søndag 30. desember 2012

ብሶት የወለደኝ እያለ የሚመጻደቀው ወያኔ ብሶተኞችን እየፈለፈለ ነው


በአገራችን ውስጥ የነበረው ብልሹ አስተዳደር በፈጠረው ኢፍትሃዊነት ብሶት አርግዞ ለድል ያበቃውን ጠመንጃ እንደመዘዘ በኩራት የሚደሰኩረው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ፡ የመንግሥት ሥልጣንን የሙጥኝ በማለት በህዝባችን ላይ እየፈጸመ ባለው ሰቆቃ ተማርረው በተራቸው ብሶት አርግዘው ጠመንጃ ለማንሳት የሚገደዱ ሃይሎችን በየቀኑ እየፈለፈለ መሆኑ በተግባር እየታየ ነው።
ወያኔ የድጋፍ መሠረቴ ነው ከሚለው የትግራይ ክልል ውስጥ የወጣው የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ወይምዴሚት በሚል ምህጻረ ቃል ከሚጠራውና በርካታ የትግራይ ወጣቶችን ማሰባሰብ ከቻለ ድርጅት ጀምሮ “በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የብሄር እኩልነት ካባ አከናንቤያችኃለሁ” ብሎ ወያኔ ከሚመጻደቅባቸው ህዝቦች አብራክ የወጡየኦሮሞ፣ የኦጋዴን፣የቤነሻንጉል፣ የጋምቤላ፣ የአፋርና የደቡብ ህዝቦች የዚህን ዘረኛ ሥርዓት እብሪትና ጥጋብ አስተንፍሰው የተዋረደውን ክብራቸውን ለማስመለስ  መሳሪያ አንስተው መፋለም ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
በወያኔ የዘር ፖለቲካ ከማለዳው ጀምሮ የጥቃት ሰለባ የሆነውና እንደ ባዕድ ወራሪ በሰላም ከየሚኖርባቸው ክልሎች ታድኖ የሚባረረው አማራም “በዘር መደራጀት ከጥቃት የሚያድን” ከሆነ በሚል ቁጭት ተደራጅቶ የትጥቅ ትግሉን ጎራ መቀላቀሉን አስታዉቋል። በብሄር እኩልነት ስም በየክልሉ ለተሾሙ ምስለኔዎች በታኮነት የተመደቡ ዘረኞች በህዝባችን ስም እየማሉና እየተገዘቱ የሚያደርሱት ግፍ አስመርሯቸው ጠመንጃ ካነሱ ከነዚህ የብሄር ድርጅቶች በተጨማሪ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ላለፉት 12 አመታት ከወያኔ ጋር የሽምቅ ውጊያ እያካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባርም የተፈጠረው ወያኔ በህዝባችንና በአገራችን ላይ በሚፈጽማቸው ወንጀሎች ብሶት ባረገዙ ዜጎች መሆኑን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ የለም።
ሰሞኑን ደግሞ የወያኔን ዘረኛና አምባገነናዊ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ በትጥቅ ትግል ለማስወገድ በአገር ወዳድና ለህዝብ ተቆርቋሪ በሆኑ ዜጎች ስብስብ፤ ወጣቶችና፣ ምሁራን የተሞላ ድርጅት ማቋቋሙን ለህዝብ ይፋ ያደረገው “የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል” ካሰራጨው መግለጫ መረዳት እንደተቻለው፤ ወያኔ ድርድርና እርቅ የማይገባው፣ ትዕግስትን እንደፍራቻ፣ አርቆ አሳቢነትን ደግሞ እንደ ሞኝነት የሚቆጥር በዚህም ስሌት ሕዝብን ለዘላላም እየረገጠና እየዘረፈ ለመግዛት ቆርጦ የተነሳ እኩይ ኃይል በመሆኑ ወያኔን ሊገባው በሚችል ብቸኛ ቋንቋ በማነጋገር የአገዛዝ ዕድሜውን ለማሳጠር ቆርጦ ብረት ያነሳ ሃይል ተፈጥሯል።
ግንቦት7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ሲያስጠነቅቅ እንደኖረው ፋሽስት ጣሊያን ሞክራ ባልተሳካላት የመንገድና የህንጻ ግንባታዎች ተደልሎ ወይም ከግማሽ በላይ የሆነውን ህዝባችንን ለረሃብ በዳረገ ወያኔ ግን ልማትና እድገት ብሎ በሚጠራው ለውጥ ተታልሎ ክብሩንና ነጻነቱን አሳልፎ በመስጠት እስከወዲያኛው ለወያኔ ባሪያ ሆኖ ለመገዛት የተዘጋጀ ህዝብ የለም ብሎ ያምናል።
ወያኔ ጥጋብ በወለደው እብሪቱ በማንአለብኝነት የህዝብን መብትና ነጻነት ረግጦ በአፈና ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች አለኝታየ በሚላቸው የፖሊስ፣ የደህንነትና ወታደራዊ ኃይሎች እስከ መጨረሻው አጠናክር ለመቀጠል የሚችል አድርጎ ያስባል። በዚህም ምክንያት እስካፍንጫው ባስታጠቀው ወታደር ብዛትና በነዋሪው ቁጥር ልክ ህዝብ መሃል ባሰማራው ሰላዮች የተገነባው የፍርሃት ግምብ የሚናድም መስሎ አይታየውም። ሃቁ ግን በግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል የተሰባሰቡ ወጣቶችም ሆኑ ወያኔን በአራቱም የአገራችን ማዕዘናት ለመግጠም ጠመንጃ ያነሱ ሃይሎች ወያኔ ህዝባችንን ሊያስፈራራ የሚችልበትን ሁሉ በጣጥሰው ለመውጣት ምንም ችግር የሌለባቸው መሆኑን ነው።
ንቅናቄያችን ግንቦት 7 ወያኔ ገንብቻለሁ ብሎ የሚኮፈስበትን የፍርሃት ግምብ ደርምሰው ለነጻነታቸው ሲሉ ውድ የህይወት ዋጋ ለመክፈል በግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ዙሪያ መሰባሰባቸውን ይፋ ያደረጉ ወጣቶች የተነሱለትን ክቡር አላማ ያደንቃል። በዚህም ምክንያት ለነጻነቱ ቀናኢ ለሆነው ህዝባችን ያቀረቡትን የትግል ጥሪ ወቅታዊነት ሁሉም እንዲረዳው የበኩሉን አሰተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
posted by AYANA KEBEDE

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar