tirsdag 26. februar 2013
ፌስቡክን ለመታገል የቆረጠ የሚመስለው ታገል ሳይፉ!
በግምት ከአንድ ወር በፊት ይመስለኛል ታገል በግጥም መድብሉ ባሰፈረው “መታሰቢያ እና ምስጋና” ምክንያት በፌስቡክ ተቃውሞ የቀረበበት ታገል ከቁምነገር መፅሔት የየካቲት እትም ጋር ባደረገው ቃለምልልስ የ…ቀረበበትን አስተያየትና ተቃውሞ በሰከነ ሁኔታ በመሞገት ፋንታ ከመስመር በወጣ መልኩ አንድ ሚሊዮን እንኳን ያልሞላውን ኢትዮጵያዊ የፌስቡክ ተጠቃሚ በጅምላ ዘልፏል።በውኑ ታገል ፌስቡክን ያውቀዋል ተጠቃሚስ ነው? ወይንስ በሆድ አሳዳሪዎቹ የተሰጠው አጀንዳ አለ!?የታገል ፌስቡክን የማውገዝ ምክንያት ምን ይሆን!? እለት እለት እየተጠናከረ በመጣው አፈና ምክንያት ፌስቡክን እንደመተንፈሻ እና መንግስትን ለመታገል እንደዋነኛ መደራጃ እያገለገለ እንደሚገኝ ግልፅ ነው ታዲያ ሁሉንም ነገር ካላፈኑ እንቅልፍ የማይወስዳቸው ወያኔዎች የፌስቡክ ነገር ከቁጥጥራቸው እንደወጣ ስለተገነዘቡ ፌስቡክ የሚፈጠሩ ግሩፖቹን፥ገፆችንና የግለሰብ ፕሮፋየሎችን እየተከታተሉ ከመዝጋት ባሻገር ፀረ-ፌስቡክ የሆነ ዘመቻ ከጀመሩ ውለው አድረዋል እስከአሁን ፀረ-ፌስቡክ የሆኑ የፕሮፓጋንዳ ስራዎች በኢቲቪ፥ በሪፓርተር እና በዛሚ ኤ.ኤፍ.ኤም ቀርበዋል።ከሆድ አሳዳሪዎቹ ጋር እንዘጭ እንዘጭ ያበዛው “ታዋቂው” ታገል በወያኔ እየተካሄደ ያለው ፀረ-ፌስቡክ ዘመቻ እራሱን አካል ስለአደረገ ይመስለኛል ከመስመር በወጣ መልኩ ፌስቡክና ፌስቡካውያንን በአንድ ከረጢት አጭቆ የዘለፈው።=>>ሙሉውን ቃለምልልስ አያይዠዋለውና ያንብቡት
ታገል ሳይፉ ከቁምነገር መፅሔት የየካቲት እትም ጋር ያደረገው ፀረ-ፌስቡክ ቃለምልልስ በከፊል።
ታገል የሰጠውን ቃለምልልስ እንዳለ አላቀረብኩትም ነገር ግን በኔ እይታ የገረሙኝን ጥያቄና መልሶች እንዳለ አቅርቢያቸዋለሁ።
ቁምነገር፦ አዲሱን መፅሐፍህን መታሰቢያነቱን ለመለስ ልጆች ማድረግህን ፖለቲካዊ ትርጉም የሰጡት ሰዎች ነበሩ ምን ትላቸዋለህ?
ታገል፦ ብዙም የምልሽ ነገር የለም ማንኛውም ጤነኛ ሰው አንብቦ ሊረዳው የሚችለው ነገር ነው ።ራስሽ አስቢው መታሰቢያነቱ “አባታቸው ለሚወዳቸው ልጆቹ ፍቅር የሚሰጥበትን ጊዜ ያጣ ሙሉ እድሜውን ለሕዝብና ለሀገር የሰጠ ነበር” ይላል ። መቸም አባትየው ለሀገሩ ጊዜውን መስጠቱን ደጋፊውም ተቃዋሚውም የማይክደው ነገር ነው።አከራካሪው ጉዳይ ለሀገሩ በሰጠው ጊዜ ምን ያህል ጠቀማት ጎዳት የሚለው ይመስለኛል።እኔ እዚህ ውስጥ አልገባሁም።የኔ ጉዳይ ልጆቹ ናቸው ልጆቹ ደግሞ የፖለቲካ ምልክት የለባቸውም። ምን አልባትም እነኝህ ልጆች ከየትኛውም ተቃዋሚ ወገን በላይ የገዥው ፓርቲ ነገር አይጥማቸው ይሆናል። የአባታችንን ፍቅር ነጥቆናል ብለው ሊያስቡ ይችላሉ።እኔ እዚህ ውስጥ አልገባውም ነገር ግን እኔም አባትነኝና ባባታቸው የጊዜ እጥረት አባታዊ ፍቅሩን አጥተው መኖራቸው ብቻ ሳይሆን አጥተው መቅረታቸው እንደሰው ሊያሳዝነኝ ይችላል እናም መታሰቢያነቱን ለነዚህ ልጆች ለማድረግ አባትነት ውስጥ ያለው ሰብዓዊነት ብቻ በቂ ነው።ይሁን እንጅ እንደተባለው አይነት ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው መታሰቢያ አድርጌ ቢሆን ኖሮ ስህተት ነበር ማለት አይደለም።ከፈለግኩ ለወሰንጋላ ለአዳልሞቲም መታሰቢያ ማድረግ መብቴ ነው።መፅሐፌን ለማን መታሰቢያ ማድረግ እንዳለብኝና እንደሌለብኝ የሚነግረኝ ካለ መልሸ የምነግረው “ልኩን የማያውቅ ደፋር” መሆኑን ብቻ ነው።
ቁምነገር፦ በምስጋናው ገፅ ላይ ለአቶ በረከት ያቀረብከውን ምስጋና ያልወደዱልህ ሰዎች አሉ?
ታገል፦ ቅድም እንዳልኩሽ ማንኛውም አንባቢ የአንድን ደራሲ መፅሐፍ ሲገመግም ጣልቃ ከማይገባባቸው ጉዳዮች አንዱ የመታሰቢያ ገፅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የምስጋና ገፅ ነው።አንድ ደራሲ ለህሊናው ታማኝ ከሆነ የሚያመሰግነውን ሰው የሚመርጠው ሰውየው በሌሎች አይን የሚታይበትን ገፅታ ከግምት ውስጥ አስገብቶ መሆን የለበትም ይልቁንስ ሰውየው በእርሱና በስራው ላይ ካሳዳረው በጎ ተፅእኖ አንፃር ነው።በተረፈ በማይመለከተው ጉዳይ ገብቶ ማንን ማመስገን እንዳለብህና እንደሌለብህ እኔ ልንገርህ ማለት ትልቅ ጅልነት ይመስለኛል እንዲያውም (የአንድ ወዳጄን አባባል ልዋስና) ከዚህ አይነቱ ጅል ጋር ሲነፃፀር ቂሉ ማሞ አራዳ ነው ማለት ይቻላል።
ቁምነገር፦ አንዳንድ ሀብታሞችን በሰፊው ማመስገነህን ያልወደዱልህ አስተያየት ሰጭዎች አሉ?
ታገል፦ እውነቱን ለመናገር እዚህ ገፅ ላይ ደሀን የማመሰግንበት ምንም ምክንያት አልነበረም(ለዚህ አባባሌ ይቅርታ እጠይቃለው) ከሀብታሙም ቢሆን እኔን ሳይሆን ኪነጥበቡን ለማገዝ የጣሩት ተመርጠው ተመስግነዋል።(ታገል በሌሎች ሀገሮች መንግስት የጥበብ ሰዎችን በገንዘብ እንደሚረዳ እያስረዳ ይቀጥላል)
ቁምነገር፦ ከግጥሞቹ መጨረሻ ላይ መታሰቢያነቱን ያበረክትላቸውን ሰዎች (ከተለመደው ውጭ) በጣም ታሞግግሳቸዋለህ ብለው የሚተቹህ አሉ።
ታገል፦ ያልተለመደ ነገር ያልተለመደን ነገር ያስከትላል ልክ ነው በግጥሞቹ መጨረሻ ላይ እነ ልዑል ራስ መንገሻን የመሳሰሉ ታላላቅ የሀገር ባለውለታዎችን ደስ እያለኝ አመሰግናቸዋለው። በዚህ ዘመን ባለውለታን ማክበር ትልቅ ስቃይ ነው እንደ ጤናማ ነገር ተለምዶ የማይሰቀጥጠን ማንቋሸሽና ማዋረድ ነው።ከዚህ የተነሳ ሰው ሲሞገስ ለምን እንላለን ነገር ግን ዳገቱ የቁልቁለቱን ያክል ነው የሚባል ተረት አለ።ምን አልባት በየፌስቡኩና በየሚዲያው ታላላቅ የሀገር ባለውለታዎች የሚናገሩትን በማያውቁና የማያውቁትን በሚናገሩ ምላሶች ዝቅ ዝቅ መደረጋቸው ከፍ ከፍ እንዳደርጋቸው ያነሳሳኝ ይመስለኛል ።ስለዚህ ጀግኖችን ለማንሸራተት ያበጁት ቁልቁለት ካልሰቀጠጣቸው የቁልቁለቱን ያክል ብድግ ያለውም ዳገት ሊረብሻቸው አይገባም።ምክንያቱም የኔን ዳገት የፈጠረው የነሱ ቁልቁለት ነው።
ቁምነገር፦ እስከአሁን ድረስ በፌስቡክ ላይ ለወረዱብህ ውግዘቶች ይኸን ሁሉ ምላሽ ይዘህ ድምፅህን ያጠፋኸው ለምንድን ነው?
ታገል፦ ከመፅሐፍ ቅዱስ የምወደውና የሚመራኝ አባባል አለ።”የባልቴቶች ከሚመስል ወሬ እራቅ” ይላል። እኔ ድሮ የማውቀው የባልቴቶች ወሬ በረከቦት ዙሪያ እንደነበር ነው።አሁን ወጣት ባልቴቶቻችን የሚሰበሰቡበት ረከቦት ፌስቡክ ሆነ።ስለዚህ ከዚህ አካባቢ ወሬ /መልስ ባለመስጠት/ መራቅ ነበረብኝ።
ቁምነገር፦ ከዚህ ሁሉ ውዥንብር አንፃር ፌስቡክ ጠቃሚ ነው ትላለህ?
ታገል፦ ጠቃሚነቱ ምንም አያጠያይቅም ግን ይህን የሚወስነው አጠቃቀማችን ነው።እዚህ ላይ የማስታውሰውን ገጠመኝ ልንገርሽ ከአንድ አዛውንት ጋር ታክሲ ውስጥ ቁጭ ብያለሁ ከውጭ ጆሮው ላይ ሎቲ አንጠልጥሎ ጎዳናውን የሚያቋርጥ አንድ ወጣት ተመለከትኩና ወደ እኝህ አዛውንት ዘወር ብየ “አባቴ በእናንተ ዘመን ሰዎች አንበሳና ቀጭኔ ገድለው ነበር ሎቲ የሚያንጠለጥሉት ይህ ወጣት ምን ገድሎ ይመስሎታል ሎቲ ያንጠለጠለው?” ስል ጠየኳቸው አዛውንቱም አየት አድርገውት “እንግዲህ ይህ ደግሞ ጊዜ ገዳይ ይሆናል በዛ ፌስ ቡካችሁ” ነበር ያሉኝ። እንደኔ እንደኔ ፌስቡክ ላይ ችግር የሚፈጥሩት ለፌስቡክ ክብር የሌላቸውና ፋይዳውን በቅጡ ያልተገነዘቡት ወገኖች ናቸው።እነዚህ ወገኖች ድሮ ድሮ ስማቸውን ደብቀው በየሽንትቤቱ ግድግዳ ላይ ብዙ አይነት ሀሜቶችንና ነውሮችን ሲፅፉ የኖሩ ይመስለኛል።አሁን ደግሞ ፌስቡክን እንደሽታ አልባ የሽንት ቤት ግድግዳ ሳይቆጥሩት አልቀረም። ድሮ በሽንት ቤት ግድግዳ ላይ እንደሚያደርጉት ዛሬም ስማቸውን ደብቀው ያሻቸውን ነውር ይፅፋሉ ።ያም ሆኖ ፌስቡክ የሽንት ቤት ግድግዳ ሆኖ የቀረው በነዚህ ወገኖች ደካማ ግንዛቤ ብቻ እንጅ በአግባቡ የሚጠቀሙት ወገኖች አይደለም።
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar