ድምፃችን ይሰማ
በእርግጥ ግለሰቡ የባለስልጣን ግብር አላቸው?
ባሳለፍነው ሳምንት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ዲኤታ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ኢትዮ ቻናል ከተባለው ጋዜጣ ጋር አንድ ቃለመጠይቅ አድርገው ነበር፡፡ ጋዜጣው የመንግስት ፕሮፓጋንዳ መንዣ መሳሪያ ከሆኑ ‹‹የግል›› ጋዜጣዎች ውስጥ አንዱ እንደመሆኑ ምን አይነት ይዘት ያለው ነገር እንደሚያወጣ ለብዙዎች ድብቅ አይደለም፡፡ ያወጣውም ብዙዎች ከሱ የሚጠብቁትን ፕሮፓጋንዳ አይነት ጽሁፍ ነበር፡፡ ኢቲቪ የፍርድ ቤት ትእዛዝን ጥሶ ባስተላለፈው አሳፋሪ ‹‹ዶኩመንታሪ›› ፊልም የተነሳ የደረሰበትን ውግዘት እና የፕሮፓጋንዳውን መክሸፍ ሊያስተባብሉ ነበር አቶ ሽመልስ ከማል በኢትዮ ቻናሉ ቃለ መጠይቅ ብቅ ያሉት፡፡
ቃለ መጠይቁ ከአንድ ትልቅ የመንግስት ባለስልጣን እንደመምጣቱ ጨዋነትን የተላበሰና ደረጃውን የጠበቀ መሆን በተገባው ነበር፡፡ ያ ግን አልሆነም፡፡ አስገራሚ በሚባል ደረጃ ከቃላት አጠቃቀሙ ጀምሮ በሁለመናው ዝቅ ያለ እና የወረደ ነበር፡፡ ቃላቶቹ ተራና ‹‹የመንደር›› ከመሆናቸውም ሌላ ግለሰቡ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የሻቸውን የሚናገሩ እንደሆኑ ያሳብቁ ነበር፡፡ አንድ የመንግስት ባለስልጣን የሚናገራቸውን ነገሮች የኋላ ውጤት ያለምንም ማገናዘብ እንዳመጣለት መናገሩ አገራችን ውስጥ በመንግስት እና በግለሰብ መካከል ያለው ለውጥ ከነጭራሹ እየጠፋ መምጣቱን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡
ግለሰቡ በረዥሙ ቃለ መጠይቃቸው በርካታ ሀሳቦችን አንስተዋል፡፡ ሁሉንም እዚህ እያነሳን ልንነጋገርባቸው ባንችልም የተወሰኑትን ብቻ ጠቀስ ጠቀስ እያደረግን ምልከታችንን እንሰጥባቸዋለን፡፡
አቶ ሽመልስ በቃለ መጠይቃቸው እጅግ አብዝተው ያነሱት ስለ ‹‹ሽብርተኝነት›› ነው፡፡ የተለያዩ ፖለቲከኞች ስለሽብርተኞች እና አልቃይዳን ስለመሳሰሉ ድርጅቶች የተናገሯቸውን አንዳንድ ጥቅሶች እየጠቀሱ፣ ስለፈንጂ ጉዳት እያነሱ ከኛው ሰላማዊ እንቅስቃሴ መሪዎች ጋር ለማገናኘት ይሞክራሉ፡፡ ሁለቱ የሰማይና ምድርን ያህል የሚራራቁ ነገሮች እንዴት እንደተገጣጠሙላቸው ግልጽ አይደለም፡፡ ‹‹… ይሄ ሴራ ተግባራዊ ሆኖ ቢሆን ኖሮ በበርካታ ንፁኃን ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ኑሮ ላይ፣ በህይወታቸው፣ በንብረታቸው ላይ በግምት ሊሰፈር የማይችል እጅግ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል እሙን ነው፡፡ ስለዚህ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ከፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ጋር ባደረገው ክትትል ይሄንን ሴራ ገና በእንጭጩ ለማምከን ችሏል›› ሲሉም የማይመስል ነገር ይናገራሉ፡፡ አመት ያለፈው እንቅስቃሴያችን ሰላማዊ ብቻ መሆኑ አይደለም ለአገራችን ይቅርና ለዓለምም ተረጋግጧል፡፡ መንግስት በየጁሙአው ‹‹ድንጋይ ይወረወራል›› በሚል ተስፋ እንዲሰባበሩ አንዋር መስጊድ በተቃውሞ ሰአት የሚያስቆማቸው አንበሳ አውቶቡሶች እንኳን አንድም ቀን የመሰበር እጣ አላጋጠማቸውም፡፡ አቶ ሽመልስ ግን በኢቴቪ የተላለፈውን መረጃ አልባ ዶኩመንተሪ ‹‹ባናሳየው ኖሮ አገሪቷ ትፈርስ ነበር›› ለማለት ይዳዳቸዋል፡፡ ይህንኑ ‹‹ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል›› የሚለውን ንግግር ከመደጋገም ባለፈ አንዳችም ማስረጃ ያላቀረበውን ፊልማቸውን እየጠቆሙም ሌላ አስገራሚ ነገር ይነግሩናል፡-
‹‹እነዚህ ሰዎች ከኃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው መሆኑን መነሻቸውም፣ ማምሻቸውም፣ ግባቸው ፖለቲካዊ መሆኑን እነሱ የሚፈልጉትን የአንድ እምነት ህግጋት እና ይሄንን ህግጋት የሚያስፈፅም አምባገነናዊ ኃይማኖታዊ መንግስት የመገንባት ዓላማ ያላቸው መሆኑን የሚያጋልጡ በርካታ ሰነዶች እየወጡ ነው፡፡ የዚህ ሰነድም አንደኛው የዶክመንተሪው ዓላማም ይሄ ነበር›› ይሉናል፡፡ ፊልሙ ላይ ሕዝቡ እንደተመለከተው ከኮሚቴዎቻችንም ሆነ ከሰላማዊ እንቅስቃሴያችን ጋር የተያያዘ በርካታ የሰነድ ማስረጃ ይቅርና አንድ እንኳ ሰነድ ሊቀርብ አልቻለም፡፡ ይህንን ፊልሙን ያየ ሁሉ አይቶታል፡፡ በተመልካቹ ዘንድ ዜሮ ተቀባይነት ያገኘውም በዚሁ እንደሆነ የዘነጉት ይመስላሉ – አቶ ሽመልስ፡፡ ወረድ ብለው ደግሞ ግለሰቡ ሌላ አስገራሚ ነገር ጠቅሰዋል፡፡ ኮሚቴዎቻችንን አስመልክቶ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥተዋል፡- ‹‹…እነዚሁ የምናውቃቸው ዛሬ የሙስሊም መሪዎች ነን ምንትሴ ነን እያሉ የወጡ አክራሪዎች ናቸው – እነሱ ናቸው ይሄንን ስብከት የሚያሰራጩት – ይሄን መላው የኢትዮጵያ ሙስሊም አበጥሮ ያውቀዋል፡፡ በዚህ የሚታለል የለም – ዓላማው ይሄ እንዳልሆነ ይታወቃል›› ብለዋል፡፡
ቃለ መጠይቁን የሞሉትን ‹‹ምንትስ…. ቀጣፊ›› … ወዘተ አይነት ቃላቶች አቶ ሽመልስ ለተቀመጡበት ወንበር እንኳ የማይመጥኑ አሳፋሪ መሆናቸውን ለጊዜው ትተነው ሀሳቡ ግን እጅግ ከእውነታ የራቀ መሆኑን ማስግዘብ ያሻል፡፡ ‹‹መላው የኢትዮጵያ ሙስሊም አበጥሮ ያውቀዋል›› ማለታቸው በተለይ ትልቅ ሹፈታቸው ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙማ ከማን ጋር እንደሆነ በበቂ ሁኔታ አሳይቷል፡፡ ‹‹መሪዎቻችን ይፈቱ!›› የሚል ድምጹን በኢድና በአረፋ ሚሊዮኖች ሆኖ፣ በሌሎችም በርካታ የጁምአ ስግደቶች በተደጋጋሚ አረጋግጧል፡፡ ግለሰቡ ‹‹አክራሪዎች›› ሲሉ ያንጓጠጧቸውን ኮሚቴዎች ህዝበ ሙስሊሙ ‹‹ብርቅዬ የሰላም አምባሳደሮቻችን›› እያለ ነው የሚጠራቸው፡፡ በጥር ወር 2005 ብቻ በአገር አቀፍ ደረጃ 35 ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተደርገዋል፡፡ ሕዝቡ ወደ አደባባይ የወጣው ለምን እንደሆነም መንግስትና ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፉ ማህበረሰብም ጭምር ያውቀዋል፡፡ መንግስት አመቱን ሙሉ በዚህ ጉዳይ ተወጥሮ የቆየውኮ ጉዳዩ የህዝብ እንጂ ‹‹የጥቂት አክራሪዎች›› ስላልሆነ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ አቶ ሽመልስ ሳያውቁት ቀርተው አይደለም – የፖለቲካ ስራ ሆኖባቸው እንጂ፡፡
ሌላ ንግግራቸውን እንመልከት፡- ‹‹የሽብርተኝነት ዋና ዓላማ ህብረተሰቡን ተከታታይ የሆነ የፍርሀትና የሥነ ልቦናዊ ሰቀቀን ውስጥ መክተት ነው፡፡ የፖሊስ ሥራ ደግሞ ከወንጀል ሥራ እና ፍርሀት፣ ከወንጀል ሥጋት ነፃ ማውጣት ነው›› ይሉናል፡፡ ይህን በመርህ ደረጃ መቀበል ለማንም አይቸግርም፡፡ ለሽብርተኝነት ጥሩ ገለጻ ነው የሰጡት አቶ ሽመልስ፡፡ እስቲ ራስዎ ባወጡት መስፈርት እያሸበረ ያለው ማን እንደሆነ እንመልከት፡፡ ሰሞኑን በውድቅት ሌሊት የታጠቁና ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ ፖሊሶች በየሰፈሩ የሙስሊሞችን ቤት ያለምንም የፍርድ ቤት ማዘዣ ዘልለው እየገቡ፣ እየደበደቡና ያገኙትን ውድ ንብረት (ወርቅና ብር) በግድ እየዘረፉ፣ ከዚያም አልፈው በቤቱ የሚገኘውን ቅዱስ ቁርአንና አረብኛ የሀዲስ መጽሀፍት ‹‹ይተረጎማሉ›› በሚል እየወሰዱ ነው የሚገኙት፤ ልክ እንደ ደርግ ዘመን! ሙስሊሙ በየቤቱ ስጋት ውስጥ ነው ያለው፤ ሽብር ውስጥ!!! እያሸበረው ያለው ደግሞ እርስዎ ‹‹ሥራው ህዝቡን ከወንጀል ሥራ እና ፍርሀት፣ ከወንጀል ሥጋት ነፃ ማውጣት ነው›› ሲሉ ያንቆጳጰሱት ‹‹ፖሊስ›› ነው፡፡ በየጁምአው የሰላማዊውን ሙስሊም ድምጽ ለማፈን ጠመንጃውን ወልውሎ ቆመጡን እየወዘወዘ የሚወጣው የእርስዎና የባልረቦችዎ ታዛዥ የፖሊስ ሀይል ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ተገለባብጧል… እርስዎ ደግሞ የሚነግሩን ሌላ እኛ የማናውቃት ኢትዮጵያ ያለች እንዲመስል አድርጎናል…. መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ የማይገባባት…. ፖሊስ ህዝቡን ከስጋት የሚጠብቅባት…!!!
ክፍል ሁለት ይቀጥላል
አላሁ አክበር!
http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/6265
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar