fredag 14. desember 2012


የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የመድረክ አመራር አባላት በእስራት ተቀጡ
ታምሩ ፅጌ (ሪፖርተር ጋዜጣ)
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋ መምህርና የመድረክ ፓርቲ አመራር አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች
ስምንት ተከሳሾች፣ ከሦስት ዓመታት እስከ 13 ዓመታት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ትናንትና
ተወሰነባቸው፡፡ በሽብርተኝነት ወንጀል በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የተመሠረተባቸውን ክስ ሲመረምር
የሰነበተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ትናንትና በሰጠው
የቅጣት ውሳኔ፣ አንደኛ ተከሳሽ የነበሩት አቶ በቀለ ገርባን በስምንት ዓመታት፣ የኦህኮ ፓርቲ አመራር
የነበሩትን አቶ ኦልባና ሌሊሳን በ13 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
ሌሎቹ ተከሳሾች ማለትም ወልቤካ ለሜ፣ መሐመድ ቡሳ፣ ሐዋ ዋቆ፣ ደረጀ ከተማ፣ አዲሱ ሙከሪና
ገልገሎ ቱፋ ከሦስት እስከ 12 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ኦልባና
ሌሊሳና አቶ ገልገሎ ቱፋ ለአራት ዓመታት ከማንኛውም ማኅበራዊ መብቶቻቸው ታግደዋል፡፡ ሌሎቹም
ለሁለት ዓመታት ታግደዋል፡፡
አቶ በቀለ ገርባ በ2003 ዓ.ም. የተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፍ ሲመረምሩ በአጋጣሚ ያገኟቸውን ተማሪዎች፣ ‹‹ገዢውን መንግሥት
መጣል አሁን ነው›› በማለትና በመመልመል ለኦነግ በመሥራትና ኦፌዴንን ከለላ በማድረግ የሽብር ተልዕኮ ሲፈጽሙ ነበር በማለት
መከሰሳቸው ይታወሳል፡፡
አቶ ኦልባናም በአምቦ ተማሪዎችን በመመልመልና ወደ ኦነግ እንዲገቡ በማደራጀት ፀረ ሽብር ተግባር ሲፈጽሙ እንደነበር፣ ሌሎቹም እስከ
ኬንያ ድረስ በመሄድ ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ፣ ከኦነግ ጋር በመሥራት የሽብር ተልዕኮ ሊፈጽሙ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ
ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን መሠረት መከላከያ ቢያቀርቡም፣ የዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን
ሊያስተባብሉ አለመቻላቸውን በመግለጽ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ያቀረበው የቅጣት ማክበጃ ቅጣቱ
ከብዶ እንዲወሰን ነበር፡፡
ተከሳሾቹ የቅጣት ማቅለያ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ አቶ በቀለ ጥፋተኛ አለመሆናቸውንና አድርገዋል በተባሉት ጉዳይ ላይ ምንም ነገር
እንዳልፈጸሙ፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ሲታገሉ ሕዝቡን በድለው ከሆነ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ከመጠየቅና ባለቤታቸው በእሳቸው
ምክንያት ከሥራ በመባረራቸው ልጆቻቸው ያለ ገቢ ከመኖራቸው በስተቀር፣ ምንም ያጠፉት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ አቶ ኦልባናም
ለምን እንደታሰሩ አለማወቃቸውን ከመግለጽ በስተቀር ምንም ባለማለታቸው በሁለቱም ላይ ቅጣቱ ከብዶ ተወስኗል፡፡ ሌሎቹ ባቀረቡት
የቅጣት ማቅለያ መሠረት ቅጣቱ ቀሎ ተጥሎባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሳ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት የወሰነባትን የ14 ዓመታት
እስራትና የ33 ሺሕ ብር ቅጣት የተቃወመችው መምህርትና ጋዜጠኛ ርዕዮተ ዓለሙ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ
የተጣለባት ቅጣት ወደ አምስት ዓመታት ዝቅ ማለቱ ይታወሳል፡፡ በድጋሚ የሕግ ስህተት መፈጸሙን በመግለጽ ለሰበር ሰሚ ችሎት
ያቀረበችውን አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ትናንትና ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar