ከ............................(በዙቤር ጥላሁን)
ፍቅር ሲባል ደም ስራቹህ ነዉ አይደል የሚቆመዉ፡፡አፈቀርኩኝ ስላቹህ ከማን እንዳትሉኝ ግን ፍቅር ያዘኝ.............. ነገሩ እንዴት መሰላቹህ የዛሬ 6 ዓመት ማለትም 2000 በሚሊኒዬም ፍቅር ያዘኝና የማረገዉ አጣሁ፤ምክንያቱም ማንን እንዳፈቀርኩ ማረጋገጥ አቃተኝ፡፡ማሰብ ጀመርኩኝ ያፈቀርኩት ለካ በ1995-1999 ድረስ ሳጠናዉ የነበርኩት ኢስላም ሁኖ አገኘሁት፤ምንኛ የሚያምር ፍቅር መሰለህ ኢስላም፡፡ኢስላም የአላህና የመልዕክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) ፍቅር ማለት ነው። የአላህና የመልዕክተኛው ፍቅር በያንዳንዱ ሙስሊም ልቦና ውስጥ ሊሰርፅ ይገባል። ማንም ሰው ጥልቅ የሆነ የአላህና የመልዕክተኛው (ሶ.ዐ.ወ) ፍቅር ሳይኖረው እውነተኛ ኢስላማዊ ህይወት ሊኖር አይችልም። ኢስላም እንዲሁ ብቻ እምነትና የቅዱሳን በዓላት ጥርቅም አይደልም።ታዲያ ለምን ከኢስላም ፍቅር አይዘኝ፤ኢስላም የፍቅር ኃይማኖት ነው። ፍቅሩ የእውነት ፍቅር ነው። ባህሮችና ውቅያኖሶች ቀለም ፈጥረው ቃላት ቢመሰርቱ ይህን እውነተኛ ፍቅር መግለጽ ይሳናቸዋል። ኢስላማዊ ፍቅር የምር ፍቅር ነው። ልቦች የሚርበተበቱለት፣ ዓይኖች የሚያነቡለት፣ እጆችና እግሮች የሚዝሉለት፤ አዕምሮ ሙሉ ለሙሉ የሚንበረከክለት ልዩ ፍቅር። ይህ ፍቅር አላህን ቀጥሎም መልዕክተኛውን ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) ከማፍቀር ጀምሮ ለምድር ፍጥረታት ሁሉ የሚሰጥ ፍቅር ነው።
ፍቅር የኢስላም ምሰሶው ነው። እምነት ያለ ፍቅር ባዶ ነው። ፈፅሞ አይሞላም። ፍቅር የእምነታችን ጥንካሬ ማሳያ መነጽር ነው። ፍቅራችን ሲያብብና ውዴታችን ሲጎመራ እምነታችን ያንፀባርቃል፤ ያበራል፤ ሽታውም ለአለም ሁሉ ይደርሳል።እዉነተኛ አፍቃሪ መሆን ከፈለክ ከኢስላም ማለትም ከነብዩ ታሪክ ተማር፡፡የዘመናችን ወጣት ፍቅርን በካፌ ብቻ ነዉ የሚገልጸዉ፤ወደ ካፌ ዘዉ ያለ ሁሉ የሚመለከተዉ ጥንድጥንድ ሁነዉ በየካፌ ወምበር የሚያሞቁትን የካፌ ጄኔረነሽን(KAFE GENERETION)ቱልድ ነዉ የሚያየዉ፡፡ስለ ካፌ ጄኔሬሽኖች ሌላ ጊዜ ነዉ የምጽፈዉ ኢንሽአላህ፡፡አሁን ግን እኔን ስለ ያዘኝ ፍቅር ባጭሩ ላዉጋቹህ፡፡ፍቅር ማለት በቃላት ውርጅብኝ የሚገለፅ የስሜት ዱላ አይደለም። ነገር ግን ፍቅር እውነትን ያዘለ፣ ቁርጠኝነት የታከለበት፣ ወደ ጥሩ ስራ የሚመራ መንገድ ነው። የእውነት ፍቅር ልብን ያርበደብዳል፤ አያስቀምጥም ለመልካም ስራ ያተጋል፤ ለእውነትና ለፍትህ ዘብ ያቆማል። በጥሩ ስራም ይገለፃል። በልብ የተቃኘው እና በምላስ የተላወሰው እንዲሁም በአካላት መልካም እንቅስቃሴ የታጀበው ፍቅር፤ እውነትኛ ፍቅር ይሰኛል።የነቢዩ ፍቅር ደስታን ይለግሳል፣ በሀሴት ይሞላል። የምር ያዝናናል ወደ ቀጥተኛውም መንገድ ይመራል።
ነቢያችን (ሶ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡- “እናንተ ዘንድ እኔን ከወላጆቻችሁ፣ ከልጆቻችሁና፣ ከሰው ልጆች ሁሉ በላይ ተወዳጅ እስካልሆንኩኝ ድረስ የአንዳችሁም እምነት አልሞላም” (ቡኻሪ)።
ነብዩን መውደድ ማለት ሕዝባቸውን (ኡማቸውን) መውደድ ማለትም ጭምር ነው። ለኡማቸው አባላት ጥንቃቄ ልናደርግና ለነርሱም አንድነትና ህብረት ልንሠራ ይገባል። በማንም ሠው ላይ (በተለይም በሙስሊም ላይ) መጥፎ ነገር ልናስብ ወይም ቂም ልንይዝ አይገባም። ረሱልን የወደደ፣ እርሳቸው ያፈቀሩትን ሁሉ ያፈቅራል፤ ያከበሩትን ሁሉ ያከብራል። ነቢዩ ፍጡርን ሁሉ ይወዱና ለነሱም ይሳሱ ነበር። እኛም ለፍጡራን ሁሉ ልንሳሳና ልናዝን ይገባናል። ለአንዳቸውም የጥላቻ መንፈስ በውስጣችን ልናሳድር አይገባም። ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) ያፈቅሩትን እኛ ጠልተን እንዴት የሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) ወዳጅ መሆን እንችላለን? አነስ ኢብኑ ማሊክ ነቢዩ እንዲህ በማለት መከሩኝ ይላል፡- “ልጄ ሆይ! ቀንንና ምሽትህን ለማንም የጥላቻ መንፈስ ሳይኖርህ ማሳለፍን አትዘንጋ!” ከዚያም እንዲህ አሉኝ “ልጄ ሆይ! ይሄ የኔ ፈለግ ነው፣ ፈለጌን የወደደ በእርግጥ እኔን ወደደ፣ በእርግጥ እኔን የወደደ ከኔ ጋር በጀነት ይሆናል” (ቲርሚዚ)።ፍቅር እስከ ጀነት በኢስላም ነዉ ያለዉ፡፡ይህ እንዳያመልጣቹህ ካፌ ጄኔሬሽን............ካለኒካ ጉዞ እስኪ ይቅርባቹህ.........ካፌ ጄኔሬሽን፡፡
የፍጥረታት መሪው ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) የተላኩት ለዓለማት እዝነት ነው። በአለም ላሉ ፍጥረታት ሁሉ እዝነት። በዚህ ቃል የታነፀ የነቢዩ (ሶ.ዐ.ወ) ወዳጅ በእርግጥ ለሰው ልጅና ለፍጥረታት ሁሉ ያዝናል። ከዚህች ዓለም ላይ ድህነትን፣ ችግርን፣ ሰቆቃንና ረሀብን ለማጥፋት ይጥራል። ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) ኢ-ፍትሀዊነትን ለማጥፋት ተልከዋል። ሙሐመድን (ሶ.ዐ.ወ) የሚወድ ሁሉ ለሰላምና ፍትህ፣ ለነፃነትና መረጋጋት ዘብ ይቆማል። ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) የሰውን ልጅ ከዚያ ከባድ የእሳት ቅጣት ለመታደግ ተልከዋል። የነቢዩ አፍቃሪ ሁሌም ለሰው ልጆች የእውነትንና የስኬትን መንገድ ይሰብካል። በትህትናና በርህራሄ ወደ አላህ ይጠራል- ድንቅ ምሳሌ፣ ድንቅ እዝነት፣ ድንቅ ትህትና፣ ድንቅ ሰው፣ ከታላቅ መልዕክት ጋር!!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar