልና።
ሰላሳ ሶስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች (በሗላ ላይ ቁጥራቸው በሶስት ወይም ባራት ቀንሷል) ባነሱት የምርጫ ህግ ይከበር ጥያቄ ላይ ተንተርሶ የተናገረው የወያኔው አፈ ቀላጤ “ተቃዋሚዎች ኖሩም አልኖሩም በምርጫው ላይ ብዙ ለውጥ አይኖርም” ነበር አለው። ይህን በብዙ መልኩ መተንተን ይቻል ይሆናል ባጭሩ ግን መልክቱ ተቃዋሚዎች ኖሩም አልኖሩም ምራጫውን በምንፈልገው መልኩ የምናስኬደው እኛ ወያኔዎች ነን፣ ተቃዋሚዎች ኖራችሁም አልኖራችሁም ውጤቱ ታውቋል፣ ተቃዋሚዎችን የምንፈልጋችሁ ላሯሯጭነት ብቻ ነውና ሌሎችንም ማለት እንደሆነ መገመት ከወያኔና አገዛዙ ጋር ከለሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለቆየ ማንኛውም ዜጋ የሚያስገርም አይሆንም።
ባለፉት የወያኔ ምርጫዎች መታዘብ እንደተቻለው በእንደዚህ ያሉ ኩነቶች ወቅት ወያኔ የሚገርሙ ድርጊቶችን ባጋጣሚ ሳይሆን ሆን ብሎ፣ በማንአለብኝነት ሲተገብር ቆይቷል እየተገበረም ነው። ከዚህ በፊት ወያኔን ወክለው በይስሙላ ምርጫው ላይ ተሳትፈው የነበሩ ዜጎችን ያለ ምንም ጭንቀት ሕዝብን በመናቅ ገለልተኛ ነኝ እያለ እራሱን በሚያታልለው የወያኔ ምርጫ ቦርድ ውስጥ እንዲሰገሰጉ በማድረግ የወያኔን አሸናፊነት ህጋዊ ሽፋን እንዲሰጡ ሲያደርግ መቆየቱና እያደረገም መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል።
ከዚህም በተጨማሪ ወያኔ የሚተማመንበትና ኩኩ ብሎ የሚታዘዝ ለማግኘት እርግጠኛ ሳይሆን ሲቀር ከዚህ በፊት የሚያውቃቸውን መልካም ታዛዦቹን ከከፍተኛ ወታደራዊ ስልጣን ሳይቀር አውርዶ በእንደዚህ አይነቶቹ የቀልድ ምርጫዎች ላይ ተሳትፈው አሸነፋችሁ እንዲባሉ ሲያደርግ መቆየቱ ያደባባይ ሚስጥር ነው። ከዚህ እጅግ የከፋውና ቀልድ ለማለትም የሚያስቸግረው ደግሞ ወያኔ  ሰሞኑን ለወረዳና አካባቢ ምርጫ እያደረገው ነው የተባለው ነው።  ባደባባይ ከአምስት ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት የሚለፈው ወያኔ በተለይ በአዲስ አበባ ለምርጫ የሚያቀርበው በመቸገሩ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ሃላፊዎችን ለምርጫ ለማቅረብ ወስኖ ማስመዝገቡ እየተወራ ይገኛል። ይህ ማለት ደግሞ ሁሉም የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ተቋማት ሙሉ በሙሉ በወያኔ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ያረጋግጣል ማለት ነው።
ከዚህ በፊት አንዳንድ መስሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወይም እጅግ በጣም የሚበዛው የስልጣን ቦታቸው በህወሃትና ወያኔዎች መወረሩ በጥናት መረጋገጡና መገለጹ የሚታወቅ ሲሆን በሰሞኑም ወያኔ ለይስሙላ ምርጫው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሌሎች ቀሪ የሕዝበ አገልግሎት ተቋማትም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ  በራሱ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን እንደከዚህ ቀደሙ ጥናት ሳያስፈልግ  ወይም ማንም ሳይጠይቀው በራሱ መንገድ ወያኔ አረጋግጧል። ይህም ማለት ወያኔ በሁሉም መስሪያ ቤቶች ሰርጎ ገብቶ የወያኔውን ምርጫ ቦርድን ሳይቀር በራሱ ሰዎች መቶ በመቶ ተቆጣጥሮ የፈለገውን እየገፋ ያሻውን እያወጣ ቀጥሏል። ስለዚህም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕዝብን እንወክላለን እስካሉ ድረስ እንደዚህ ካሉ ቀድመው ከተጠናቀቁ የይስሙላ ምርጫዎች ይልቅ ሕዝባዊ እምቢተኝነትን በማጠናከር ሕዝቡ ለመብቱ እንዲነሳና ነፃነቱን ራሱ እንዲያስከብር ለማድረግ የበኩላቸውን መወጣት ከሕዝባዊ ተወካይነታቸው በተጨማሪ የዜግነት ግዴታቸው ነው። አበቃሁ።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar