ድምፃችን ይሰማ
ፖሊስ ሲያስርና ሲደበድብ ውሏል
ሕዝቡ ‹‹እናንተ ለማሰር የምትተጉትን ያህል እኛም ትግላችንን ለማስቀጠል ዝግጁ ነን››
የተቃውሞአችንን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ለአንድ ወር ያህል በተለያዩ ዝግጅቶች ሲካሄድ የቆየው የ‹‹365 ቀናት ለሃይማኖት ነጻነት›› የመጨረሻ ጁምዓ መርሐ ግብር ትግበራ በስኬት ተጠናቋል፡፡ በዚህ የቃልኪዳን ሳምንት የሚል ስያሜ በተሰጠው የሳምንቱ እና የቀኑ መርሐ ግብር እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝበ ሙስሊም በአዲስ አበባና የተለያዩ ክልል ዋና ዋና መስጊዶች በተቃውሞና በዱአ ታጅቦ ውሏል፡፡ የዚህ ሳምንትን ተቃውሞ ልዩ ያደርገው የነበረው መጅሊሱ መውሊድን እንደ መግቢያ በር በመጠቀም ሙስሊሙን ለመከፋፈል ጥረት ሲያደርግበት የነበረው መሆኑና ትግሉን አጠናክረን ለመቀጠል ቃል እንደ አዲስ የገባንበትና ለአላማችንም ጽኑ መሆናችን ያሳየንበት ሳምንት መሆኑ ነው፡፡

በአዲስ አበባ የተቃውሞ ማዕከል በሆነው አንዋር መስጊድ ሰዉ በአካባቢው በጊዜ ተገኝቶ የነበረ ሲሆን ለወትሮው ሕዝብ የማይደርስባቸው ቦታዎችም በሰዉ ቁጥር መብዛት የተነሳ በሰጋጆች ተሸፍነው ነበር፡፡ ተቃውሞው የጁምአው ሶላት እንደተጠናቀቀ በተቀመጠለት መርሐ ግብር መሰረት ሲጀመር ኅብር የፈጠሩ የአንድነት ድምጾች የአካባቢውን መንፈስ ከመቅጽበት ለውጦታል፡፡ ‹‹አንለያይም…… አንለያይም…››፣ ‹‹ቃላችን…አንድ ነው!!››፣ ‹‹በቃላችን… እንፀናለን!!››፣ ‹‹የሃሰት ክስ…አይገዛንም›› ‹‹ኮሚቴው…ይፈታ›› እና ሌሎችም የትግሉን መንፈስ የሚያንጸባርቁ መፈክሮችን በድምቀትና በከፍተኛ ወኔ ሕዝቡ ሲያሰማ ተስተውሏል፡፡ በአንዋር ከተሰሙት የተቃውሞ እና ትግሉን ለመቀጠል ከተሰጡት ቁርጠኝነት የተሞላባቸው ድምጾች ውጪ የተለያዩ መፈክሮች፣ ባነሮች፣ የኢትዮጰያ ባንዲራ እና ሌሎችም የትግሉን ስሜት የሚገልጹ ምልክቶች ታይተዋል፡፡
በክልሎች የተካሄደው ፕሮግራም እንደ አዲስ አበባው ሁሉ ደማቅና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የተገኘባቸው ነበሩ፡፡ በኦሮሚያ በሻሸመኔ፣ በጅማ፣ በመቱ እና በባሌ የተደረጉት ተቃውሞዎች ቃልኪዳኑን በማደስና ትግሉን ወደፌት ለመቀጠል ቁርጠኝነታቸውን አሳይተውበት ተጠናቋል፡፡ በደቡብ ክልል ወልቂጤ ከተማም የተደረገው የቃልኪዳን ፕሮግራም በፍጹም መንፈሳዊነትና ለቅሶ ጭምር የታጀበ ነበር፡፡
ከእነዚህ አካባቢዎች ውጪ ተቃውሞ የተካሄደባቸው አካባቢዎች በሰላም ተጀምረው የተጠናቀቁ ቢሆንም በአዳማ እና በደሴ ከተማ የጸጥታ ሀይሎች መስጊድ ውስጥ በመግባት ድብደባ እና እስር ፈጽመዋል፡፡ በሁለቱም አካባቢዎች በተነሳው የጸጥታ ችግር የመስጊድ ኮሚቴዎችና ፖሊሶች በጋራ በመጣመር ፖሊሶች መስጊድ ውስጥ ገብተው ድብደባ እና እስር እንዲፈጽም ግብዣ በማቅረብ የተሰላ ነበር፡፡ በደሴ የዝምታ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ሙስሊሞችን ፖሊስ መስጊድ ውስጥ ገብቶ እንዲደበድብ አዲሶቹ የመጅሊስ ኮሚቴ አባላት በማይክራፎን ጥሪ በማድረግ ፖሊስ እርምጃውን እንዲወስድ በር ከፍተዋል፡፡ ፖሊስም የመስጂዱ ውስጠኛው ክፍል ውስጥ ድረስ በመግባት ብዙዎችን ቁስለኛ በማድረግ ቀሪዎችን ደግሞ ጭኖ ወስዷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩም በአዳማ ከተማ ጃሚእል ሀቢብ መስጊድም ተቃውሞ ላይ የነበሩ ሙስሊሞችን ለመደብደብ እና ለማሰር በመጅሊሱ እና መስጊዱ ካዲሞች ተጋብዞ ወደ መስጊዱ የገባው ፖሊስ በመስጊዱ ውስጥ በነበሩ ሙስሊሞች ላይ ከፍተኛ ድብደባ የፈጸመ ሲሆን ሸሽተው ሲወጡ የነበሩ በርካቶችንም አስሯል፡፡ ለሰላማዊ ጥያቄያችን ዛሬም ምላሹ ድብደባና እስር ቢሆንም ጥያቄያችን እስኪመለስ ሁሉን ተቋቁመን በመንገዳችን እንደምንዘልቅ የዛሬው የቃልኪዳን ውሎአችን ለሁሉም ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
አላሁ አክበር!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar