የቃሊቲ ወይስ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ምስጢሮች?
በግሩም ተ/ሀይማኖት
‹‹የቃሊቲ ምስጢሮች›› የሚለውን መጽሐፍ ለመቃኘት ወደድኩ፡፡
ወዳጄ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› የሚል መጽሐፍ ማሳተሙን በኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ፎረም እና ማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ማስታወቂያ አየሁና ተደሰትኩ፡፡ ምክንያቱም ቃሊቲ የታጎሩትን የፖለቲካ ትኩሳቶች፣ አፈናዎች..የመሳሰሉትን ያስቃኘናል ብዬ ነው፡፡ ሲሳይን እንኳን ደስ ያለህ ያልኩት ከልብ ነበር፡፡ ደስታዬን ለእሱ አደረስኩና መፀሐፏን ፍለጋ በየአቅጣጫው አዳረስኩ፡፡ መጽሐፏን ለማንበብ ጓጉቼ ነበር እና ኢትዮጵያ ከገባ፣ ካገኙት እንዲያመጡልኝ ከየመን የሚመላለሱ ነጋዴዎችን ተማጸንኩ፡፡ የየመናዊያንን አባባል ያስታወሰኝ ክስተት ተከሰተ፡፡ ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› የሚለውን ሳይሆን ‹‹የቃሊቲ ምስጢሮች›› የሚል በጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን የተጻፈ መጽሐፍ አመጡልኝ፡፡ ‹‹ምነው ያልኩሽ መጽሀፍ የለም?›› አልኩ፡፡ ያው ነው ያንን ስላጣሁ ይሄም ስለቃሊቲ ነው የሚያወራው ብዬ አመጣሁት አለችኝ፡፡
የመናዊያኑን መድኃኒት ወይም ሌላ ነገር ልትገዙ ወደ አንዱ ሱቅ ጎራ ስትሉ የፈለጋችሁትን እቃ ስትጠይቁ ከሌለ የለም አይሏችሁም፡፡ ‹‹..ሀዘ ነፍሱ ሸሪካ ዋህድ..›› /ይሄ በአንድ ድርጅት የተመረተ ነው/ ይላሉ፡፡ ከሚፈልጉት ጋር ፈጽሞ የማይመሳሰል እቃ አንስተው፡፡ አስቡት ሚዝል ፈልጋችሁ ፓራሲታሞል ሰጥተው ያመረተው አንድ ድርጅት ነው ሲሏችሁ፡፡ ለእኔም የተላከችው ልጅ ያው ሁለቱም ስለቃሊቲ ነው ብትለኝም ሁለቱም በነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች የተፃፉ ስለሆነ እንዲያውም ይበልጥ ተደሰትኩኝ፡፡ ምክንያቱን ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን መጽሀፍ ማሳተሙን ባለማወቄ እና በአጋጣሚ በማየቴ ነው ደስታዩ እንጂ የአንዱ ከአንዱ ይበልጣል ብዬ አይደለም፡፡ ሁሉም የየራሱ አጻጻፍና መንገድ አለው፡፡ ደግሞም ለእኔ ሁለቱም የማላበላልጣቸው የሞያ ጓደኞቼ ናቸው፡፡
ከጓደኝነታቸውም በላይ ግን ለመጽሐፉ ያሳቀፉትን አንኳር እና ንጥር ሀሳብ ነው ማጣጣም የፈለኩት እና…..
‹‹የቃሊቲ ምስጢሮች›› የሚለውን መጽሀፍ መታተም እንዴት አንዱም ማህበራዊ ድረ-ገጽ አላስተዋወቀም? የሚለውን እሳቤ እያንከላወስኩ ወደ ንባቤ ገባሁ፡፡ ለህዝብ ያለማሳወቁ ድክመት ያለው ማን ጋር ነው? ይህን የመሰለ አነጋጋሪ መልዕክት ለምን ተዋጠ? የሚለውን ጥያቄ በውስጤ ሳንጎዳጉድ ነው አንብቤ የጨረሰኩት፡፡ የመጨረሻውን ገጽ የመደምደሚያውን ምዕራፍ እስካጣጥም የተለያዩ መላምቶች በውስጤ ብልጭ!!..ይሉና አንዳንዶቹ ሲጎሉ እውነታነታቸውን ሲያሳዩ ሌሎች በቂ ምክንያት ሳይኖራቸው ቀርቶ ይከስማሉ፡፡ እንደኔ እንደኔ ከሆነ መጽሀፉ ስልታዊ ገለጻን፣ ስሜታዊነትን፣ በተጻራሪ ሽፍንነትን፣ የሀገራችን የፖለቲካ ሰዎች ማንነትን..የነጻ ፕሬሱን ጥንካሬና ጥቂት ድክመትን..ብቻ ሁሉን ለመነካካት ሞክሯል፡፡ ሞክሯል ብቻ ሳይሆን ገመና ገልጧል፡፡ ድንገት በርካታ ድረ-ገጾች ያልነኩት፣ ያላስተዋወቁት በስም ብቻ ተቆልለው የምናቃቸውን አውርዷቸዋል፡፡ ግዙፍ የሚመስሉ የፖለቲካ ሰዎች በእስር ቤት የነበራቸውን አሳፋሪ ውስጣዊ ማንነት ማጋለጡ ይሆን ውግዝ ከመአሪዮስ ያስባለው የሚል እሳቤ ከሁሉም ጎልቶ ሲሞግተኝ ነው አንብቤ የጨረስኩት፡፡
እውን በዚህ ምክንያት ከሆነ ይህ መጽሐፍ መታተሙን አንዳቸውም ለአንባቢ እንዲደርስ ጠቆም ያላደረጉት አልኩ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ያለባቸውን ችግርና የአቋም ዝንፈት አስተውያለሁ፡፡ አንዳንዴ ድረ-ገጾቹን አይና የመናገር ነጻነት፣ የመጻፍ ነጻነት…ቅብርጥሴ እያሉ የሚጮሁት ለምንድን ነው? ከራሳቸው ያልተጀመረ ነጻነት ከማን እንዲጀመር ናፋቂዎች ናቸው..ብዬ አስብ ነበር፡፡ ማጣራት ፈለኩ እና ወደ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን ስልክ መታሁ፡፡ ውስጤ የገመተውን እውነት ሆኖ ማግኘቴ ገርሞኛል፡፡ በእርግጥም የማስተዋወቅ ግዴታ የለባቸውም፡፡ ቆየት ብሎ ግን ሀበሻ ድረ-ገጽ ብቻ ዳሶታል፡፡
ሌሎቹ ላይ ስፈልግ ያላየሁት ከእኔ ድክመት ካለ ይቅርታዬን ቀድሜ ላስቀምጥ፡፡ ግን በተስፋዬ ገ/አብ ጽሁፍ ውስጥ ባገኘሁት አባባል ልጠቀምና ጎግል አቃጣሪውም ስጠይቀው አላቃጠረልኝም፡፡ ወሰንሰገድ ግን ለብዙዎች ቢልክም ሊረዱት የፈቀዱት ጥቂቶች መሆናቸውን ነገረኝ፡፡ በእርግጥ ሁሉም ማህበራዊ ድረ-ገጾች ነጻ ናቸው ወይ? የሚል እሳቤ ሁሌም የማስበው ቢሆንም ለማጣራት ራሱን የቻለ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ የመናገር ነጻነት፣ የመጻፍ መብት ይከበር ካሉ እነሱ የወደዱትን ጽሁፍ አስፍረው ሌላውን ማገድ ነጻ ያሰኛቸዋል ወይ? አያሰኝም፡፡ የሚደግፋቸውን ጽሁፍ አስፍረው እነሱ የሚወዱዋቸውን፣ የሚያከብሯቸውን ወይም የሚደጉሟቸው ፖለቲከኞችን የሚነካ ጽሁፍ ከገፉ ከመንግስት መገናኛ ብዙሀን በምን ተለዩ? የሚል እሳቤ ሁሌ ይሞግተኛል፡፡
ሌላው ቀርቶ ብዙዎቹ ድረ-ገጾች እዚህ የመን ውስጥ በርካታ ወገኖች እያለቁ፣ በርካታ ወገኖች እየወደቁ ሌሎች በጉዞ ላይ ሆነው ችግር አለ፡፡ ለህዝብ አሳውቁልን፣ ወገን እያለቀ ነው ስንል ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው ሁሌ ያሳፍረኛል፡፡ የህዝብ ቁስል ቁስላቸው ካልሆነ፣ የህዝብ እንባ ካልታያቸው፣ የወገን ማለቅ ካላሳሰባቸው አላማቸው ምን ይሆን? የሚል ጥያቄ ውስጤ ይንጎዳጎዳል፡፡ በአንድ ወቅት የመን በጦርነት ስትናውዝ 8 ኢትዮጵያዊያን ሞተው ሆስፒታል ራሴ ሄጄ ሬሳውን ማየቴን ሁሉ እየጠቀስኩ በችግር ውስጥ መሆናችንን አሳይቼ የጻፍኩትን ዜና ከሁለትና ሶስት ድረ-ገጾች ውጭ አልዘገቡትም፡፡ በተቃራኒ አንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ በሌሉበት ተከሰው ፍርድ ቤት ምስክርነት ሊሰማ ቀጠሮ ነበር፡፡ ዳኞች ስላልተሟሉ……የሚል ዜና ድረ-ገጾችን ሁሉ አጣቦ ነበር፡፡ ልብ በሉ ሚዛን የሚደፋው የቱ ነው የህዝብ ዋይታ፣ እልቂት ወይስ የአንድ መንግስትን ተቃዋሚ በሌሉበት ተከሶ ፍ/ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ? መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ህዝብ የሌለበት ምንድን ናቸው?…..በእርግጥ ሁለቱም ዜና ነው ለምን ጎን ለጎን አይለጠፍም?
አሁን ወደ መጽሐፉ ልመለስ፡፡ በመጀመሪያ በጎመን ደንደስ…ምን ይወደስ ያስባለኝ ነገር ወሰንሰገድ አውቆ ይሁን ሳያውቅ ሰፍሯል፡፡ ‹‹…ባስታወስኩት ቁጥር የህመም ስሜት የሚፈጥብኝ ‹‹ቴር ዶ ዞም›› የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ ስለሚረዱ ኢትዮጵያዊ ወንድ ህጻናት ላይ የተፈፀመውን የወሲብ ጥቃት ነው፡፡..… ይሁን እንጂ የድርጅቱን ስራ በበላይነት የሚመሩት የውጭ ዜጎች ዕድሜያቸው ከ10-13 ዓመት የሆኑ ህጻናት ወንዶችን እያባበሉ የወሲብ ጥቃት እንደሚፈጽሙባቸው ተደረሰባቸው፡፡ ይህንን አፀያፊ ተግባር ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋለጠቸው በድርጅቱ ውስጥ በክሊኒካል ነርስነት ተቀጥራ ስታገለግል የነበረቸው ወ/ሮ ትዝታ ገብሩ ናት፡፡ ዜናውን ከሁሉ ቀድሞ ያወጣው ደግሞ ‹ሪፖርተር› ጋዜጣ ነበር፡፡…›› ብሎታል ወሰንሰገድ እንደመግቢያ ያሰፈረው ጽሁፍ ላይ፡፡ እውነታው ግን ይሄ ነው ወይ?
ፈረንሳያዊው ሚስተር ማርክ /ከጊዜው ርዝመት አንጻር ስሙን ሙሉውን ማስታወስ አልቻልኩም/ ለቴር-ዴዞም ስራ ቢመጣም ሰርከስ ኢትዮጵያን ያዋቀረው እሱ ነበር፡፡ በወቅቱ ይህ በቴር-ዴዞም ውስጥ የተፈጸመውን ድርጊት ሲሰማ ቁጭት ያርመጠምጠው የነበረው አብይ አየለ የሰርከስ ኢትዮጵያ የሙዚቃ እና ቴያትር ክፍሉን ይመራ ነበር፡፡ የሰርከስ ኢትዮጵያ አባላት ቡድን ጀርመን ሰንብተው ሲመለሱ ነው አብይ ስለሁኔታው ያዋየኝ፡፡ ቀጣይ ጉዞ ያደረጉት ወደ አውስትራሊያ ነበር፡፡ አስተካክሎ መረጃውን የሰጠኝ አውስትራሊያ በሄዱበት ጊዜ ነው፡፡ 15 አባላቱም እዛው ቀሩ፡፡ ዋነኛ ችግራቸው ህጻናቱ እዛ ህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ በነበሩ ወቅት ይፈጸምባቸው የነበረው ህሊና የሚጎዳ የመደፈር ድርጊት ነበር፡፡ ሰርከስ ኢትዮጵያ ውስጥ የሙዚቃ እና ቴያትር ክፍሉን የሚመራው ጓደኛዬ አብይ አየለ ስለሁኔታው ከሀገር ከወጡ በኋላ መረጃውን መስጠት የመረጠው የልጆቹንም ሆነ የራሱን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ነበር፡፡ ነግሮኝ ቅይጥ ጋዜጣ ላይ የሰራሁት በ1989 ዓ.ም መጨረሻ ነበር፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ የሰራው ከሁለት አመት በኋላ ነው፡፡ እውነታ መፋለሱን ለመጠቆም እና የአብይ አየለ ተቆርቋሪነትም እንዳይረሳ ለመጠቆም እንጂ ድርጊቱን ማንም አጋለጠው ማን አስጠሊታ እና ሰቅጣጭ ነበር፡፡ መፍትሄ የተበጀለት በመሆኑ ግን ወሰንሰገድ እንዳለው ያስደስታል፡፡
በዚህ የቃሊቲ ምስጢሮች መጽሀፍ ውስጥ ታሪካዊ ኩነቶች ሰፍረዋል፡፡ እንደዋዛ ልናያቸው የማይገቡ በኢትዮጵያ መንግስትን ለመጣል በምርጫ ላይ ታሪካዊ የህዝብ ድምጽ የታየበት ወቅትን ተከትሎ የመጣ ክስተትን ነው የዳሰሰው፡፡ የ1997 የኢትዮጵያ ታሪካዊ ምርጫን ውጤት መንግስት በመደፍጠጡ ህዝቡ ድምጹን ለማስከበር ያደረገው እንቅስቃሴ አይረሴ ነው፡፡ ከሰባ ሺህ በላይ ህዝብ በየእስር ቤቱ የታጎሩበት እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባሎች ታድነው ቃሊቲ ወህኒ ቤት በተጣሉበት ጊዜ የነበረውን ቆይታ አሞናሙኖ አስፍሮታል፡፡ አሞናሙኖ ስል በጣም የተጋነነ ያስመስለው ይሆን? የወሰንሰገድ አጻጻፉን ሳይሆን ታሪኩ ላይ ብቻ ነው ትኩረት ሰጥቼ የሸከሸኩት፡፡ ቅንጅት ተብሎ ሲጠራ ውስጣችን ተንሰራፍቶ የተጎበረ ትልቅ ተስፋ ነበር፡፡ የነበረውን እውነታ የሚንድ አሳፋሪ ገመናቸውን አሳይቶናል፡፡ ተችቷቸዋልም፡፡ ከተተቹት ውስጥ ግን በስም የተጠቀሰው አንድን ሰው ብቻ መሆኑ ሳያስገርመኝ አላልፈም፡፡ የትችት ካራው ያላረፈባቸው የወዳጅነት፣ የሰፈር ልጅነት ካባ ያለበሳቸው ሰውም አሉ፡፡ ምላሽ ባገኝ ደስ የሚለኝ ለምን ይህ ሆነ የሚለውን ነው፡፡
በማዕረጋቸው እየጠቀሰ ከሚተቻቸው ውስጥ ደግሞ አንድ ዶክተር ላይ በጣም በጠነከረ መልኩ ያዘንብባቸዋል፡፡ በእርግጥ ሰውየው ተገለባባጭ ናቸው የሚለው ሀሜት ቀድሞ የተሰማ ቢሆንም ትችቱ ከብዶባቸዋል፡፡ የሆነ ሆኖ የ1997 ተቃዋሚዎችን ድክመት መግለጹ ለቀጣዮቹ ጠቋሚ አይሆንም ማለት አይቻልም፡፡ የመጽሀፉንም ሆነ የተቃዋሚዎቹን ድክመቶች እንደድክመት ጥንካሬዎቹን እንደጥንካሬ ማየት ቢቻል ውጤት ይኖረዋል፡፡ ፖለቲከኞቻችንም ሁሌም እንደበግ ‹‹እንክ..እንክ…›› እንድንባል ብቻ አትጠብቁ፡፡ ከነስህተታችሁ እየተጎበራችሁ ማን ከኔ በላይ አይነት ህሳቤ ይዛችው አትጓዙ፡፡ ከአንድ ምሁር ተብዬ ፖለቲከኛ የማይጠበቅ አንድን ብሔረሰብ ድፍጥጥ የሚያደርግ ንግግር እየሰማን እስከመቼ ዘም ማለት የለብንመን፡፡ የእናንተ ዶክተር፣ ኢንጂነር እና ፕሮፌሰርነት ያመጣው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ስህተታችሁ ሲነገራችሁ ማረምን ብትለምዱ ነገጠንክራችሁ ትቀርባላችሁ፡፡ ስህተት ነጋሪውን መርገምና መኮነን ባህል ባናደርግ ይመረጣል፡፡
ብዙ በጭፍን የሚደረጉ ነገሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወያኔን እየተቀሙ እና መንገድ እየከፈቱለት መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar