onsdag 27. februar 2013

ጋዜጠኛ ውብሸትና አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር ሊፈቱ ነው


የካቲት ፩፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በሽብርተኝነት ተከሰው በወህኒ ቤት የሚገኙ በጣም በርካታ እስረኞች የይቅርታ ፎርም እንዲሞሉ እየተደረገ መሆኑን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ገለጸ።
ተመስገን ፦<<አቃቤ ህግ ዕዳ አለብህ >>በሚል ርዕስ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ  ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና አቶ ዘሪሁን ገብረ-እግዚአብሔር  በብዛት ከሚለቀቁት እስረኞች ጋር  አብረው እንደሚፈቱ ምንጮች አረጋግጠውለታል።
<<ይህ የሚደረገው ምንአልባት የሀይለማርያም መንግስት ሪፎርም /ማሻሻያ/ የማድርግ ዕቅድ ካለው በዚሁ ሊጀምር አስቦ
ሊሆን ይችላል፤ አሊያም እንደተለመደው እስረኛ በመልቀቅ የፖለቲካ ማሻሻያእንደተደረገ ለማስመሰል ይሆናል>> ብሏል ተመስገን።
በሌላ በኩል በዛሬው ዕለት  በከፍተኛው ፍርድ ቤት የእነእስክንድር ነጋን ንብረት ለመውረስ ፍትህ ሚንስቴር የመሰረተው ክስ ሲታይ መዋሉን ጋዜጠኛ ተመስገን ጨምሮ ገልጿል።
እስክንድር  ቀደም  ሲል፦‹‹የታሰርኩት በግፍ ስለሆነ ንብረቴን አትውረሱ ብዬ አልከራከርም፤ ዛሬውኑ ልትወስዱት ትችላላችሁ›› በማለት ስለ ንብረቱ አለመከራከሩን ያወሳው ተመስገን፣ የአበበ በለውን ንብረት በተመለከተ የተመሰረተው ክስ ተከሳሹ በሌለበትመታዬቱን አመልክቷል፡፡
 እንደ ተመስገን ገለፃ የአንዱአለም አራጌ ባለቤት ደግሞ በስሟ የተመዘገበው መኪና መወረሱ አግባብ እንዳልሆነ በጠበቃዋ በአቶደርበው ተመስገን አማካኝነት ተከራክራለች፡፡

 ፍርድ ቤቱም በጉዳዩ ላይ  ውሳኔ ለመስጠት  ለመጪው ሚያዚያ አስር ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል።
<<በእኔ ግምት ቀጠሮው እንዲህ የራቀው መጋቢት አስራ ስምንት ቀን እነእስክንድር የጠየቁት ይግባኝ የመጨረሻ ውሳኔ ስለሚሰጥበት ከዛ በኋላ የንብረቱን ጉዳይ ለመጨረስ ይመስለኛል>>ሲልም  ጋዜጠኛ ተመስገን ግምቱን አስቀምጧል።
 ዓቃቢ ህግ ቀደም ሲል የእስክንድር ንብረት ተብለው ከቀረቡት ባለሁለት ፎቅ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት፣ በባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል ስም የተመዘገበ የቤት መኪና፣ እንዲሁም የእስክንድር እናት ንብረት የሆነ በአንድ ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤትን ለመውረስ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ያስታወሰው ተመስገን ፣ በዛሬው የችሎት ውሎ በእናቱ ስም የተመዘገበውን ቤት እንደተወው ገልጿል።
አዲስ ታይምስ መፅሄት የእናቱ ቤት  በንብረት ውርስ ዝርዝር ውስጥ መግባቱ ተገቢ እንዳልነበር  ደጋግማ መግለጿን ተመስገን አስታውሷል።
ተመስገን ጽሁፉን ሲያጠቃልልም፦<<ይህንና ዓቃቢ ህግ በእስክንድር እናት ስም የተመዘገበውን መኖሪያ ቤት ከሚወርሳቸው ዝርዝር ውስጥ በማውጣቱ ምንም አይነት ምስጋና የለኝም፡፡ ምክንያቱም እንኳን ንብረታቸው ሊወረስ ተከሳሾቹም ምንም ጥፋት ያላጠፉ ንፁሀን ናቸው ብዬ ስለማምን፡፡ስለዚህም አሁንም እንዲህ እላለሁ፡- ዓቃቢ ህግ ዕዳ አለብህ! አዎ እዳ አለብህ!! ንፁሀን ወንድሞቻችንን ይቅርታ ጠይቀህ እስክትለቅልን ድረስ!!!>>ብሏል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar