tirsdag 29. januar 2013

ታደሰ በዛብህ የመርካቶው አይጥ


ታደሰ በዛብህ በተወለደ በአስራ አንድ ዓመቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር – መስከረም 26/1981 ራሱን በማጥፋት ከዚህ ዓለም ተለየ።
Tadesse Bezabh Ethiopian adopted kid in Germany1
ስለ ታደሰ በዛብህ ለመጻፍ ካሰብኩ ብዙ ጊዜ ነው። ቀን ሞልቶልኝ ተሳክቶልኝ አልጻፍኩትም። ሰሞኑን ሁለት ገጠመኞቼ ታደሰን እንደገና እንዳስበው አደረጉኝ። አንደኛው በጀርመን “ራይን ላንድ ፋልዝ” በሚባለው ክፍለ ሃገር ውስጥ ፋልዝ (PHALZ) በመባል በሚታወቅ ጋዜጣ ይታተማል። ይህ ጋዜጣ በ20.01.2013 እትሙ (Gestatten: Neger) በሚል ርዕስ ስለ <<ኒግር>> (“Neger” በእንግሊዘኛ ቋንቋ ደግሞ “Nigger”)በሚመለከት የተጻፈውን ካነበብኩ በኋላ ሲሆን በሁለተኛ ደግሞ እዛው ጀርመን ውስጥ በማደጎነት የተሰጠ አንድ አፍሪካዊ ሕጻን ከተገናኘሁ በኋላ ነው።
በዚህ ከላይ በጠቀስኩት ጋዜጣ ላይ የተጠቀሰው ጽሁፍ እንደሚያመለክትው በጀርመን ሃገር የሚታተሙ የሕጻናት መጽሐፍ ውስጥ ኒገር (Neger) የሚለው ቃል ስለሚገኝ ቃሉን ከመጽሐፍቶቹ ውስጥ መውጣት አለበት የሚል ነው።
ጋዜጣው ውስጥ ያለውን ዝባዝንኬ ትተን በተለይ በጀርመን የሕጻናት መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ዘረኛ ቃላት በምናስብበት ወቅት ከዛው ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ችግሮች በቀላሉ ልናልፋቸው አንችልም። በጋዜጣው ላይ የተጠቀሰው የሕጻናት መጽሐፍ ለምሳሌ( Der NegerkÖnigin in Pipi Langstrumpf –) <<የኒግር>> ንግሥት ይባል የነበረው ከሚቀጥለው እትም በኋላ  (Südsee Kőnig-) የደቡብ ባሕር ንጉስ በሚል እንደሚጠራ ይገልጻል። በጀርመን ሃገር ያሉ ጥቁር ሕጻናት በዚህ  ቃል ምክንያት ብዙ ችግር ትምህርት ቤት ውስጥ እንደሚደርስባቸው ደግሞ የሚካድ አይደለም።
ከሁሉ የሚገርመው በጀርመን ሃገር “Neger” የሚለውን መጠርያ እንደ ቤተሰብ ስም (family name) የሚጠቀሙ ነበሩ። ስሙን እንዴት እንዳገኙት ባይታወቅም ይህንን የሚል መጠሪያ 470 ሰዎች የሚሆኑ ቤተሰቦች ይጠሩበት እንደነበር በ2008 ተገምቷል። ቢሆንም ብዙዎቹ በአካባቢያቸው በሚደርስባቸው ስድብ ምክንያት ስማቸውን ለመቀየር ተገደዋል። ከዚህ ተነስተን ያለውን ሁኔታ ስንገመግመው በጀርመን የሚገኙ ጥቁር ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን መከራ መገንዘብ እንችላለን። በቅርብ ቀን በጀርመን ከፍራንክፈርት ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ ሠፈር ያገኘሁት አንድ አፍሪካዊ ሕፃን ልጅ የዚህ አስከፊ የሆነ የዘር ችግር ሰለባ ሊሆን ይችላል።
ይህ ልጅ እድሜው አራት አመት አካባቢ ነው። ብርዱን ለመከላከል የለበሰው ልብስ ድቡልቡል አስመስሎታል። ክብ ፊቱ፣ ካደረገው ኮፍያና አንገቱ ላይ ከተጠቀለለት የአንገት ኩታ ማህል፣ በነጭ ጥርሱ ታጅባ ለተመለከታት ደስታን ትፈጥራለች። ከልጁ ፊት አንዲት የክረምቱ ብርዱ ሰውነቷን እንደ ወረቀት ነጭ ያደረጋት ጀርመናዊ ትራመዳለች። ልጁ ከኋላዋ እየተከተለ ፣ <<ማማ ፣ ማማ>> እያለ ይጠራታል። ሌሎች ጀርመኖች ልጆቻቸውን ከሕጻናት መዋያ እያደረሱ ሲመለሱ ገልመጥ እያሉ ይህንን ድርጊት እንደ አስደናቂ ትርዕይት ይመለከታሉ። ከምሄድበት መንገድ አሳብሬ ወደ እሱ አካባቢ ስሄድ፣ ልጁ በመቆም ወደ እኔ በመመልከት ያጠናኝ ጀመር። የእኔ ጥቁረት ከእሱ ጋር በመመሳሰሉ ይመስለኛል አተኩሮ ተመለከተኝ።
በጀርመንኛው(guten Morgen) ጉትን ሞርገን – መልካም ጠዋት ብዬ ሰላም አልኩት።
ትንሽ ተመልክቶኝ መልስ ሳይሰጠኝ ወደ እናቱ እየከነፈ ሄደ። እናቱም ሰላም አትለውም እንዴ? ብላ ጠየቀችው። የእናቱን እግር ጨምድዶ ይዞ እንደገና ያጠናኝ ጀመር። ለእናቱ ሰላምታ ሰጥቼ ። ቆንጆ ልጅ አለሽ በማለት ስለ ልጁ ለማወቅ ያለኝ ጉጉት ስለገፋፋኝ ወሬ ጀመርኩ። እናቱም ልጇ ቆንጆ ስለተባለ አመስግናኝ ልትሄድ ስትል ወሬዬን በመቀጠል የእኔ ልጅም እዚህ ሕጻናት መዋያ ነበረች። በጣም ጥሩ የሆነ የሕጻናት መዋያ ነው አልኳት።
- በመንገዱ ላይ ሌላ ሴት መጥታ ወደ እኔ በመመልከት እናትየዋን ሰላም ካለች በኋላ፣ ሁል ጊዜ ልጠይቅሽ እፈልጋለሁ “የልጁ አባት እሱ ነው?” ብላ እናቲቱን ጠየቀቻች።
- እናቲቱም “አይደለም” በማለት አጭር መልስ ስጥታት ጉዟችንን ቀጠልን።
- “መቼም እኛ ጀርመኖች ስንባል የማያገባንን ወሬ መሰብሰብ አንወዳለን አለችኝ?”
- “ጀርመኖች ብቻ ሳይሆኑ ወሬ መውደድ  የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው ብዬ መለስኩ።”
በተለይ የዘርን ጉዳይ በተመለከተ ብዙ ጀርመኖች ዘረኛ በመሆናቸው እንደዚህ ዓይነት ወሬ እንደሚጥማቸው አላጣሁትም ነበር።
ሕፃናት መዋያው ጋር ስንደርስ ጠብቀኝ ብላ ልጁን ልታደርስ ወደ ውስጥ ገባች። በራፉ ላይ የቆመችው አስተማሪ ልጁን ተቀብላት ተመለሰች።
- “ለመሆኑ ልጅህ ስንት ዓመቷ ነው ?”
- “አስራ ስምንት ሆኗታል።”
- “እኔ ደግሞ ትንሽ መስላኝ ለልጄ ጓደኛ እንድትሆን ልጠይቅህ ነበር።” አለችኝ።
- “ጓደኛ የለውም ወይ?” ብዬ ጠቅኋት።
- “አይ አፍሪካዊ የሆነ ጓደኛ ለማለት ነው።”
- “አዎ ችግር ነው። እዚህ አካባቢ አፍሪካውያን በብዛት ስለማይገኙ መሞከር ነው አልኳት።” በዚያውም አያይዤ። “የማደጎ ልጅሽ ነው?” ብዬ ጠየቅኋት።
- “አዎን። የዛሬ ሁለት ዓመት እኔና የሴት ፍቅረኛዬ ለእረፍት ምዕራብ አፍሪካ ሄደን መንገድ ላይ ሲለምን አገኘነውና በማደጎ ልጅነት ይዘነው መጣን።”
ሴትየዋ ከሌላ ሴት ጋር እንደ ባልና ሚስት እንደምትኖር ሳውቅ ደነገጥኩ። የደነገጥኩት ለእሷ ሳይሆን ይህ ልጅ ወደ ፊት ምን ችግር በትምህርት ቤትም ሆነ በአካባቢው እንደሚደርስበት ስለገመትኩ ነው። አሳዛኝ ነው። ይህ ልጅ ወደ ፊት ስለ ቤተሰቡ መጠየቁ አይቀርም። ስለሃገሩ መጠየቁ አይቀርም። እያደገ ሲሄድ በሁለት እንስት ቤት ውስጥ በማደጎ ማደጉ የሚፈጥረው ችግር ትንሽ አይደለም። ከሴትየዋ ጋር ትንሽ ተጨዋውተን ተለያየን። ግን የልጁ ሁኔታ ከጭንቅላቴ ሊጠፋ አልቻለም። ብዙ አወጣና አወርድ ጀመር።
በዚህ በጀርመን ሃገር ውስጥ አንድ አሳዛኝ ታሪክ ተፈጽሟል። ይህ ታሪክ በመጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል።  የመጽሐፉ ርዕስ “Tadesse Warum” – “ታደሰ ለምን” ማለት ነው።
ታደሰ አዲስ አበባ በነበረበት ወቅት
Tadesse Bezabh Ethiopian adopted kid in Germany2ታደሰን ብዙ ጊዜ አስበዋለሁ። በሰው አገር የደረሰበት ስቃይ ትንሽ አይደለም። ዛሬ ይህንን ልጅ ሳይ ታደሰን ለምን ከሃገሩ ልጆች ጋር በትንሽ ጽሁፍ አላስተዋውቀውም ብዬ አሰብኩ። ሳይታወቅ ከሚቀር ይሻላል። Irmhild SÖhl – የምትባል ጀርመናዊት የታደሰ የማደጎ እናት ስለ ታደሰ ከፃፈችው መጽሐፍ ላይ የተወሰነው ለማቅረብና ታደሰ በወገኖቹ እንዲታሰብ ማድረግ አለብኝ ብዬጀመርኩ።  ታደሰ በዛብህ የተወለደው በሰሜን ኢትዮጵያ በወሎ ክፍለ ሃገር ነው። ታደሰ በተፈጥሮው የቋንቋ ስጦታ ሰለነበረው የጀርመን ቋንቋ አቀላጥፎ ይናገር ነበር። ታደሰ ምንም እንኳን የጽሁፍ መረጃ ተገኝቶ በየትኛው ቀን እንደተወለደ ባይታወቅም እድሜው ተሰልቶ በ1969 መወለዱ ታውቋል።
የታደሰ ሕይወት ገና ከመጀመሪው አስቃቂ ነበር። ገና የ5 ዓመት ልጅ እያለ አባቱ እፊቱ ሲገደሉ ተመከልክቷል። ከዛም እናቱ ወደ አዲስ አበባ ይዛው ተሰዳለች። አባቱ የተገደሉበት ምክንያት በውል ባይታወቅም ወቅቱ አብዩት የፈነዳበት ነበር። የመንግሥት ታጣቂዎች የፈለጋቸውን የሚያደርጉበት ወቅት ስለነበረ አባቱ በአብዮት ደጋፊዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ነው።
ታደሰ አባቱ ከተገደሉ በኋላ ከወሎ ክፍለሃገር ወደ አዲስ አበባ ከባዱንና አድካሚውን ጉዞ አድርጎ ከእህቱ ከኑኑ ጋር አዲስ አበባ እንዲመጣ ተገዷል። እናቱ አዲስ አበባ መርካቶ ውስጥ ከብዙ ችግር በኋላ እንጀራ እየጋገረች ልጆቿን ለማሳደግ ትጥር ነበር። በዚህ ወቅት ነበር ታደስ << የመርካቶው አይጥ >> የሚለው ስሙን ያገኘው። ታደሰ በዛብህ ከእህቱና ከእናቱ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ከነበሩበት(DED & Terre des  Hommes) የእርዳታ ድርጅቶች ጋር የተገኛኙት።
Tadesse Bezabh, Ethiopian in Germanyበዚህ ወቅት በደቡብ ጀርመን በባደን ቩተንበርግ ክፍለ ሃገር – የዞል ቤተሰቦች (Familie Sőhl) ከአምስት ልጆቻችው ጋር የገጠር ኑሮን የሚመስል ቤት ሠርተው በውስጡም( ውሻ ፣ ዶሮ ፣ ፈረስ ፣ . . .  ) የመሳሰሉትን እንስሳት በማካተት ለመኖር ይፈልጉ ነበር። የዞል ቤተሰቦች አንድ ልጅ ከሦስተኛው ዓለም ለማሳደግ በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት ከብዙ ትግል በኋላ በግንቦት 1976 ታደሰ በዛብህን ከብዙ ትግል በኋላ  በማደጎ ልጅነት ተሰጣቸው።
ታደሰ በግንቦት ወር ፍራንክፈርት አውሮፕላን ጣቢያ ላይ ከአዲሱ ቤተሰቦቹ ተገናኝቶ የጀርመን ቋንቋ መማር ጀመረ። በነሃሴ ወር አዲሶቹ ወላጆቹ በሚደነቁበት ሁኔታ የጀርመን ቋንቋን ካለስህተት ይናገር ጀመር።
ታደሰ በዛብህ አርቆ አስተዋይ ነበር። ይህንን አርቆ አስተዋይነቱን በሚመለከት   ሕይወቱ ካለፈ 8 ዓመት በኋላ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ይጽፋቸው ከነበሩት ደብዳቤዎች ውስጥ አንዱን “ZEIT” የሚባለው የጀርመን ታዋቂ ጋዜጣ 12.05.89 እትሙ ይዞ ወጥቷል።
Tadesse Bezabh letter
ትርጉሙም ፡ -
እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ። እድሜዬም አሥር ዓመት ነው። በአንድ ጀርመናዊ ቤተሰብ ውስጥ የማደጎ ልጅ ነኝ። እኔ እንደማውቀው ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ፖሊሶች መንገድ ላይ ስለሚተኩሱ(ስለሚገድሉ) ፍርሃት አለብን። እናንተ ደግሞ አሁን እዚህ እናንተ ጥገኞችን ለመቀበል ካልፈለጋችሁ በስደተኞች ውስጥ ያለውን ፍራቻ  ለብዙ ጊዜ እንዲኖር ታደርጋላችሁ። ይህ ደግሞ በጣም መጥፎ ነው። አንድ ሰው በስደት ወደ እዚህ ከመጣና እናንተ መኖር ከከለከላችሁትና ሃገሩ ደግሞ መሄድ ካልቻለ መኖር አይችልም ማለት ነው። ይህ ደግሞ ትንሽም ቢሆን እንደ ይሁዳውያን ላይ እንደተፈጸመው ነው።በዚህ ምክንያት ነው ለመርዳት ዝግጁ መሆን ያለብን ።
ታደሰ ዞል ሚሸልባህ
ከዚህ ደብዳቤ እንደምንረዳው ይህ ልጅ ገና በአሥር ዓመቱ ከራሱ ችግር አልፎ የሃገሩ ልጆች ችግር ያሳስበው እንደ ነበር ነው።
ይቀጥላል
26 January 2013

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar