I wish democracy and unity for Ethiopia
ያልሆንከውን ለመሆን! (ትችቴ ለተቃዋሚ እስላም ወገኖቼ)
ጌታቸው ረዳበኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ተቃውሞ አሰሙ በሚል ርዕስ አልጀዚራ በአረብኛ ያስተላለፈውን ዜና ሳዳምጥ የዜናውን ዝርዝር ሁኔታ የተቀረጸው ስዕለ-ድምፅ/አውድዮ ቪዲዮ የታየው ገጽታ “ኢትዮጵያዎች” ሲሆኑ፤ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ቋንቋ ግን “ዓረብኛ” ነበር። የተጠቀሙበት ዓረባዊ ቋንቋ/ መፈክር/ መላው ዓለም በሚከታተለው የዜና ማስተላለፊያ ጣቢያ ስእለ ድምጹ ተለቅቆ ሳዳምጥ “ክው” ነበር ያልኩት! ለምን? የሚል ጥያቄ ድቅን አለብኝ። ቁጭትም፤ሃዘንም፤ውስጣዊ ስበራትም ጨመረብኝ።ሃዘኔ መልስ ሊያስገኝልኝ አልቻለም። መልሱ የሚገኘው ከነዚህ ወገኖቼ ነውና ጥያቄየን ለነሱ ላቅርብ። ቁጭቴ፤ ሃዘኔም ይሁን ብስጭቴ በነዚያ ምስኪኖች ላይ ሳይሆን የነዚህ ምስኪኖች ሕሊና ያጠቡ ቅኝ ገዢ ዓረቦች እና ተባባሪ የውስጥ አርበኞቻቸው ላይ ነበር። እነዚህ ወገኖች የሃዘኔ መነሻ ከምን እንደመነጨ እንደሚረዱልኝ ተስፋ አለኝ። ካልተረዱልኝም ፤ታሪክ አንድ ቀን ጠያቄየን ሊመልሰው ይችላል የሚል ተስፋ አለኝ። እውነቱን ተናግሮ በመሸበት ማደር የኔ ምርጫ ሀኖ አግኝቼዋለሁና የሚወረወርብኝ ፍላጻ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።
እኔ እስከማስታውሰው ድረስ የ1966 አብዮት የኢትዮጵያ እስላሞች ጥያቄአቸውን/ ተቃውሞ ሲያስሰሙ መፈክሮቻቸው ሁሉ በአረብኛ ሳይሆን በሚኰሩበት በአገራቸው ቋንቋ በመጠቀም ነበር ባደባባይ ለዓለምና ለታሪክ አስመዝግበው ያለፉት። ታዲያ የዛሬ የ2012 (ፈረንጅ ዘመን) 2004 (ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር) ወጣቶች ምን ነካቸው?
ኢትዮጵያ የቋንቋ እና የባሕል እናት እንደሆነች ለእነዚህ እንደ እኔ እኩል በዛች በተባረከች ጥንታዊት አፈር ለተፈጠሩ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቼ/እህቶቼ የሆኑ ዜጎች ሳስታውሳቸው እውነታው እነሱም እንደማይስቱት ተስፋ አደረጋለሁ። ባጭር አማርኛ “የቋንቋ ድሆች አይደለንም”። የኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ቋንቋን ንቆ “በዓረብኛ” ቋንቋ በመጠቀም፤መፈክሮችን እና መልእክቶችን ለዓለምም ሆነ ለኢትዮጵያ ወገኖቻቸው ማስተላለፍ ወይንም የዓረብ ቋንቋ መጠቀም “ሃይማኖትን” አያመላክትም። ምክንያቱም ዓረብኛ ሃይማኖት ሳይሆን ቋንቋ ነው፡ መነጋገሪያ መሳሪያ ነው። ዓረብኛ የእስላሞች ብቻ ሳይሆን የክረስትያኖችም ጭምር ነውና የእስልምና ቋንቋ ነው ብለው ከሆነ ተሳስተዋል እና የእስላሞችን መብት ለማስጠበቅ ዓረብኛን ከማስተጋባት ጋር በምንም መንገድ አይገናኝም።
ታዲያ ዓረብኛ የእስላሞች ቋንቋ እንዳልሆነ ከተማመንን እንኚህ ኢትዮጵያዊያን እስላሞች ለምን ከኢትዮጵያ አገራቸው ብሔራዊ ቋንቋ “አማርኛ” ይልቅ የባዕድ ቋንቋ የሆነውን ዓረብኛን አዲስ አበባ አንዋር መስጊድ ውስጥ ባካሄዱት ሰላማዊ የመብት ጥያቄ /ተቃውሞ/ ላይ ያስደመጡን መፈክር ለምን የዓረብኛ ቋንቋን ቅድሚያ ሰጥተው የመልእክታቸው ማስተጋቢያ እንዲሆን መርጠው በመላ ዓለም አንዲሰተጋባ እና እንዲደመጥ ምርጫቸው ሆነ? ከወንድሞቻችን /እህቶቻችን የተደመጠው አረባዊ ፣መፈክር ሊቢያ “ጋዳፊን’ ለማውረድ፤ ቱኒዚያ ውስጥ አሚርን ለማውረድ ፤ እና “ሙባረክን” ለመቃወም “ካይሮ ግብፅ ውስጥ ‘በታሕሪር አደባባይ” ላይ የተስተጋባው ዓረባዊ መፈክር እና ባብዛኛዎቹ አረብ አብዮት አደባባዮች የተካሄደ የዓረቦች አገር በሚመስል መልኩ ነበር የተስተጋባው ።ለምን? ይህ ዓረባዊ መፈክር በገላጭነቱ ከአገራችን ኢትዮጵያዊ ቋንቋ በምንኛው መመዘኛ ነው መፈክሩን ለማስተጋባት ተመረጠው?
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕዝብ እንዲያደምጣቸውም ሆነ ብሶታቸው ለማስተላለፍም ሆነ ድጋፍ ለማግኘት ሕዝቡ በሚጠቀምበት ብሔራዊ ቋንቋ መጠቀም ያሳፈራቸው ሚዛን ምን ይኖራል ብለው ይሆን? ወይንስ እንደዘመኑ ወረርሺኝ “አማርኛን” የመጥላት እና የነፍጠኞች ቋንቋ ስለተባለ እነሱም በዛው በተሳሳተው ዘመን አመጣሹ የወያኔ፤የኦነጐች እና የኦጋዴን ሶማሌ ብሔራዊ ነፃ አውጪዎች የተሳሳተ የአማርኛ ቋንቋ ጥላቻን ለመከተል? መልሱ ለነዚህ ውንድሞች ልተወው። አረቦች በተለይ ቱኒዚያ ውስጥ ደምቆ የወጣው መፈከር እና እንዲሁም ግብፅ፤የመን፤ባህረይን፤ሶርያ እና ሌሎችም ውስጥ “አላህ አክበር” እና “Ash-shaʻb yurīd isqāṭ an-niẓām (الشعب يريد إسقاط النظام “ሕዝቡ ይህ መንግስት ከስልጣኑ እንዲወርድ ይፈልጋል” የሚለው ዓረባዊ አቀፍ የአብዮት መፈክር ሲስተጋቡ፤ ኢትዮጵያዊያን እስላሞች ደግሞ አህባሽ ከመጅሊሳችን ይውጣ ከሚለው የአረብኛ መፈክራቸው ሌላ በዚህ ስዕለ ድምፅ ላይ የምትመለከቱት ተቃዋሚዎቹ የተጠቀሙበት ዓረባዊ ቋንቋ “አላህ ወአክበር!” “አላህ ኢለላህ!” እና በደምብ የማይደመጠው የሚከተለውን ዓረባዊ መፈክር እና የጣት ቅሰራ ስታይል/ ቅጅhttp://youtu.be/Lm4krGL9TZw ስትመለከቱት የመጀመሪያው ቪዲዮ ይላል አንድ ተንታኝ ሲያስረዳ “Infact if you watched the first video, they are already chanting the Egyptian revolutionary slogans.”ይላል። (መፈክሮቻቸው ይመሳሰላሉ ወይስ አይመሳሰሉም በሚለው ሳይሆን ትኩረቴ- ቋንቋው ላይ ነው) ። “አልጀዚራ ውስጥ የተላላፈው ዜና ሳዳምጥ ጭራሽኑ ቋንቋው እና የተቃዋሚው መልክ የማይገናኝ፤የወተት እና የኑግ ቅብ/ከለር አብሮ የማይሄድ “ያልሆንከውን ለመሆን መመኮር ያህል ነበር”።
ኢትዮጵያዊያን እስላሞች ኢትዮጵያዊያን እንጂ አረቦች አይደሉም። ታዲያ ለምን አረብኛ አስፈለገ? “አላህ ወአክበር እና ኢላህ አለላህ!” የሚሉ “ሃይማኖታዊ” መፈክሮችና እና ያስተጋቧቸው አስተዳደራዊ የመብት ጥያቄዎች ኢትዮጵያዊ ቋንቋቸው በሚገባ ሊገልጽ እንደሚችል ማንኛችንን የምናውቀው እውነታ ነው። ታዲያ ለምን ያልሆንከውን ለመሆን አረባዊ ቋንቋን መበደር አስፈለገ? አረቦቹ ሲሰለፉ ሰንደቃላማቸውን አሸብርቀው እያውለበለቡ ነበር ያየናቸው በእኛዎቹ እስላሞች ግን ሚሊዮን ተቃዋሚ ሲሰለፍ ያገራቸወን ሰንደቃላማ ለብሰውም ሆነ አሸብርቀው ይዘው ተውበው በክብር በዓለም ፊት ኮርተው ላለመታየት ያገዳቸው ምስጢሩ ምን ይሆን? ሚሊዮን ሕዝብ ወጣት ሲሰለፍ ሚሊዮን ሰንደቃላማ አውለብልበው ቢታዩ ኖሮ ምንኛ ባማረባቸው ነበር? አለመታደል ሆኖ እንደ ወጣት አረቦቹ ኢትዮጵያዊ ሰንደቃላማቸውን ለብሰው /አውለብልበው ይህንን ግርማ ሊያሳን አልበቁም፡ ለምን?
በስእለ ድምጹ አንዳየነው በሰልፉ ላይ የተሳተፉት አብዛኛዎቹ ወጣት እስላሞች ናቸው። እነኚህ ወጣቶች ጀግኖች ወላጆቻቸው ኢትዮጵያዊያን የሚያኮራ ቋንቋና ሰንደቃላማ አበርክተውላቸው አንደሄዱ ያውቃሉ? ባንድ አሜሪካ የዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር የሆነ ካንድ ከማውቃቸው ኢትዮጵያዊያን ቤተሰብ ጋር የተዛመደና ለኢትዮጵያ ያለው ፍቅር ከፍተኛ በመሆኑ የእስላሞቹ ተቃውሞ በኢትዮሚዲያ ላይ የተለጠፈው “ስእለ ድምጽ” ተመለክቶ ኖሯልና በአልጀዚራ የተላለፈው የአረብኛ ዜና አረብኛ መሆኑን ቢገነዘብም ተቃዋሚዎቹ ያስተጋቡበት መፈክር ምን እንደሆነ ስላልገባው ቤተሰቡም ሆነ እኔኑንም ስለተጠቀሙበት ቋንቋ ለማወቅ ምን እንደሆነ እንድነግረው ደውሎ ሲያነጋግረኝ እኔ ለራሴ “መፈክራቸው” ዐረብኛ በመሆኑ ምን እንዳሉ ስላልገባኝ “አሁን ስራ ላይ ነኝ እና ዝርዝር ሁኔታው እነገርሃለሁ ብየ የተሰማኝን ውስጣዊ ስብራት ሸፍኜ በዘዴ አሰናበትኩት”።
ሚሊዮን የሚገመቱ ሰልፈኞች የተጠቀሙበት ቋንቋ “አረብኛ” ነው እና አልገባኝም ብየ ብነግረው “ኢትዮጵያዊያን ሆነው እንዴት የራሳቸው የመነጋገሪያ እና የመጻፊያ ቋንቋ እያላቸው በአረቦች ቋንቋ መልእክታቸውን ለማስተላለፍ መረጡ?” ቢለኝ ምን ብየ አንደምመልስት እኔኑም ግራ ስለገባኝ እስኪ ይህ ጥያቄ ለኔ ስትሉ ሳይሆን ለባእድ ጠያቂዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ሲያቀርቡላችሁ መልሳችሁ ምን ይሆን?
የሃይማኖት ተከታዮች በሚያንጸባርቁት የተሳሳተ “ባሕልን የሚጻረር” “አለባበስም ሆነ አነጋጋር” ሲከተሉ የሚወቅስ/እንደኔው ዓይነቱ የሚጽፍ ጸሐፊ/ተቺ ሲያገኙ “እጅግ ያወግዙት ይሆናል”። ጭራሽኑ አንዳንዶቹ ደናቁርት ምሁራን ተብየዎችም “በሃይማኖት ላይ ጣልቃ አትግቡ፤ጭጭ በሉ፤ወደ ሌላ መንገድ ይወስደናል፡……” መንካት መነካካት “የተከደኑት ትሎችን የባሰውኑ ያፈላቸዋል/እንዲባዙ ያደርጋል…. እንደ ጸረ እስላም ሆኖ ይተረጎማል//////ወዘተ/ .” በማለት ውዥምብር ውስጥ ሊከቱህ ይሞክራሉ። በኔ በኩል ይሄ አይሰራም።
ምክንያቱም፤ፈረንጆች “The more we study the more we discover our ignorance”. ይላሉ። ባንድ ጉዳይ ላይ ተከታታይ ጥናት ስናካሂድ ድንቁርናችን የት እንደሆነ ለማወቅ የማይነካውን መንካት ምንነቱ ለማወቅ ይረዳናል።” እስላሙም ሆነ ክርስትያኑ ወጣት የአገሩ ሉአላዊ እሴቶች ምን እንደሆኑ እና ለአገሪቱ ማገርና ዋልታዎች ያለው ክብር እጅግ የደነቆረ ግንዛቤ አንዳለው ሁላችንም እንመን። ጐልተው የሚታ የእስላም ወገኖቻችን እና የክርስትያን ወገኖቻችን ድክመቶች ወደ ሕዝብ ጀሮ እና ዓይን ማድረስ ተገቢ ነው። ክርስትያኖች (ኦርቶዶክሶችን ነው) ያላቸው ላገራቸው ቋንቋ አጠቃቀም ክብር አና የሰንደቃላማ ልዕልና እስላሞቹም እኩል መራመድ ይኖረባቸዋል። ሌላ ቀርቶ የተሰበሰቡበት መስጊድ በኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ማሸብረቅና ማስዋብ ክብር እንጂ ውርደት አይደለም፡ አብዛኛዎቹ የክርስቲያን ቤተጸሎት ውጪያቸው እና ደጅያቸው ባገሪቱ ሰንደቅ ሲያስውቡ ለምን መስጊዶች እንደዚያ አሸብርቀው አንደማይታዩ ለኔ ግልጽ አይደለም። ሁላችንም መወያየት ያለብን የአገር ከብር እና ሉአላዊ ግዴታን የማንነት ሃቅ እየመነመነ ሲሄድ አንድ ቦታ ቆም ብለን ችግሩ አንዳይቀጥል ፖለቲከኞች፤ሃይማኖት እና የሳይንስ እንዲሁም የሕብረተሰብ ምሁራን እና ጸሐፍቶች በጉዳዩ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል።
ስርአቱ የአገሪቱን ክብሮች ሲንቅ ሰርአቱን ስለጠላነው እኛም አብረን የውጭ አገሮች መሳሪያ የሆነው የወያኔ ስርዐት እሴቶቻችንን ስለጠላቸው እኛም እሱን ተከትለን ከጣልናቸው የመብታችን ጥሰት ተጠያቂዎቹ ስርአቱ ብቻ ሳይሆን እኛም ጭምር ነን።
እኔ ካናዳ ውስጥ በሃዋርያ ጋዜጣ ላይ ከ16 ዓመት በፊት ይመስለኛል እስላሞችን በሚመለከት ያላቸውን ጭቆና በሰፊው ጽፌአለሁ። ብዙ የምስጋና ንግግርም አሜሪካ ሳንታክላራ እስላሞች መስጊድ ውስጥ እና በሌሎች ከተሞች መስጊዶች ውስጥ ባደረጉት ስብሰባዎች ጋዜጣውን በማንበብ በጻፍኩት ላይ ከፍተኛ ምስጋና እንደተቸረኝ አብዱል በተባለው የድሮ ጓደኛዬ እንደተነገረኝ አስታውሳለሁ።ለዚህም ምስጋናየን በዚህ አጋጣሚ አቀርባለሁ። ቢሆንም ከዚያ በሗላም ጭቆናቸውን ብቻ ሳይሆን ማስተጋባት ያለባቸው እነሱም እሳለሞቹ እራሳቸውም ቢሆን ኢትዮጵያዊነታቸውን/ዜግነታቸውን፤ ከሄደ ወይንም ከሚመጣ ወይንም ካለው ከሚጨቁናቸው መንግስታዊ ሰርዓት ጋር ማያያዝ ፤ማፍረስ፤መቀጠል፤ መበጠስ እንደሌለባቸውም አስታውሼአቸዋለሁ።
ምክንያቱም ጭቆናቸው ወይንም ብሶታቸው ከስርዓቶች ጋር አያይዘው የዜግነታቸው ምንጭ የባህላቸው፤የቋንቋቸው ሰጪ እና ከልካይ አድርገው ካቀረቡት፤ ባህላቸው፤ሃይማኖታቸው፤ቋንቋቸው(ጠቅላላ የዜግነታቸው ምልክቶች የሆኑት/እስቶች/ዋና ዋና መልህቆቹ በሰርዓቶች ምክንያት የዜግናታቸው ምልክቶች/ዓርማዎች በሌላ የባሕር ማዶ የባእድ ቋንቋ፤አለባበስ፤ዜማ፤ እምነት፤አመጋገብ እና አኗኗር፤በመቆጣት ወይንም በብስጭት እና ስርዓቱ ደስ አይበለው እልክ ውስጥ በመግባት የሚተኳቸው ከሆነ፤ የዜግነት ትርጉም በቅጡ አልገባቸውም እና ግልጽ የሆነ ትችት እና ውይይት መካሄድ አለበት እላለሁ።
አንድ ማሕበረሰብ እስላሙም ሆነ ክርስትያኑ ወይንም ሃይማኖት የሌለው ዜጋ በአገሪቱ ሰንደቃላማ፤ ጀግኖች፤ባሕሎች፤አለባበሶች በጠቅላላ “Organic” አገራዊ/አገር በቀል የሆኑ መሰረቶቻችን ካላመኑ እና እነኚህ “አገራዊ መብቶችን” ካልተቀበሉ እና አክብሮት ካልሰጡ ጎድሎብናል ብለው የሚጠይቋቸው መብቶች ሲያቀርቡ “በተጓዳኝ አብሮ የሚሄዱ እነሱም ማክበር ያለባቸው ያገሪቱ መሰረታዊ የዜጎች ግዴታዎች አክብራችሗል ወይ?” ተብለው ሲጠየቁ ማክበራቸውን በበቂ መመለስ ይኖርባቸዋል።
በኤስያ አገሮች፤ በላቲን፤ አፍሪካ፤በቸችኒያ እና በመሳሰሉት አካባቢዎች እስላሞች የመብት ጥያቄ ሲያቀርቡ የሚጠቀሙበት ቋንቋ የያገራቸው ቋንቋ እንደሆነ ይህ ጽሑፍ ሳገናዝብ የታዘብኩት ነው። አሁን ያለቺው ሚስኪንዋ ኢትዮጵያ የወለደቻቸው ወጣቶች የሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች፤ የሚዘፍኑት እና የሚወዛወዙት ቅላጻ/ዳንኪራ፤አለባበስ፤አረማመድ እንዲሁም የስማቸው መጠሪያ ሁሉ የባዕድ ስም ሆኗል። ባለፈው ሁለት ወር ያቀረብኩት ትችት “አዲስ አበባ” ውስጥ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ት/ቤቶች/ንግድ ቤቶች/ጎደናዎች/የጋዜጦች የመጠሪያ ስም/የራዲዮ እና የስእለ ድምፅ መገናኛ ጣቢያዎች ሁሉ የባዕድ ስም እንደሆነ አገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ጋዜጠኞች የቀረበው ማስረጃ በማጣቀስ እንድትመለከቱት ማቅረቤን ይታወሳል። ይህ የባሕል ወረርሺኝ በሰፊው ሲዘመትብን የሃይማኖት መሪዎች ቅድሚያ ተሰልፈው ጥቃቱን ማስቆም ሲገባቸው እነሱም በዛው የባህል ወረርሺኝ ተካፋዮች/ተጠቂዎች ሆነዋል። ታዲያ ለማን ይጮህ?
አስቀድሜ ለመግለጽ እንደመኰርኩት ዓረብኛ የእስልምና ቋንቋ እንዳለሆነ ተናግሬአለሁ። ዓረብኛ የዓረቦች እንጂ የእስልምና ቋንቋ አይደለም። ሃይማኖት ቋንቋ የለውም። ክረስትያን ዓረቦችም ቋንቋቸው አረብኛ ነው። ዓረብኛ ከመፈጠሩ በፊት እስልምና አልተፈጠረም። ስለሆነም እስልምና ከመፈጠሩ በፊት አረብኛ እስልምና የማይከተሉ ወይንም ሃይማኖት ያልነበራቸው የአረብ ዜጎች የመነጋገሪያ ቋንቋ እንጂ እስልምና ሃይማኖት የፈጠረው ቋንቋ አይደለም። በዚህ ተማምነን የኢትዮጵያ እስላሞች ቋንቋ ሳይቸግራቸው ለምን አረብኛን ቀዳሚ መቀስቀሻ መፈክራቸው ሆኖ በዓለም ፊት ሊደመጥና ሊስተጋባ ቀዳሚ መፈከሪያቸው እንዳደረጉት ለኔ ግልጽ አይደለም።
እስላም ወገኖች ሲጸልዩ ለምንድነው በዓረብኛ የሚጸልዩት? ለምንስ እሳለማዊ ቅዱሳን መጻሕፍት ቢያንስ በብሔራዊ ቋንቋችን በአማርኛ ተጽፎ የመጸለያ ቋንቋ በማድረግ ዓረብኛውን አያስወግዱም? ቋንቋችን የላንቃ ፤የልሳን ሃዲዶች የያዘ እንደሆነ እያተወቀ እና ያውም ይበልጥ ዓረብኛ ያላካተታቸው ብዙ ፊደሎች በራሳችን ፊደሎች ውስጥ እያሉን ለምን አረብኛ ተመረጠ? የሚል ነበር እስላም ጓደኞቼን ያነጋገርኳቸው። ሲያስረዱኝ (ሌሎች እንደሚሉት ብለው ነው ያስረዱኝ) ቁርኣን ቢተረጐም ፤ሲተረጎም የትርጉም መዛባት ያመጣል ይላሉ፤ለዚህ ነው። ብለው መልስ ሰጡኝ።
በኔ በኩል ይህ ምክንያት በቂ አይደለም። ስለተሰበኩ እውነት የመሰላቸው ደካሞች የተቀበሉት ወይንም አረቦች ሆን ብለው ወደ እየ አገሩ ቋንቋ ቢተረጐም መልእክቱ ይዛባል በማለት ሽፋን በመጠቀም “አረብኛ በመላ ዓለም ህያው ሆኖ እንዲቆይ” የሚጠቀሙበት ተንኮል መሆኑን አትጠራጠሩ። ምክንያቴ አጭር ነው። መጀመሪያ ሃይማኖት በተለይ አላህ በፈጠርኩላችሁ የገዛ ቋንቋ መነጋገሪያችሁ እንደትነጋገሩበት እና እንድተማማሩበት እንጂ “በዓረብኛ” ብቻ እንዲሰበክ ብሎ ማስተማሩን እጠራጠራለሁ። ሃይማኖት እንዲስፋፋ ከተፈለገ የያንዳንዱ ሕብረተሰብ መነጋገሪያ ልሳኑ ተጠቅሞ “አላህን/ፈጣሪን” ቢያመሰግን ምንም ኩነኔ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ።
ሌላው ምክንያት ቁርአን ተጽፎበታል በሚባለው አረብኛ ቋንቋ እራሱ በሚጠቀሙ አረቦችም መካካል የተለያየ አረብኛ እንደሆነ የምናውቀው ሃቅ ነው። ተማሩ የሚባሉት ሼኮች/ቃዲዎች/ሙላህ/ሓጂዎች….. ሲያስተረጉሙት ብቻ ሳይሆን ሲሰብኩበትም የቁርዓኑ መልእክት/ይዘት አባባል የየራሳቸው አተረጓጐም ስለሚጠቀሙ አንዱ ሺዓ/አ አንዱ ሱኑ፤ አንዱ አሕባሽ፤አንዱ ዋሃቢ አንዱ ሱፊ፤ አንዱ አሕማድያ፤ ወዘተ… ወዘተ… በማለት ቅራኔ ውስጥ ሲገቡ “አረብኛ” ስለተጻፈ/ስለተሰበከ ቅራኔው/ልዩነቱ ሊያስወግደው አልቻለም። ስለዚህ አረብኛው ቁርአን ተተርጎሞም ሆነ ቅዱሳን የእስልምና የጸሎት ድርሳኖች/መጽሐፍቶች በአማርኛ ተጽፈው ባማርኛ ጸሎት ቢያካሂዱ ቅራኔው/ያመለካከት ልዩነት ልክ እንደ አረቦቹ ሰባኪዎች እንደተጠበቀ ሆኖ “ባገራቸው ቋንቋ ስለሰበኩ እና ጸሎት ስላደረጉ” የበለጠ ክብር እና የማንነት ኩራት ያላብሳቸዋል የሚል እምነት አለኝ። ባጭሩ ለማለት የፈለግኩት ግጭቱ ያስከተለው “አማርኛ ስለተጠቀሙ ሳይሆን አረቦችም በአረብኛም ጽፈው እና ሰብከውም ቢሆን እርስ በርሳቸው የሚያሳዩዋቸው ግጭቶች/ልዩነቱ ሊያስቆሙት አልቻሉም። አረብኛው ከግጭት ማስጣል ካልቻለ ‘ቅራኔ ለቅራኔው” አማርኛውን/ተጠቅሞ ጸሎት በማድረስ የራስን ማንነት አጥብቆ መያዝ አዋቂነት ነው።
እስላሞች የሚለብሱት ረዢም የዓረቦች ቀሚስ ሒጃብ፤ ቡርቃ፤ ጁባህ ወዘተ….ወዘተ…..የአረቦች ልብስ እንጂ እስላሞች ልብስ የግድ አይደለም። ረዡሙ እና ስሱ ልባሳቸው እስልምና ከመፈጠሩ በፊት ሲለብሱት የነበረ ላሀሩሩ የምድረባዳው አረብ የተመረጠ አማራጭ/ተስማሚ “ባህላዊ የአረቦች ልብስ” አንጂ ለእስላሞች ብቻ የተሰጠ ልብስ አይደለም። ያሁኖቹ ወጣት እስላሞች ግን በጠለቀ ሁኔታ አረባዊ አለባበስ አጥቅቷቸዋል። ለምን?
የአገራችን እስላሞች የጥንቶቹ ኢትዮጵያዊያን እስላሞችን ስትመለከቱ በግብርናው ገጠርም ሆነ በከተማው ኢትዮጵያዊ አለባበሳቸው እና ባሕሪያቸው አንደጠበቁ ሆነው ነበር ያሳደጉን እና ስናከብራቸው ፤ስንዛመዳቸው ስንወዳቸው ሲወዱን የቆዪት። ቋንቋችን፤ አለባበሳችን፤ አነጋገራችን፤አካሄዳችን እና ባሕሪያችን ኢትዮጵያዊ እንዲሆን የዜግነት ግዴታ ነው። ባህሎቻችን ከተጠቁ መብራቶቻቸን ናቸው እና ለእንቅፋት እና ለሕሊና ባርነት እንጋለጣለን።
ባሕሎቻችን ጨለማ ውስጥ ታስረን በምንገኝባት በዛሬቷ የወያኔ ኢትዮጵያ እስር ቤት ውስጥ በፈተና ማዕበል ሕሊናችን ታውሮ ስንንገዳገድ የሚመመሩን የማንነት ምርኩዞቻችን ናቸው።የተስፋ ጨረሮቻችን ናቸው እና ተስፋ ለመጨበጥ ብሔራዊ እሴቶቻቸን እንዳይጠቁ የመጠበቅ አደራ አለብን።
በዚህ አጋጣሚ ብዙ ኢትየጵያዊ ብሔራዊ ጀግኖች እስላሞች እንደ ዝነኛው ገጣሚና የሰብአዊ መብት ተሟጓች የኢሕአፓው አሊ ሁሴን እና በየቦታው የሚገኙ በረካታ እስላም ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊ እስላም በባህልም በትርጉምም ቆመው አኩሪ ዜግነታቸውን የተወጡ አርበኞቻችንን ሳላመሰግን ሳልጠቅስ እና ለታሪክ ሳላወሳ አላልፍም።
አርግጥ ያለንበት ዘመን ፈታኝ ነው፤ ጠዋት የሆንነውን ማታ ሆነን አንገኝም። ፈተናው ምንም ቢከብድ ኢትዮጵያዊ ቆዳውን ነብር ዥንጉርጉርን መለወጥ ከቶ እንዴት ይቻለዋል?የተባለው ለዚህ ትውልድ የተላከ ወጣሪ መልእክት ነው። አመሰግናለሁ።
(408) 561- 4826 መጽሐፍቶቼን ለመግዛት ዕደል ያላገኛችሁ ጥቂት ቅጂዎች ስለቀሩ ደውላችሁ ማግኘት
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar