ይድረስ ለኢንተርኔት ድኅረ -ገጽ ሃላፊዎች
ከብስራት ኢብሳ (ሆላንድ) 26-01-2013
ድሮ የምደግፈው የነ አበበ ጉርሙ የመቻል እግር ኳስ ቡድን ከጠፋ ከዓመታት ቦኋላ በትላንቱ ምሽት ለመጀመርያ ጊዜ የተከታተልኩትን ፣ በደቡብ አፍሪካ ፣ ብሔራዊ ቡድናችን ባሳዛኝ ሁኔታ በቡርኪና ፋሶ ተሸንፎ ጨዋታው ሲያልቅ ፣ ተደብሬ የቴለቪዢኑን መስመር ከኢውሮ እስፖርት ወደ ደች የዜና መስመር ቀይሬ ከባለቤቴ ጋር የዓለም ዜና ማዳመጥ ጀመርን ፡፡
በአፍሪካ አህጉራችን ፣ ማሊ ውስጥ ፈረንሳይ “የአልካሂዳን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር“ በሚል ርዕስ ዙርያ ፣ ፈረንሳይ ሁሌ ለዚህ አይነተግባር የምታሰማራቸውን ፣ ቅጥረኛ (ፈረንጆቹ ሜርሲነሪ የሚሉት) ወታደሮቿን እንደላከች በምስል በተቀረጸ ፊልም ካሳዩ ቦኋላ ፣ አንድ ሆላንዳዊ ድሮ በእንደዚህ አይነት ውትድርና ተቀጥሮ የነበረ ፣ ስለ ቅጥረኛ ወታደር ልምዱን ለተመልካችና አዳማጭ እንዲያካፍል ጋዜጠኛው አቀረበው ፡፡
እንደ ጀብደኛው የቀድሞ ቅጥረኛ ወታደር አገላለጽ ፣ ለእንደዚህ አይነት ውትድርና መቀጠር የሚፈልጉ ሰዎች ፣ የተለያየ የግል ችግር ያለባቸው ፣ ዓላማ የሌለው ጀብዱ መስራት የሚወዱ፣ ለገንዘብ የሚሞቱ…ወዘተ ዘርዝሮ ፣ የስልጠናው ክብደት፣ ያሰልጣኞቹን ኢ- ሰባዊ የጭካኔ አያያዝና ፣ ኮርሱን ጨርሰው ከተልዕኮዋቸው በህይወት የሚመለሱበት ዕድል ምን ያህል የጠበበ እንደሆነ በጣም ሰፋ አድርጎ ልምዱን አካፈለ፡፡
ከረዥም ልምዱ በተለይ ቀልቤን የሳበው፣ ሲቀጠሩ አዲስ የውሸት ስም እንደሚወጣላቸና ፣ ትክክለኛ ስማቸውን የያዘ ፓስፖርታቸውን፣ የባንክ ካርዳቸውን ፣ መንጃ ፍቃዳቸውን …ወዘተ ማንኛውም ከእውነተኛ ማንነታቸው ጋር የተያያዘን ዶክሜንት እንደሚያቃጥሉና፣ አዲሱን ስማቸውን ብቻ የሚገልጽ መታወቂያ ተሰርቶ እንደሚሰጣቸው የተናገረው ነበር ፡፡
ይህንን የሚያደርጉበት ምክንያትም፣ ቅጥረኞቹ የሚላኩበት ሃገር እንዲሰሩ የሚታዘዙት፣ በሃገሩም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለና ፣ ኢ- ሰባዓዊ የሆነ ድርጊት እንደሆነ ቀድመው ስለሚያውቁት ፣ የግል ሃላፊነትን ላለመውሰድና ከተጠያቂነት ለመሸሽ እንደሆነ አስረዳ፡፡
ፕሮግራሙ ሲያልቅ ፣ ስለሰማሁት እያብሰለሰልኩኝ፣ ዘወትር ዓርብ ማታ ፣ ወደ ምኝታዬ ከመሄዴ በፊት ፣ እንደ ድሮ ካዛንቺስ ወይም ባንቢስ ፣ ሦስቱ በር ፣ አምስቱ በር ፣ አደዋ መደዳ የመዝናኛ ስፍራዎችን የሚያካክስልኝ ፣ አዲሱ የሽማግሌ የመዝናኛ ስፍራዬ የፓልቶክ መደዳ ጎራ ብዬ አንድ ሁለቱ ዘንድ ሃዘን ተቀምጠው ስለደረስኩኝ ዘግቼ ፣ የኢሜል መልዕክት እንዳለኝ ስፈትሽ አንድ በብዕር ስም የተጻፈ፣ በግለ ሰብ ስብዕና ላይ የሚያተኩር ዘገባ አየሁ፡፡ ፀሐፊ የራሳቸውን ስም ሸሽገው ፣ የሚወቅሱትን ግለሰብ ስም ፀሐይ ላይ አስጥተውታል፡፡ እኚህ ፀሃፊ እንደ አተናተናቸው ፣ ለሃገር ተቆርቋሪ ፣ እረዥም ዓመታት በሆላንድ የኖሩ ፣ ብዙ ውጣ ውረድ ያዩ ናቸው፡፡ ፀሃፊው ማን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ አልሞከርኩም ፡፡ ምክንያቱም ፀሃፊው ሲጽፉ ሊያስጠረጥሩ የፈለጉት ሰው ስላለ ፣ እሳቸውን መተባበር አልፈለኩም ፡፡ በትክክለኛ ስማቸው በማይጽፉ ተቺዎችም ይሁን አስተያየት ሰጪዎች ፣ እንኳን አቅዋም ለመውሰድ ፣ ላለማንበብ ከወሰንኩኝ ስለሰነበትኩኝ ፣ እንደዚህ አይነት ፣ ስም የለሽ ደብዳቤዎች ሲመጡ ፣ በቀጥታ የምልካቸው ወደ የቁሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ነበር ፡፡
በዚህ ምሽት ግን በኳሱ ብስጭትና ፣ በቅጥረኛው ወታደር ታሪክ እየተገረምኩኝ ሳላስበው የእኚህን የብዕር ስም ትችት ግማሹን አንብቤ ነው፣ ማንበብ እንዳልነበረብኝ ከሃሳቤ የነቃሁት፡፡ ግማሽ ቃሌንም ቢሆን ለማክበር ጽሁፉ ማንበብ አቋርጬ ፣ እንደተለመደው ወደ ቆሻሻ ቅርጫት ስፍራው አስተናግጄው ወደ መኝታዬ ሄድኩኝ ፡፡
ነገር ግን እንደተመኘሁት ያቺ በስህተት ያነበብኳት እንደ አቦል ቡና እንቅልፍ ነስታኝ መገላበጥ ጀመርኩኝ ፡፡ ድሮ እኔም በስሜ መጻፍ ከመጀመሬ በፊት በግለሰብ ዙርያ ሳይሆን በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ እጽፍ ስለነበር ፣ የብዕር ወይም የውሸት ስም መቼና እንዴት? እንደተጀመረ ፣ ለምን ? ማን እንደጀመረው ለማወቅ ማሰላሰሌን ተያያዝኩት ፡፡ እኔን እንደዚህ በጨረፍታ ያነበብኩትን እንቅልፍ የነሳኝ ፣ የሚጻፍባቸው ግለሰቦችንና ፣ ፀሐፊው እራሱ እንቅልፍ አጥቶ በዚህ የእስፖርት ግር ግር ለዚህ ጉዳይ ጊዜውን ያጠፋው ምን ያህል የተጎዳና ፣ እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው ይሆን ? ወይስ እንደተለመደው የወያኔ ተላላኪዎች ? እያልኩኝ እያሰላሰልኩኝ እንቅልፍ አሸለበኝ ፡፡
ይህንን እንቅልፍ የነሳኝን የብዕር ስም አመጣጥ ቅድመ ታሪክ ለማወቅ ዛሬ ጠዋት ከቁርስ ቦኋላ ባለቤተን ወደገበያ ብቻዋን ልኬ ፣ የተለመደ ጉግሌንና ፣ ዊኪፒዲያን አገላበጥኩኝ ፡፡ የደረስኩበትንም ማሰርያ ለአንባቢዎቼ አካፍዬ ለመገላገል ወሰንኩኝ ፡፡ስለዚህ ይህ መልዕክት በብዕር ስም ስለተላከልኝ መልዕክት አስተያየት ለመስጠት ፣ ወይም የብዕር ስምን በደፈናው ለማውገዝ አይደለም፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት ፈረንሳዮች ለቅጥረኛ ወታደር ብቻ ሳይሆን ፣ ለመደበኛ ወታደሮቻቸውም ፣ ከፈረንሳይ አብዮት በፊት ጀምሮ ፣ ከሙሉ ስማቸው መጨረሻ ፣ ኒክ ኔም ፣ ተደጋጋሚ ስሞችን ለመለየት ፣ ወታደሩ ከመጣበት አካባቢ መንደር ፣ መንገድ ፣ ተራራ ስም ጋር የሚያያዝ ፣ ወይም በሰውየው ሰውነት ላይ ከሚታይ የተለየ ነገር በማያያዝ ተቀጥላ ስም ያወጡለት ነበር ፡፡ በሃገራችንም ጀብዱ የሰሩ ጀግናዎች ከፈረሳቸው ስም ጋር (ታጠቅ፣ ገስግስ፣ አባ ቦራ .ወዘተ.) እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ በተረፈ ከተወሰነ ሙያቸው፣ ባህሪያቸው ፣ ከሚወዱት ነገር ፣ ከሚያዝወትሩት ፣ መርሳት ከማይፈልጉት ፣ ….ወዘተ ጋር በተያያዘ የሚወጡ ብዙ አይነት ፣ የብዕር ፣ የመድረክ ፣ የእስክሪን ፣ የሃይማኖት ፣ የተልዕኮ …መዘርዘር እስከሚሰለቸን ብዙ አይነት የተለያዩ (ፔሱዶኒም ፣ ኒክ) ስሞች መጠቀም በዓለማችን የተለመደ ነው ፡፡
እንዲሁ በፖለቲካውም ዓለም ከአስራ ስምንተኛውና ፣ አስራዘጠነኛው ዘመን ጀምሮ ፣ ለህቡዕ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለቀስቃሽ ጋዜጦች፣ ለህቡዕ እንቅስቃሴዎች ፣ ለካድሬ ስሞች፣ የብዕር ወይም የድብቅ ስም ተጠቅመዋል ፡፡ ለምሳሌ ሌኒን ፣ እስታሊን ፣ ትሮትስኪ … ወዘተ የካድሬ (የፖለቲካ)ስማቸው እንጂ ፣ ትክክለኛ ስማቸው ሌላ ነው ፡፡ ብዙዎቹ ቀሪውን እድሜያቸውን ከትክክለኛ ስማቸው በላይ የሚታወቁበት ወይም የሚጠሩበት በአንድ ወቅት ፣ ለሆነ ምክንያት ወይም ችግር ባወጡት ስማቸው ነው ፡፡ በኛም ሃገር በባህላችን በስማችን ላይ ፣ እንደ ቅጽል ፣ ከምግባር ፣ ወይም ከድርጊት ጋር በተያያዘ ምክንያት እንጨምር ነበር ፡፡ ከዚህ ባሻገር ፣ በሃገራችን እንደ ውጪው ሃገር ፖለቲካ የብዕር ስም መጠቀም የተጀመረው ፣ ይኔ ትውልድ ሥርዓቱን መታገል ከጀመረና ፣ የግራው ፖለቲካ ወደ ሃገራችን ከገባ ቦኋላ ፣ እራስን ከአገዛዙ የፖሊስና የጸጥታ አፈና ላለማጋለጥና ፣ ፍልስፍናውን እንደፈጠሩት የቀደምት ፖለቲከኞችን መንገድ እንደፋሺንም ጭምር በመከተል ነበር ፡፡
ሆኖም በአንድ በተወሰነ ወቅት፣ ይህ እራስን ከአንባገነኖች አፈና ተደብቆ የማታገያና የመታገያ ዘዴ፣ ሌሎችም ፣ እንደ ማፍያ አይነት ወንጀለኛ ድርጅቶች ከምዕራቡ ዓለም ጀምሮ ለመጥፎ ተግባር መጠቀም ጀመሩ ፡፡ ከላይ ቅጥረኛው ወታደር እንደ ነገረን ፣ በፖለቲካውም ሆነ በማፍያው ዓለም ፣ ስማቸውን እየደበቁ በማስፈራራት በመዝረፍ ፣ ስም እያስጠፉ እራሳቸውን ለመጥቀም ፣ ለማበልጽግና ቦኋላም እራሳቸውን ከሃላፊነትና ፣ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የብዕር ስምን መጠቀም ቀጠሉ፡፡
ባጠቃላይ የብዕር ስም ሌላውን አጥቅቶ ለመደበቂያ ፣ ለወንጀል ተግባር ፣ ሌላውን ለማስጠርጠር ፣ ለመከፋፈል ፣ ስም ለማጥፋት አይሁን እንጂ ፣ ማንም የብዕር ወይም የውሸት ስም የመጠቀም መብትም አለው ፡፡ በሚወዳት ፍቅረኛው ፣ በምታደንቀው ጀግና ስም ፣ በምንወደው መፈክር ….ወዘተ ፣ የብዕር ስም መጠቀም ተንኮልና ሴራ እስከሌለው ድረስ ፣ ችግር የለውም ፡፡ ወይም በአገዛዙ ላይ ለህይወታቸው የሚያሰጋ ትችት የሚያቀርቡና ፣ ሃገር ውስጥ መግባትና መውጣት የሚፈልጉ እስከሆኑ ድረስ ፣ በበኩሌ ችግራቸው ይገባኛል ፡፡
በተረፈ ተቺዎች አውሮፓና ፣ አሜሪካ ተቀምጠው ከሐገሩ እንደ ከሳሾቹ ለተሰደደ ፣ በግልጽ ማንነታቸውን አሳውቀው የመተቸትም ሆነ የመቃወም መብት የተጠበቀበት ነጻ ሃገር ቁጭ ብለው ፣ የሚጽፉትን በእውነት የሚያምኑበት ከሆነና ሌላ የተደበቀ ተንኮል ከሌለበት ?፣ ወይም ተገዶ በተጽዕኖ ፣ አሊያም ገንዘብና ስልጣን አታሎት ካልሆነ በስተቀ ፣ የሚተቸውን ሰው ስም እየጠቀሰ የራሱን ስም የሚደብቅበት ምክንያት የለም፡፡
(በእርግጥ አንዳንድ የሌላውን ቀልብ ለመሳብ ፣ የውይይት ማዕከል ለመሆንና ለሚቀጥለው ተንኮላቸው ሽፋን ለመጠቀም ፣ ሌላ ሰው እንደጻፈ አስመስለው በራሳቸው ላይ የሚጽፉ እንዳሉ ፣ በተለያዩ መጻህፍት ያነበብናቸውና ፣ “ተደራራቢ ስብዕና “ፈረንጆቹ “መልቲፕል አይደንቲቲ“ የሚሏቸው የግለሰብ ባህሪዎች መኖራቸውን ስንዘነጋ ፡፡)
ወደ ጀመርኩት ልመለስና ፣ እንዲያውም በቅርቡ የተጀመረው ፣ “በአንድ ጠጠር ሦስት ወፍ“ እንደሚባለው ፣ ስምን መደበቅ ብቻ ሳይሆን ፣ ጸሃፈ አስመስለው ለማሳጣት የሚፈልጉትንም ሰው የአጻጻፍ ዘዴ ፣ የፊደሉ አመራረጣቸው ፣ የአርስት አሰጣጣቸው ፣ ቅንፍና ኮማ ሳይቀር ሊያስጠረጥሩ እንደሚፈልጉት ሰው አድርገው መጻፍ ጀምረዋል፡፡ በዚህ ዘዴ የሚፈጽሙት ደባ ሊያጠቁ የሚፈልጉትን አስጠርጥርጥረው ያስነጥሉታል፣ ያስጠሉታል፡፡ የሚሰድቡትንም ግለሰብ በዚህ አይነት ስሙን ያጠፋሉ ፡፡ በሁለቱ ግለሰብ ፣ ወይም ድርጅት ወይም ቡድን …ወዘተ መሃል ቅራኔ ፈጥረው ያተራምሳሉ ፡፡ ይህ አይነት የተቀነባበረ ሴራ ደግሞ ፣ በግለሰብ የሚሰራ ፣ ወይም አንድን ሰው ብቻ ለመጉዳት ወይም ለመጥቀም ሳይሆን ፣ ከኋላው ወፍራም መዳፍ ያለበት ወያኔያዊ ወይም ሻቢያዊ ተልዕኮ ብቻ ሳይሆን ፣ አንዳንድ ሃላፊነት ከማይሰማቸው ተቃዋሚም ሰፈር አካባቢ ከሆነ ? በጣም አደገኛና በታታኝ ሴራ ስለሆነ ፤ የድህረ -ገጽ ሃላፊዎች ፣ እንደዚህ አይነት ዝቅ ያለ ደረጃ ወርደው ለሚከፋፍሉን ፣ ትግሉንም ሆነ ታጋዮችን ስለሚያዳክም መተባበር የለባቸውም ፡፡
ትችት ተገቢ ነው፡፡ አንድ ተቺ ስለ ግለሰብ የሚጽፈውን የሚያምንበት ከሆነ እራሱን መደበቅ የለበትም፡፡ የማያምንበት ወይም የሚፈራ ከሆነ አርፎ መቀመጥ ይችላል ፡፡ ነገር ግን እሱ ማንነቱን ማሳወቅ ፈርቶ ፣ የሚከሰውን ሰው ስም እየጠቀሰ ፣ ያልጻፈን ሰው እያስጠረጠረ የሚደበቅ ሰው የሚመሳሰለው ፣ ከኋላ አድፍጦ ከሚተኩስ ፈሪ ሰው ጋር ብቻ ነው ፡፡
ስለዚህ የኢንተርኔት ድህረገጽ ሃላፊዎች ፣ እንደነዚህ አይነት ሃላፊነት የማይሰማቸው ፣ እንደ ቅጥረኛው ወታደር ከተጠያቂነትና ፣ ከሃላፊነት ለማምለጥ ፣ ተደብቀው በብዕር ስም ደባ የሚሰሩትን ፣ ድህረ ገጾቻችሁ ላይ ለማውጣት አትተባበርዋቸው ፡፡ በማንኛውም ሃይማኖት፣ ሞራል፣ ኤቲክስ ፣ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ይህን አይነት አሰራር ፣ አይከተልም ፡፡( በእርግጥ በአንባቢ እጦትና ፣ በራሳቸው ምርጫ ስሜታዊ አሉባልታወችን በማስተናገድ ድህረ ገጾቻቸውን በዚህ አይነት ጽሁፍ ለማጨናነቅ ከወሰኑት በስተቀር) ማንም ለፍትህና ለዲሞክራሲ የሚታገል ፣ የኢንተርኔት ድኅረ-ገጽ ሃላፊዎች ፣ ከአርዕስቱ ወጥቶ በግለሰቦች ስብዕና ላይ በሃሰት ስም ጀርባ ተደብቀው የተንኮል ድራማ ዘመቻ ለማስነበብ የሚፈልጉትን ተንኮለኞች እንደማይተባበሩ ተስፋ አለን ፡፡
በተረፈ በኳሱ ጨዋታ ብንሸነፍም ፣ ከኳሱ ጀርባ ተከፋፍለን እንድንቆም ተዘጋጅቶ የነበረውን ድራማ ፣ አብዛኛው ወገናችን ነቅቶ ፣ ከብሔራዊ ቡድናችን ጎን በመሰለፍ የተዘጋጀውን ወጥመድ በማክሸፉና ፣ በአንድነት ቆሞ ለወገኑ ድጋፉን መስጠት በመቻሉ ፣ ሌላ የሕብረትና ፣ የጸባይ ድል ስለተጎናጸፍን ፣ በደቡብ ያጣነውን ኳስ ፣ ከደቡብ እንስከ ሰሜን ፣ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ተያይዘን አንድነታችንን ያደስንበትን አዲስ ክስተትና ፣ ድል ! ! እንደተፈጠረ ሳንረሳ፣ ይህንንም እያዳበርነው ፣ እያቀጣጠልነው ወደፊት እንቀጥል በማለት የሽማግሌ ምክሬን አስተላልፋለሁ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ከከፋፋዮች ይጠብቃት ፣ እኛም እንተባበረው !!
http://www.ecadforum.com |
mandag 28. januar 2013
ከብዕር ስም ጀርባ (ከብስራት ኢብሳ)
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar