ራዕይ›› መፈክርም ግንባሩን የታሰበውን ያህል ወደ አንድ ለማሰባሰብ አቅም ያጠረው ይመስላል፡፡ ጥገናዊ ለውጦቹም እንዲሁ አትራፊ መሆን አልቻሉም፡፡ መሀል አራት ኪሎ በሚገኘው የኢህአዴግ ጽ/ቤት ግድግዳ ላይ የተሰቀለው የመለስ ፎቶም ‹‹ሸምጋይ›› አልሆናቸውም፡፡ በብሄር ተኮር ፍላጎት የሚወዛወዘው የኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስትም ለሁለት ወር ከአስር ቀን ያህል ያለ ሚንስትሮች ምክር ቤት (ካቢኒ) ስልጣን ላይ የቆየ ቢሆንም፣ ህዳር 20/2005 ዓ.ም. ካቢኔውን ሲያቋቁም ሁለት ተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና ሶስት ሚኒስትሮችን ለፓርላማው በማቅረብ እንዲሾሙ አድርጓል፡፡ በዚህ ፅሁፍም የሁለቱን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሮች ሹመት ከህገ-መንግስቱ አኳያ ያለውን ህጋዊነት እና ከሹመቱ ጀርባ ያሉ ፖለቲካዊ መግፍኤዎችን እንዳስሳለን፡፡
ስንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች?
በኢትዮጵያ አውድ ስለስልጣን ስንነጋገር ለህጋዊነቱ ማረጋገጫ የሚሆነን በራሱ በገዥው ፓርቲ ‹‹ፊታውራሪነት›› በ1987 ዓ.ም. የፀደቀው ህገ-መንግስት ነው፡፡ ስለዚህም የሶስቱ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሮች ሹመት ምዘና መነሻም ይህ ይሆናል፡፡
ህገ-መንግስቱ በአንቀጽ 9 በግልፅ ‹‹የሕገ-መንግስት የበላይነት›› በሚል ርዕስ፣ በቁጥር ሶስት ላይ ያስቀመጠው እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹
በዚህ ህገ-መንግስት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግስት ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡››
እንግዲህ ይህ ድንጋጌ በግልጽ በመቀመጡ ይመስለኛል የ‹‹ሶስቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች›› ሹመት ‹‹ኢ-ህገ-መንግስታዊ›› የሚል የተቃውሞ ወጀብ የከበበው፡፡ የዚህ ተጠየቅም ሄዶ ሄዶ የሚያርፈው ህገ-መንግስቱ ላይ በመሆኑ፣ መከራከሪያ የሚሆነው ህገ-መንግስቱ ስለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሿሿም በአንቀፅ 75 ላይ ያስቀመጠው ነው፡፡ በዚህ አንቀፅ መሰረትም አንድ እንጂ፣ ሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም አይቻልም፡፡ በተጨማሪም ህገ-መንግስቱ በእንዲህ አይነቱ ድንገቴ የውስጥ አብዮት በሚነሳበት ወቅትም ቢሆን የሁለቱ ምክትሎቹን የመሰለ ሹመት እንዳይኖር በር የዘጋ ነው፡፡ የህግ ባለሙያዎች ትንታኔም ‹‹በህግ ያልተገለፀ ነገር፣ እንዳልተፈቀደ ይቆጠራል›› ሲል ይህንን ሀሳብ ያጠናክራል፡፡
አዲሱ ሹመትም ያፈረሰው የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 75 ‹‹ስለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር›› በሚል ርዕስ ስር የገለፀው እንዲህ ይላል፡-
1.
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ሀ) በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይተው የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል፣
ለ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖሩበት ጊዜ ተክቶት ይሰራል
መቼም እንዲህ ተብራርቶ የተቀመጠ ህግን ‹‹ለትርጉም አሻሚ ነው›› ልንለው አንችልም፡፡ ምክንያቱም ይህ አንቀጽ ሌላ ቀርቶ ‹‹ወዘተ›› እንኳ ብሎ ያልተገለፀ ስልጣን አልሰጠም፡፡ በአናቱም ‹‹ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ እንዲህ ያደርጋሉ፣ ይህንን ይቆጣጠራሉ፣ በክላስተር ይታቀፋሉ…›› ሲል የደነገገው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ንቅፈ-ክበብ ግልፅና አጭር ነው ማለት ነው፡፡ ይኸውም ‹‹ዋናው በሌለበት ጊዜ ተክቶ መስራት››፣ እና ‹‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይቶ የሚሰጠውን መተግበር››፡፡ ከዚህ አኳያም ነው በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ ‹‹የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ›› እና ‹‹የኢኮኖሚ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ›› የሚለው የሁለቱ ሰዎች ሹመት ህገ-መንግስታዊ ዕውቅና የለውም ወደሚል መደምደሚያ የሚያደርሰን፡፡
በእርግጥም ጉዳዩን በጥቅሉ ስናየው የሁለቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹመት የህገ-መንግስት ድጋፍም ሆነ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህም ሹመቱ ሊያያዝ የሚችለው ከፖለቲካ ውሳኔ ጋር ብቻ ነው፡፡ በዚህም ሕገ-መንግስቱ በይፋ ተጥሷል፡፡ ይህ ማለት ስርዓቱ ከህግ-ውጭ ሲሰራ ይህ የመጀመሪያው ነው እንደ ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የኢህአዴግ የኋላ ታሪኩ የሚነግረን ዘመኑን ሙሉ ህገ-መንግስቱን እንዳሻው ሲጥሰው፣ አሳስቶ ሲተረጉመው፣ ሲያሴስነው፣ ሲገፋው እንደነበር ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው
የፖለቲካ ጠቀሜታውን በማስላት ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ይህ ህገ-መንግስት ህልውናው የሚገለፀው ተቀናቃኞቹን ለማጥቃት ባስፈለገ ጊዜ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ (በድህረ ምርጫ 97 ለእስር የበቁት የቅንጅት አመራሮች ‹‹ህገ-መንግስቱን ለመናድ አሲረዋል›› በሚል ክስ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት አለሙ፣ አንዱአለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፣ እነ ጄኔራል ማሞ ተፈራ… የመሳሰሉትም ቃሊቲ የተወረወሩት ‹‹ህገ-መንግስቱን ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል›› ተብለው እንደሆነ ይታወሳል)
የሆነ ሆኖ ህገ-መንግስቱ በአቶ መለስ ዘመን እንደ ግለሰብ፣ እንደ ህወሓት እና እንደ ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲጣስ ተመልክተናል፡፡ ለምሳሌ በ93ቱ የህወሓት ክፍፍል ወቅት መለስ ራሳቸው ህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን የልዩነት ችግር ለመፍታት ሲሉ ‹‹የህወሓት ህገ-ደንብ ድርጅቱን ከአደጋ ስለማይከላከለው፣ ከህግ ውጭ ተጉዘን በህገ መንግስቱ መጠቀም መቻል አለብን›› ብለው በአደባባይ ተከራክረዋል፡፡ የተከራከሩበትንም ወደተግባር መቀየራቸው ይታወሳል፡፡ የተቃወማቸውም አልነበረም፡፡ ይህን የሰውዬውን መከራከሪያ አሁን ለተከሰተው ኢ-ህገ-መንግስታዊነት የህወሓት ሰዎች እንዴት እንዳዋሉት አንድ መላምት ልንሰጥ እንችላለን፡፡ እንደሚታወቀው፤ ኢህአዴግ ላረቀቀው ህገ-መንግስት ተከብሮ መኖር ራሱን ብቸኛ ዕምነት የሚጣልበት ቡድን አድርጎት ያስባል፡፡ ‹‹እኛ ከሌለን ሀገሪቱ ትበታተናለች›› የሚለው ፍልስፍናው፤ እርሱ በስልጣን ላይ ካልቆየ ህገ-መንግስቱ በአንድ ምሽት ብትንትኑ ሊወጣ እንደሚችል ከልቡ እንዲያምን አድርጎታል፡፡ ስለዚህም፤ በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን ሽኩቻ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድም ቢሆን ማርገብ ካልተቻለ ፓርቲው ሊፈራርስ ከዚያም እነርሱ እንደሚያምኑት ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ሊያበቃለት ይችላል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊትም ፓርቲውን ኢ-ህገ-መንግስታዊ በሆነ መንገድ በማቆየት፣ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን መጠበቅ ያስፈልጋል የሚል ይሆናል፡፡ እንግዲህ የአቶ መለስ ተተኪዎችቸውም እናስቀጥለዋለን የሚሉት ‹‹ሌጋሲ›› በዋናነት ህግ መጣሱን እንደሆነ እያሳዩን ነው፡፡
ይህንን የስርዓቱ ድርጊት በማስረጃ ለማሳየት ያህል የሚከተሉትን የህግ ጥሰቶች ማንሳት እንችላለን፡፡ የሰላሳ ሰባቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ሹመት አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም ህገ-መንግስቱ የጄነራሎችን የማዕረግ አሰጣጥ የሚፈቅደው በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት ሲሆን ብቻ ነው፡፡ እዚህ ጋር ያለው የህግ ጥሰት ለመኮንኖች የተሰጠው ሹመት አቶ መለስ ህይወታቸው አልፎ ተተኪ ጠቅላይ ሚንስትር ባልተመረጠበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ኃይለማርያም ደሳለኝ ‹‹ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር›› ተብለው የቆዩበት ጊዜም እንዲሁ ህገ ወጥነት ነው፤ ህገ-መንግስቱ ‹‹ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር›› ለሚባል ሹመት እውቅና አይሰጥምና፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብለው ሳይሾሙም ለሁለት ወር ያህል ሀገሪቱ ያለመንግስት የቆየችበት ጊዜም የዚሁ ተመሳሳይ የህግ ጥሰት ነው፡፡ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ካቢኔያቸውን ሳያቋቁሙ እስከ ህዳር ሃያ ቀን ድረስ የቆዩበት ሁኔታም ኢ-ህገ-መንግስታዊ ነው፡፡
የሹመቱ አደጋ
ስርዓቱ ጉልበታም መሪውን በሞት ከተነጠቀ በኋላ የተለያዩ ክፍተቶች ተፈጥረውበታል፡፡ እነዚም ክፍተቶች በሂደት በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍተው ሊጠራርጉት እንደሚችሉ ስጋት ላይ በመውደቁ ይመስለኛል-የህገ-ወጡ ሹመት አላማ፡፡ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮቹን ብዛት ከአንድ ወደ ሶስት ከፍ ያደረገው ይህ ሁናቴ እንደ አንድ መፍትሄ በመውሰዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ አካሄድ በአራቱ ፓርቲዎች ውስጥ ለተፈጠረው የኃይል ሽኩቻ እንደ እሳት ማጥፊያነት ካልጠቀመ በቀር ዘላቂ መረጋጋትን ማስፈን አያስችልም፡፡ እንዲያውም በግልባጩ አደጋውን ሊያባብሰው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ማዓከላዊ መንግስቱ በህገ-መንግስቱ ውስጥ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይኖር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተክቶት ይሰራል›› የሚለውን ድንጋጌ የመተግበር ግዴታ ውስጥ ቢገባ ለመተግበር ከባድ ነውና፡፡ መላ ምቱን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ አቶ ኃይለማርያም፣ የአቶ መለስ ዕጣ ቢያጋጥማቸው ማን ነው የሚተካቸው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ሙክታር ከድር ወይስ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ወይስ ደመቀ መኮንን? ግልፅ የሆነ ነገር ስለሌለ ‹‹እገሌ ይተካል›› ማለት አይቻልም፡፡ ምክትሎቹ በተመሳሳይ ደረጃ ያሉ ይሁኑ ወይም የተለያዩ አልተነገረም፡፡ ይህ ደግሞ ሶስቱም እኩል የአልጋው ወራሽ ሆነው ሊፋጠጡ የሚችሉበትን ዕድል ያሰፋዋል (ቢያንስ እንዲህ አይነት አደጋዎች ቢከሰቱ እንደ መውጫ በር ለመጠቀም ‹‹ተቀዳሚ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር…›› የሚል አንደኛው ከሁለቱ ሚኒስትሮች የሚለይበት ደረጃ ቢሰጥ ወይም ሁለቱ ምክትሎች ለአንደኛው ምክትል ተጠሪ ለማድረግ አለመሞከሩ የሰዎቹን ችኮላ በግላጭ ያሳያል፡፡ ምናልባት ደመቀ ቀድመው የተሾሙ በመሆናቸው ብኩርናውን ይወስዱ ይሆናል ተብሎ ታስቦም ከሆነ አሁንም ይህ የቢሆን ምልከታ ህገ-ወጥነቱ ከማባባስ ውጪ የሚጨምረው አንዳች ነገር የለም)
በአናቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመተካቱ ስራ ከታሰበው በተቃራኒ ሄዶ ቀላል ቢሆን እንኳ ምክትሎቻቸው ብቁ አይደሉም፡፡ በልምድም በተቀባይነትም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ የፓርቲው ግዙፍ አደጋዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ የስልጣን ሹመት የብሄር ተዋፅዖን ለማቻቻል የተደረገ ሊሆን ይችላል የሚለው መከራከሪያ ከኢህአዴግ ሁለንተናዊ ባህሪ ጋር ሲዛመድ አንድ ከባድ መዘዝ ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ ፓርቲው እስከአሁን ከሄደበት መንገድ አንፃር ከውስጡ አንድ ብቸኛ ጡንቸኛ ሰው መምጣቱ
ላይቀር ይችላል፡፡ የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት የፓርቲው መርህ እና በድህረ-93 መንግስታዊ ተቋማት እንጂ የፓርቲው ጠቀሜታ በአቶ መለስ ስልጣን ጠቅላይነት የተነሳ እየሟሸሹ መጥተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአቶ መለስ አርቃቂነት ፓርቲው በሀገሪቱ ላይ ሊከውናቸው ያሰባቸው የተንሻፈፉ የልማታዊ መንግስት ፅንሰ-ሀሳቦች የአንድን ጉልበታም መሪነት መምጣት የግድ ይላሉ (መለስ ይህን ጉዳይ ተቋማዊነት ለማልበስ መሞከራቸው ሳንዘነጋ) በዚህን ወቅት የትኛው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አልያም ከየትኛው ብሄር የሚነሳ ሰው ወደዚህ መንበር ይመጣል? …መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡ መቼም ከህወሓት ለሚነሳ ሰው የሌሎቹ ብሄር አባላት እንደበፊቱ በዝምታ ያዩታል ማለቱ ያስቸግራል፡፡
ሌላኛው የአዲሱ ሹመት አደጋ የስልጣን ተዋረድን ለመጠበቅ ወይም በሚኒስትሮች መካከል ተግባብቶ ለመስራት እንቅፋት መሆኑ ነው፡፡ የስራ ልምድ እና ቀደምትነትን (ሲነየሪቲን) መሰረት ያደረገ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከ15 አመታት በላይ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሆነው በመስራት በቦታው ላይ የዳበረ ልምድ ያላቸው ሶፊያን አህመድ፣ አሁን ተጠሪነታቸውም ሆነ ሪፖርት የሚያቀርቡት ለጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን፣ ‹‹የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ›› ሆነው ለተሾሙት (በልምድም በቀደምትነትም ከእርሳቸው በእጅጉ ለሚያንሱት) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት እንቅፋቶች መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ምናልባትም በእንዲህ አይነት ልዩነት የተነሳ በሁለቱ ባለስልጣኖች መካከል ቅሬታ ወይም አለመግባባት ቢፈጠር ችግሩ ከእነርሱ አልፎ የድርጅቶቻቸው ኦህዴድ እና ህወሓት የመሆን ዕድል አለው፡፡ እዚህ ጋ ሊነሳ የሚችለው ሌላው የሹመቱ ኢ-ህገ-መንግስታዊነት በራሱ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ ሰባ ስድስት፣ በቁጥር አራት እና ስድስት ላይ ‹‹የሚንስትሮች ምክር ቤት›› ስልጣን ተብሎ የተቀመጠው ፋይናንስን እና ኢኮኖሚን የሚመለከተው ለዶ/ር ደብረጽዮን መሰጠቱ ነው፡፡ …እናም እነዚህ ብጥስጣሽ ምክንያች እርስ በእርሳቸው የሚጋመዱበት አጋጣሚ ከተፈጠረ አደጋው እውን ይሆናል፡፡
ከሹመቱ ጀርባ
ትልቁ ጉዳይ ኢህአዴግ በዚህ ደረጃ ህገ-መንግስቱን ንዶ፣ አዲስ የስልጣን ቦታ ለመፍጠር ያስገደደው ምንድር ነው? የሚለው ይመስለኛል፡፡ ከዚህም አኳያ የተወሰኑ ነጥቦችን ከሹመቱ አንጓ ውስጥ እንምዘዝ፡፡
ደህና! ኃይለማርያም ደሳለኝ ተሿሚዎቹን ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ባፀደቁበት ወቅት ‹‹ምክንያቴ›› ብለው ከዘረዘሩት እንነሳ፡-
‹‹
የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ለማጠናከር፣ ያስፈፃሚነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ ለማድረግ የተጀመረው ጥናት በመጠናቀቁ፣ በጥናቱ በርካታ ልምዶች በመቀመሩ፣ በአዲሱ ትውልድ የኢህአዴግ አመራር የመተካካት ሂደትን መሰረት በማድረግ አስፈፃሚ አካል ለማጠናከር ዓላማ ያደረገ…››
ይህ ምን ማለት ነው? ምክንያትስ ብሎ ማን ይሆን ያዘጋጃው? ይህ ሁኔታ ሰዎቹ ምን እየሰሩ ነው ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ የምክንያቱ ቅሽምና የሚጀምረው በተገለፀው ዝባዝንኬ ነገር ብቻ አይደለም፣ በዝርዝሩ ውስጥ ‹‹ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ›› የሚል ነገር ለይስሙላ እንኳ ባለመካተቱ ነው፡፡ መቼም ይህ ምክንያት ሌላውን ቀርቶ ራሳቸውንም ሊያሳምን አይችልም፡፡ ባይሆን በግልፅ እንዲህ ቢሉ የተሻለ ነበር፡-
‹‹
እኔ እንደ መለስ ዜናዊ ሀገር ለመምራት የሚያስችል አቅም ስለሌለኝ፣ ስልጣኔን ህገ-መንግስቱ ከሚፈቅደው ውጪ አከፋፍያለሁ፤ ወይም መለስ ዜናዊ ስልጣን ጠቅልለው የያዙ አምባገነን ስለነበሩና አሁን ደግሞ እርሳቸው ስለሌሉ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ተከትለን የስልጣን ክፍፍል አድርገናል››
ይህ ቢያንስ ለአንድ ሀይማኖታዊ መፅሄት በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ላይ ‹‹እኔም እንደ ዳዊት ጨርቄን ልጣልለት›› እያልኩ እዘምርለታለሁ ካሉት አምላካቸው ጋር እንዳይቀያየሙ ያደርጋቸው ነበር፡፡
የሆነ ሆኖ ከዚህ ሹመት ጀርባ ያደፈጠው እውነታ በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የፖለቲካ ሽኩቻ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ መምጣቱን አመላካች ያደረገው ይመስለኛል-በተለይም በህወሓት እና ኦህዴድ ውስጥ፡፡ ይህ ማለት ግን ህወሓትና ኦህዴድ ተቃቅረዋል ማለት አይደለም፡፡ በእኔ እምነት ቅሬታ አለ ብዬ የማስበው በሁለቱም ድርጅቶች በራሳቸው ውስጥ ነው-በላይኛው የአመራር አባል እና በካድሬዎች መካከል፡፡
በዚህ ከተስማማን የህወሓት ብቸኛ ችግር የሚመስለኝ መካከለኛና የበታች ካድሬዎቹ ‹‹መሪዎቻችን በደምና አጥንት ያገኘነውን ስልጣን፤ በመተካካት ስም አስወሰዱብን›› የሚል ግሩምሩምታ ከማሰማታቸው ነው የሚተሳሰር ነው፡፡ እናም ከዚህ አንፃር ሊሆን ይችላል ድርጅቱ ከህገ-መንግስቱ ይልቅ የፖለቲካ ጉልበቱን ለመጠቀም የተገደደው፡፡ የኦህዴድ የውስጥ ንትርክም የዚሁ ተመሳሳይ ነው፡፡ ‹‹ኦሮሞ መቼ ነው በቁመቱ ልክ ስልጣን የሚይዘው?››፡፡ ለዚህም ነው ይህ አይነቱ የብዙሀኑ ካድሬ ቅሬታ በሰፊው ከተዛመተ ከራሱ አልፎ አባል ድርጅቶችንም ጠራርጎ የሚያጠፋ አብዮት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት የገባቸው ‹‹አስማት ማሳየት›› የማይሳናቸው የህወሓት ወሳኝ የአመራር አባላት፣ ኢ-ህገ-መንግስታዊ በሆነ አካሄድ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ቦታ ለኦህዴድ በመስጠት ለቅራኔው ጊዜያዊ ማስተንፈሻ መዘየዱ ተሳክቶላቸውል፡፡
‹‹
ህወሓት እየመጣ ነው!››?
በርከት ያሉ የፖለቲካ ተንታኞች ‹‹ህወሓት ወደ ስልጣን እየመጣ ነው›› የሚል አንድምታ ያለው ትንተና እያቀረቡ ነው፡፡ ይህ ግን ስህተት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ህወሓት መጀመሪያውንም የትም አልሄደምና (ከመንግስታዊነት ይልቅ ብሄር ተኮር ገፅታ ያላቸው መከላከያ፣ ደህንነት፣ ኢኮኖሚ…የመሳሰሉት በመለስ ዘመንም ሆነ መለስ ካለፉ በኋላ በፓርቲው የብረት መዳፍ ስር እንደዋሉ ናቸው)፡፡ እነዚህ ተቋማት ደግሞ ለህልውናው እና የበላይነቱን ለማስከበር ወይም እንደ ተቺዎች አገላለፅ ‹‹ለፖለቲካ አስማቱ›› ቁልፍ የስልጣን መገልገያ መሳሪያዎች መሆናቸው አያከራክርም፡፡ እናም ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርገው መሾማቸው ለህወሓት የሚጨምረው የፖለቲካ ጉልበት የለም፡፡ ባይሾሙም የሚያጎሉት ነገር የለም፡፡ መጀመሪያውንም የተቀነሰ ነገር አልነበረምና፡፡
ይህ አንድ እውነት ነው፡ ድርጅቱ በመለስ ሞት የተነሳ በተፈጠረበት የፖለቲካ መሳሳት ችግር ላይ መውደቁ ደግሞ ሌላ እውነት ነው፡፡
ህወሓት ፩
የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ደመቀ መኮንን ወደ ስልጣን በመምጣታቸው የህወሓት አመራር የተሰማው ቅሬታ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የኃይለማርያምም ሆነ የደመቀ ሹመትን የቀመረው ራሱ ህወሓት ነው፡፡ ከዚህም ተነስተን የቅሬታ እና የተፈነገልን ስሜት የበረታው በመካከለኛና በታችኛው ካድሬ ሰፈር ነው ወደሚል መደምደሚያ እንደርሳለን፡፡ እዚህ ጋ እንደ አይነኬ ነገር ተሸፍኖ ማለፍ የሌለበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ጥቂት ሚዲያዎች እንደሚሉት ‹‹የትግራይ ህዝብ ስልጣን ለምን ከትግራይ ሰው ተወስዶ ለወላይታ ተሰጠ›› የሚል ተቃውሞ የሌለው መሆኑን ነው፡፡ በእርግጥ የዚህ አይነቱ ፍረጃ የትግራይ ህዝብንና ህወሓትን አንድ አድርጎ ከመመልከት አባዜ የሚመጣ ስለሆነ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም የጠመንጃው አስተዳደር በኦሮሞ ወይም በአማራ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ትግራይንም የሚጨምር ነውና፡፡ ህወሓት ወላይታን በጊንጥ እየገረፈ፣ ትግራይ ሲደርስ በልምጭ አይቀይረውም፡፡ ወጥ አምባገነን ባህሪይ የተጠናወተው ነውና፡፡ (ይህንን በህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን የተገፋን ስሜት በማጋጋሉ ረገድ ለድርጅቱ የንግስቲቷን ‹‹ሸረሪት›› ያህል ተፅእኖ ፈጣሪ የነበሩትና በአቶ መለስ የተንገዋለሉት የአቦይ ስብሃት ነጋ እጅ ያለበት ይመስለኛል)
የሆነ ሆኖ ህወሓት በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ተጽእኖ በመጠቀም ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልን ህገ-መንግስታዊውን አሰራር ባልተከተለ መልኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ያደረገው፣ ለካድሬዎቹ ‹‹የሞትንም እኛ፣ ያለንም እኛ! ተረጋጉ›› የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ሊሆን ይችላል፡፡
ህወሓት ፪
ህወሓት ከመለስ ህልፈት በኋላ በ1993 ዓ.ም. ከድርጅቱ ተባረው ከወጡት አመራር (የእነስዬ፣ ተወልደ ቡድን) ጋር ዕርቅ ፈጥሮ በጋራ እንዲሰራ ከካድሬውና ከደጋፊው ግፊት እየበረታበት እንደሆነ ተሰምቷል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ የህወሓት የመከራ ወራት እየተቃረበ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ምክንያቱም የ93ቱ ልዩነት ከድርጅቱ በወጡት የአመራር አባላት እና በአቶ መለስ መካከል ‹‹ለኃይል የበላይነት›› የተደረገውን ትግል ተከትሎ የመጣ እንጂ እንደ ድርጅት የተስተዋለ ወይም በርዕዮተ-ዓለም አለመስማማት የተከሰተ አይደለም፡፡ እናም አሁን ያለው የህወሐት አመራር ‹‹የመለስን ራዕይ አስቀጥላለሁ›› በሚል ከሚያቀነቅነው መፈክሩ አኳያ ‹‹ከነስዬ ቡድን ጋር ታረቁ›› የሚለው ውትወታ ሲደመርበት ፓርቲውን ቅርቃር ውስጥ ይከተዋል፡፡ መለስ ራሳቸው በክፍፍሉ ወቅት ‹‹ህወሓትን ከአናት ያበሰበሱ›› በሚል የወነጀሏቸውን የአመራር አባላት ወደ ድርጅቱ እንዲመለሱ በማድረግ ‹‹ከመለስ ራዕይ ጋር ወደፊት›› እየተባለለት ካለው ፖለቲካ ጋር ማስታረቁ የሚቻል ነው ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡
ይህም ሁኔታ በሁለት መንገድ ህወሓት ላይ ተጽእኖ ያሳደረ ይመስላል፡፡ የመጀመሪያው ‹‹አሁን ያለው የህወሓት አመራር አቅም ስለሌለው ከተባረሩት የቀድሞ አመራር ጋር እርቅ በመፍጠርና ወደ ድርጅቱ እንዲመለሱ በማድረግ አቅሙን ማጠናከር አለበት›› የሚለውን የካድሬዎቹን ጉትጎታ አልሰማም ማለቱ አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው፡፡ በእርግጥ ህወሓት ለዚህ ግፊት ምላሽ ይሆን ዘንድ ደብረጽዮንን ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ እንዲይዙ በማድረግ፣ ለሀሳቡ አቀንቃኞች ‹‹ጠንካሮች ነን!! እነስዬ አያስፈልጉንም!! ባስፈለገን ጊዜ የፈለግነውን ስልጣን መያዝ እንችላለን!!›› የሚል ስውር መልዕክት አስተላልፏል፡፡ የሹመቱ ህጋዊ አለመሆንም ትንተናውን በደንብ የሚያጠናክር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ከኃይለማርያም ጀርባ ያለው ጠንካራ የህወሓት መዳፍ በፈለገ ጊዜ የፈቀደውን ለማድረግ ህገ-መንግስቱም ሆነ የተቀጥላ ፓርቲዎቹ ፖለቲካዊ ጉልበት ሊያቆመው እንደማይችል ያሳየበት አጋጣሚ ነውና፡፡ (በነገራችን ላይ ሰሞኑን ለመጀመሪያ ጊዜ እነስዬ የህወሓት ጉባኤን ረግጠው ሲወጡ የሚያሳየው የቪዲዮ ሙሉ ፊልም ‹‹We will never forget this day›› /መቼም የማንረሳው ዕለት/ ከሚል መልዕክት ጋር በተለያዩ ሚዲያዎች እንድናየው መለቀቁ የተፈጠረውን ውጥረት የሚያሳይ ይመስለኛል)
ሁለተኛው የሹመቱን ፖለቲካዊ አንድምታ የሚያመላክተው ‹‹ከእነ ስዬ ጋር ካልታረቃችሁ ውርድ ከራሴ›› ለሚሉ ካድሬዎች እና ደጋፊዎች በክፍፍሉ ዘመን፣ ከመለስ ይልቅ ከእነ ስዬ ጎን ቆመው የነበሩትን ደብረጽዮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በማድረግ ‹‹ከጀርባ እነሱም ከጎናችን ናቸው›› የሚል ነጠላ ዜማ በመልቀቅ ግፊቱን ለማቀዝቀዝ የተደረገ የሚያስመስሉ ነገሮች መኖራቸው ነው፡፡ (እንደሚታወቀው ደብረጽዮን ከክፍፍሉ በፊት በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ‹‹የመምሪያ ኃላፊ›› የነበሩ ሲሆን፣ ክፍፍሉን ተከትሎ አሰላለፋቸው ከድርጅቱ ከተወገዱት ጋር በመሆኑ፣ በአቶ መለስ ትዕዛዝ ከሀላፊነታቸው ተነስተው፣ በትግራይ ክልል የአንድ ወረዳ አስተዳዳሪ ተደርገው መወርወራቸው ይታወሳል፡፡ ሰውዬው የወረደባቸውን ‹‹መዓት›› ችለው ድምፃቸውን በማጥፋት እስከ ዶክትሬት ዲግሪያቸው ድረስ መማር እንደቻሉና በሂደት ፀባያቸውን አርቀው፣ ግለሂሳቸውን አውርደው፣ በአቶ መለስ የመጨረሻ ዘመን አካባቢ ወደ ስልጣን ሊመጡ ችለዋል)
ህወሓት ፫
ሶስተኛው የሹመቱ የቢሆን ምልከታ (ሴናሪዮ)፣ አቶ መለስ ህይወታቸው ባለፈ ጊዜ ህወሓትን ችግር ውስጥ የከተተው ጉዳይ ዳግም እንዳይፈጠር ለመከላከል ታስቦ የተደረገው ነው፡፡ እንደሚታወሰው የሰውየውን መሞት ተከትሎ ህወሐት በህግም ሆነ በአሰራር ቦታውን ሊወርስ የሚችልበት ምንም አይነት ክፍተት አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም ቦታው በቀጥታ የሚገባው ለምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ነውና፡፡ ስለዚህም ከዚህ በተወሰደ ትምህርት በቀጣይ እንዲህ አይነት ሁናቴ ቢፈጠር ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፣ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትን መንበር ይዞ መጠባበቅ ለነገ የማይባል የቤት ስራ በመሆኑ ይመስለኛል፣ ደብረጽዮንን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ወደ ስልጣን ማምጣት ያስፈለገው፡፡
እዚህ ጋ የሚነሳው ሌላኛው መላ-ምት፣ የህወሓት ዕቅድ ደብረጽዮንን ለድንገቴ ለውጥ ተጠባባቂ እንዲሆኑ አድርጎ አስቀመጠ እንጂ፣ በሚቀጥለው ምርጫ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመጡ ይፈልጋል የሚል አለመሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም ህወሓት እንደ አቶ መለስ አይነት ድንገተኛ ተፈጥሮአዊ አደጋ ካልተፈጠረ በስተቀር፣ ወቅቱን ጠብቆ በሚቀጥለው ጊዜ በሚካሄደው ምርጫ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቦታ መልሶ ለመያዝ የሚፈልገው በደብረጽዮን በኩል ሳይሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርጎ ባስሾማቸው ቴዎድሮስ አድሀኖም ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ፡፡
ይህንን መከራከሪያ የሚያጠናክርልን ቴዎድሮስ አድሀኖም እስከ አዲሱ ሹመታቸው ጊዜ ድረስ በሰሩበት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር መስሪያ ቤት የተሻለ የተባለለት ተቋማዊ ለውጥ ያመጡ (በአንፃራዊነት ከሌሎች ተቋማቶች የእርሳቸው የተሻለ እንደሆነ ተደጋግሞ ተነግሮለታል) ሆነው ሳለ ወደ ሌላ ኃላፊነት መቀየራቸው ነው፡፡ እናም ህወሓት ሹመቱን ሀገሪቱን ለመጥቀም እና የተሻለ ስራ ለመስራት አቅዶ የሰጠው ቢሆን ኖሮ፣ ሰውዬው በሀላፊነታቸው ቢቀጥሉ ይበልጥ ጠቃሚ መሆናቸውን ከማንም የተሻለ ስለሚያውቅ፣ ልምድ ካካበቱበትና ውጤታማ ሆነውበታል ከተባለው ሀላፊነታቸው ወደ ማያውቁት አዲስ ስራ ባልቀየራቸውም ነበር፡፡ ይህ ያለአንዳች ቅድመ-ዝግጅት ድንገት በነሲብ የተደረገም አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ብርሃነ ገብርክርስቶስ በትጥቅ ትግሉ ዘመን የህወሓት የውጭ ግንኙነት ሠራተኛ፤ እንዲሁም ከድል በኋላ በአሜሪካ እና በቤልጂዬም አምባሳደር ሆነው ከመስራታቸውም በላይ፣ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እየሰሩ በመሆናቸው ለቦታው ከቴዎድሮስ በእጅጉ በላቀ ሁኔታ መመጠናቸው ሌላውን ቀርቶ የህወሓትን ተቀናቃኞቹ ሳይቀር ስለሚያሳምን ኃላፊነቱን ለእርሳቸው ይሰጥ ነበር፡፡
እናም ህወሓት በቀጣይ በምዕራባውያንም ሆነ በበርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ‹‹የተሻሉ›› እንደሆነ የሚነገርላቸውን ቴዎድሮስ አድሀኖምን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ ላይ አስቀምጦ፣ ከእጁ ላመለጠው ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን እያዘጋጃቸው ይመስላል፡፡ ሬኒ ሌፎርት የተባለ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የረዥም ጊዜ አጥኚም ‹‹Ethiopia: Meles rules from beyond the grave, but for how long?›› በተባለ ጽሁፉ ይህንን ሁኔታ ‹‹ኃይለማርያም በህወሓት ዘንድ እንደ ሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ነው የሚታዩት›› በማለት አብራርቶታል፡፡ በዚህም ቴዎድሮስ አዳህኖም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ሆነው ‹‹ሰውነታቸውን እያፍታቱ›› ያሉት ህወሓት የቤት ስራውን አጠናቅቆ ወደ ቤተመንግስቱ እንዲገቡ እስኪያመቻችላቸው ነው የሚለው ሙግት ጠንክሮ የሚወጣ ሆኗል፡፡
በእርግጥ ይህንን አይነቱን ‹‹ቼዝ›› ለመጫወት ብአዴንም የህወሓትን ያህል ምኞት ያለው ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ምኞቱ ‹‹ያለጠንካራ መዳፍ›› ብቻውን የሚፈጥረው ነገር ያለመኖሩ ‹‹እጅ ሰጥቶ›› እንዲቀመጥ ሳያደርገው አልቀረም፡፡ ይህ የህወሓት አቅም በዚሁ የሚቀጥል
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar