ከእሥር ቤት የተላከ መልእክት ዳግማዊ ጉዱ ካሣ – አዲስ አበባ
እናንተ እምታዩኝ እኔ እማላያችሁ፣
ከወያኔ እሥር ቤት ነጻ የወጣችሁ፣
በያላችሁበት እንደምን አላችሁ፡፡
ውድ አንባቢያን! የነገር ሱስ ያለበት ሰው አርፎ መቀመጥም ሆነ መተኛት ያስቸግረዋልና፣ ምንም እንኳን በዘመናችን የዓለም ታላቋ እሥር ቤት በሆነችው በኢትዮጵያ እምብርት በአዲስ አበባ ከወገኖቼ ጋር የትግራይ መኳንንንት በራሳችን መሃንዲሶችና በራሳችን ወጪ ከቻይና በሚቸራቸው ያልተቆጠበ እገዛ ጭምር ባስገነቡት ሰፊ እሥር ቤት ውስጥ ተጠፍንጌ ብገኝም በሆነ መንገድ ብትደርሳችሁ ከሚል ቅን አስተሳሰብ በመነሳት ይህችን አጭር የብሶት መልእክት ልኬላችኋለሁ፡፡ አንብቡ – ከማንበብ ይቀራል እንዲሉ፡፡
ዘወትር የሚጨቃጨቁ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ ባል ሆዬ በሚስት ንዝንዝ ይመረውና በግላጭ አሥሮ ሊገርፋት የቤታቸውን በርና ጭላንጭል መግቢያ ሁሉ መዝጋት ይጀምራል – “ቆይማ፣ ዛሬ አንቺን ል..ክ ካላስገባሁ ወንድ አይደለሁም፤ ተናንቀናል፤ እኔ ነኝ ወይንስ አንቺ አባውራ በዚህ ቤት? አ.ላ..በዛሽ.ው..ም?” እያለ በማጉተምተም ነው ታዲያን ያን ገላጋይ ገብቶ ጠብ እንዳያበርድ የሚገታ ተግባር የሚያከናውን ያለ፡፡ ሚስቲትም እግገኑ መሃል ላይ ቆማ ባልዬው በንዴት እየፎገላ የሚያደርገውን በአግራሞት ትታዘባለች፡፡ አለችውም “ ተው እባክህን፣ ቤቱን እንዲህ ጥርቅም አድርገህ አትዝጋው፤ ግዴለህም ገላጋይ መግባቱ ከሁለት ለአንድኛችን ሊጠቅመን ይችላል፡፡…” እሱም ይላታል “ኧረ የታ..ባሽንስና! አንቺን ቀጥቅጦ ዶሮ ጠባቂ ማድረግ ነው እንጂ የምን መታገስ ነው ከእንግዲህ! ትግስቴ አለቀ፤ በቃ፤ እላዬ ላይ እኮ ነው ጥሬ እንትንሽን እያስቀመጥሽብኝ ያለሽው” እያለ አንዲትም ጮራ ማስገቢያ’ንኳ ሳይተው ሁሉንም የቤቱን ቀዳዳ ወታትፎ ይዘጋል – ገላጋይ ቀርቶ ሲደበድባት የሚታዘቡ እማኞችም እንዳይኖሩ ለማድረግ በሚመስል ሁኔታ፡፡
ድብድቡ ተጀመረ፡፡ ባል የያዘውን ቆመጥ አንዴም ሳይሰነዝር ሚስቱ ትቀማውና ያንን ጥላ በርግጫና በጡጫ ታጣድፈው ያዘች፤ አጋድማም እሆዱ ላይ በመቀመጥ ትጎደፍረው ጀመር፡፡ ባል አፍ ብቻ ሆኖ ቀረው፡፡ ያኔ ጩኸቱን ያቀልጠው ገባ፤ ጎረቤትም ገብቶ እንዳይገላግል ቤቱ ስለተዘጋጋ ምርጫ በማጣት የቤቱን ዙሪያ ከብቦ መጨረሻውን ለማየት ይጠባበቅ ይዟል፡፡ በማከያው ባልዬው ‹ኧረ ተጋደልን! ድረሱልን!› እያለ ቀድሞ ራሱ የዘጋውን ቤት በኃይል በርግደው እንዲገቡና እንዲገላግሉት የውጪዎቹን መለመን ያዘ፡፡ ጩኸት ሰምተው የመጡና በቤቱ ታዛ ሆነው ‹እባካችሁን ምን ነካችሁ ወይ በራሳችሁ ተገላገሉ አልያም ክፈቱልንና እናገላግላችሁ› ሲሉ የነበሩ ጎረቤቶች የባልዮውን ተማጽኖ ሲሰሙ እልህ ገባቸውና ‹ለይና ንገረን!› ብለው ድርቅ አሉ፡፡ ባልዬውም ሲብስበት ‹ኧረ ገደለችኝ – ድረሱልኝ› ሲላቸው መሸጎሪያውን እንደምንም አውልቀው ገቡ፡፡ ሴትዬዋ ግን ብልህ ነበረችና የባሏ ‹ወንድነት› ጥያቄ ውስጥ ገብቶ የቡና ማጣጫ እንዳይሆንባት ከባህል አኳያ በመሥጋት ገላጋዮቹ ከመግባታቸው አስቀድማ ከላይ ሆና በቡጢና በክርን ስትለሸልሸው እንዳልነበር ከመቅጽበት ወደሥር ትገለበጥና ሰዎቹ ሲገቡ ባል ከላይ ሆኖ በተራው ሲነርታት ይደርሳሉ፡፡ ያኔ ገላጋዮች በሁኔታው ግራ በመጋባት ‹እንዴ አቶ እገሌ፣ ይተዋት እንጂ፣ የዛሬን ይማሯት እበካዎን፤ ሴት ልጅ እንዲህ አትመታም› ቢሏቸው ጊዜ ‹ ተውኝ እባካችሁን አዲስ ግልብጥ ናት!› ብሎ አሳ(ቀ)ቃቸው ይባላል፡፡
ይህን ታሪክ ያመጣሁት አለነገር እንዳልሆነ መቼም ይገባችኋል፡፡ ወያኔ በአሁኑ ወቅት ያልጠረቃቀመብን በርና መስኮት የለም፡፡ ሁሉም የመተንፈሻ መንገድ ተዘግቷል፡፡ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እጅግ በሚገርም ሁኔታ በለዬለት ሕዝባዊ እሥር ቤት ውስጥ እንገኛለን፡፡ መጨረሻውን ያሳምርልን እንጂ እንደአያያዛችን ከሆነ ወያኔዎች፣ ለምርምር ወደኅዋ እንደሚላኩ ዐይጦችና ዝንጀሮዎች የላብራተሪ እንስሳና ዕቃ አድርገውናል፡፡ የሥልጣን መልቀቂያቸው ወቅት እየደረሰ መምጣቱን አንዳች ነገር ሹክ እያላቸው ይመስለኛል አሁን አሁንማ የለዬላቸው ጨቡዴዎች እየሆኑ ነው፡፡ አናታቸው ከተመታ ወዲህ በተለይ የወለደች ውሻ ሆነዋል፡፡ ሥልጣንና ጥቅም እንዲህና እስከዚህ ያራዣል ማለት ነው? እንዴ፣ አበዱ እኮ፡፡
ዜጎች በርሀብና በርዛት እያለቁ ባሉበት ሁኔታ በሙስናና በዝርፊያ ከመነመነ የሀገር ካዝና ብዙ ገንዘብ ወጪ ሆኖ ኢሣትን ካዘጉ ሰነበቱ፤ ኢንተርኔትን ከዘጉም በጣም ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን በፕሮክሲዎች እየገባን ስለሀገራችን አንዳንድ ዜናዎችን እንቃርም ነበር – ያንንም ሰሞኑን አጠናክረው ጨርሶውን ዘግተውታል፡፡ ወደየትም ሂድ ከኢቲቪና ሬዲዮ በስተቀር ሌላ አማራጭ እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ ይሄ ነገር ወዴት እያመራ ነው ሲባል መልሱ አንድም ወደነጻነት ነው አለበለዚያም ወደለዬለት ጥንታዊ የባርነት ዘመን ነው፡፡ የትግራይ መኳንንት እስከዚህን ርቀት ሄደዋል፡፡ በአባታቸው አነጋገር ‹መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው›፡፡
ለምሳሌ ይህ የምልከው ጽሑፍ ከልምድ ተነስቼ ከመገመት በስተቀር በየትኘው ድረገፅ ይውጣ አይውጣ አላውቅም፡፡ አንዳንድ የኢሜል መልእክቶችን ግን አገኛለሁ፡፡ እዚህ እኛ ጋ ኢሜልም በግድ ነው እሚሠራው፡፡ በነገራችን ላይ ታዲያ በኢሜል ከሚላኩልኝ መጣጥፎች መካከል አንድ አስገራሚ መልእክት ሰሞኑን በጥሞና አነበብኩ፡፡ የወጣው በኢትዮጵያን ሪቪው ነው አሉ፡፡ የጻፈውም ሰው ብፁዕ ወቅዱስ አባ ሙሉጌታ ወልደ ገብርኤል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ፣ ወእጨጌ ዘመንበረ አቡነ አረጋዊ ወተክለ ሃይማኖት፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያን ፕሬዚደንት ወአኀው ዘጉጅሌ ተጋሩ ወየንቲ ትግራይ … ነው አሉ፡፡ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ ዘርዝሬ መጨረስ ባለመቻሌ ይቅርታ፤ ግን እኮ ሁለት ክፍት የሥልጣን ቦታዎች ስላሉ መጥቶ አንዱን ቢይዝና እንዲህ በሩቅ ሆኖ ለወያኔ ከመንሰፍሰፍ ቢቆጠብ ጥሩ ነበር – የመለስና የአባባ ታምራት ማለቴ የአቶአባ ገብረ መድኅን ማለቴ ነው (ዳሩ ከአለባበስና ከወንበር ትልቅነትና ማማር በስተቀር በሁለቱ የአጋንንት ሠራዊት አባላት መካከል ምን የጎላ ለውጥ አላቸው?) ፡፡ (ዱሮ ነው አሉ- አንዲት የቤተ መንግሥት ተጎራባች ተርቲበኛ ወይዘሮ፣ ወይዘሮ ውባንቺን ቡና ስትጠራ መንጌን ሆን ብላ ተወችው አሉ፤ ያኔ ውባንቺ ሆዬ – ‹እንዴ፣ ባለቤቴንስ ለምን አትጠሪውም?› ብላ ብትጠይቅ – ‹ ምን ማለትሽ ነው፣ያን ሁሉ ሹመት እስክጠራ ቡናየ ይቀዝቅዝ?› አለቻት አሉ፡፡ በ‹አሉ› እና በቅንፍ አለቅን ጓዶች፡፡)
አንዴ ሰው፣ አንዴ አፈር መሆን በተለይ በዚህ ዘመን እየተለመደ የመጣ ነገር ሆኗል፡፡ ቀሲስ ሙሉጌታ (በድጋሚ – ዛሬ እንኳን ከዲቁና ላውጣው እንጂ!) አንዳንዴ – በል ሲለውና ኅሊና የሚባል ነገር ካለው ወደኅሊናው ሲመለስ አንጀት አርስ የሆኑ ጽሑፎችን ይጽፋል(ራሴን ተቃረንኩ ልበል?)፤ አንዳንዴ ለራሱም የሚገባው የማይመስለኝን የሰሞኑን መሰል ወለፈንዴ ጽሑፍ እንደጦጣ ይሞነጫጭራል – ግዴለም ስለተናደድኩ እንደዚህ ልበል፤ ይሄን ጊዜ ታዲያ ሰውዬውም ሆነ ጽሑፉ አይገቡኝም፡፡ እኔም ለነገሩ ለርሱና እርሱን ለመሰሉ ወለፈንዴዎች የማልገባ ወፈፌ መሆኔን አላጣሁትም፡፡ አዎ፤ በያለንት እንበድ – ጊዜው ነው፡፡ የሰው እንጂ የጊዜ ዕብድ ባይኖርም፡፡ ግን ድንበር ዘልለን ወደቡጢና ወደቁረቋሶ እንዳንገባ እንጠንቀቅ፡፡
ቢያድለን የአንዲት ሀገር ዜጎችና የአንድ ሕዝብ አካል እንደመሆናችን ከጎጥና ከቋንቋ ወያኔዊ የመከፋፈያ ሥልቶች ብንወጣና ለሁላችንም ምቹና ገላጣ ቦታ ላይ ብንገናኝ ደስ ባለኝ፡፡ ያ ለጊዜው ካልተቻለና እስኪቻልም ድረስ መገናኘት የሚቻለን በዚህን መሰሉ መድረክና በቃላት ነውና ቀን አልፎ ቀን ሲተካ፣ ክፉ ዘመን አልፎ ወርቃማ ዘመን ሲብት አንገት ለአንገትና ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈን ይህን የመከራና የክፍፍል ጊዜ እያስታወስን በፍቅር እስክንሳሳም ድረስ ባለን ብቸኛ አማራጭ በብዕር ‹እንነጋገር›፡፡ ብዙ ነገሮች የሂደቶች ውጤቶች መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ መግባባት ሂደታዊ ነው፤ ጥላቻን ማስወገድ ሂደታዊ ነው፤ ፍቅርን መመሥረት ሂደታዊ ነው፤ ዴሞክራሲን ማንገሥ ሂደታዊ ነው፡፡ ስብዕናን ከአሉታዊ ወደአወንታዊ መለወጥ ሂደታዊ ነው፡፡ አስተሳሰብንና አመለካከትን ከአንድ ጫፍ ወደሌላ ተቃራኒ ጫፍ መለወጥም ሂደታዊ ነው፡፡ ማደግም መቀጨጭም የሂደት ውጤቶች ናቸው፡፡ በሂደት የማያልፍ ዕደገት መለኮታዊ እንጂ እውናዊና ዘለቄታዊ አይሆንም ቢባል እንደአጠቃላይ ግርድፍ እውነት የሚያስኬድ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ መተነኳኮሳችን ጤናማ እንጂ ያን ያህል አፈንጋጭ ክስተት ሊባል የሚችል አይደለም እላለሁ፡፡ ይህ ዓይነቱ ነገር እንደመጥፎ ዕድል ሆኖ በኛ በኢትዮጵያውያን ይበረታ እንደሆነ እንጂ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ነው፡፡ ለምሳሌ ሦርያውያንን ብንመለከት ተቃዋሚዎች ከጨፍጫፊው የወያኔ ዘረኛ ቡድን ማለቴ የአሳድ የ’minority’(አናሳ) መንግሥት ጋር ብቻ ሳይሆን እርስ በርስም ይፋተጋሉ፤ ይጣላሉ፤ ይወጋገዛሉ – በዚህ ወይ በዚያ ምክንያት፡፡ በሂደት ግን ይታረቁና አንድ ወደመሆን ይደርሳሉ፡፡ ሰሞኑን የመሠረቱት ‹Coalition›ንም የዚህ ምሥክር ነው – ለነገሩ በጋራ ግንባርና ኅብረት ፈጠራስ እኛን የሚስተካከል የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በየትኛውም ጎራ ያለን ወገኖች እንወቃቀስ፣ ‹እንዘላለፍ› ይሁንና ብትቀጥንም ትንሽ ምክንያት እንድትኖረንና ያቺንም ምክንያት የማስረዳት የሞራል ግዴታ እንዲኖረን ራሳችንን እናሰልጥን – አሁን ሀለቃ ሙሉጌታን እየወቀስኩ ያለሁት ለምሳሌ መረን በለቀቀና ብዙዎቻችን ከሚገባ እውነት በተቃረነ መልክ ኢሣት ላይ ባቀረበው ትችቱ ተነክቼ ከዚያ ይልቅ ደርዝ ያለውና ተጨባጭ የሆነ ትችት እንዲያቀርብ ለመገፋፋት እንጂ የመሳደብና የመንቀፍ አራራ ኖሮብኝ ያንን በእግረ መንገድ ለመወጣት አይደለም፡፡ አለበለዚያ ከሜዳ እየተነሳን የጭቃ ጅራፋችንን በምንጠላው ሰው ወይም ድርጅት ብንለጥፍ ራሳችንን ትዝብት ውስጥ ከመክተትና ምናልባትም በትግሉ ላይ አንዳች ጊዜያዊ ጥላ ከማጥላት ባለፈ ለሀገርም ሆነ ለራሳችን የምንፈይደው ነገር እንደሌለ መረዳት ይኖርብናል፡፡ እኔ ይህን ስል ሰውን ቅቤ እየቀባሁ እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ይህኛው አነጋገሬ ግለሰባዊ ሳይሆን ሀገራዊ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ እስከየትኛውም ደረጃ መሄድ ይቻላል፡፡ በሀገር ጉዳይ ግን ያን ያህል መለያየት የለብንም፡፡ ጥቁርን ነጭ፣ ነጭን ጥቁር እስከማለት የደረሰ ድፍረትና ጀግንነት የተሞላበት ልዩነት ውስጥ ከገባን የአንድ ሀገር ልጆች መሆናችን ራሱ ያጠራጥራልና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባን ጊዜ ላይ መድረሳችንን ልናጤን ይገባናል፡፡ ብዙ ነገሮች ፈር እየለቀቁ ነውና በተለይ ከእውነት ጋር እየተላተምን የምንገኝ ዜጎች በምንም መንገድ idiomatically call it at the end of the day or (at the beginning of the night, and as to me, ‘at the end of this absolute darkness’) ተጎጂዎቹ እኛና እኛ ብቻ መሆናችን የታመነ ስለሆነ የተዘጋውን የውስጥና የውጭ ዐይናችንን ብዙ ሳይመሽብን ልንከፍት ይገባናል፡፡
ሙሉጌታ እልም ያለ የወያኔ ደጋፊና ይህ ሥርዓት አይነካብኝ የሚል ግን በተቃውሞው ጎራ ውስጥ የመሸገ የሚመስለው በርሱ ቤት አሁንም ያልታወቀበት እንደሆነ የሚገምት አደገኛ የሀገር ፀር ነው – በአሥር ጣቴ እፈርማለሁ፡፡ እኔ እልም ያልሁ ፀረ ወያኔ ነኝ – ወያኔ ካልጠፋና ሥርዓታዊ መንግሥት ካልተመሠረተ ሀገር የለንም ብዬ የማምን፣ ‹ክንዴን ሳልንተራስ› የወያኔን ግፈኛ ሥርዓት በምችለው ከመጋፈጥ ወደኋላ አልልም ብዬ በአዲስ አበባ ኢንተርኔት ካፌዎች ሌባ ጣት የምትባል አዲስ ጠበንጃ ታጥቄ የሸፈትኩ እንዴት ያለሁ የፈሪ ‹ጀግና› መሆኔን ለአንባቢያን የምገልፀው በከፍተኛ የጭቁኖች ኩራት ነው፡፡ እኔና ሙሌ የምንለያይባቸው ብዙ ነገሮች አይኖሩም አይባልም፤ ሁሉን መዳሰስ ደግሞ አይቻልም፡፡ ሙሉጌታ በጭፍኑ – ለዐይኑን ጮፉኖ ማለት ነው- ይህችን ሀገር ትግሬ ካልገዛት – ጳጳሱም፣ ኤጲስ ቆጶሱም፣ ፓትርያርኩም፣ ሊቀ ትጉሃኑም፣ ቄሰ ገበዙም፣ ቀዳሽ አስቀዳሹም፣ አፋዳሽ አወዳሹም፣ ፣ ሌላው ቀርቶ ግብር አድቃቂዋ ዐቃቢትም ሳትቀር ትግሬዎች ካልሆኑ ሀገር አትጠናም የሚል ‹እንደኔ ያለ› ጠንቋይ ወይም እንደብሉዪው ሕዝቅኤል ያለ ነቢይ ብቻ ሊደርስበት የሚችል አቋም ያለው ይመስለኛል – በቀጥታም ባይል (እንዲልና እስኪልም አይጠበቅም) ከአያያዙ ይህን የመሰለ አቋም የሚያራምድ ይመስለኛል – እንዲያ ባይሆን ኖሮ የብዙኃን ብሶት መተንፈሻ የሆነውን(እርሱ ቅንብር ነው ብሎ ቢያምንም) ኢሣትን ያን ያህል እግርና እጅ በሌለው ክስ አይሉት ወቀሳ – ስም በሌለው ነገር- እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ አድርጎ ባልተሞላፈጠበት ነበር የሚል የከረረ ግምት አለኝ፡፡ እኔ የኢሣት ጠበቃ ለመሆን ዳድቶኝ አይደለም – በጭራሽ፤ እኔ ራሴም ብዙውን ጊዜ እተቻቸዋለሁ – ዝግጅታቸውን እንዲያሻሽሉ ካኝ ወገናዊ ተቆርቋሪነት በመነሣት – ( ነገሩ የመተቸትና ያለመተቸት ጉዳይ ሳይሆን ወያኔዊ ትችትና ኢ-ወኔያዊ ትችት እመለያየቱ ላይ ነው – የመጀመሪያው ለልምድ ልውውጥና ለእርምት ሲሆን ሁለተኛው ለበጎ ሳይሆን ግዳይ ለማስቆጠርና በወያኔው መንደር ‹ነገሩ ምንም እንዲህ ቢሆን የእናንተው ነኝና በቁርጥ ቀን አለሁላችሁ› የማለት ያህል ተቃዋሚን ለመወንጀል ታስቦ ነው – የቀድሞ ኢትዮጵያውያን ፈረንጆች ይህን ነገር ‘AmareAregawi (አጠር ሲል ‹Amaragawi›) Syndrome’ ይሉት ነበር አሉ – በዚህ ፈገግ የማይል ወያኔ ነው!)፡፡ እንከን የለሽ ነገር በሌለባት ዓለም ውስጥ የምኖር የሚመስለኝ ሞኝ እንዳልሆንኩ ብገልጽ የሚያነውረኝ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን የነገሮች ሾርኒያዊ አካሄድ ስለሚገባኝ የሰዎችን አነጋገር በብልት በብልት እየመደብኩ በማይበት ጊዜ የሙሉጌታና የኢሣት የጠብ መነሾ ሊከሰትልኝ ባለመቻሉ በጣም ከመገረም አልፌ ይህን የማያገባኝን ስንክሳር እስከመጻፍ ደርሻለሁ፡፡ ያን መነሻና መድረሻ የሌለውን ጽሑፉን አንብቡት – ውሉ ባይያዝላችሁም ሙልዬ ለተቃውሞ ጎራ ያለውን ሾንዳራ አመለካከትና ጭፍን ጥላቻ እንዲሁም ለወያኔው ሥርዓት ያለውን ታማኝነት ትታዘባላችሁ(እንዲህ ሊነጋ በሬየን አረድኩ አለች አሉ አንዷ የሙሌ ዓይነት የማይነጋ የሚመስላት ለዋህ)፤ ምን ዓይነት ሰው ይሆን ግን – መልኩን ባየሁት! ኢሣቶች ግን ምን ያህል በድላችሁት ይሆን ይህን ሰውዬኣችንን? አይ፣ ግዴላችሁም ይቅርታ ጠይቁት፡፡ በጣም እኮ ነው እየተንጨረጨረባችሁ ያለ – በፈጣሪ ያስኮንናችኋል ይቅርታ ባትጠይቁት፡፡ የትኛዋን ስስ ብልቱን ነክታችሁበት ይሆን? እስኪ በሞቴ በኢሣጥኔ መይሉልኝ ይህን ጉድ፡፡ ደግሞስ ፊት ነሱኝ ያላቸው ድረገ ፆች ምን አለ በሁሉም መርበበ-ወሬ ወጥቶ እንዲነበብ ዕድሉን ቢሰጡት? ምን ክፋት አለው? ጽሑፉ ራሱ እኮ በቂ ነው ለመነበብም ሆነ ላለመነበብ፡፡ የምን እገዳ ነው! ሃሳብና ሃሳብ ቢጋጩ እኮ በሂደት ሁሉም እዬጠራ ይሄዳል፡፡ ሙሉጌታን የሚያንገበግበውን ሥጋት ልናጤንለት ይገባል፡፡ ምናልባት የአሁኖቹ የትግራይ መኳንንት ከሥልጣን መገለል (የማይቀር መሆኑ በአፅንዖት ይያዝልኝ) ሌላውንና ንጹሑን ኢትዮጵጵያዊ የትግራይ ዜጋ የሚነካ መስሎትም ሊሆን ይችላል’ኮ፡፡ አለበለዚያ እንደቀትር እባብ እንዲህ ባልተወራጨ ነበር – (ጎበዝ! ቃላት አጠቃቀም ላይ እንደኔ ጠንቀቅ ማለትን ዕወቁ! ‹ባልተቅነዘነዘ› ማለት አቅቶኝ መሰላችሁ? ነውር ስለሆነ ነው ያን ያልተጠቀምኩበት፤ ለሰዎች ስሜት መጠንቀቅም ግዴታችን ነውና ይህ ዓይነት ነገር ይታሰብበት፤ እየተናደዳችሁም እንዳትጽፉ አደራችሁን፤ በንዴት ጊዜ ልጅ አይቀጣም ይባላል፡፡ ሙሌም እኮ በንዴት ጊዜ መጻፍ ያውቅበታል – በተለይ ወያኔ ከተነካችበት፡፡)
እኔም ከሙሌ በተቃራኒ የኢትዮጵያ ነገር ሲነሳ እንዳንዳች ያደርገኛል – አያችሁልኝ – ያቺ ቃል ለራስ ስትሆን እንዴት ትከብዳለች? የወያኔ ጥሩ ጎን በጭራሽ ሊታየኝ አልፈልግም – ምንም ደግ ነገር ስለሌለው ግን አይደለም(እንዴ፣ የጣሊያን ወራሪም እኮ ከጥፋቱ በተጓዳኝ የሚያስመሰግነው እንዲያውም ከወያኔዎቹም በበለጠ ስንትና ስንት ነገር ሠርቶ ነበር – ሊያውም ባምስት ዓመት ውስጥ ብቻና እየተዋጋም)፡፡ እናም በውጭ የምትኖሩ ወንድሞ እህቶቼና ባገር ውስጥ ያላችሁ እህቶቼ( እንዴ – ከኔው ጀምሮ ባገር ውስጥ ምን ወንድ አለና ወንድሞቼ ልበል ዱሮውንስ – መቱን አኮላሽተውን! አሁን አሁንማ ከመራቢያነት ባለፈ ለመሽኛም ስንፈልገው እያጣነው ነው፡፡ ከናካቴው በእንቅልፍ ልባችን ቆርጠው ሳይወስዱት ይቀራሉ? ለነገሩ በእውናችንስ ቢሆን ማን ከልክሏቸው! ጩቤና ጎራዴው ያለ በነሱ እጅ፡፡)
የወያኔ የኳሻርኳር (kwashiorkor)) ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በጭራሽ በፊቴ ዝር አይልብኝም፤ ሚሊዮኖች ይልሱትን ይቀምሱትን አጥተው በኑሮ ውድነት እየተጠበሱ ከአጠቃላዩ ሕዝብ ግፋ ቢል 10 በመቶ የማይሆኑ ቅንጡ ዜጎች የሚያሽቃንጡባቸውና የሚዳሩባቸው የአስፋልት መንገዶች፣ ባሉን ውስንና ጠባብ መንገዶች የሚርመሰመሱ አውሮፓ ውስጥም ሳይቀር ውድ የሆኑ አውቶሞቢሎች፣ እዚህና እዚያ (ብዙውን ጊዜ) ባዶኣቸውን የተገተሩ የብዙ ትግሬዎችና የጥቂት ኢ-ትግሬዎች ሀብቶች የሆኑ የሥራና የመኖሪያ ሕንፃዎች፣ ምርታቸውን ባብዛኛው ለውጪ ገበያ የሚልኩ የነእንትና ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች ስሜቴን በጭራሽ አይማርኩትም፡፡ (እንዴ? እኛ እየተራብንና እየተቁለጨለጭን – ማን እንደዜጋ ቆጥሮን – ስንትና ስንት የቁም ከብት፣ የዳልጋና የጋማ ከብቶች ሥጋ (ለሚፈልጉ ሁሉንበል ሀገሮች) ፣ እህልና ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ የሰላሱት እህሎች፣ ቆዳና ሌጦ፣ ዳቦና ፌጦ፣ ቡና(እኔ የገብስ ይሁን የሽምብራ ቅልቅል በስኒ 10 ብር ሆኖብኝ ለሱም አቅሙን አጥቼ በየበረንዳው እያፋሸግሁ – አይይይ… ይችን ቀንማ በፍጡም አልረሳትም!)፣ ይሄ ሁሉ የሀገር ምርት ይበልጡን በሕገ ወጥ ንግድ ልክ እንደአለኝታቢሱ ከርታታ ዜጋ በባሌም በቦሌም ከሀገር እንደሚሰደድ ታውቁ የለም እንዴ?)፡፡ የወያኔ ብልጭልጭና ሸውራራ ዕድገት ስሜቴን ሊገዛ ያልቻለው እንግዲ‹ክ› ወያኔን ስለምጠላ ብቻ እንዳይመስላቸሁ፡፡ እንደነገርኳችሁ ይህ የኳሻርኳር ኢኮኖሚ ጥቅም ለጥቂቶች ሲሆን ጉዳቱ ግን ለብዙዎች በመሆኑ ነው፡፡ እንጂ ለታይታ ያህልማ ሀገራችን በዕድገት እየተመነደገች ያለች መምሰሏ የታወቀ ነው፡፡ በዘልማዳዊው የነፍስ ወከፍ ገቢ ሥሌት መሠረት የኔ ዓመታዊ ገቢ ቢታይም የሐጎስና የአላሙዲን ገንዘብ ለኔ ለአጣሙዲኑ (ሲሉ ሰምቼ ነው) ለዳግማዊ ጉ. ካሣ ምን ይፈይድልኛል? እነሱ ጠግበው ሲያገሱ የነሱ ብስናት ሊገድለን የተቃረበ እጅግ በርካታ ሚሊዮን ሕዝብ በአጠገባቸው እየተንጠራወዝን የፈጣሪን ፍርድ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡
ፐርካፒታንና ይህን ዕድገት ተብዬ የተውሳኮችና የመዥገሮች የስሚንቶና የአሸዋ፣ የብረትና የድንጋይ ቁልል ወያኔዎችና አጫፋሪዎቹ ሲፈልጉ ቀቅለው ይብሉት(እዚች ላይ የመንግሥቱ ለማን ግጥም አስታውሱ፡-
ምን ሕንፃው ቢረዝም ቢንጣለል አስፋልቱ፤
ሰው ሰው ካልሸተተ የት አለ ውበቱ!
‹ትንቢትሰ ይቀድሞ ለነገር› ማለት አሁን ነው፤ ሕንፃና መንገድ ሳይሆን በአንጻራዊ ሁኔታ እንደነገሩም ቢሆን ሰው በነበረበት ዘመን ስለሰው መጥፋት የተገለጸበት ልጨኛ ግጥም! አፈሩን ገለባ ያድርግለት)፡፡ ለእኔስ ያልተብለጨለጨ ግን በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ሆኜ ቁርስ ምሣና ራት የማገኝባት እጥን ምጥን ያለች ዕድገትና ልማት ትበቃኛለች፤ ያቺም ትመጣለች!! አድልዖ ላይ ከተመሠረተና ለበይ ተመልካችነት ከሚያጋልጥ ትልቅ ዕድገት ይልቅ በረከቱ ለሁሉም የሚተርፍ የተስተካከለ የልማት ዕቅድና ተግባራዊነት የበለጠ ዋጋ አለው፡፡ ያኔ ሁሉም ይተጋል፤ ሁሉም ከሁሉም ይተባበራል፡፡ ተጨባጭ ዕድገትና ልማት የሚመዘገበውም ያኔ ነው፡፡ ‹በፍርድ ከተነዳች በቅሎዬ አለፍርድ የተዘገነች ቆሎዬ› ይባል የለም? የኛ የምንለው ሰው ሲመጣ ራቁታችንንና ባዶ ሆዳችንንም ሆነን ከእርሱው ጋር ሞታችንና ትንሣኤያችን አንድ ይሆናል፡፡ እነዚህ ሽል መንጣሪ የትግራይ መኳንንት ግን በአንዱ ጉሮሮ አጥንት እንዲሰነቀር፣ በሌላው ጉሮሮ ቅቤ እንዲንቆረቆር የሚያደርጉ፣ አንዱ አፈር እንዲግጥ ሌላው ጮማ እንዲቆርጥ ሌት ተቀን እሚማስኑ፣ አንዱ ውሃም አጥቶ ጭቃ እንዲመጥ ሌላው ዊስኪና ኩርቫይዘር እንዲጨልጥ የሚያደርጉ የአድልዖ ፋብሪካ ሰብኣዊ ማሽኖች ስለሆኑ በነሱ የሚመጣ ዕድገት (ልማት ሊያመጡ እንደማይችሉ አረጋግጫለሁና) ባፍንጫዬ ቀርቶ በቁርጭምጭሚቴ ይውጣ፡፡ መብትን መጠየቅና ለመብት መቆርቆር ደግሞ ዘረኝነትና ሽብርተኝነት ሳይሆን ተፈጥሯዊ የአልሞትባይ ተጋዳይ አጠይቆ ነው፡፡ ይህን ሸፋፋና ‹amorphous› ሥርዓት ለማቆየት ነው እንግዲህ ጓል አደይ – ኦ ቃል ሳትኩ መሰል – ወዲ አደይ ሙሉጌታ መከራውን እየተመለከተ ያለው፡፡ ዛሬ ምን ነካኝ – ፍዳውን እያዬ ያለው ተብሎ ይስተካከልልኝ እባካችሁን፡፡ ለነገሩ ቢበቃኝስ? ስለኳሻርኳር ከዚህ በታች ያለውን ሳታይ ግን አደራህን ማንበብህን እንዳታቆም፡፡
ለመሸጋገሪያነት አንዲት መፈክር ቢጤ ላሰማ መሰለኝ፡-
ባሽር አል አሳድ በሦርያ ላይ እያወረደው ካለው ዓይነት ሰቆቃና መከራ ኃያሉ አምላክ ሀገራችንን ይጠብቅ!!
ኳሻርኳር ይሉሃል ይሄ ነው! (ዋናው ምንጭ ከምስሉ ግርጌ አሉልህ – ማይክሮሶፍት ኢንካርታና ኢንተርኔት ናቸው) እያንዳንድህ በዓለም የተበተንህ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁላ ሀገርህ እንደነዚህ ሕጻናት በኳሻርኳራዊ የኢኮኖሚ ‹ዕድገት› የተቆዘረች መሆኗን ተረዳና ለወደፊት ሀገርና ትውልድ እንዲኖርህ በምትችለው ሁሉ ቆርጠህ ታገል – በሀገር ቤት ከአስተማማኝ ሥፍራ የትግል ጥሪ ሲድርስህ ነገ ዛሬ እንዳትል – የጥሪውን አስተማማኝነት የምትረዳውም በብርቱ የኅሊናና የአምልኮት ጸሎት ነውና ከፈጣሪህ ጋር ቶሎ ታረቅ፡፡ ከእግዚአብሔር ውጪ ለዚህች ሀገር መፍትሔ የለም፤ አለቀ – ደቀቀ፡፡ እሱ ሲል ሴከንድ አይፈጅበትም፤ እንዲል ግን የእኛም አስተዋፅዖ ያስፈልጋል – የልብህን መሻት ይመረምራልና አሁኑኑ ሻ(ድንግርግር አይበልህ ‹ሻ› ቃል ነው)፤ እንደጀመረ ይጨርሰዋል – የድርሻህን እንድትወጣ ግን አምላከ ኢትዮጵያ ይፈልጋል፡፡ ቀድሞውንም በእግዚአብሔር ፈቃድና ልዩ ጥበቃ እንጂ እንደወያኔዎች ቢሆን ኖሮ አንድም ኢትዮጵያዊና አንድም ታሪካዊ ቅርስ እስካሁን ሊገኝ ባልቻለ ነበር፡፡ ስለዚህ በባዕድ አምልኮና አስተሳሰብ ከመነዳትና ‹የምን ፈጣሪ ነው› እያሉ ከመገዳደር በመቆጠብ በየሃይማኖትህ በርትተህ ጸልይና ሀገርህን ከነዚህ የነቀዙ የትግራይ መኳንንት ዘረኛ አገዛዝ፣ ከነዚህ ምሕረት የሚባል የማያውቁ የናቡከደነፆር አረመኔያዊ አገዛዝ ጭራቆች ተረከብ፡፡ የዛሬን ጠግበህ ማደርህ ቁም ነገር እንዳይመስልህ – ሰው ደግሞ በመብል ብቻ ሊኖር የሚገባው አጋሰስና ጌኛ ፍጡር አይደለም – ሊሆንም አይገባውም፡፡ በምግብ ብቻ መኖር ቢቻል ኖሮ ስንትና ስንት ዜጎች ለእሥር ባልተዳረጉ፣ ለስደት ባልተጋለጡ፣ አንዳንዶች ቢፈልጉ በውጪው ዓለም አንቀባርሮ የሚያኖራቸውን ሀብትና ገንዘብ በመናቅ ከአክሳሪው የፖለቲካ ትግል ጋር ግብ ግብ ባልገጠሙ፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቢቀጠሩ በሺዎች የሚገመት ወርኃዊ ደሞዝ ማግኘት እየቻሉ ‹የሀገራችን ፖለቲካ ከዕድፉና ከጭቅቅቱ ነጽቶ አንድ ቀን ነፍስ ይዘራ ይሆናል› በሚል ተስፋ አቋማቸውን ከሕዝብ ጎን ባላስተካከሉ … አንዳንዶችም ከስደት ይልቅ ባላቸው ሀብትና ንብረት በሀገራቸው ተዘባንነው በኖሩ – ግን ካለኅሊና ነጻነት መዘባነን፣ ካለመንፈስ ነጻነት በቀየህ መኩራት የለምና ለዚህ ሲሉ ብዙዎች ይታገላሉ – በመጨረሻው ደግሞ ፍሬ ማፍራታቸው አይቀርም፡፡ ለከርሱ የሚኖር እንስሳ ብቻ ነው – ሰው ሆኖ ለከርስ ካደረ ከእንስሳም በታች ሆኗል፤ ምክንያቱም መብቱን የማያስከብር ቫይረስና ጀርምም ቢሆን በዚህች ምድር የለምና! ለአብነት ጉንዳንን ተመልከት – ሱሪህን ነው የሚያስወልቅህ – ባደባባይ ነው የምታዋርድሽ፡፡ እኛ ግን ፓንታችንንም ለወያኔ አውልቀን እንዳሻቸው እንዲያደርጉን ፈቅደንላቸዋል፡፡ አይዘግንንህ – እውነቱን ብቻ ነው እየተናገርኩ ያለሁ – እነሱም ይሄን ያውቁታል- ይሄን ብቻም ሳይሆን መጨረሻቸው እንደተቃረበና ከፍርድም እንደማያመልጡ አሳምረው ያውቁታል – ለዚህም ነው የሌሊት ወፎች እየተቅነዘነዙ ያሉት – የሌሊት ወፎች ነው ያልኩት – እነሙሉጌታ አላልኩም፡፡ ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጠሩሽ አይክፋሽ ነው ነገሩ፡፡ ለማንኛውም ይህንን ተረዳ፡- ልጆችህና የልጅ ልጆችህ ተመልሰው መግቢያ ሀገር ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንደአንደኛው የፈረንሳይ ሉዊሶች ‹After me the Deluge!› ብለህ በራስን አድን የአህያዋ ፍልስፍና ተደብቀህ የምትኖር ከሆነ ወዮልህ! እንዳማሩ መሞትና እንዳማሩ መኖር ሁልጊዜ የለም፡፡ ለሽንትህ አስብለት፤ ለዘርህ ዋስ ጠበቃ ሁንለት – ተበትኖ መቅኖ አጥቶ መቅረት የለበትም፡፡ የሰው ወርቅ ምን ጊዜም የሰው ነው – አያደምቅም ብቻ ሳይሆን ጭራሹንም አያምርም፡፡ የራስ ቀዳዳ ከሰው ጨምዳዳ በእጅጉ የተሻለ ነውና በጋራ ማሰብ እንጀምር፡፡ በዘርና በጎሣ እየተናቆሩ ባንክንና ኢንተርፕራይዝን ባለፈ አስደናቂ አካሄድ በዘውገኝነት ደዌ ተለክፎ ጎጣዊ ፅላት መቅረጽና ቤተ ክርስቲያን መገንባት አለወጉ በየዘርም መጸለይ አላዋጣም፤ አያዋጣምም፡፡ አቡነ አረጋዊን ነው የምላችሁ፡፡ አቡነ ተክሌ፣ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራና አቡነ አረጋዊ አሁን ቢነሱ ስቀው አያባሩም፡፡ እግዚአብሔር ተረስቶ ዘር እንዲህ ሲነግሥና “ጳጳስና የሀገር መሪ በግድ ከትግራይ ካልሆነ ጥቅማችን ይጓደላል፤ አገዛዛችንም ይሻራል፤ በሠራነው የእጃችንን እናገኛለን” የሚለውን የማያዋጣ ክርክር ቢሰሙ እንዴት እንደሚያፍሩብን ይታያችሁ፡፡ በጊዜ ሰው እንሁን፡፡ ሀገር አሳጥቶን ያለው የወያኔ ስግብግብ ተፈጥሮና በፍርሀት ካባ የተጀቦነ፣ በዘረኝነት መርዝ የተለወሰ፣ በውጪዎች አበረታቾች የተደገፈ የአናሳ ዘውግ አገዛዝ ስለሆነ በተባበረ ግን ዘመናዊ ንቃተ ኅሊናን በተላበሰ ትግል አክሽፈን በትክክለኛ የምርጫ ሂደት ብዙኃን በሚመርጡት የመንግሥት አስተዳደር እንመራ – ቢያንስ በቀያችን እንደሰው እንድንቆጠር፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar