lørdag 26. januar 2013

የመምህርነት ሥነ ምግባር ሲጎድፍ


የመምህርነት ሥነ ምግባር ሲጎድፍ
መምህርነት የሰው ልጅ ኣዕምሮ በጽኑ መሠረት ላይ ታንጾ የሚያድግበት ሙያ ነው። ሙያውን ወደ ተግባር ለውጠው እነጻውን
የሚያከናውኑትም በዘርፉ የተሰለፉ መምህራን ናቸው። በዚሁ በተከበረው የሁሉም ኣመንጪ በሆነው የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ
መምህራን በሙያዊ ሥነ ምግባራቸው የተከበሩ ናቸው።
መምህራን ኣይዋሹም፣ ኣያዳሉም፣ ኣይሰርቁም፣ ዘር ኣይለዩም፣ ሰብኣዊ መብት ኣይጋፉም፣ የሚያስተምሩኣቸው ልጆች ሁሉ
ልጆቻቸው ናቸው። ሁሉም ፊደል የቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ፊደል ከቆጠሩበት የቄስ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ደረሱበት
የትምህርት ደረጃ ድረስ ያስተማሩዋቸውን መምህራኖቻቸውን ሲያዩ እንደ ወላጆቻቸው በታላቅ ኣድናቆት ይቀበሉኣቸዋል።
መምህራኑም ያስተማሩዋቸውን በሺህዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ተማሪዎቻቸውን ሲያዩና ማንነታቸውንና የመማር ማስተማር ሂደቱ
የተከናወኑባቸውን ትምህርት ቤቶችና ኣካባቢውን ወይም ቦታውን ሲነግሩዋቸው ልጆቻቸውን ያገኙ ያህል ደስታ ይሰማቸዋል።
ይረካሉ፣ ይደሰታሉ፣ እንደ ልጆቻቸው ያህል እቅፍ ኣድርገው ይስሙኣቸዋል።
መምህራን በሚያስተምሩበት ጊዜ በየክፍላቸው ከተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ የኢትዮጵያ ልጆችን በቀለም ቀርፀው
የወደፊት የሀገር ተረካቢዎችን ያዘጋጃሉ። በክፍላቸው ውስጥ ያሉትን ተማሪዎች በፆታ፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣
በክልላዊነት፣ በጎጠኝነት ወጥመድ ውስጥ ተጠምደው ኣድሎ ኣያደርጉም። ያስተምራሉ፣ ያስተማሩትን ምን ያህል እንደ ቀሰሙ
ለማወቅ ይፈትናሉ፣ ያገኙትን የፈተና ውጤት ይሰጡኣቸዋል።
መምህራን ንፁሁ የተማሪዎቻቸው ኣዕምሮ ጥላሸት እንዳይቀባ በጥንቃቄ እንዲታነፅ ይጥራሉ። ከሚያጠለሹ ችግሮችም
ይከላከላሉ። በዚህም የተነሣ ለመምህራን ሐቁ ሐቅ ነው፣ ሐሰትም ሐሰት ነው። ኣንዱን ለሌላው መጠቀም ሞራላቸውና ሥነ
ምግባራቸው ኣይፈቅድላቸውም። ሐሰትን በሐሰትነቱ፣ ሐቁን በእውነትነት ያስተምራሉ። ሐሰቱን እውነት ብለው ካስተማሩ
የተማሪዎቻቸውን ንጹሁን ኣዕምሮ ጥላሸት መቀባት ስለሚሆን ኣያደርጉትም። ተማሪዎቻቸውን በሐሰት መንገድ ማስተማር ቀጣዩን
ትውልድ የውሸታም መንጋ መሰብሰብ ስለሚሆን ኣያደርጉትም።
መምህራን ኣትግደሉ ይላሉ እንጂ ግደሉ ኣይሉም። መምህራን ልዩነቶችን በመወያየት ፍቱ ይላሉ እንጂ በጠመንጃ ይፈታል
ኣይሉም። መምህራን ጠመንጃውን ወደ ማረሻነት ለውጠን ለሥራ እንነሣ ይላሉ እንጂ ጠመንጃ ኣምላኪነትን ኣይደግፉም፣
ኣያስተምሩም። መምህራን ተዋደዱ፣ ተፋቀሩ ይላሉ እንጂ እርስ በርስ ጎራ ለይታችሁ ተደባደቡ፣ ተጣሉ ኣይሉም። መምህራን
ኣዕምሮ የተሰጣችሁ እንድታስቡበት ነውና ተጠቀሙበት ይላሉ። መምህራን የሰው ልጅ ከኣንድ ወንዝ የተቀዳ ስለሆነ በዘር ላይ
ተመስርታችሁ ልዩነት መፍጠር ሔዶ ሔዶ ወደዚያው ወደ መጣንበት የወንዝ ምንጭ ስለሚወስደን ከንቱ ፍልስፍና መሆኑን
ኣበክረው ይመክራሉ፣ ያስተምራሉ እንጂ የመለያየትን ኣባዜ ኣይቀበሉም፣ ኣያስተምሩም።
የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ኣንድን መኪና የውስጥ ኣካላቷን ለየብቻው ሠርተው ለመንቀሳቀስ እንዲችልና ተመርቶ ለሰው ልጅ
ግልጋሎት እንዲውል ኣድርገው ሰዎች ይጠቀሙባቸዋል። መምህራንም ልጆችን ሞርደው የሚያወጡ ሐቀኛ የሰው ልጅ ኣዕምሮ
ቀራጮች ናቸው። መኪናውን ፈልስፈው ሠርተው በጥቅም ላይ ያዋሉትን ባለሙያዎች ያሰለጠኑትም መምህራን ናቸው። በዚህ
የሥራቸው ውጤት ይኮራሉ፣ ይደሰታሉ፣ ይወደሳሉ። ኅብረተሰቡም ያከብራቸዋል፣ ይወዳቸዋል።
የትናንትናው መምህር የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ኣቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ ይሠራ በነበረ
ጊዜ ሐሰቱን በእውነት ካባ እየሸፋፈነ ለሥልጣን ምን ያህል ጉጉት እንደነበረው የሥራ ባልደረቦቹና ተማሪዎቹ የነበሩ
መስክረውበታል። ከመምህርነት ሥነ ምግባር ወጥቶ እንደነበረም በማስረጃ በተደገፈ ማንነቱን ቁልጭ ኣድርገው ኣስቀምጠዋል።
ከሰለጠነበት ሙያዊ ሥነ ምግባር በተቃራኒው ቆሟል። ኣሁን ደግሞ ይፈልገው የነበረው ሥልጣን መጥቶ ኣምባገነን ወንበር ላይ
ሲኮፈስ ይበልጥ እውነት የምትባለዋን ቃል እየቆረጫጨማት ነው። ግን ኣላመጦና ኣጣጥሞ መዋጡ ላይ ጉረሮው ላይ ተሠንቅሮ
እያሰቃየው ስለሆነ የራሱን መፍትሔ ለራሱ፣ ለቤተሰቡ፣ ለወላጆቹና ለዘመድ ኣዝማዱ ሲል ቢፈልግ የተሻለ ይሆናል። ወላጆቹ
በልጃቸው ድርጊት ተከብረው በኖሩበት ቀበሌ ኣፍረውና ተሸማቀው እንዳይኖሩ ለነርሱም ቢያዝንላቸው ይበጃል።
እስካሁን ባለው የልጃቸው ሹመት በሹመት ላይ እየጨመረ መምጣት እንኳን እነርሱ እርሱም ያልጠበቀው ስለነበር “ኢየሱስዬ”
ያመጣው ነው እያሉ ሲፈነድቁ ነበር። ያሁኑም ሹመት ሲመጣ ይበልጥ ፈንድቀው እንደነበርና    “ኢየሱስዬ”  ምን ኣመጣህልን
ብለው እንደነበር ጥርጥር የለም። የሹመቱ ድግስ ተበልቶ  ሳያልቅና ለኢየሱስም ምስጋና ማቅረቡ ሳይቋረጥ የውርደት ውርጅብኝ
ከያጣጫው ሲወርድበት ድንገተኛ መናደድ ሳይሰማቸው ኣልቀረም። “ልጃችን እንደዚህ ያለው ወንጀል ውስጥ እጁን ኣያስገባም።
እንደተለመደው ይኸንን ያልሆነውን ሆነ ብለው የሚያስወሩትና የሚያወሩት ነፍጠኞች ሳይሆኑ ኣይቀርም።”  ሳይሉ ኣልቀረም።
ብለው ከሆነ ተሳስተዋል። ካላሉም ልጃቸው ከኢትዮጵያውያን ፊት ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት ልቦናው ወደ ኢትዮጵያና
ኢትዮጵያውያን እንዲመለስ ”ኢየሱስዬን” ይለምኑ፣ ያስለምኑ።
ከትውልድ ቀዬኣችን ኣታፈናቅሉን፣ ለዝንተ ዘመናት ከኖርንበት ኣባራችሁ ለረሃብና ለሞት ኣትዳርጉን  ስለኣሉ ብቻ ሱሪዎች በገፍና
በግፍ መጨፍጨፋቸውና እሬሳቸው ጫካ ውስጥ መጣልና ለኣውሬና ኣሞራ መሰጠቱን ኣቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ያለርሱዕውቅና የተፈጸመ እንዳልሆነ ኅሊናው ያውቃል። ሐሳቡ ከታችም ይቅረብ ወይም ከላይ ትዕዛዞቹ በተዋረድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ
ወደ ታች ወርደው ነው ተግባራዊ የሆነው። ይህ ዘግናኝ የሰው ልጅ ጭፍጨፋ በሚስታቸውና በልጆቹም ላይ የኅሊና ዕረፍት
የሚነሣ ደወል እያቃጨለባቸው ነው። ኣንደኛው የሰው ልጅ እንደዚያ በገዛ ወገኑ መጨፍጨፉ ሲዘገንናቸው ሁለተኛ ፈጻሚው
ደግሞ ኣባታቸውና ባሏ በመሆኑ ይበልጥ የኅሊና ቀውስ ይሆንባቸዋል።
ኣቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንኳን የኢትዮጵያን ሕዝብ ቀርቶ ለጋ ዕድሜ ላይ ያሉትን የልጆቹንም ሞራል እያላሸቀ ነው። የሌለውን
ኣለ (ውሸት)፣ ያልተወለደውን ተወለደ (ውሸት)፣ ልማት ሳይኖር ኣለ (ውሸት)፣ ሰዎች እየተራቡ ምን ጠፍቶ (ክህደት)፣ ሰዎች
የሚላስና የሚቀመስ ኣጥተው ሆዳቸው ከወገባቸው ጋር ተጣብቆ እየታዩ የሽብርተኞች ወሬ ነው (ውሸት)፣ የእህል ዋጋ የናረው
ጤፍ በላተኛው ስለበዛ ነው (ክህደት) የመሳሰሉ ከእውነታው ጋር የማይገናኙ ኣስተያየቶችን ሲመልሱ እንኳን ማስተማር ቀርቶ
በደጃፉም ያለፉ ኣይመስሉም። የእህል ዋጋ መወደድ በቂ ምርት ሳይኖር ስለቀረ እንጂ የኣንድ የምርት ተጠቃሚ ስለጨመረ
ኣይደለም። የሕዝብ ቁጥር በኣንድ ጀምበር የሚያድግ ኣይደም። በያመቱ ዕድገቱ የሚኖር ሲሆን ኣዋቂ የመንግሥት መሪዎች
በረጅምና ኣጪር ዕቅዶቻቸው ይኸንን መሰሎችን  ኣብረው ስለሚያቅዱ ችግር ኣይፈጥርም። ኣቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንኳን
ለዓመት ቀርቶ ለኣንድ ወርም ኣርቀው የሚያስቡና የሚያቅዱ ኣልመሰሉም። በዚህም ኣቀራረባቸው ኣንድ በማስተማር ሙያ
ተሰማርቶ የነበረ ግለሰብ የሚመልሰው መልስ ስለኣልነበረ በሙያው ላይ ኣላግጠውበታል። የኢኮኖሚውን ኣካሄድም
ኣዛብተውታል። ኣንድ ወቅት ላይ በኣንድ ሀገር ሕዝቡ ተርቦ ወደ ቤተ መንግሥት ሄደው ለንግሥቲቷ ጩኸታቸውን ኣሰሙ።
ንግሥቲቷም ሰገነቷ ላይ ወጥታ :ምን ሆነው ነው የሚጮሁት” ብላ ስትጠይቅ ስለራባቸው ነው ብለው መለሱላት። “ለምን ኬክ
ኣይበሉም” የሚል መልስ መስጠቷ በራሷ ዓለም ብቻዋን የምትኖር እንጂ ከሕዝብ ጋር ሆና የሕዝቡ ኣለኝታና ደጋፊ እንዳልነበረች
ነው። ኣቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝም የኢትዮጵያን ሕዝብ ኣለማወቃቸው ነው እንጂ ከሕዝቡ ስንት በመቶው ነው ጤፍ
ተመጋቢው? እርሱስ ያደገው በበቆሎ ኣይደለመ ወይ? ጤፍ በላተኛው በዝቶ ጤፍ ከተወደደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ዘንጋዳ ይበላ
የለ ወይ? የእነዚህስ ምርት ኣጥጋቢ ነው ወይ?
ሰዎች በገፍና በግፍ እንደ ዱር እንስሳት ከየቤታቸውና ከየመንገዱ እየታፈሱና የሐሰት ክስ እየተመሰረተባቸው እየታሰሩና እየተገረፉ
ሲሰቃዩ እያዩና እያወቁ የታሰረ የለም(ክህደት)፣ ሱሪዎችን በጠራራ ፀሐይ ከመንደራቸው ኣፍሰው እርስ በርስ እንደ ግመል መንጋ
ኣስተሳስረው እየተነዱ ጫካ ተወስደው በሩምታ ተኩስ ሲረሸኑና የቻሉትን ያህል በግሬደር ኣፈር ሲመልሱባቸውና ያልቻሉትን
እዚያው ጫካ ውስጥ ጥለው የኣውሬና ኣሞራ ቀለብ ሲያደርጉ ማንም የተገደለ ሰው የለም (ውሸት)፣ የወላይታ ተወላጆች ከኣዲስ
ኣበባ እየታፈሱ ሲታሰሩ የወያኔ ኣመራር እንከን የለውም የሚልና የመሳሰሉትን ሲዋሹና ሲክድ ልጆቹ፣ ሚስቱና ወላጆቹ
ይሳቀቃሉ። ልጆቹ ሳንወለድ በቀረን ብለው ከርሱ መወለዳቸውን ሲፀፅታቸው ሚስትም የተጋቡበትን ቀን እየተራገሙ እንደሆነ
ማንም ይፈርዳል። ወላጆቹም ልጃችን ኣዋረደን ብለው ይፀፀታሉ።
ልጆቹ፣ ሚስቱ፣ ወላጆቹና ዘመድ ኣዝማድ ደስ ይላቸው የነበረው በጀግንነት፣ በርኅራኄ ኣድራጎቱ፣ በኣመራር ብቃቱ፣ በኣስተዳደር
ኣስተዋፅኦው በሕዝብ ሲወደስ ነበር። ሕዝብ ሲረግመው ግን ይሰቀጥጣቸዋል። ልጆቹም በመጨረሻው እንደ ስምሃል መለስ ተስፋ
ቆርጠው ጠጪና ዱሪዬ ሊሆኑ ይችላሉ። ትምህርት ቤት በነፃነት ሔደው ከጓደኞቻቸው ጋር ሲማሩና ሲጫወቱ ውለው በነፃነት
ወደ ቤታቸው ተመልሰው በነፃነት በልተውና ጠጥተው ሲኖሩ ዛሬ ግን ዱብ ዕዳ ወርዶባቸው የቁም እስረኞች ሆነው ሲወጡና
ሲገቡ ባጠቃላይ እንቅስቃሴኣቸው ሁሉ በቁጥጥር ሥር ሲውል የኣባታቸውን የወያኔ የዛፍ ላይ ሹመት ሳይረግሙ ኣይቀሩም።
ሳይፀፅታቸው ኣይቀርም። ሚስትም የወያኔ ኣቀንቃኝ ካልሆነች የልጆቹን ሐሳብ ሳትጋራ ኣትቀርም።
ከመነሻው ጀምሮ ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት መምህራን በትክክለኛ መንገድ ላይ ሆነው ትክክለኛውን ዕውቀት የሚያስተላልፉ
እንጂ በጥቅማ ጥቅም እየተታለሉ የሰውን ልጅ ኣዕምሮ የሚያላሽቁ ስለኣልሆኑ ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ወደ ሙያው ሥነ ምግባር
ተመልሶ ራሱን ከኢትዮጵያ ሕዝብ የወንጀልነት ፍርድ ቢያድን ለራሱም፣ ለቤተሰቡም፡ ለወላጆቹና ለዘመድ ኣዝማድ ውርደትና
ኣንገት መድፋት ያድናል።
የመምህርነት ሙያ ክብር ስለሆነ የሙያው ሥነ ምግባር መጉደፍ የለበትም። ይከበር!
ቸሩ ነኝ                                        abatemsas@gmail.co

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar