fredag 28. desember 2012

” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አመራር ለሃይማኖቱም ሆነ ለአጠቃላይ ለስርዓቱም አደጋ ወደ መሆን ተቃርቧል”- ስብሃት ነጋ ቃለ ምልልስ

” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አመራር ለሃይማኖቱም ሆነ ለአጠቃላይ ለስርዓቱም አደጋ ወደ መሆን ተቃርቧል”- ስብሃት ነጋ ቃለ ምልልስ

by freedomofspeech4

(በፋኑኤል ክንፉ)
አቶ ስብሃት ነጋ (አቦይ ስብሃት) ህወሓትን ከ1971 እስከ 1981 ዓ.ም በሊቀመንበርነት የመሩ ግንባር ቀደም ታጋይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ከፓርቲው አመራር አባልነት የለቀቁ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሠላምና የልማት ኢንስቲትዩትን በዋና ዳይሬክተርነት ይመራሉ። በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አነጋግረናቸዋል።
ሰንደቅ፡- ከቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ ያለው የአመራር ለውጥ ሒደት እንዴት ተመለከቱት?
አቶ ስብሃት፡- በአሁን ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕገ መንግስታዊ ስርዓት አላቸው። ይህ የሆነው ግን ዕድለኞች በመሆናቸው ሳይሆን በረጅምና መራራ ትግላቸው የስርዓቱ ባለቤት መሆን በመቻላቸው ነው። ሕገ መንግስቱ መሰረታዊ ማንነታቸውን የመዋዕሉ ሁኔታዎችን በትክክል ያንፀባርቃል። በዚህ ሂደት፣ ማለትም ኢትዮጵያ ራስዋን በማወቅ ሂደት፣ ወሳኝ ሚና ያካሄደውና በሕገ መንግስቱ መሰረት በሕዝብ የተመረጠ ኢህአዴግ አለ።
ስለዚህ ኢህአዴግ ዕጩ አመራሮችን ይዞ ፓርላማ አቀረበና አፀደቀ። ሌላው አካሄድ ለዘለዓለም ዝግ ስለሆነ ሂደቱ የግድ መሆን ያለበት ሕገ መንግስታዊና ኢህአዴጋዊ በመሆኑ ባልገረምም፤ የሂደቱ ውጤት ግን አስደስቶኛል። ከዚህም በተጨማሪ እንደሌሎቹ የኢህአዴግ የአመራር አባላት ትምህርታቸው መሬት ነክቶ ከሕዝብ እንደገና ተምረው ሃቀኛ ኢትዮጵያዊነታቸውን እያረጋገጡና እየተረጋገጠ የመጡ አመራሮች ናቸውና ያስደስታል።
ሰንደቅ፡- ከአመራር ለውጡ ሽግግር በኋላ አራቱ ድርጅቶች (ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን) ስልጣኑን በጋራ የተከፋፈሉት ይመስላል። በምክንያት የሚነሳው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ሁለት ተጨማሪ ሹመቶች መሰጠታቸው ነው። ይህ ሒደት የኢህአዴግን ጥንካሬ አያሳይም እንዲሁም ሕገመንግሥቱን ይጥሳል የሚል አስተያየት እየቀረበ ነው ያለው። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
አቶ ስብሃት፡- የአመራር ለውጥ ሽግግር የተባለው ትክክል አይመስለኝም። ክፍት የአመራር ቦታ ስለነበር መደረግ የነበረበት የተለመደ የጠ/ሚኒስትር እና የምክትል ጠ/ሚኒስትር ሹመት ነው። ከዚህ በኋላ ከህወሃትና ከኦህዴድ በም/ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ተሾሙ። ከኢህአዴግ ውጭ ሌላ ቢያደርጉ ድርጅቱም፣ ፓርላማም ሕዝቡም አይቀበልም። የኢሕአዴግ ሕዝባዊ አመለካከትና ይህ ሕዝባዊ አመለካከት የነደፈው ፕሮግራም ስለሆነ የሚያራምዱት የሚሾሙት ከአንድ ድርጅት ብቻ ቢሾሙ ኑሮ ኢሕአዴግች እስከሆኑ ድረስ ብዙ የተለየ ትርጉም አይሰጡትም። ስለዚህም ሁለቱ ሹመኞች ከአንድ ድርጅት ብቻ ለማግኘት ስላልቻለ ወይም እኔ እንደሚመስለኝ የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና ከግምት ውስጥ ያስገባ አመዳደብ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ጉዳዩ የድርጅት እንጂ የሃገር መሰረታዊ ፖለቲካዊ ጉዳይ ስላልሆነ እዚህ ጋር እንተወው።
ሌላው የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አደረጃጀት ድሮም የነበረ ነው። አደረጃጀቱ ከጠቀሜታ አንፃር መመልከቱ ተገቢ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም፣ በመሰረተ ሃሳብ የጋራ አመራር ያጠናክራል። የጋራ አደረጃጀትና አመራር ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜም በድርጅቱ ውስጥ የጋራ አመራር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው ይታወቃል። አሁን በተዘረጋው የጋራ አመራር ጊዜ ሳይወስዱ ወቅታዊ ችግሮችን መፍታት ጀምረዋል። ለምሳሌ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ እየታየ ያለው እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ተስፋ የሚሰጥ ነው። ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ወደዚህ አደረጃጀት መግባታቸው ምን ያህል ለጋራ አመራር መነሳሳታቸው ነው የሚያሳየው። ይህም በመሆኑ ጥራት ያለው ፈፅሞ ወደኋላ የማይመለስ እርማት ከገመትነው ጊዜ ባጠረ ይመጣል።
ይህ አደረጃጀት ህገ መንግስቱ ይጥሳል፣ አይጥስም እኔ ልመልሰው አልችልም። ህገ መንግስቱን ጥሶ ከተገኘ በህገ መንግስቱ መሰረት ህገ መንግስቱን ማሻሻል ወይም ሌላ መንገድ መፈለግ ነው እንጂ፤ የአሁኑ ሰፋ ያለ የጋራ አመራር የሚያረጋግጥ አደረጃጀትና አሰራር መቀጠል አለበት የሚል እምነት አለኝ። በጣም የሚገርመኝ ነገር ግን ሕገመንግስቱ ተጣሰ ብለው ከሚጮሁና ከሚያለቅሱት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ሕገመንግስቱ ይቀደድ ብለው ሲፅፉና ሲናገሩ የነበሩ ናቸው። ሆኖም ግን ከጠያቂዎቹ ሰዎች መካከል በቀናነት ጥያቄውን የሚያነሱ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም እገምታለሁ። ያም ሆነ ይህ ሕገመንግስቱ ተጥሶ ከሆነ በባለሙያዎች ቢታይ ጥሩ ይመስለኛል።
ሰንደቅ፡- በአመራር ለውጡ (ሽግግር) ላይ የእርስዎ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል? በዚህስ ነጥብ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድንነው?
አቶ ስብሃት፡- በዚህ ሂደት ውስጥ የእኔ ሚና ምን እንደነበረ ለምን ጠየቅከኝ? የአመራር አባል አይደለሁም። ተራ አባል ነኝ። በየት በኩል ወደ ሂደቱ እገባለሁ። በምንም አጋጣሚ ቀዳዳ አግኝቼ ገብቼ የራሴ ያልሆነ የሰው ስራ ብሰራ፤ ማለትም ስርዓት አልባ ብሆን ሰውም ባያየኝ ሕሊናዬ ምን ይለኛል? ተቋማዊ ስርዓቱ በመራራ ትግል የተገነባ የህዝብ የፀጋዎች ፀጋ ነው። በየደረጃው በየስራ መስኩ ሃላፊነትና
ተጠያቂነት ተሸክመው ለሚመደቡ ሰዎች ተሸንሽኖ ተሰጥቷል። ሁሉም ዓይነት ምርትና ግልጋሎት በዚህ ፋብሪካ ነው፤ በተቀመጠው ዋጋ ጥራትና መጠን የሚመረቱት። የሰው ሃይል፣ እህል፣ መብራት፣ ፍትህ፣ ትምህርት ወዘተ የሚመረቱት፤ በዚሁ በተቋማዊ የስራ ሂደት ነው። አንድ ሰው ወይም ቡድን ይህንን ካፈረሰ በሞተር ውስጥ አሸዋ እንደጨመረ ነው፤ መቆጠር ያለበት። ተቋማዊ ስርዓት የሁሉም ፀጋዎች ፀጋ ስለሆነ ይህንን የሚጥስ የወንጀለኞች ወንጀለኛ ነው፤ ብር በእጁ ባይገኝም።
ማወቅ ያለብህ ስርዓት ከጣስኩ ከግንቦት ሰባት፣ ከኦብነግ እና ከኦነግ በምን እለያለሁ። ስለዚህም ምንም ሚና አልነበረኝም። ተራ አባል ነኝ። ከቅርብ አለቃዬ ስለምድብ ስራዬ ስላለው ሁኔታ እነጋገራለሁ። አሁን እንደውም ጥሩ አስታወስከኝና ጊዜ ካላቸውና ከፈቀዱልኝ አጀንዳ ባይኖረኝም አወራቸዋለሁ። አብዛኞቹ ለዓመታት አላየሁዋቸውም። እንደማውቃቸው አዳማጮችና ለሕዝብ የሚጠቅም ካለኝ ተቀባዮች ናቸው። ከድርጅቱ ውጭ የሚፃፉና የሚወሩም በመንገዳቸው እየተከታተሉ ቁም ነገር ካገኙበት ይጠቀሙበታል።
ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል አቶ መለስ በታመሙ ጊዜ አቶ መለስ ቢያልፉም ድርጅቱ ይቀጥላል ብለው ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘም “የመለስ ራዕይ” በሚል ከድርጅቱ በላይ አቶ መለስ የገነኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል የሚሉ ወገኖችም አሉ። በእዚህ ላይ የእርሶ አስተያየት ምንድ ነው?
አቶ ስብሃት፡- እኔ ያልኩት፣ አቶ መለስ ቢያልፉም አገሩ የስርዓት አገር ሆኗል። ስለዚህም ስርዓቱ ይቀጥላል። ድርጅቱ (ኢሕአዴግ) የስርዓቱ አንድ አካል ነው። ዋናው የስርዓቱ ምሶሶና ባለቤትነቱ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሆነው ሕገመንግስቱ ነው።
ስለ ራዕይ ምንነት አፈጣጠርና ባለቤትነት በአጠቃላይ በጣም ትንሽ ግንዛቤ ነው ያለኝ። ስለዚህ ጉዳይ በርካታ ፅሁፎች ስላሉ ለጉዳዩ የእውቀት ቅርበት ያላቸው ሰዎች በፈለጉበት አግባብ ቢያስተምሩን በየደረጃው ያለ የፓርቲ፣ የመንግስት፣ የግል ባለሃብቱ እና ሕዝቡ በጠቅላላው ይማርበታል።
እንደ ኢትዮጵያ መንግስት እና እንደድርጅት ሁለት መሰረታዊ ራዕዮች አሉ። እነሱም፤ እንደመንግስት ራዕይ፣ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ላይ የተገነባች አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያን መፍጠር ሲሆን ለዚህ ራዕይ መሰረት የሆነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት ነው። ባለቤቶቹም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ናቸው። ሕገ መንግስቱም በስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ በሕዝቦች ፈቃድ የተፈጠረች ጠንካራ ፌደራላዊ ኢትዮጵያን መገንባት ተችሏል። ባለቤቶቹም ሕገ መንግስቱን እየተጠቀሙበት፤ እየጠበቁት ይገኛል።
በድርጅት የተቀመጠው ራዕይ፤ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ወደ ብልፅግና ማድረስ ነው። ይህን ራዕይ ለማሳካት ድርጅቱ ዴቬሎፕመንታል ዴሞክራሲ ቲየር ተግባራዊ ለማድረግ በራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።
ከላይ ከተቀመጡት ራዕዮች መሠረታዊ ሃሳብ አንፃር ራዕይን ስንመለከተው፤ ራዕይ አርቆ ወደፊት ነው የሚያየው። መስመር፣ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና እቅድ ከዚህ ከተቀመጠው ራዕይ ነው የሚመነጩት። ሌላው ዋናውና መሰረታዊ የራዕይ ባህሪና ይዘት ደግሞ ለተፈፃሚነቱ ሰፊው ሕዝብ በየደረጃውና አቅሙ በፈቀደለት ሁኔታ የተቀመጠውን ራዕይ መጋራትና ባለቤት መሆን አለበት። ፈረንጆቹ እንደሚሉት “Shared vision” የሚሉት አይነት ነው።
ስለዚህም በእኔ በኩል የራዕይ አፈጣጠርና ባህሪ እንዲሁም ባለቤትነት ለጊዜው እስኪጠና አቆይተነው፤ በመለስ አመራር ሰጪነት የተጀመረው የድርጅቱን ራዕይ በመጀመሪያ ህወሓት ቀጥሎም ኢህአዴግ የድርጅቱን ራዕይ በባለቤትነት (Shared vision) ወስደውታል። የእኛም ነው ብለው ተዋድቀውበታል። ሕገ መንግስቱም እንደዚሁ ባለቤቱ መላው ሕዝብ ተመሳሳይ ዋጋ ከፍለውለታል። ስለዚህም በግለሰብ ብቻ ላይ የተቀመጠ ራዕይ ሳይሆን የሁላችንም እሴት የሆነ የጋራ ራዕይ ነው ያለው። ቁም ነገሩ ራዕዩ የማናው ሳይሆን፤ ራዕዩን በጥልቀትና በስፋት ማስረፅና ማስፈፀም መቻል ነው። ከራዕይ ጋር ያለኝን አረዳድ የሚቀይር መሰረታዊ ጥናትና ድምዳሜ ከመጣ ትክክለኛውን ለመቀበል ችግር የለኝም።
ሆኖም ግን ህወሓትና ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ለማወቅና የችግሮችዋ መንስኤና መፍትሄ በማስቀመጥ የተለያዩ ግብዓት ቢኖራቸውም መለስ ወሳኝ ሚና ሰርቷል። በትግበራ የነበራው ሚና ቀላል አልነበረም። መለስ ከማውቃቸው የኢትዮጵያ መሪዎች አዋቂና እውቀቱን በተግባር ለህዝብ ጥቅም ያዋለና እንዲጠቅምም ያደረገ ቀዳሚ ሰው ነው። ከእሱ ተግባር መረዳት የሚቻለው ትምህርት በቀጥታ ለሕዝብ ጥቅም ማዋል ባህል ማድረግ መጀመሩን ነው። አሁንም ከመለስ የበለጡ ሕዝባዊ ሙሁራን “Organic elite” ለማምረት ስለምንችል ይህን የሰው ሃይል የማምረት ራዕይ አጥብቀን መያዝ መተኪያ የለውም፡፡ በተግባርም እያየነው ያለነው ኢትዮጵያ የተጨባጭ እውቀት ምንጭ አምራች መሆን እየጀመረች መሆንዋ ነው፡፡
ሰንደቅ፡- በቅርቡ “ኢትዮጵያ በአማራ ብሔርና በአርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ መገዛት አለባት” የሚለው አስተሳሰብ ተቀብሯል ሲሉ ተናግረዋል ተብሏል፤ በዚህ ላይ ማብራሪያ ቢሰጡበት።
አቶ ስብሃት፡- አሁን የጠየከኝ ጥያቄን ስብሃት ብሎታል ተብሎ የአማራ ህዝብ ቢሰማ፤ ስብሃት አይልም ነው የሚለው። እንደሱ ብዬ ከሆነና ካረጋገጠም ወንድማችን ታሟልና እናሳክመው ነው የሚለው እንጂ፤ ብሔረ አማራን ስብሃት ሰደበ በሚል ስሜት ቅር አይለውም። እንደሚታወቀው ባለፉት የነፍጠኛ ስርዓቶች ምክንያት የአማራ ብሔር ምንም የተለየ ጥቅም ሳይጠቀም፣ የአማራን ህዝብ እንዲጠላ አድርገውታል። ሳይዘርፍ እንደ ዘራፊ፣ ሳይጨቁን እንደጨቋኝ እንዲቆጠር ተደርጓል። ህዝብ እንደ ህዝብ አይጨቁንም። ስለዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሌሎች ብሔሮች ቀስ በቀስ ሁኔታዎችን እየተረዳቸው ነው። አሁንም እንዳለፈው ተስፋ የቆረጡ ጥቂት ምሁራን ኦርቶዶክስ ሃይማኖትና ብሔረ አማራን ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ። የአማራ ህዝብ በምሬት ከታገሉት የኢትዮጵያ ብሔሮች መካከል አንዱ ነው። ስለዚህም ብሔረ አማራ በዚህ የመንደር አሉባልታ ዳግም መጫወቻ አይሆንም። ጠንካራ ዲሞክራሲያዊና ልማታዊ መስመር የያዘ ፓርቲም አለው። ጥሩ ምሳሌዎች ከሚባሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች አንዱ ነው።
ሌላው፤ ስርዓታችን ማየት ይጠቅም ይሆናል። ህገመንግስቱ ሲያረቁት ሰማንያ በመቶ የሚሆን ስልጣን ብሔር ብሔረሰቦች ለራሳቸው ነው የወሰዱት። አውቀው ስለወሰዱት ብቻ ሳይሆን አውቀውም በንቃት እየጠበቁት ነው። የሚያስተዳድራቸው ራሳቸው አውቀው የመረጡት አካል ነው። በፌዴራል ያለው ስልጣንም በብሔሮች የተመረጡ ወኪሎቹ ናቸው። በቀጥታም በተዘዋዋሪም ይቆጣጠሩታል። የፌዴራል አቋቋምና የኃላፊነት አሰጣጥ ያሸነፈ ፓርቲ ነው የሚያደላድለው። በኔ በኩል አሸናፊው ፓርቲ የተመረጥኩበት አጀንዳ ለመተግበር ሁሉም ከአንድ ብሔር፣ ሁሉም ከአንድ ሃይማኖት፣ ሁሉም ከአንድ ፆታ ካለ ስራው በብቃት ከተፈፀመ ምንም ዓይነት ቅሬታ አይፈጥርም። የተጣራ ስርዓት ለአድልዎ ምንም ዓይነት በር የማይሰጥ በቦታው ስላለ ማንም ሰው ቅር ሊለው አይገባም። በአሁኑ ጊዜ ማንም ግለሰብ ማንም ድርጅት እንደፈለገ አያዘውም። የባጀት ድጎማ ራሳቸው ብሔሮቹ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው የሚወስኑት። ባጭሩ ስርዓቱን ማየት ነው። መስተዋት ነውና እንኳን እኔ ኢህአዴግም ሊያዛባው አይችልም።
በተያያዘም፤ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ምንም እንኳ የመንግስት ጥገኛ ሆኖ በመቆየቱ እጅግ ቢጎዳም በሀገሪቱ በሁሉም መስኮች የነበረው ሚና መተኪያ የለውም። ከመንግስት ይለይ፣ ከፖለቲካ ነፃ ይውጣ ቢባልም አሁንም ከፖለቲካ መድረክነቱ ሊወጣ አልቻለም። የእምነቱ አመራርም ቢሆን የአማኙን መንፈሳዊ ህይወት ሊያረካ አልቻለም። ከዚህ አልፎም አሁን ባለው ሁኔታ ሳይረባበሽ እንደማይቀር ነው የሚገመተው። ለሁለት ተከፋፍለዋል። ይህን መሰል አደጋ ቤተክርስቲያኒቱ አጋጥሞት አያውቅም።
ቤተክርስቲያኒቱ ለሁለት የከፈለው ውጭ ያለው ፓትሪያርክ የሚያራምዱት እንቅስቃሴ መሆኑ በስፋት ይታመናል። ይህ አልበቃ ብሎ የአሜሪካው ሲኖዶስ የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚደግፍ ይወራል። አገር ውስጥ ያለው ሲኖዶስም የቤተክርስቲያኒቱ ህልውና ቆርቁሮት ተነስቶ ይህን ድርጊት አላወገዘም። የእስልምና አክራሪነት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ደጋፊ ከሆነም መንግስት እርምጃ መውሰድ ነበረበት። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ትኩረት ካልሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አመራር ለሃይማኖቱም ሆነ ለአጠቃላይ ለስርዓቱም አደጋ ወደ መሆን ተቃርቧል። እነዚህ ችግሮች ፈጥነው ከተወገዱ ግን እምነቱ በእምነቱ ፀጋነቱ ይቀጥላል። እስካሁን ድረስ የፖለቲካ መድረክ ሆኖ መቀጠሉ ግን ብልሽቱ የውስጡ የአመራሩ የራሱ ነው። በርካሽ ጥቅማቸው ውስጡ ቢዳከም ሌሎችን መጫወቻ ማድረግ ነበረባቸው ማለት አይደለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡
ሰንደቅ፡- ከሰሞኑ በአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ዝርጋታ ጋር በተያያዘ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት እንደሚነሳ ተገልጿል። ይህም ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ውዝግብ አስነስቷል። በአንዳንድ ወገኖች ኢህአዴግ ለአለፉ የሀገሪቱ ታሪኮች ቦታ ስለማይሰጥ ነው የሚል ክስ የሚያቀርቡ አሉ። እርስዎም በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ስብሃት፡- ስለ አዲስ አበባ ማስተር ፕላን ማለት መንገድ በየት ያልፋል፣ ምን ህንፃ ይሰራል፣ የት ወዘተ ምንም የማውቀው የለም። ሲፈርስ፣ ሲሰራ፣ የሚሰራውም ሲዘገይ ነው እንደማንኛውም ሰው የማየው። ምንም እንኳን የልማት አቅጣጫችን ከገጠር ወደ ከተሞች ያተኮረ ቢሆንም ከተሞች ተገቢ ትኩረት ማግኘት አለባቸው የሚል እምነትም አቅጣጫም አለ። ያለፉት ስርዓቶች የተውልንን የከተማይቱ ጉድ ያልተማረም በዓይኑ ቁልጭ ብሎ ስለሚታየው ምንም ዓይነት የስታትስቲክስ ማስረጃ አያስፈልገውም። አዲስ አበባ ከተማ አልነበረም። እኛ ከተማ እንዳልሆነ መገንዘባችን ታላቅ እርምጃ ነው። ከዚህ በመነሳት ከተማ ለማድረግም ተጀምሯል። እያፈረስክ ነው የምትገነባው። ማፍረስና መገንባት መጠገን አያቋርጥም። እኛ የሰራነውም የሚቀጥሉ ትውልዶች ለነሱ እንደሚመች አፍርሰው ይገነባሉ። ከበፊቱም እኛ ከሰራነውም ለቅርስነት የሚቆዩ ይኖራል። እድገት ማፍረስና አብልጦ መገንባት ነው። እንደኛ እያፈረሰ አብልጦ የሚገነባ ሰው ነው ከወዲሁ መፍጠር ያለብን። ከአባቶቻችን በልጠን ስለተገኘን ነው፤ አዲስ አበባ ለህዝባችን የበለጠ እንደምትመች ለውጭ ተመልካችም ክፉ እንዳትሆን እያፈረስናትና እየገነባናት ያለነው።
እንዳልከው የታላቁ አቡን፣ የብፁዕ እና ጀግናው ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት እንደሚነሳ እኔም ሰምቻለሁ። እውነት የሚነሳ ከሆነ ለአዲስ አበባ ህዝብ ምቾት ነው ሊሆን የሚችለው። ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ የህዝቦች ታሪክና ለኢትዮጵያ ጀግኖች ካለው ክብር ተነስቼ ሳየው
ቢያንስ ሐውልቱ እንዳለ በተሻለ ቦታ ይቆማል። እኔ እንደምገምተው ግን ሌላ የቅርስነትና የሞያ ችግር የማይፈጥር ከሆነ በጣም ግዙፍና ታሪካቸውን በሚገልጽ መልኩ እንደገና ተሰርቶ ከፍ ባለ ቦታና ብዙ ሰው በሚያየው አደባባይ የሚተከል ይመስለኛል።
ኢህአዴግ ለታሪካችን ቦታ አይሰጥም የሚለው መነሻው ከየት እንደሆነ አላውቅም። ኢህአዴግ በታሪክ እያላዘነ፣ ታሪክ እየረገመ፣ ታሪክ እያደነቀ አይኖርም ብትል ትክክል ነው። ከታሪክ ይነሳል እንጂ በታሪክ ብቻ አይኖርም። በጎም ይሆኑ መጥፎ ከሁለቱ ተምሮ ህዝብን እንደመነሻ ወስዶ ታሪክ ለመስራት የተነሳ ነው ኢህአዴግ። ህውሓት ከወሰድን እንደድርጅትም እንደ ክልል መስተዳድርም የታሪክ ቅርስ ዓርማው አድርጎ ነው ትግሉ የጀመረው። ኢህአዴግም ያሳለፍነው የባከነ ዘመን እያስታወሰ “ቁጭት” የሚል ፅሑፍ ዘርግቷል። ብዙ ሊቃውንት፣ አርቲስትና መለስ የተካፈሉበት “እንደገና” የሚል ገናናው ታሪካችን የሚያስታውስ ዶክመንተሪ ፊልም ተሰርቷል፤ በቴሌቭዥንም ተላልፏል። ታሪካችን በተሟላ ሞያዊና ትክክለኛ በሆነ መንገድ ባለመፃፉ ወይም ተፅፎ ከሆነ ባለማግኘታችን ትክክለኛውን ትምህርት አልወሰድንም ልንሆን እንችላለን።
እኔ በበኩሌ ከታሪካችን መታወቅ አለባቸው የምላቸው ባጭሩ የነበረውን ስርዓትና ተጨባጭ ሁኔታ ሳንለቅና ዘመናዊ የምትባለውን ኢትዮጵያ መነሻ በማድረግ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ብንመልስ ይጠቅም ይሆናል። እነዚህም፤ መስራት የሚገባንና መስራት የምንችለውን አሟጠን ሰርተናል ወይ?፣ አፈፃፀሙስ ምን ያህል ትክክል ነበር?፣ ማድረግ ያልነበረብን አድርገናል ወይ?፣ የኢትዮጵያ ፊውዳሊዝም በምን ምክንያት ነው ከሌሎች አገሮች ፊውዳል ስርዓቶች የከፋና ዕድሜውም የረዘመ የሆነው የሚሉ ጥያቄዎችና ሌሎችም ካሉ የሚመልስ ታሪካዊ ፖለቲካዊ ወዘተ ፅሑፍ አጥርተን ብንይዝ ለወደፊት እንዳንሳሳትና እንዳንተኛ ተጠንቅቀን እንድንሄድ ይረዳናል የሚል እምነት አለኝ። ወይም ይህ የመሃይም ሀሳብ ነው ከተባለም ከራስ መማር መተኪያ ስለሌለው ሙሁራን በሚመስላቸው ትክክለኛውን ታሪካችን ማስተማር ቢጀምሩ የጋራ መከራችን ለአንድነታችን ምንጭ ይሆናል። ኢህአዴግ ለታሪክ ደንታ የለውም ማለት ግን ተረት ብቻ ሳይሆን የተረት ተረትና በተለያዩ ምክንያቶችና ከተለያዩ መነሻዎች ተነስተው የተወሰኑ ተስፋ የቆረጡ ምሁራን የሚያናፍሱት የስም ማጥፋት አጉል ሙከራን አይገነዘብም ማለቴ አይደለም።
ሰንደቅ፡- ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ በኢህአዴግ ውስጥ ክፍፍል ተፈጥሯል የሚሉ ወገኖች አሉ። እነዚህ ወገኖች አንደኛው ቡድን በእርስዎ እንደሚመራም ይገልፃሉ። ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
አቶ ስብሃት፡- በኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና በኢህአዴግ ራሱ በየወቅቱ የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ነበሩ። በታወቀው የድርጅቱ መዋቅርና ስርዓት ውይይት ይደረግበታል። ስምምነት ሲደርስ ተግባራዊ ይሆናል። በዚህ ሂደት ኢህአዴግ ራሱን በቀጣይነት እያደሰ ቆይቷል። እስካሁን ድረስ በድርጅቶቹ ይሁን በኢህአዴግ መከፋፈል የሚባል ነገር አጋጥሞ አያውቅም። በዚህ ሂደት በተለያዩ መለኪያዎች ለኢህአዴግ ብቁ ያልሆኑ ሰዎች ይባረራሉ ወይ በራሳቸው ለቀው ወደ ሚመጥናቸው “ድርጅት” ሄደው ይወሸቃሉ ወይም በልካቸው አዲስ “ድርጅት” ይፈጥራሉ። ኢህአዴግ ግን ጥንካሬውን ይዞ ይቀጥላል። አሁን በኢህአዴግ የሚታይ የሚሰማ ፖለቲካዊ ጥያቄ ያለ አይመስለኝም። ካለም ያው እንዳለፈው ጸጋ ነው። መከፋፈል ግን አይፈጥርም። በአፈፃፀም ዙሪያ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ። መኖርም አለባቸው። ብዙ እርምት የሚያስፈልጋቸው የአፈፃፀም ድክመቶች አሉ።
ሰንደቅ፡- ሰሞኑን በትግራይ ተምቤን ወረዳ ውስጥ በአሉላ አባነጋ ስም ይጠራ የነበረውን ት/ቤት በአቶ መለስ ስም እንዲጠራ ተወስኗል የሚል በመገናኛ ብዙሃን በስፋት ተዘግቧል። ይህ አሰራር ታሪክን ጠብቆ ከማቆየት አንፃር ምን ያህል አግባብ ነው ይላሉ?
አቶ ስብሃት፡- አልተወሰነም። አይወሰንም። ህወሓት እና የትግራይ ሕዝብ ታሪክ ምን እንደሆነ ጠንቅቀው የሚረዱ ናቸው። ለመሆኑ ለምን ትግራይን አትጠይቅም!!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar