ህወሀት ከመነሻው ሲመሰረት አላማ አድርጎ የተነሳው የኢትዮጵያን ህዝብ ማንበርከክን፣ ማዋረድን እና የትግራይን የበላይነት ማረጋገጥን ነው።
የትምወርቅ አበበ
በእርግጥ ኢትዮጵያ የጋራችን ናት? ሀያ አንድ ዓመት ቀላል ዕድሜ አይደለም። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ በለየለት የጭቆና ፣የአፈና ፣ የአድሎና የግፍ አገዛዝ ውስጥ ለወደቀ እያንዳንዷ ቀን እንደ መርግ የከበደ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም። ህወሀት ከመነሻው ሲመሰረት አላማ አድርጎ የተነሳው የኢትዮጵያን ህዝብ ማንበርከክን፣ ማዋረድን እና የትግራይን የበላይነት ማረጋገጥን እንደነበር ዛሬ ለአደባባይ እይታ የበቁት ሰነዶች ምስክሮች ናችው። የነዚህ ሰነዶች ዋነኛ ሐሳብም በእያንዳንዱ የህወሀት አባል አዕምሮ ውስጥ ተኮትኩቶና አድጎ በግልጽ ወደ ተግባር መተረጎም ከጀመረ አመታት መቆጠራችው ግልጽ ሆኗል። የወያኔ የትግል እንቅስቃሴ የተጀመረው በ 1966ቱ ህዝባዊ ንቅናቄ ማግስት መሆኑን በእርግጥም የተመለከተ የወያኔ አላማ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር መውጋት ፣ ማጥቃትና ማጥፋት እንጅ የጭቆና ስርዐትን መታገል እንዳልነበር በቀላሉ መረዳት ይችላል። ምክንያቱም የ1966ቱ ህዝባዊ አብዬት ዘውዳዊውን ስርዐት አስወግዶ ፣ መሬት ለአራሹን አውጆ ይበል የሚያሰኝ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ነበር። በእርግጥም የህወሀት መስራች አባላት በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዐተን ለመመስረትና ብሔራዊ ጭቆናን ለማስወገድ አላማ ከነበራቸው የዚህ ትግል አካል ለመሆን መሞከር ይችሉ ነበር ። ምናልባትም ይህ ህዝባዊ አብዮት የተነሳበትን ዓላማ እንዳይስት ከፍተኛ ድርሻም ሊኖራቸው ይችል ነበር ብሎ ማሰብም የዋህ አያሰኝም። ይህም ሆኖ የህወሀት የትግል እንቅስቃሴ የተጀመረው ብሄራዊ ጭቆናን ለማስወገድ ፣ በሀገሪቱ ውስጥ የፍትህ የበላይነት ለማረጋገጥ ፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዐትን ለመመስረት አይደለም የሚሉ ወገኖች የሚያቀርቡት ዋንኛ መከራከሪያ ደርግ ስልጣን ይዞ በተረጋጋ ሁኔታ ሀገሪቱን መምራት እንዲችል እድል ሳይሰጠው ርዕዮተ ዓለሙ ሳይታወቅ ፣ የስርዐቱ እምነት እና የፍልስፍና ፈለግ በወጉ ሳይለይ ነው ወያኔ ጦር ያነሳው ይላሉ። ይህ ደግሞ ህወሀት ጠቡ ኢትዮጵያ ከምትባል ሀገር ጋር መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ዕውነት ነው። በእርግጥም ህወሀትም ቢሆን ይህን ከመነሻው አልካደም። እስከዛሬ ድረስ ያልተቀየረው ስሙም ቢሆን የሚያመለክተው የትግራይ ነፃ አውጭ ጦር መሆኑን ነው። ሙት መውቀስ ሆነ እንጂ ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የምትባል አገርን በጠንካራ ክንዳቸው ደቁሰው ለ 21 ዓመት ሲገዙ ፣ አንድም ቀን ቢሆን የሳቸው ዋና ጉዳይ የትግራይ የበላይነትን ማረጋገጥ መሆኑን ዘንግተው አያውቁም። ለዚህም በየደረጃው የሚሾሟቸውን ባለስልጣናት ዝርዝር መመልከት በቂ ነው። በእርግጥም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠመንጃ ላነሱላት ትግራይ የፖለቲካ የበላይነት ብቻ በቂ ነው የሚል የዋህነትም አልነበራቸውም። የኢኮኖሚ የበላይነት በሌለበት የፖለቲካውን መዘውር መጨበጥ ዘላቂነት እንደሌለው ለመገንዘብም ለአንድ ቀን እንኳን አልዘገዩም። በመሆኑም ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር እየገዙ ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ግብር እያስገበሩ ፣ የሀብት ክፍፍሉን ሚዛን ወደ ህወሀት አባላትና …. ደጋፊዎች እንዲያዘነብል በማድረግ ያሰቡትን አሳክተዋል። ስለዚህም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሀብት ክፍፍል ወደ አንድ ወገን ያዘነበለ መሆኑን ለማወቅ ጥናትና ምርምር ማድረግ ከንቱ ድካም ሆኗል። ምክንያቱም ዛሬ ላይ ሚስጥር መሆኑ ቀርቶ እውነቱ ፍንትው ብሎ ከሚታይበት ደረጃ ላይ ተደርሧል። ባለፉት ሀያ አመታት ይህ ነው የሚባል ስራ መስራታቸው የማይታወቅ ፣ ነገዱ እንዳይባል በነጋዴነት ንግድ ፍቃድ እንኳን የሌላቸው ፣ በሀገሪቱ የግብር ከፋይነት መዝገብ ውስጥ ስማቸው ተፈልጎ የማይገኝ ባለሚሊዮኖች ቁጥር በወያኔ ሰፈር የትየለሌ ደርሧል። ግለሰቦች ነግደው ሲያተርፉና ሀብት ሲያፈሩ ኢኮኖሚ ያድጋል፣ የስራ ዕድል ይፈጠራል፤ ዜጎችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዚህ ዕድገት ትሩፋት ተጋሪ ይሆናሉ፣ ሀገርም ያድጋል። ስለዚህ ባለሚሊዮኖች ሲበዙ እልልታችን ካልተሰማ የሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ሚስጥር ተሰውሮብናል ማለት ነው። ነገር ግን ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ ሲከብሩ ፣ ህግ አክብሮ የሚሰራውን ሀገሬ ከገበያ ሲያስወጡ ፣ ፍትህ በጎደለው መንገድ የውድድር ሜዳውን ሲቆጣጠሩ “ለምን?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። በተለይ ደግሞ ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር ኢትዮጵያ የምትባል ከ ሰማንያ በላይ ብሄር ብሄረሰቦችን የያዘች ሀገርን እየመሩ “እንኳን ከእናንተ ተፈጠርን ፣ ጀግኖች ናችሁ…..’’ እያሉ ሌላውን ህዝብ ምርኮኛ ፣ የእሳቸውን ወገን ጀግና አድርገው በአደባባይ ሲናገሩ ለማድመጥ የሚገደድ ህዝብ ፣ ገንዘብ ፣ ሀብት፣ ፀጋ ፣ ሁሉ ወደ ህወሀት ያመራሉ ቢል አይፈረድበትም። ምክንያቱም፣ እውነቱም ይኼው ነው። ለነገሩ ዛሬ የመንግስት ሀብት ሙሉ በሙሉ በህወሀት ቁጥጥር ስር መሆኑን ለመገንዘብ ቀላል ነው። (እዚህ ላይ እውቁን አርቲስት ታማኝ በየነን ለጥልቅ ተመልካችነቱ ፣ እውነትን ፍለጋ ለሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት ማመስገን ተገቢ ነው።) ቁልፍ ቁልፍ መንግስታዊ የፋይናንስ ተቋማትን እና የልማት ድርጅቶችን የሚመራቸው ማነው? ብለን ብንጠይቅ መልሱን ቁልጭ ብሎ እናገኘዋለን። ዋና ስራ አስኪያጅ በአጋጣሚ ባይሳካ ምክትሉ በእርግጠኝነት ከህወሀት ወገን መሆኑ ጥርጥር የለውም። ለነገሩ ከዋና ስራ አስኪያጅ በላይ የቦርድ ሰብሳቢም ከህውሀት የሰው ሀይል አስተዳደር መመደቡ ግድ ነው። በጥቅሉ፣ ከላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ፣ ዝቅ ሲል ሚንስትሮች ፣ ሲወርድ ዳይሬክተሮች ፣ ዋና ስራ አስኪያጆች ፣ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጆች በተደራጀ መንገድ የመንግስትን ሀብት ህወሀት እንዳሻው እንዲጠቀምበት ፣ እንዲያዝበት ፣ የወደደውን እንዲጠቅምበት ፣ የጠላውን እንዲመታበት ያለመታከት ይሰራሉ። ስለዚህ የመንግስት ሀብት የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑ ቀርቶ የአንድ ድርጅት ሀብት ሆኗል ማለት ይቻላል።
ህወሀት ግን በዚህ ብቻ የሚበቃው ሆኖ አልተገኘም። የራሱን የንግድ ድርጅት ኤፈርትን አቋቁሞ የሀገሪቱን የንግድ ስርአት እያዛባ ፣ የግል ባለሀብቱን በተደራጀ የፋይናንስ አቅሙ እያዳከመና ከገበያ እያስወጣ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት እያካበተ ይገኛል። ህወሀት በዚህ ተግባሩ እጅግ በጣም ስለሚኮራ የትግራይን የበላይነት ለማስፈን ያደረገው ትግል ፍሬ ማፍራቱን በአደባባይ ከመናገር ወደ ኋላ ያለበት ቀን የለም። በዚህም ከወያኔ ጎራ ያልወገነውን ኢትዮጵያዊ የበይ ተመልካች በማድረግ ዕንቁልልጨ ይጫወትበታል። እንዲያውም ሰሞኑን “ነፍሳቸውን ይማረውና” ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር የትግራይን የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ዕቅድ ሲፅፉ መክረማቸውን ጓዶቻቸው ይፋ አድርገውልናል። የሳቸውን ዕቅድ ለማሳካትም ኤፈርት ያለ እንቅልፍ እንደሚሰራ ሰምተናል።
‘የኢትዮጵያው’ ጠቅላይ ሚኒስትር ጊዜ ተርፏቸው እነሱ እንደሚሉት “በፌዴራላዊ የመንግስት አስተዳደር ስርዐት” በምትመራ ሀገር ውስጥ የአንድን ክልል የረጅም አመት የኢኮኖሚ ስትራተጂ ሲፅፉ፣ ሲቀርፁ እንደኖሩ እንድንሰማ የተደረገው “ምን ታመጣላችሁ? ተቃጠሉ ፣ እርር ድብን በሉ” ለማለት መሆኑንም እንገነዘባለን። ስለዚህ በፌደራል ስርዐት አወቃቀር በአንድ ክልል አስተዳደር ውስጥ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጣልቃ እየገቡ ነው ብሎ መጮህ ምንዱባን ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ከቅንጦት ነው የሚቆጠረው። የሚንስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ፣ የሀገሪቱ የበላይ ፈላጭ ቆራጭ መሪ የትግራይን የኢኮኖሚ ስትራተጂ ቁጭ ብለው ከፃፉ የበጀት ድልድሉ ፣ የልማት ዕቅዱ እንዴት ያለ አድሎ ፣ በነፃ ህሊና ፤ አሳማኝ በሆነ መርህ ይከናወናል? ብሎ መጠየቅ መቸም ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ እንደሚሉት ነው። ልብ በሉ፣ ኤፈርት በሀገሪቱ ውስጥ ከመንግስት ቀጥሎ ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅስ ድርጅት መሆኑንም ሳንጠይቃቸው ነግረውናል። መቸም የስብሀት ነጋን ማንነት ለምናውቅ አላማው ግልፅ ነው። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ሀብት በህወሀት ቁጥጥር ስር መሆኑን፣ ከመንግስት ቀጥሎ ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅሰው ኤፈርት ደግሞ የህወሀት አንጡራ ሃብት መሆኑን ፣ ባለፉት ሃያ አመታት የንግዱን ዘርፍ የህወሀት ሰዎች ምንጩ ባልታወቀ ሀብት መቆጣጠራቸውን ስንመለከት ሀገሪቱ ምን ቀራት? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። በእርግጥ ኢትዮጵያ የጋራችን ናት? የሚለው ጥያቄም መልስ ማግኘት አለበት። በእርግጥ መጠየቅ ብቻውን ብዙም ፋይዳ አለው ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ምክንያቱም ፣ በሙት መንፈሳቸው ዛሬም ሃገሪቷን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር የተጫናቸውን አፈር አራግፈው፣ ከአንገታችው ቀና ብለው “ውሾች ይጮሀሉ፣ ግመሎች ይሄዳሉ” የሚል ምላሽ ይሰጡናል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar