ደጀ ሰላም Deje Selam
|
- የአባቶችን እርቀ ሰላም አስመልክቶ ከጀርመን ፍራንክፈርት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተላከ መግለጫ
- ግልጽ ደብዳቤ:- ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ
- “አቤቱ ለአፌ ጠባቂ፣ ለከንፈሮቼም ፅኑዕ መዝጊያ አኑር”
Posted: 30 Nov 2012 05:46 PM PST
(READ THIS NEWS ARTICLE IN PDF)
(ደጀ ሰላም፤ ኅዳር 22/2005 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 30/2012)፦ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባቶች በእርቀ ሰላም ዙሪያ ለመነጋገር የአንድ ሳምንት ዕድሜ በቀራቸው በአሁኑ ሰዓት ከተለያዩ አካላት የሚላከው የድጋፍ መግለጫ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ቀደም ብሎ “ከጉባኤ ካህናት ወምዕመናን ለቤተክርስቲያን ሰላም” ተማጽኖ ባሻገር አስመልክቶ ጀርመን አገር ፍራንክፈርት ከተማ የሚገኘው የሐመረ ብርሃን ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መግለጫው አውጥቷል። ሙሉውን ከዚህ ያንብቡ።
|
Posted: 30 Nov 2012 05:59 PM PST
ኅዳር ፲፮ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“በትሕትና፡ዅሉና፡በየዋህነት፡በትዕግሥትም፤ርስ፡በርሳችኹ፡በፍቅር፡ታገሡ፤
በሰላም፡ማሰሪያ፡የመንፈስን፡አንድነት፡ለመጠበቅ፡ትጉ።” ኤፌ 4:2-3
ግልጽ ደብዳቤ (PDF)
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ
ዋሽንግተን ዲሲ
ለብጹዕ አቡነ ናትናኤል
ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ
አዲስ አበባ: ኢትዮጵያ
ለብጹዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
በያላችሁበት:
ብጹዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ መርቆሬዎስ : ብጹዕ አባታችን አቡነ ናትናኤል እና ብጽዓን አባቶች
ቡራኬያችሁ ይድረሰን !
ጉዳዩ : በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያለውን ልዩነት አስወግዶ ሰላምና አንድነትን ስለማምጣት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወልድ ዋሕድ ብላ አምና ርትዕት ሃይማኖትን ስታስተምርና ስትመሰክር ከመኖሯ በተጨማሪለሀገራችን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ መኩሪያ የሆኑትን ብዙ የታሪክ ቅርሶችንና ሀብታትን አበርክታለች::ለመጥቀስ ያህል ሥነ ሕንጻ፣ ቋንቋ ከነ ሥነ ጽሑፉ፣ ሥነ ሥዕል፣ ዝማሬ፣ የሀገር ፍቅርንና ጀግንነትን ማንሳት ይቻላል:: ይሁን እንጂ ይህች ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት የሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፤ በአሁኑ ጊዜ፤ በፓትርያርክ ሲመት ምክንያት በሃይማኖትና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን በአስተዳደር ከሁለት በላይ ተከፍላለች።በዚህም ምክንያት በሀገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስና በውጪው ዓለም የሚንቀሳቀሰው ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሁም ገለልተኛ ነን በሚሉ አድባራት በመከፋፈሏ፤ የምእመናን ሕብረትና ሰላምጠፍቶ ልጆቿ ለነጣቂ ተኩላ ተጋልጠው እየዋለሉ ይገኛሉ። “ዝሆንና ዝሆን ቢጣሉ ተጎጅው ሣሩ ነው” እንዲሉ አባቶቻችን በአስተዳደር በመለያየታቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ጉዳት ደርሶባታል:: እናንተ አባቶቻችን መለያየቱ ያስከተለውና እያደረሰ ያለው ጥፋት ይሰወራችኋል ባንልም እኛም ልጆቻችሁ ብናስታውሳችሁ መልካም ነው ከማለት አንጻር፤ ከብዙ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እንጠቁማለን።
1. አስተዳደርና የተቋም ጥንካሬ
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በክፍፍሉም ሆነ በተለያዩ የአስተዳደር ብልሽቶች ምክንያት ሕዝበ ክርስቲያኑ ተገቢውን መንፈሳዊ አመራር እያገኘ ነው ያለውማለት አይቻልም:: ለምሳሌም የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።
1. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መዳከም ( ግልጽነት፤ ተገቢ ቁጥጥር፤ ፍትሐዊነትና ቅልጥፍና አለመኖሩ፤ በአንጻሩ ሙስናና ዘረኛነት መንሰራፋታቸው፤)
2. ለእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን የሥልጣን እርከን፤ ግልጽ የሆነ፤ የተሟላ የምደባ መስፈርት አለመኖሩ፤
3. የቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ ሕግ (ቃለ ዓዋዲው) በትክክል ተግባር ላይ አለመዋሉና ተዛማጅ ችግሮች፤
4. የኦርቶዶክስና ሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ዋነኛ መሠረት የሆነው ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ/APPOSTOLIC SUCCESSION/ እና ተዋረዳዊ/ ሰንሰለታዊ የቤተ ክርስቲያንመዋቅር (Hierarchy) አለመጠበቅ::
2. ገዳማትና አድባራት፣ አብነት ትምህርት ቤቶች ተገቢውን ድጋፍ ያለማግኘታቸው
5. ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ የሆኑ፣ የሊቃውንት መፍለቂያ የነበሩ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ጉባኤያት እየተበተኑ ነው:: የብዙ መናንያንና ባህታውያን መጠጊያ/ታዛ የነበሩ ገዳማትና አድባራት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እየተቃጠሉና እየፈረሱ ነው:: በከተማና በገጠር ያሉ ገዳማትና አድባራት በልማት እየተመካኘ ይዞታቸውን እየተነጠቁና ሕጋዊ መብታቸው እየተደፈረ ነው::
6. ለኢየሩሳሌም ገዳማት እንደ "ዴር ሡልጣን" እና ሌሎችም ገዳማት የሚያስፈልገው የዲፕሎማቲክና የሌላም እርዳታ ተዳክሟል፤
ከሀገር ውጭ በስደት ያለው ሕዝብ በአንድነትና በጋራ እየተመካከረ በሀገር ቤት ያለውን መንፈሳዊ አገልግሎት በማገዝ አድባራት፤ ገዳማትንና አብነት ት/ቤቶችን በበቂ ሁኔታ መደገፍ እንዳይችልየውግዘቱና የአስተዳደር ልዩነቱ ሳንካ ሆኗል:: (እዚህ ላይ መጠቀስ የሚገባው፤ ውጭው ዓለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን፤ በየዓመቱ፤ ከ3-4 ቢሊዮን ዶላር ወደ ሀገር ቤት እንደምናስተላልፍ በጥናት የተረጋገጠ እውነት ነው። ነገር ግን፤ በተከሰተው የእርስ በርስ መለያየት ምክንያት ለቤተ ክርስቲያናችን የምናደርገው ርዳታ ከአቅማችን ጋር ሲነጻጸር እጅግ አናሳ ነው።)
3. የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን መጠናከር
7. በልዩ ልዩ ሥፍራዎች በአክራሪዎችና በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ላይ ግፍ እየተፈጸመ ነው:: በጅማ፣ በኢሉባቦር፣ በአርሲና በሌሎችም ቦታዎች ክርስቲያኖች በነጻነት ፈጣሪያቸውን እያመለኩ ባሉበት በሰይፍ ስለት እንደተቀሉ፣ እሳት እንደተለቀቀባቸው ሀገር የሚያውቀው እውነታ ነው::
8. ያለውን አስተዳደራዊ ክፍተት በመጠቀም የቅድስት ቤተክርስቲያንን መሠረተ እምነት ለመለወጥ የሚታገለው የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ተጠናክሯል:: በስማችን የሚጠሩ፣ የአበውን ስምና ማዕረግ የያዙ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን እንጀራዋን የሚቆርሱ ነገር ውስጣቸው ቀሳጭና ኢ-ኦርቶዶክስ የሆኑ ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እንክርዳድ እየዘሩ ይገኛሉ።
4. ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት በሚገባው መጠን ያለመስፋፋት
Ø ምዕመናን የሚያስተምራቸው በማጣትና በልዩ ልዩ ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ተስፋ እየቆረጡ ወደ ሌሎች የእምነት ድርጅቶች ፈልሰው እየሄዱ መሆኑን በሀገራችን ዘመን አቆጣጣር ፲፱፻፺፱/፳፻ ዓ/ም የተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ያሳያል:: በዚህ ቆጠራ መሠረት የኦርቶዶክስ ምዕመናን ቁጥር ከሌሎች እምነቶች ቁጥር ጋር በንጽጽር የነበረበት ሁኔታ ከአስር ዓመት በፊት ከነበረው፲ በመቶ ቀንሶ ታይቷል::
Ø በቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ትምሕርት በተለይ ለወጣቱና ለሌሎች ዜጎችም በቂ አለመሆኑ (እንደ እንግሊዝኛ ባሉ የዓለም ቋንቋዎች አለመጠቀም ጭምር)፤
በዚህም ምክንያት፤ የዚህች ቀደምት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎትና ዕድገት እንዲሁም ሊበረክትላት የሚችለው ድጋፍ የሚፈለገውን ያህል ሊዳብር አልቻለም። ይህንን ከባድ ችግርበሚገባ በማጤን፤ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭው ዓለም የሚገኙ የተለያዩ አካላት በቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ጉባኤዎች በማከናወን፤ መግለጫዎች በማውጣትናበደብዳቤዎች በመማጸን ሰላምን ለማምጣት ሰፊ ጥረት አድርገዋል እያደረጉም ይገኛሉ።
በሀገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ባወጣው መግለጫ፤ ካካተታቸው ውሳኔዎች ውስጥ አንደኛው፤ የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ሕግ እስከ ኅዳር ፴ ቀን፳፻፭ ዓ/ም ድረስ እንዲጠናቀቅና የፓትርያርክ ምርጫውም እንዲቀጥል ወስኗል። በአንጻሩ ደግሞ በውጭው ዓለም በሀገረ አሜሪካ የሚገኘው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የሚመራውቅዱስ ሲኖዶስ በ11/2/2012 ባወጣው መግለጫ 4ኛው ፓትርያርክ፤ አቡነ መርቆርዮስ ፤ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው የቀድሞ መንበራቸው እንዲይዙና የቤተ ክርስቲያኗን አንድነት ወደ ቀድሞክብሯ ማምጣት የሚያስፈልግ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን አረጋግጧል።
ከላይ እንደ ተገለጸው፤ በሁለቱም አካላት የተነሳው የሃሳብ ልዩነት የቤተክርስቲያንን ዘላቂ ጥቅም በማሰብ በውይይት ሊፈታ የሚችል መሆኑን እናምናለን:: ለዚህም ኅዳር ፳፮ ቀን ፳፻፭ ዓ/ምአካባቢ፤ ለሶስተኛ ጊዜ ዳላስ ሊከናወን የታቀደው የሰላምና የአንድነት ጉባኤ እንዲቀጥል የሁለቱንም ወገኖች ይሁንታ ማግኘቱ ሁሉንም የቤተክርስቲያን ልጆች ያስደሰተና በታላቅ ጉጉትና ተስፋ እንዲጠበቅ አድርጎታል።
እኛም በሰሜን አሜሪካና ካናዳ በተለያዩ ግዛቶች የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባላት የሆንን ካህናት፡ ዲያቆናት፡ የሰንበት ት/ቤት አባላት፡ ማኅበራትና በጠቅላላውምዕመናን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ሌት ከቀን ደፋ ቀና እያለ ለእርቀ ሰላሙ እየሠራ ካለው የሰላምና እንድነት ጉባኤ ጎን በመሠለፍ በተለያየ መንገድ የድርሻችንን የድጋፍድምጽ እያሰማን እንገኛለን።
በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተጋረጡት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊወገዱ የሚችሉትና መፍትሔ የሚገኝላቸው ፤ ዕርቀ-ሰላም ወርዶ፤ በፍቅር፤ በሕብረት፤ ተቀናጅተን ስንሠራ በመሆኑ አባቶቻችንከሁሉ በፊት ለሰላምና አንድነታችን ቅድሚያ እንድትሰጡልን፤ ይህን በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ላይ እየተጻፈ ያለውን መጥፎ ታሪክ የሚቀይር ፤ ተስፋ ለቆረጡ ምዕመናንና ምዕመናት የሚያጽናና ታላቅ ገድል እንድትሠሩልን እንለምናለን::
በማስከተልም ይህ ያለንበት የመለያየት ዘመን አቁሞ የአንድነት ዘመን እንዲሰፍን የተማጽኖ ድምጻችንን ስናሰማ በሁለቱም ወገን ያሉ አባቶቻችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መለያየትን ሰብረውአንድነትን እንደሚያበስሩን በመተማመን የሚከተሉትን የመፍትሔ ሃሳቦች በታላቅ ትህትና እናቀርባለን::
1. የቤተ ክርስቲያን አንድነት መሠረት የሆኑ ካህናትና ምእመናን በተፈጠረው ልዩነትና መከፋፈል ከፍተኛ ተጐጂ በመሆናቸው ቀደም ሲል በተደረገው የእርቅ ስምምነት መሠረት በሁለቱም በኩል የተላለፈው ውግዘት ትኩረት ተሰጥቶት እንዲነሳ እንዲደረግ፤
2. በአባቶች መካከል የተፈጠረው ችግር ሌላ 6ኛ ፖትርያርክ ከመመረጡ በፊት ጊዜ ተሰጥቶት ውይይት ተደርጐበት ወደ አንድነቱ እንዲመጣ፤
3. በታሪክ አጋጣሚ በጥቃቅን ክፍተቶች በውስጥና በውጭ ችግሮች የመጡባትን ፈተናዎች በጥንቃቄ አጥንቶ አስቦና ግንዛቤን አዳብሮ ውሳኔ ለመወሰን : የቤተክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ ራዕይ: ስትራቴጂካዊ እቅድና ፕላን የሚነድፍ አባቶችንና የቤተክርስቲያን ልጆች የሆኑ ምሁራንን ያቀፈ ሁሉን አቀፍ ጉባዔ እንዲደረግ፤
4. አባቶቻችን የፖለቲካውን ጉዳይ ለፖለቲከኞች ሰጥተው በሃይማኖት አንድነት ያሉትን ጥንካሬዎች ቅድሚያ በመስጠት አንድ መንጋ አንድ እረኛ የሚኮንበት ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲወሰን፤
5. ቤተ ክርስቲያናችን የምትመራበትን ሕገ ቤተክርስቲያን /ቃለ ዓዋዲን/ በውጪውም ዓለም ያለውን አስተዳደሯን የሚያማክል ይዘት እንዲኖረውና ለሁሉም ተደራሽ የሆነ አካሄድ እንዲኖረው እንዲደረግ፤ እንደዚሁም በየደረጃው ባሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅሮች ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን እንዲሰፍን የሚያደርግ አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል ሆኖ እንዲሻሻል እንዲደረግ ፤
6. በአስተዳደር ልዩነቱ ምክንያት ከተዋረዳዊ/ ሰንሰለታዊ የቤተ ክርስቲያን መዋቅር (Hierarchy) ወጥተው ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ወደ መዋቅሩ የሚገቡበት ሁኔታ እንዲመቻች ፤
7. በውጪው ዓለም ያሉ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ጉዳይ ላይ በደረጃቸውና ኑሯቸውን መሠረት ባደረገ መልኩ ተሳታፊ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲመቻች፤
በአጠቃላይ አባቶቻችን በሰውና በእግዚአብሔርም ፊት የሚከበሩበትን እርቀ ሰላምና አስተዳደራዊ አንድነትን በማምጣት አንድ ሃይማኖት፣ አንድ መንበር፣ አንድ ፖትርያርክ፣ አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ( ማለትም አንድ እረኛ አንድ መንጋ) እንዲኖረን የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርጉ በመስቀል ላይ ደሙን ባፈሰሰላት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አምላክ ስም እንማጸናለን።
በመጽሐፍ ቅዱስ “በገዛ ደሙ የዋጃትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቋት ዘንድ እናንተን ጳጳሳት አድረጎ ለሾመባት ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ( ሐዋ 20፡28)። እንዳለ፤ አባቶቻችን ጥንቃቄ የተሞላበት፤ የትኛውንም ወገን የማይጎዳ በተለይ መንጋውን አንድ የሚያደርግ እና የሚያስደስት፤ ታሪክ የሚዘክረው ትውልድ የሚወርሰው እርቀ ሰላምን በማድረግ የዘመናችን ሰማዕታት ትባሉልን ዘንድ በተማሕጽኖ እንጠይቃለን።
የአባቶቻችን አምላክ ቸሩ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነትን፤ ለሀገራችን ዕድገትና ብልጽግናን ያድልልን!
|
Posted: 30 Nov 2012 04:48 PM PST
አብዩ በለው (abiyuye@gmail.com)
ኮሎምቦስ/ኦሃዮ ኖቨምበር 29, 2012
ምክንያተ ጦማር
ከላይ በርዕሱ እንደተቀመጠው አዘውትሬ የምጎበኛት የቀደመችይቱ ደጀ-ሰላማችን “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ የት ነዎት?” በሚል ርዕስ በድጋሚ “እንደገና እንጠይቅ” በሚል ባስነበበችን አነስተኛ መጣጥፍ (የአፍልጉኝ ማስታወቂያ አይነት ነገር) ላይ የእኛን የአንባቢዎቿን “አስተያየት” እንድናካፍላት በተማፀነችው መሰረት ፣
እንዲሁም በደጀ ሰላም በኩል የተነሳው መጠይቅ በሌሎችም የዜና አውታሮችና የጡምራ መድረኮች በተደጋጋሚ ሲቀርብ በማየቴ እግረ መንገዴን ጉዳዩን እየተከታተሉ ለሚገኙ ወገኖቼ በሙሉ የእኔን የግል እይታ፣ ሃሳብና፣ እምነት ለማካፈል ወደድኩና ነው፡፡
መልካም ንባብ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ እና ....
፩ ፡- “….የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፍን አልከፈተም”
ፈጣሪያችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ማድረግ ሲችል አስቀድሞ በነብዩ በኢሳያስ “እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፍን አልከፈተም ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፍን አልከፈተም” ኢሳ. ፶፫፥፯-፰ ተብሎ እንደ ተነገረለት ዘመኑ ሲደርስ እርሱ ፍፁም ንፁህ ሳለ እንደ ክፉ ወንጀለኛና እንደ በዳይ በአለማዊው ዳኛ ፊት በፍርድ አደባባይ ቀርቦ “የሚከሱህን አትሰማም?” እየተባለ እርሱ ግን በከሳሾቹ ፊት አንዳች ቃል ሳይናገር መከራውንና አሳሩን ሁሉ ታግሶ በደሙና በሞቱ ነፃ እንዳወጣንና ቅድስት ቤተክርስቲያኑንም እንደ ዋጃት በተረዳ ነገር እናውቃለን፡፡
ዛሬም በዘመናችን ይህቺው አማናዊት ቅድስት ቤተክርስቲያ አስቀድሞ ከ37 ዓመታት በፊት በህወሃት/ኢህአዴግ በኩል “ሞት” እንደተፈረደባትና በዚህ የእኩዮች ውሳኔ ጦስ የቤተክርስቲያኒቱ መሪ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ከመንበራቸው በፖለቲካዊ ውሳኔና በሃይል መወገድና ለስደት መዳረግ እንዲሁም በምትካቸው ሟቹ አባት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ(ነብስ ይማር) እንዲሁ በተመሳሳይ ፖለቲካዊ ውሳኔ “በመንበረ ተክለሃይማኖት” መቀመጣቸው ዛሬ ላይ ሁነን ስንመዝነው “እውነትና ንጋት”ን በከንቱ ማነብነብ ይሆንብኛል፡፡ ምክንያቱስ ቢሉ አንጋፋዎቹ የፓርቲው መስራቾችና መሪዎች እነ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ ክንፈ ገ/መድህን(ነብስ ይማር)፣ ታምራት ላይኔና፣ እንዲሁም በቅርቡ ስብሃት ነጋ (አቦይ) በቃልም በመጣፍም በልበ ሙሉነት ገልጠውታልና ነው፡፡
ይልቁንም በማያውቁት በደልና ጥላቻ አስቀድሞ ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር በአንድነት የተፈረደባቸው እኒህ አረጋዊ አባት ለማያውቁትና ለአስጨናቂው ክፉው ስደት ሲዳረጉና በዚያ ሁሉ ግፍና መከራ ሲያልፉ እርሳቸውም እንደ ፈጣሪያቸው በኢህአዴጋዊያን ሸላቾች ፊት እንዲሁ “ዝም” ማለትን እንደመረጡ እናስተውላለን፡፡ ይህ “ዝምታ” እንደምንስ ያለ ክርስቶስን የመምሰል ድንቅ ህይወት? እንደምንስ ያለ መታደል ይሆን?
፪፡- ጲላጦስም “ይህን ያህል ሲከሱህ አንዳች አትመልስምን?”
ዛሬ እንዲህ እውነቱ ሊገለጥ በአለፍት 20 ዓመታት የብፁዕ አባታችን ስደት በተመልከተ ብዙዎች እጅግ ብዙ ብለንበታል፡፡ አንዳንዶቻችን ትንትናኔዎችን በመስጠት፣ ጥቂት የማንባልም አቋም በመያዝ እረጅም እርቀት ስንጓዝ ከርመናል፡፡ በዚህም ምክንያት የአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች ከሦስት ተከፍለን ግማሾቻችን ከአሳዳጆቹ ፣ ግማሾቻችን ከተሳዳጁ አባት፣ ቀሪዎቻችንም በቤተክርስቲያናችን የመከራ ዘመን ገለልተኞች ነን (ገለልተኝነቱ ምኑ ላይ እንደሆነ ባይከሰትልኝም) ከሚሉቱ ወገኖች ጎን ተሰልፈን በከንቱ ስንቅበዘበዝ መኖራችን ዛሬም መቋጫ ያላገኘ የክርስትናችንና የኢትዮጵያዊ አንድነታችን ፈተና መሆኑ በእጅጉ ይገርመኛል፡፡
ይለቁንም ይህ ኢህአዴጋዊ ድል ዛሬም ድረስ ተሻግሮ እነ አቦይ ስብሃትን በየመድረኩ በድል አድራጊነት ዳንኪራ ቢያስረግጣቸውም እኛ የአደራ ልጆቻቸው ሳንቀር ከከሳሾቻቸው ጀርባ አሸምቀን ብዙ እጅግም ብዙ ዘላብደናል፡፡ ጭራሽ ወደ ዓለም አደባባይ ወጥተው የየዜና ማሰራጫዎቻችን ግብዓት እንዲሆኑ ብዙ ለፍፈናል፡፡ ምን አልባትም ከሳሾቻቸውና አህዛብም ከሚወተውቱት በላይ እኛ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች በቁንፅል ዘመናዊነታችን “እውነቱን ለአህዛብ ይናገሩ” እያልን ዘብዝበናቸዋል፡፡ እርሳቸው ግን መሪያቸው እርሱ እውነተኛው መንፈስ ቅዱስ ነበርና የመረጣቸው እርሱ ክርስቶስ በጲላጦስ አንደበት “ይህን ያህል ሲከሱህ አንዳች አትመልስምን?” ብሎ እንደገና ጠየቀው ጌታችን ኢየሱስ ግን ጲላጦስ እስኪደንቀው ድረስ አንዳች አልመልሰም” ማር. ፲፭፥፬-፮ እንደተባለለት እንዲሁ ዛሬ ዓለም ይልቁንም የተገላቢጦሽ እኛ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች እስኪደንቀን ድረስ አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ለ21 ዓመታት በከሳሾቻቸውና በእኛ በልጆቻቸው ፊት ለዓለሙ የወሬ መሸቀጪያ መድረክ አንዳች ሳይሉ ሁላችንም እዚህ ደርሰናል፡፡
፫፡- “አቤቱ ለአፌ ጠባቂ፣ ለከንፈሮቼም ፅኑዕ መዝጊያ አኑር”
ልበ ዐምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “አቤቱ ለአፌ ጠባቂ፣ ለከንፈሮቼም ፅኑዕ መዝጊያ አኑር” መዝ ፵፥፫ እያለ እንደፀለየው ሁሉ በዚህ ሁሉ መተራመስና ውዥንብር መካከል የቅዱስ አባታችን አቋምና ምላሽ ግን ፍንትው ያለ፤ ለአለፍት ረዥም የመከራ ዓመታት በብቸኝነትና በፅናት የዘለቀ አንድና አንድ ነበር፡፡ይኃውም በሰው ዘንድ የማይቻል የሚመስል ቅዱስ ዳዊት እንዳለው ለከነፈሮቹ ጠባቂ መላዕክት ለተኖሩለት ግን እንደሚቻል ያረጋገጠ ፍፁም ዝምታ፡፡ ዝም! ጭጭ!
ይህ አባታዊ “ዝምታ” ደግሞ እጅግ የሚገርም ነው፡፡ አብዛኞቻችን የቤተክርስቲያናችንና የሃገራችን ጉዳይና የወደፊት እጣ ፋንታ የሚገደን ወገኖች በቅርበት እንደምንከታተለው ከሆነ ቅዱስ አባታችን እንኳንስ በአለማዊው የመካሰሻ መድረክና የዜና አውታሮች ይቅርና በእርሳቸው ስም በስደት የተሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያደርጋቸው ጉባኤዎች ላይ እንኳ በእጅጉ ዝምታን የሚያበዙና በተለይም አሳዳጆቻቸውን በተመለከተ በሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት የከሳሽነት ቃል ተናግረው እንደማያውቁ ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡
ይሁንና ይህ አስቀድሞ ጲላጦስን እንደ አስደነቀ ያለ የ“ደጀ ሰላም”ንም ሰላም የነሳ ፍፁም ዝምታ! ከቶ ከወዴት ይገኛል? እንደ ቅዱሱ ንጉስ ዳዊት “አቤቱ ለአፌ ጠባቂ፣ ለከንፈሮቼም ፅኑዕ መዝጊያ አኑር” እያለ አብዝቶ ለተማፀነና ከላይ “እኔንም ምሰሉኝ” ካለው ከዝምታ ባለቤት ከእርሱ ከክርስቶስ ዘንደ ለተሰጠው እንጂ ለሌላ ከቶ ለማን ይቻለዋል?
“ደጀ ሰላም”ና ጥያቄዋ
ደጀ ሰላም ማን ናት? በሚለው ክፍሏ ላይ ባሰፈረችው መነሻነት መድረኳ በቤተክርስቲያናችን ጉዳይ ላይ የሚነሱትን የህዝበ-ክርስቲያኑን የተለያዩ ጥያቄዎች ይዛ መውጣቷና ለነዚህም ምላሽ ማፈላለጓ የተሰለፈችለት አላማዋ በመሆኑ የሚመሰገን ተግባር እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ በዚህም መነሻነት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስን አባታዊ ቃል ለማስተናገድ መንቃሳቀሷ በተለይም መድረኳ“የምትሰራውን እስካወቀች ድረስ” ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ ነገርግን ሁኔታዎች ሁሉ ከ“እንቁላል”ም በላይ “እንቁላል” በሆኑበት በአሁኑ ሰአት ይህን “ጥያቄ” “እንደገና እንጠይቅ” በሚል በድተደጋጋሚ መወትወቷ ምነው ይህ ነገር አለበዛም? መካሪስ የለንም?( ኃሳብ መጠየቁ እንዳለ ሆኖ) እንድል አስገድዶኛል፡፡ ለምን ቢሉ ነገርዬው፡-
፩ኛ. የተቀደሰውን ሁሉ ለ“ዕርያዎች” ቢሆንብኝ
ለእኔ እንደ አንድ ክርስቲያን እጅግ እያሳቅቀኝና ዘወትር ከሚያሳስቡኝ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ነገር ቢኖር የቤተክርስቲያናችንን ችግሮች ለመፍታት የምንከተለው መንገድ ነው፡፡ ይልቁንም ዓለማዊውን የፍትህ ተቋማትና የዜና አውታሮች የሙጥኝ የማለታችን ነገር፡፡
ፈጣሪያችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በህያው ቃሉ “ዓለምን አትውደዷት” በማለት እንድንለያትና ለክርስትናችን የሚበጅ አንዳች መልካም ነገር እንደማናገኝባት፤ ይባስ ብላ ቅዱሳኑን እንደምታሳድድና በስሙም ለተጠራነው ሁሉ ሰይፍና ሾተልን እንደምታዘጋጅ እንደ ተመሰከረላት፤ ይልቁንም በነገሯ ሁሉ እንዳንተባበራት እንደ ታዘዝንባት እናውቃለን፡፡
ነገር ግን እኛ በተለይም የዛሬዎቹ ከዚች እኩይ ዓለም ዘንድ ለሃይማኖታዊ ችግሮቻችን “መፍትሔ” ፍለጋ ወደ መፍረጃ አደባባዮቿ እየወጣን እርስ በእርሳችን የምንካሰሰውና የሙግት ስይጥንናችን በአህዛብ ሁሉ መንደር እንዲናኝ ብሎም “ክርስትናችን” በእነርሱ ዘንድ “እንዲመሰከርልን” ለዚህም የዓለምን ወሬ-ነጋሪዎችን ቀልብ ለመሳብ የምናደርገው ፍትጊያ እንዲሁም በዚህ ሁሉ ጥቃቅን መስመሮች መካከል ዘወትር ለእርያዎች የምናዝረከርከው የቤታችን ገመና የትየለሌ ነው፡፡ ይህንም ስጋቴን አብዛኛው ህዝበ ክርስቲያን እንደሚካፈለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ደጀ ሰላምንም ጨምሮ ማለቴ ነው፡፡ በዚህም ላይ መድረኳንም የሚያዘገጁ ወንድሞች ብዙ ተመራምረው በግሩም ሁኔታ ለእኛም እያስተማሩን እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ታዲያ የቀደመችይቱ ውዷ ደጀ ሰላም ምነው ይህን ከንቱ መንገድ የሙጥኝ አለች? ሁሉም ነገር ወደ … ሆነሳ?
፪ኛ. ጲላጦስ ጲላጦስን ቢሸተኝ
ቅዱስ አባታችን የደረሰባቸውን ግፍና መከራ ይልቁንም በእርጅና ዘመናቸው የሚጎነጩትን መራራውን የስደት ኑሮ ታግሰው በከሳሾቻቸው ፊት እንደ አምላካቸው ፍፁም ዝምታን በመረጡና በተለይ ይህን ለሰሚው እንኳ ግራ የሚያጋባ የቤታችንን ጉድ ለዓለምና የዜና አውታሮቿ ባለመሸቀጣቸው በእኛዋ “ደጀ ሰላም” ዘንድ እንደ “መደበቅ”ና “መጥፋት” ተቆጥሮ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ የት ነዎት?” “ለምን ድምፅዎትን አንሰማም?” “ሀሳብዎን ለምን አይገልፁም?” “ከምዕመኖችዎ ጋር በትርጁማን፣ በስማ በለው፣ በተላላኪ፣ በሦስተኛ ወገን መነጋገር መቼ ነው የሚያበቃው?ለማለት እንወዳለን”… ወዘተ እየተባለ መዘብዘቡ እጅግ አሳፍሮኛል፡፡ ገርሞኛልም፡፡ ኢ-ክርስቲያናዊም እንደሆነም ይሰማኛል፡፡
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነውና መድረኳን ትዝብት ላይ የሚጥለው ጭብጥ ደግሞ ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ ለዘመተባቸው ለዓለማዊው የዜና አውታርና ጋዜጠኞች ያላሰለሰ ውትወታና ወከባ ሳይበገሩ በመንፈስ ቅዱስ ጥበቃና መሪነት (በግሌ እንዲህ አይነት ማስተዋልና ፅናት ከመንፈስ ቅዱስ ብቻ የሚገኝ እንደሆነ ስለማምን) ቤተክርስቲያናችን የምትጠብቅባቸውን ወቅታዊ አባታዊ ምላሻቸውንና አቋማቸውን ማግኘት ለሚገባቸው የቤተክርስቲያኒቱ አካላት በተለይም ሃገር ቤት ለሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስና ለዐቃቤ መንበሩ ለብፁዕ አቡነ ናትናኤል በትክክለኛው ወቅትና ጊዜ ግልፅ ደብዳቤ እንደፃፉና በስልክም ተገናኝተው መወያየታቸው እየታወቀ ይህንንም ዜና እራሷ ደጀ ሰላም፡-
፩ኛ. በጥቅምት 5/2005 ዓ.ም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስን ምስል በማስደገፍ “ዐቃቤ መንበሩ ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋር የስልክ ውይይት አደረጉ” (ሰረዝ የተጨመረ) እንዲሁም፣
፪ኛ. በድጋሚ ጥቅምት 15/2005 ዓ.ም “የዕርቀ ሰላሙ ውይይት በመጪው ህዳር ወር ይቀጥላል” በሚለው ርዕስ 2ኛ አንቀፅ፣ 5ኛ መስመር ላይ “ እርቀ ሰላሙ ከተፈፀመ ዘንድ አራተኛው ፓትርያሪክ ወደ መንበረ ፕትርክናው ተመልሰው እንዲቀመጡ የመሻት አቋም በደብዳቤ ጭምር በተገለፀበት አኳኃን” (ሰረዝ የተጨመረ) በማለት መዘገቧ እርግጥ ነው፡፡
ከዚህም እውነታ በመነሳት ደጀ ሰላማችን ቅዱስ አባታችን እየተጓዙበት ያለውን ድንቅ ክርስቲያናዊ አካሄድ እንደ ማበረታታትና እርሷ አብዝታ ከምታውቀው ከዓለማዊው የሚዲያ ወከባ ለመታደግ እንደመትጋት የባስ ብሎ ከባዕታቸው ለማስወጣት በሚመስልና ወደ አደባባይ ጎትቶ ለጥንተ ጠላታችንና ለታወቀው ከሳሻችን የመክሰሻና የመዘባበቻ አጀንዳ ለማቀበል እንዲህ በጲላጦሳዊ ግብር አብዝቶ መዘብዘብና መነትረክ ምን ይሉታል? ምንኛስ መውረድ እንዴትስ ያለ አለማስተዋል ይሆን?
ማጠቃለያ
እንግዲህ የህይዎታችን እራስ የሆነውን ጌታችንና መድሃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በቀራኒዮ አደባባይ አሻግረን እያየን፤ ለእኛ ሲል የሆነውን ሁሉ ዘወትር እያሰብን፤ በመዋለ ስብከቱ ያስተላለፈልንን የህይወት ቃል ጠብቀን በሥርዓትና በአግባቡ የቅድስት አማናዊት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮትና ሥርዓት አክብረን በመከተል ይህቺን አጭሯን ምድራዊ ዘመናችንን መልካም ፍሬ በማፍራት ሁላችንም በድል አድራጊነት እንድንወጣት እመኛለሁ፡፡ ለዚህም ይረዳን ዘንድ
፩ኛ. መልካም ለሆነው ክርስቲያናዊ ተጋድሎ አጋዥ ይሆኑ ዘንድ በቅንና ደጋግ ወገኖች መልካም ፈቃድ የተዘጋጁት “ደጀ ሰላም”ና መሰል መድረኮች፣
፪ኛ. የቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ “ከምር” ያገባናል በማለት “በእውነት” የአቅማችሁን በጎ ድርሻ ለማበርከት በየፊናችሁ በቡርቱ እየደከማችሁ የምትገኙ ግለሰቦችም ሆናችሁ ተቋማት፣
፫ኛ. በአጠቃላይ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች ሁሉ ፣
ታላቋ የኢ/ኦ/ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን በዚህ በእኛ ዘመን የገጠማትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች እንደ ቀደሙት ትውልዶች ሁሉ በአሸናፊነትና ዳግም በድል አድራጊነት እንድትወጣና ብሎም ዘመኑ የሚጠይቀውን ሐዋርያዊ አገልግሎቷን በላቀ ትጋትና ጥራት እንድታከናውን ይረዳት ዘንድ ፡-
- ውስጣዊ ችግሮቿን ሁሉ በአግባቡና በሥርዓት የምትፈታበት ብቃትና ጥራት ያለው የዘመናዊ ተቃማዊ አሰራር ባለቤት እንድትሆን በማሰቻል፣
- ከውጭ የከበቧትን፣ በውስጥ የገጠሟትን፣ ወደፊትም በቋፍ የሚጠብቋትን ውጫዊወቹን እንደ ዘመናዊው የሉላዊነትና የሉላዊነት ውልድ የሆኑትን እነ “ሊበራል-ክርስትና”ን የመሳሰሉትን ባላንጣዎች መመከት የሚያስችል ዘመኑን የዋጀ “ጦርና ጋሻ” በማስታጠቅ፣
- ከሁሉም በላይ ለመጪው ትውልድ የምትመጥንና የተሰጣትን አምላካዊ አደራዋን በአግባቡ እንድትወጣ ሊያግዛት ወደሚያስችል ዘመን ተሻጋሪ አቅጣጫና ምዕራፍ በመምራት፣
- እንዲሁም በሁሉም መስክ ሁላችንም በአለን አቅም ሁሉ ቤተክርስቲያናችንን ለመደገፍና የየድርሻችንን ለመወጣት እንድንችል በሚያስችል መልኩ በማደራጀት ፣
በአጠቃላይ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ወደ አንድና ወጥ አቅጣጫ ለመጓዝ የሚያስችል እቅድና እስትራቴጂ በአፋጣኝ “ይወለድ” ዘንድ ሁላችሁም በተሰጣችሁ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ተደግፋችሁ ታምጡ ዘንድ እማፀናለሁ፡፡ በተለይም ለዚህና ለተመሳሳይ አላማ አስቀድማችሁ የተሰለፋችሁ የተደራጃችሁ የቤተክርስቲያኒቱ ባለድርሻዎች ሁሉ ቅድሚያውን ትወስዱ ዘንድ የከበረ ጥሪዬ በያላችሁበት ይድረሳችሁ፡፡
በመጨረሻ
በመጨረሻም ውድ ደጀ ሰላሞች! ከዚህ ቀደም ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል ክብረት “ማህበረ ቅዱሳን”ና “አመራሩን” በሚመለከት ያቀረበውን ዝርዝር መጣጥፍ “ለቤተክርስቲያናችን አንድነትና ለማህበሩ እድገት አይበጅም” በሚል ከመድረካቹሁ እንዳነሳችሁት ሁሉ ይህን ስለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ያወጣችሁትን ጲላጦሳዊ ተንኳሽ /Provocative/ የአፍልጉኝ ማስታወቂያ ከመድረካችሁ ታወርዱ ዘንድ እንዲሁም ለዚህ ግድፈት የእርምት እርምጃ መውሰዳችሁን በክርስቲያናዊ አግባብ ለአንባቢዎቻችሁ ታሳውቁን ዘንድ በእግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ፡፡
ለብፁዕ አባታችን ትዕግስቱንና ፅናቱን የሰጠ ቅዱስ እግዚአብሔር ለእኛ ለደካማዎቹ በየጎዳናው በመካሰስና በመወነጃጀል ለምንባዝነው ሁሉ ማስተዋሉን ያድለን ዘንድ ፀልዩ፡፡
ወስብሃት ለእግዚአብሔ
|
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar