fredag 28. desember 2012

Nasrudin Ousman 12:08am Dec 29
ይህ ትውልድ ወደ ጨለማ ዘመን የኋልዮሽ ለመመለስ ፈቃደኛ አይደለም!
[“ህቡዕ ብዕር” በሚል ርዕስ ለተሰናዳው የ1 ዓመት ጽሑፎች መድበል እንደ መግቢያ የተጻፈ]
~~~~~~~~~ - በነስሩዲን ዑስማን -~~~~~~~~~~~~

ኢህአዴግ በሚቆጣጠራቸው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ስለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት አብዝቶ ይደሰኩራል፡፡ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ደግሞ ስለ ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በስነ ምግባር እና ስነ ዜጋ ትምህርት አማካይነት ለአዲሱ ትውልድ በመደበኛው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ አካትቶ ያስተምራል፡፡ ነገር ግን ራሱ ዴሞክራሲያዊ ተፈጥሮም ሆነ ባህሪ የሌለው ከመሆኑም በላይ በፖለቲካው ምህዳር እኒህን እሴቶች ሲደፈጥጥ እንጂ ሲያፋፋ አይታይም፡፡

ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ ሥልጣን ከያዘም በኋላ የአገራችን ፖለቲካ ከ1960ዎቹ የቁርሾ ፖለቲካ ባልጠገገ የባላንጣነት ቅኝት ነው የቀጠለው፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ እንደወጣ የፖለቲካ ምህዳሩን በዚህ ቁርሾ ላይ ተመሥርቶ ሲቃኝም ሆነ ከሀያ ዓመታት በኋላ በህገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን የሃይማኖት ነጻነት ለመጋፋት አልሞ ሲንቀሳቀስ ከግምት ያላስገባቸው ሁለት ትውልዶች አሉ፡፡ አንደኛው ትውልድ ኢህአዴግ በረሃ ሳለ በአምባገነኑ የደርግ ሥርዓት ታፍኖና ተረግጦ ያደገው ነጻነት ናፋቂ ትውልድ ሲኾን፣ ሌላኛው ደግሞ በራሱ በኢህአዴግ ዘመን (ለፖለቲካ ፍጆታም ቢሆን) ስለ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ነጋ ጠባ እየተደሰኮረለት ያደገው (ዛሬ በሃያዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ) አዲስ ትውልድ ነው፡፡ ስለዚህም በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን በአንድ በኩል ከደርግ ውድቀት በኋላ ዕውን ይሆናሉ ብሎ [በየዋህነት] ተስፋ ያደረጋቸውን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች/ነጻነቶች ተስፋ ባደረገው [ያልተጋነነ] መጠን ዕውን ሲሆኑ ባለማየቱ አዝኖ፣ ይልቁንም ኢህአዴግ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መደስኮር እንጂ አክብሮ ሊያስከብር የሚሻ ድርጅት ሳይሆን፣ ከነባሩ የቁርሾ ፖለቲካ አባዜ ያልተላቀቀ ድርጅት መሆኑን ተረድቶ (ፖለቲካን በመድረኳ ላይ ሳይሆን በየመከዳው ከጫት ጋር የሚያደቅ)፣ ባያገኝም የሚፈልገውን ግን የሚያውቅ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ በሌላ በኩል፣ የደርግን ሥርዓት እምብዛም የማያውቅ፣ ኢህአዴግም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ተቋማት በየራሳቸው ዐውድ የሚያስተጋቧቸውን የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እሴቶች ከጨቅላ ዕድሜው አንስቶ እየሰማ፣ በትምህርት ቤትም እየተማረ ነፃነቱን፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን በውል እያወቀ ያደገ አዲስ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) በታሕሣሥ/ጥር 2004 የአወሊያ ኮሌጅ 50 መምህራንን በአንዲት ደብዳቤ አማካይነት ለማባረር፣ በዚያው ዓመት ለምረቃ የሚበቁ ተማሪዎችንም ድካማቸውን መና አስቀርቶ ሜዳ ላይ ለመበተን ሲደፍር በቀጥታ የተላተመው ከዚህ "መብቴን አሳልፌ የምሰጥበት ምንም ምክንያት የለም" ብሎ የሚያምን አዲስ ትውልድ ጋር ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ኢህአዴግ ለፖለቲካ ፍጆታ በሚነዛው የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዲስኩር ሳያውቀው፣ ምናልባትም ሳይፈልግ፣ ከፈጠረው መብቱን ያወቀ ትውልድ ጋር ተፋጠጠ ልንል እንችላለን፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ ከቀደምት ዘመናት በተሻለ ሃይማኖቱን የማወቅ ዕድል አግኝቷል፡፡ ይህ ግን ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ ብቻ ተለይቶ በተሰጠ መብት የተገኘ አይደለም፡፡ የአገራችን ህገ መንግሥት በአንቀጽ 11 የሃይማኖትና የመንግሥትን መለያየት፣ አንዱ በአንዱ ጣልቃ ያለመግባት ድንጋጌን፣ በአንቀጽ 27 ደግሞ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ‹የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት›ን አረጋግጧል፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሙስሊሙ አነሰም በዛ የእነዚህ ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ተጠቃሚ ነው፡፡ ላለፉት 12 ወራት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እያካሄዱ ያሉት ሰላማዊ ትግል በእነዚህ ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ላይ ተነጣጥረው እየተቃጡ ያሉ የነፃነትና የመብት ጥሰቶች በማያወላዳ መልኩ እንዲያከትሙ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የችግሩ መሠረታዊ መነሾ የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ለማመን በሚያዳግት ድፍረት (Incredible boldness) በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ‹ጭው ብሎ መግባት› ነው፡፡ ‹ጭው ብሎ መግባት› የሚለውን አገላለጽ የተጠቀምሁት፣ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ አዲስ ስላልሆነ ነው፡፡ በሌሎች ሃይማኖቶች አኳያ ለመናገር ለጊዜው በቂ መረጃ ባይኖረኝም፣ ሙስሊሙን በተመለከተ ግን ቢያንስ ከ1987 ወዲህ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ከኢሕአዴግ ቁጥጥር ውጪ ሆኖ አያውቅም፡፡ የጣልቃ አገባቡን ደረጃና መልክ ስናይ ግን የአሁኑ (በጥቅሉ ከ2000፣ በይፋ ደግሞ ከሐምሌ 2003 ወዲህ ያለው) እና የከዚህ ቀደሙ (ከ1987- 2000) የሰማይና የምድር ያህል የተራራቁ ናቸው፡፡ ጣልቃ አገባቡ እንዳሁኑ ፍፁም ጀብደኝነት የተመላበት ሆኖ አያውቅም፡፡

እንደተባለው ላለፉት 18 ዓመታት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ከመንግሥት መዳፍ ውጭ ሆኖ አያውቅም፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብም አንድያ የሃይማኖት ተቋሙ ከፖለቲካ መሣርያነት ባለፈ የማኅበረሰቡን መንፈሳዊ ህይወት ለማበልፀግ የረባ ሥራ አለመሥራቱ ሲያሳዝነው ቆይቷል፡፡ እንዲያም ሆኖ ቢያንስ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 27 የተረጋገጡ መብቶቹን በመጠቀም እምነቱን በነፃነት ለማራመድ፣ ለመተግበርና ለማስፋፋት የሚያደርገው የግል እና የወል ጥረት ስላልተስተጓጎለበት ከተቋሙ ብዙም ሳይጠብቅ በሰላም ኑሯል፡፡

ከሀምሌ 2003 ወዲህ ግን የኢሕአዴግ መንግሥት አንዳችም የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ይሁንታ እና እውቅና ሳይጠይቅ፣ በዚሁ እርሱ በሚቆጣጠረው “የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተቋም” ላይ የ”አሕባሽ” አስተምህሮ አራማጆችን በመሾም፣ ይህንኑ አስተምህሮ በ'አሕባሻዊው' ጠቅላይ ም/ቤት አስፈፃሚነት፣ በኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ ውስጥ ለማስረፅ (ለመጫን ወይም ለማስጫን) በትጋት መንቀሳቀሰ ጀመረ፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በአሕባሽ አስተምህሮ የማጥመቅ “ተልዕኮና ሥልጣን” የተሰጠው “አሕባሻዊው ጠቅላይ ም/ቤት” ተልዕኮውን የሚፈጽመው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በሚያደርግለት ቀጥተኛ ድጋፍና የቅርብ ክትትል ነው፡፡

በመላ አገሪቱ ለሚገኙ የመጅሊስ መዋቅር አባላት በተከታታይ የተሰጠው የአህባሽ አስተምህሮ ሥልጠና ዕኩይ ተልዕኮ ቁልጭ ብሎ ከታየባቸው አስገራሚ ገጽታዎች መካከል በየስልጠናዎቹ መጨረሻ ላይ በ‹‹ሙስሊሙ ማኅበረሰብ›› ስም የወጣው ባለ 17 ነጥብ የአቋም መግለጫ በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጃቸው በእነዚህ ሥልጠናዎች መጨረሻ ላይ በተነበበው የአቋም መግለጫ ‹‹ሙስሊሙ ኅብረተሰብ›› የተባሉት የሥልጠናው ተሳታፊዎች በህገ መንግስት የተረጋገጡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሃይማኖት፣ የእምነትና የአስተሳሰብ ነፃነቶችን ከበጎ አድራጎት ድርጅትነት ያለፈ ቁመና ለሌለው መጅሊስ አሳልፎ ለመስጠት መወሰናቸውን በይፋ ነገሩን፡፡ በዚሁ ‹‹የአቋም መግለጫ›› ላይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አንድነት የማጠናከር ተልዕኮ አለው ተብሎ የሚታሰበው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የአመራር አባላት ‹‹ወሀቢያ እና ወሀዲያ … ሙስሊሙን የማይወክሉ ፀረ-ልማት እና ፀረ-ዴሞክራሲ በመሆናቸው ከመዋቅራችን እና ከህዝበ ሙስሊሙ የምናፀዳቸው መሆናችንን እናረጋግጣለን›› ማለታቸውንም ሰማን፡፡ ደጉ አዲስ ዘመንም በመስከረም 20፣ 2004 ዕትሙ፣ ‹‹የሙስሊሙን ኅብረተሰብ የሰላም ፍላጎት ያረጋገጠ የአቋም መግለጫ›› በሚል (ምፀታዊ) ርዕስ እኒህን ፀረ ህገ መንግሥታዊ ዱለታዎች አስነበበን፡፡

በሐምሌ 2003 በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ሐረር ካምፓስ የተጀመረው የጥምቀተ አህባሽ ሥልጠና በመስከረም የመጀመርያ አጋማሽ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ እና በኢትዮ ቻይና ቴክኒክ ኮሌጅ አዳራሾች ተካሂዶ ይህ ህገ ወጥ የአቋም መግለጫ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በታተመ በአምስተኛው ቀን (መስከረም 25) የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንግሥት ‹ወሀብያ›ን በአክራሪነት መፈረጁን ይፋ አደረጉ፡፡ [ሪፖርተር ጋዜጣ ጥቅምት 2፣ 2004] እኒሁ ደፋር ሚኒስትር በዚሁ መግለጫቸው “ኸዋሪጃ የወሀቢያ ወታደራዊ ክንፍ ነው” የሚል አስቂኝ ሀሳብ መሰንዘራቸውንም ሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ያስነበበ ይመስለኛል፡፡ …

በሌላ በኩል፣ ከነሐሤ 2003 ጀምሮ በ“የሙስሊሞች ጉዳይ” ወርኃዊ የአማርኛ መጽሔት ፋና ወጊነት “የአህባሽ አጀንዳ” እና ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ በተለያዩ የግል መገናኛ ብዙኃን (በጋዜጦችና መፅሔቶች) በተከታታይ እየተዘገበ ነበር፡፡ ይህን ዕኩይ የመንግሥት/መጅሊስ አጀንዳ በመዋጋት ዓላማ ላይ ያተኮሩ የፌስቡክ ቡድኖች መከፈት የጀመሩትም በዚሁ ሰሞን ይመስለኛል፡፡

በስደተኛው የአዲስ ነገር ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ “መንግጅሊስ” የሚል ሁነኛ ስም የተሰጠው አህባሻዊው መጅሊስ በጥምቀተ አህባሽ ስልጠናዎቹ መጨረሻ ላይ ያወጣቸውን “የአቋም መግለጫዎች” ተግባራዊ የማድረግ እንቅስቃሴውን በመቀጠል፣ ታሕሣሥ 21 ቀን 2004 ለ50 የአወሊያ ኮሌጅ መምህራን፣ ለአወሊያ መስጂድ ኢማም (አሰጋጅ) እና ለመስጂዱ ሙዓዚን (የስግደት ጥሪ አድራጊ) “ሥራችሁን እንድታቆሙ” የሚል ትዕዛዝ ያዘለ ደብዳቤ ሰጠ፡፡ ይህ እርምጃ በተዘዋዋሪ የዓመቱን የኮሌጁ ተመራቂ ተማሪዎች እንደዋዛ የመበተን ዓላማ ነበረው፡፡ ተማሪዎቹ መጅሊሱ ይህንን ድንገተኛ እርምጃ እንዲቀለብስና ቢያንስ ጥቂት ወራት ብቻ የቀራቸው የዓመቱ ተመራቂዎች ትምህርታቸውን ያጠናቅቁ ዘንድ መምህራኑ እንዲመለሱ በትህትና ጠየቁ፡፡ በመንግሥት አይዞህ ባይነት እብጠት የተሰማው “መንግጅሊስ” ለተማሪዎቹ የሰጠው ምላሽ ፍፁም ዕብሪት የተሞላበት ነበር “አይደለም ጥቂት ወራት፣ አንድ ቀን ቢቀራችሁ እንኳ መምህራኑ አይመለሱም!” የሚል፡፡

በመጅሊሱ እብሪት የተሞላ ምላሽ ሳቢያ ተማሪዎቹ “አስተማሪዎቻችን ካልተመለሱ ከዚህ ግቢ አንወጣም” ወደሚል ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አመሩ፡፡ ተማሪዎቹ በግቢው ውስጥ ተሰባስበው በችግራቸው ዙርያ ሲወያዩ፣ “መጅሊሱ ለእኛ መብት መሟገት ሲገባው፣ ጭራሽ እንዴት የመማር መብታችንን ሊነፍገን ይቃጣል?!” በማለት መሠረታዊ ጥያቄ አነሱ፡፡ የተማሪዎቹ ከአወሊያ ግቢ ሳይወጡ ውለው ማደር ቤተሰቦቻቸውን ጠራ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተማሪዎቹ ጥያቄ የአዲስ አበባ ሙስሊም ማኅበረሰብ የመወያያ አጀንዳ ሆነ፡፡ ከ35 ዓመታት በዘለቀ ዕድሜው ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ አንዳችም የረባ መንፈሳዊም ሆነ ማኅበራዊ ሥራ ያልሠራው መጅሊስ ጭራሽ ብቸኛውን ኢስላማዊ የትምህርት ተቋም ዒላማ አድርጎ ትምህርት ለማስተጓጎል መንቀሳቀሱ መላውን ሙስሊም አስቆጣ፡፡ በየሙስሊሙ ቤት የተጠራቀሙ ብሶቶች መገንፈል ጀመሩ፡፡ … ውለው ሳያድሩ የአወሊያ ተማሪዎች “ጁሙዓን በአወሊያ” በመስገድ በአጋርነት ከጎናቸው እንዲቆም ለመላው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሙስሊም ጥሪ አደረጉ በሞባይል አጭር የጽሑፍ መልዕክት፡፡ አያሌ የአዲስ አበባ ህዝበ ሙስሊም “ለበይክ!” አለ፡፡ በመጀመርያ የዋና ከተማይቱ ሙስሊም ኅብረተሰብ ከሐምሌ ወር 2003 አንስቶ በይፋ የተከፈተበትን “መንግጅሊሳዊ” የሃይማኖት ነጻነት ረገጣ ዘመቻ በሰላማዊ መንገድ በይፋ ሊታገል ተማማለ፡፡ … ቀጥሎም መጅሊሱ የጋራ ተቋሜ ነው የሚለው መላው የአገሪቱ ሙስሊም ዳር እስከ ዳር ለመብት ትግሉ አጋርነቱን በገሃድ አሳየ፡፡ … በህገ መንግሥቱ በተረጋገጠው የሃይማኖት ነፃነት ላይ የተቃጣውን ጥሰት በማያወላዳ ሁኔታ መቀልበስ የሚቻለው ህዝበ ሙስሊሙ የጋራ የእምነት ተቋሙን የራሱ ማድረግ ሲችል ብቻ መሆኑን በማመን የተጀመረው የመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነጻነት ትግል ተጠናክሮ እንደቀጠለ እነሆ አንድ ዓመቱን ደፈነ፡፡

"ህቡዕ ብዕር" በሚል ርዕስ የተሰናዳው ይህ የልዩ ልዩ ጽሑፎች ስብስብ፣ ለሃይማኖት ነፃነት መከበር ላለፈው አንድ ዓመት እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ትግል ሂደት የተበረከተ የግለሰብ በጣም ሚጢጢ አስተዋፅኦ ነው፡፡ ለሃይማኖታዊ ነጻነት መከበር በሚካሄደው በዚህ ሰላማዊ ትግል ሂደት እስካሁን ቁጥራቸው 13 የሚጠጉ ሙስሊሞች የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ሰማዕት (“ሸሂድ”) ሆነዋል አላህ ጀነትን እንዲመነዳቸው እንለምነዋለን፡፡ ሌሎች አያሌ ሙስሊሞች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ጥያቄዎቼን ለመንግሥት አቅርበው ስለመብቴ ይደራደሩልኝ ብሎ የመሠረተው የመፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በርካታ ሙስሊሞች “ህገ መንግሥታዊ መብታችን ይከበር!” ብለው ስለጮሁ ብቻ ለአስከፊ እስር፣ እንግልትና ድብደባ ተዳርገዋል፡፡ … የመንግሥት ግፍና በደል ዕለት በዕለት እየጨመረ መሄዱ ለመብትና ለነፃነት የሚደረገውን የህዝበ ሙስሊሙ የጋራ ትግል ይበልጥ አጠናከረው እንጂ ቅንጣት አላቀዛቀዘውም፤ አያቀዛቅዘውምም - ኢንሻአላህ፡፡

የህዝበ ሙስሊሙን መብትና ሃይማኖታዊ ነፃነት የማስከበር ሰላማዊ ትግልን በጠብ መንዣ አፈሙዝና በቆመጥ ድብደባ ማስቆም አይቻልም፡፡ ይበልጡንም፣ በጥምቀተ አህባሽ የመንጋ ሥልጠና መጨረሻ ላይ የወጡትን (ነፃ ፍርድ ቤት ቢኖር ኖሮ) በወንጀል የሚያስጠይቁ ህገ ወጥ “የአቋም መግለጫ” በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ ተፈፃሚ ማድረግ አይሳካም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መጅሊስን የሚፈልጉት ሲሆን ለመንፈሳዊ ህይወታቸው የሚጠቅም ስራ እንዲሠራላቸው፣ ያም ካልሆነ ቢያንስ የሙስሊሙን ህዝብ አቅም አስተባብሮ በድህነት ለሚማቅቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች የሚታደግ ጠቃሚ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ እንጂ፣ የመንግሥት መሣሪያ ሆኖ በህገ መንግሥት በተረጋገጡ መብትና ነፃነቶቻቸው ላይ እንዲፈርድና እንዲቀድ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ የአገሪቱ ህገ መንግሥት መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ እንዳይገባ የተከለውን አጥር በህዝበ ሙስሊሙ ተቋም ጭምብል ተከልሎ በአቋራጭ ለመሻገር የሚያደርገው ሙከራ ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ መሆኑን አውቆ ቢታረም፤ ራሱ የፈጠረውን ችግር በዱላና በጠብ መንዣ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ችግሩን በተገቢው መንገድ ለመፍታት በቅን ልቦና ቢንቀሳቀስ መልካም ነው፡፡

መፍትኄው አጭርና ግልፅ ነው፡፡ ኢህአዴግ በውጭ ኃይሎች (ዳረጎት እና) ግፊት 'አክራሪነት'ን በመዋጋት ሽፋን የጀመረውን ፀረ ኢስላም አጀንዳ በመዝጋት ለህገ መንግሥቱ ተገዢ ይሁን፡፡ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ስለ መብትና ነፃነቱ እያሰማ ያለው ጩኸት እረፍት እንደነሳው ልቡ እያወቀ፣ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም አል ጀዚራ ላይ ሲናገሩ እንደተደመጡት፣ “I think that is the voice of the minority” (ያ የጥቂቶች ድምፅ ይመስለኛል) በማለት የሚያታልለው ራሱንና ራሱን ብቻ ነው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 27 የተረጋገጠው የሃይማኖት፣ የእምነትና የአስተሳሰብ ነፃነት እንኳንስ በ40 ሚሊዮን ዜጋ በአንድ ግለሰብ ላይም ሊገደብ እንደማይችል “ማንኛውም ሰው…” ብሎ በሚጀምረው በዚሁ አንቀጽ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ይህን መካድ ፖለቲካዊ ብልጥነትም፣ ብልህነትም አይደለም፡፡

ኢህአዴጎች ሆይ! ቁርጡን እወቁት፤ በዚህ የመረጃ ዘመን ራሱን በእውቀት እየገነባ ያደገው ይህ ትውልድ፣ የኢስላምን ብርሃን ካየ በኋላ አባቶቹ፣ አያቶቹ እና ቅድመ-አያቶቹ ወዳሳለፉት ግፍ፣ ጭቆናና መድልዎ የሰፈነበት የጨለማ ዘመን ለመመለስ ፈፅሞ ፈቃደኛ አይደለም! ስለዚህም፣ የሃይማኖትና የእምነት ነፃነታችንን በማስከበር ብቸኛ ዓላማ የጀመርነው ሰላማዊ ትግል ከግቡ እስኪደርስ የእምነት ነፃነታችንን የሚጋፉ ማናቸውም ዕኩይ መርኃ ግብሮች እና ሤራዎች መቆማቸውን እስክናረጋግጥ ድረስ ትግላችን እንደሚቀጥል ልታውቁት ይገባል፡፡ የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅ፣ ጥራትና እልቅና የተገባው ኃያሉ ጌታችን አላህ (ሱ.ወ) በፍፁም ሀሰትን በእውነት ላይ የበላይ እንደማያደርግ ፅኑ እምነት ያለን ዜጎች ነን፡፡ …

ኢህአዴጎች ሆይ! ወደ አቅላችሁ በመመለስ የሚያስከብራችሁን ስራ ከመስራት ይልቅ “የለም ይህ የማናጥፈው ፖለቲካዊ ውሳኔያችን ነው” በሚል ግብዝነት በመብት ረገጣ መርኃ ግብራችሁ መግፋትን ከመረጣችሁ ቀጥሉበት፡፡ ለመናኛ የባዕዳን ዳረጎት ስትሉ የንፁኃን ዜጎቻችሁን ደም ለምታፈስሱት “ይብላን ለእናንተ” እንጂ፣ እኛም የጠብ መንጃ አፈ ሙዝ ፈርተን የማናጥፈው፣ ከእናንተ አሳፋሪ መርኃ ግብር እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው፣ በደስታ ህይወታችንን የምንሰዋለት “ዲን” አለን፡፡ አይደለም መታሠርና መደብደብ፣ ለዲነል ኢስላም መሰዋትም ለእኛ ክብር ነው፡፡
አላሁ አክበር!!

http://www38.zippyshare.com/v/50859047/file.html

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar