(ሪፖርተር) - ከጥቂት ወራት በፊት በኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ሊካሄድ የታሰበው ድርድር ከተቋረጠ በኋላ አንድ የቡድኑ አንጃ ከመንግሥት ጋር ለመደራደር አዲስ አበባ መግባቱ ታወቀ፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ አብዲኑር አብዱላሂ ፋራህ የሚመራው የኦብነግ አጀንዳ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እየተካሄደ ስላለው ልማት ደስተኛ መሆኑን አምኖ፣ በአካባቢው ሰላም ለመፍጠር ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ወስኗል፡፡
ባለፈው ጥቅምት ወር በናይሮቢ ሊካሄደ ታስቦ የነበረው ድርድር አንዳንድ የድርጅቱ አመራሮች የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት አንቀበልም በማለታቸው በተነሳው አለመግባባት የተኮላሸ ሲሆን፣ ለድርድሩ መቋረጥ ምክንያት የሆኑት አድሚራል መሐመድ ኡስማን በአሁኑ ወቅት በአስመራ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በድርጅቱ ብዙም ሕዝባዊ ተቀባይነት እንደሌላቸው የአንጃው መሪ አብዲኑር መግለጻቸው ታውቋል፡፡
የኦብነግን አንጃ በመወከል አዲስ አበባ የተገኙት አብዲኑር እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው ኦብነግ ውስጥ ሕገ መንግሥቱን በመቀበልና ባለመቀበል በተፈጠረ አለመግባባት መከፋፈል ተፈጥሯል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሕልፈት ምክንያት በኢትዮጵያ የሥልጣን ክፍተት ይፈጠራል የሚል ግምት የነበረው ኦብነግ በመከፋፈሉ፣ በአካባቢው ሰላምና ደኅንነት ለመፍጠር ሕገ መንግሥቱን ተቀብለው ስምምነት ከመፍጠር ውጪ አማራጭ የለም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰላም ስምምነቱ በሚፈረምበት ሁኔታ ላይ ከአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገሩ ይገኛሉ፡፡
አሁን አዲስ አበባ ገብተው ከመንግሥት ጋር የሰላም ድርድር ለማድረግ የመጡት አብዲኑር የኦብነግ የምሥራቅ አፍሪካ ወኪል፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚና የድርድሩ ቃል አቀባይና የግንባሩ ምክትል የውጭ ጉዳይ ኃላፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት አንቀበልም ማለታችን ስህተት ነበር፤›› ብለው አሁን ግን ድርድር ማድረጉ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ መንግሥትና በአንዱ የኦብነግ አንጃ መካከል በአዲስ አበባ የሰላም ስምምነት መፈረሙ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ አሊታህት ተብሎ የሚጠራው አንጃ በኢንጂነር ማኦና በሐሰን አብዲ ካህን ይመራል፡፡
ኦብነግ በኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ተብለው ከተሰየሙት ኦነግና ግንቦት ሰባት ከሚሰኙ የአገር ውስጥ ድርጅቶች ተርታ ይመደባል፡፡
|
fredag 28. desember 2012
የኦብነግ አንጃ ለድርድር አዲስ አበባ ገባ
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar