søndag 25. november 2012


ፍቱልኝ›› የተማጽኖ ግጥም አንድምታው ምን ይሆን!?
በፍቅር ለይኩን [fikirbefikir@gmail.com]
በታሪካዊው፣ የአፍሪካ ሕዝቦች የሥልጣኔ መሠረትና ሕያው የዘመናት አሻራ በሆነው በታላቁ ወንዛችን በዓባይ ላይ በመገንባት ላይ ያለውን የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተመለከተ የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላለሆኑ ተቋማቶችና ድርጅቶች ምስጋና እና የማበረታቻ ሽልማት ለመስጠት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሣትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት በሚሊንየም አዳራሽ በጠራው ዝግጅት ላይ ለመገኘት ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡
የሚሊኒየሙ አዳራሽ የሚገኝባት ቦሌ በመንገድ ግንባታው ምክንያት የወትሮ ውበቷንና ድምቀቷን አጥታ፣ በመንገዶቿና በዘመናዊ መዝናኛዎቿ የውበት ካባን በእጥፍ የደረቡ የሚመስሉ፣ ከሀገሪኛው ቋንቋ ይልቅ አውሮፓዊው ቋንቋ የሚቀናቸው የሸገርን እንስቶችና ወጣቶችን በብዛት የምታስተናግደው ቦሌ ሊያውም በተናፋቂዋ በቅዳሜ ቀን ምሽት እንዲያ በመንገዶቿ መፈራረስ ምክንያት የቆንጆዎች ድርቅ እንደመታት ታዘብኩና ለቦሌና ለቦሌዎች የመንገድ ግንባታው በቶሎ ተጠናቆ ያዩት ዘንድ በልቤ ተመኘኹላቸሁ፡፡
የውቦች መናኻሪያ፣ የኢትዮጵያዊነት ኩራት መገለጫ የአየር መንገዳችንን መጠሪያ ውቧን ቦሌ ‹‹አይዞን!›› በማለት ማጽናናት በሚመስል ስሜትና ትዝብት የትናትናዋን ቦሌ በዓይነ ኅሊናዬ እያመላለስኩ አቧራና ፍርስራሽ በዋጠው በቦሌ መንገድ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ሚሊንየም አዳራሽ በዝግታ አመራሁ፡፡
በመግቢያው በር ላይ የጥሪውን ካርድ ለጥበቃ ሠራተኞቹ አሳይቼ ወደ ግቢ ውስጥ ዘለቅኩኝ፡፡ ወደ ዋናው አዳራሽ ለመግባት ያለውን ጥብቅ የሆነ በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘውን ፍተሻ አልፌ ወደ ዋናው አዳራሹ መግቢያ አመራሁ፡፡ ግና ፍተሻው እንዲያ ሱሪ በአንገት የመሆኑ ነገር እንዴት ነው ዓባይ ወሬው እንጂ ግድቡ ቦሌ ሚሊንየም አዳራሽ መጣ እንዴ…!? ምነው እንዲህ ክፉኛ ጠረጠሩን? ባይሆን ይህን በታሪካዊውና በህልውናችን መሠረት በሆነ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ግድብ የምትሉትን ነገር ብታቆሙ ይሻላችኋል፣ አለበለዚያ ግድባችሁን የባቢሎን ፍርስራሽ ክምር ባናደርገው በሚል በግልጽና በምስጢር መክረዋል፣ ዝተዋል የተባሉት ግብፅና ሱዳን እንጂ እኛ ነን እንዴ በሚል ትንሽ ቅሬታ ቢጤ ተሰማኝ፡፡
ቅሬታዬን በውስጤ ይዤ ወደ ዋናው አዳራሽ የሚሄደውን ጎዳና በመያዝ ያመራኹት፡- ‹‹ዓባይ፣ ዓባይ፣ ዓባይ ወንዛ ወንዙ…›› የሚለውን በእጅጉ የማደንቃትን የባለ ቅኔዋንና የድምፀ ሸጋዋን የእጅጋየሁ ሺባባውን (የጂጂን) ውብ ዜማ በኅሊናዬ እያመላለስኩና በለሆሳስ እያንጎረጎርኩ ነበር፡፡
የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ክብርና ኩራት፣ አዎን! የኢትዮጵያዊነት ታላቅ እምነትና ክቡር የማንነት መገለጫ፣ የሰው ልጆች ሥልጣኔ፣ የአፍሪካዊነት ታሪክና ቅርስ ሕያው ምስክር፣ የጥቁር ሕዝቦች ዘላለማዊ የሆነ ቋሚ መዘክር፣ የኤደን ገነት ምንጭ፣ ውብ ፈርጥና ድምቀት፣ (መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የኤደንን ገነት ከሚከቡና ከሚያጠጡ ወንዞች መካከል መነሻውን ኢትዮጵያ ያደረገው የግዮን/የዓባይን ወንዝ በዘፍጥረት መጽሐፍ ፃፊ በሊቀ ነቢያት ሙሴ መጠቀሱን ልብ ይሏል)፡፡ የጥቁር አፈር ትሩፋት ድምፃዊቷ ጂጂም ስለ ትንግርተኛው ዓባይ እንዲህ ነበር በውብ ቃላት የተቀኘችለት፣ ድንቅ በሆነ ዜማ ያንጎራጎረችለት፡-
የማያረጅ ውብት፣
የማያልቅ ቁንጅና፣
የማይደርቅ የማይነጥፍ፣
ለዘመን የጸና፡፡
ከጥንት ከፅንስ አዳም፣ ገና ከፍጥረት፣
የፈሰሰ ውኃ ፈልቆ ከገነት… ዓባይ ግርማ ሞገስ…

የታሪክ አባት የሚባለው ግሪካዊው ሄሮዱተስ እንደፃፈው ‹‹ለግብፃውያን ሕይወት መሠረት››፣ ዓለምን እፁብ ድንቅና ጉድ ያሰኙ እስከ አሁንም ድረስ በምን ጥበብና ብልሃት እንደተገነቡ ለምድራችን ጠቢባን ሁሉ ትንግርትና እንቆቅልሽ ለሆኑ፣ የሰማይን አድማስ ለሚታከኩ ፒራሚዶች መገንባት ምስጢር የሆነውን ታላቁን ወንዛችንን ዓባይን ለአፍታ በዓይነ ኅሊናዬ ከምንጩ ከጣና እስከ ታላቂቷ ግብፅ፣ ሱዳንና ሜድትራኒያን ባሕር ወደ ፊትና ወደ ኋላ በታሪክ መነጽር እየቃኘኹ ወደ አዳራሹ ውስጥ አመራሁ፡፡
በአዳራሹ መግቢያ ግራና ቀኝ በሐገር ባሕል ልብስ የደመቁና ውብ ፈገግታን በሚረጩ የአገሬ ቆነጃጅት የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበልና ድንቅ የአበባ ስጦታን በምስጋና ተቀብዬ ወደፊት አመራሁ፡፡ ወደ ዋናው አዳራሽ መግቢያ በስተቀኝ በኩል በታላቁ ወንዛችን በዓባይ ላይ ግንባታው ስለተጀመረው ስድስት ሺህ ኪሎ ዋት የሚያመነጨውን የታላቁን የህዳሴውን ግድብ የሚያሳዩ መጠነኛ የፎቶግራፍ ትእይንት ዞር ዞር ብዬ ከተመለከትኩ በኋላ ወደ አዳራሹ በመግባት መቀመጫ ያዝኩ፡፡ አዳራሹ ቀስ በቀስ በሰው ተሞላ፡፡ የሃይማኖት አባቶችና ተወካዮች፣ አምባሳደሮች፣ ከፍተኛ የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የየክልሉ ርእሰ መስተዳድሮች፣ ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶች፣ ተጋባዥ እንግዶች አዳራሹን ሞሉት፡፡
የፕሮግራሙን መጀመር ለአንድ ሰዓት ያህል ያዘገየው የዕለቱ የክብር እንግዳ የጠቅላይ ሚ/ር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚ/ር እና የትምህርት ሚ/ሩ፣ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአዳራሹ ከታደሙ በኋላ ዝግጅቱ በይፋ መጀመሩ ተበሰረ፡፡
በዕለቱ የዝግጅቱ የመድረክ መሪዎች፡- ዓባይ ወንዛችንን ከኢትዮጵያዊ ክብር፣ ነፃነት፣ አንድነት፣ ማንነትና ኩራት አፍሪካንና አፍሪካውያንን እንዲሁም መላውን የጥቁር ዘር ሕዝቦችን ሁሉ ወኔ፣ ክብርና ታላቅነት ከፍ ካደረገው የዓድዋ ድል ጋር በማነፃጸር በቅብብሎሽ ያቀረቡት መነባንብ ዓባይ ከኢትዮጵያዊነት ጀግንነት፣ የሺህ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔና ጋር ያለውን ቁርኝት ወደኋላ ለጉዤ በዓይነ ኅሊናዬ እቃኝ ዘንድ አስገደደኝ፡፡
በሚሊንየሙ መድረክ የቀረበው የዐድዋው ገድልና የዓባይ የዘመናት የታሪክ ትንግርትነት ልቤን በኢትዮጵዊነት ፍቅር፣ ክብርና ከፍተኛ ስሜት የሞላ ነበር፡፡ ኢትዮጵዊነት በሺህ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ በአባቶቻችን የጀግንነትና የነፃነት ክብር የደመቀ፣ ኢትዮጵያዊነት የቀደሙ አባቶቻችን ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ወንድ፣ ሴት ወዘተ ሳይሉ በከፈሉት ታላቅ የደም መስዋእትነት ውብ ሆኖ የተሸመነ የአንድነትና የኩራት ጥበብ ምንጭ መሆኑ ጎልቶ ተሰማኝ፣ ደምቆ ታየኝ፡፡
ኢትዮጵያዊነት የፍቅር፣ የአንድነት፣ የሰላም ሰንደቅ ሆኖ ከፍ ብሎ በመስዋእትነት ደም ያሸበረቀ ዓላማ ሆኖ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከኤዥያ እስከ ካረቢያን፣ ከአውሮፓ እስከ ጃፓን ለመላው ዓለም ከፍ ከፍ ብሎ የታየ በዘመናት ርዝማኔ ያልደበዘዘ ውበት መሆኑን ለራሴ አወጅኹ፡፡
ይህን ከእኛ አልፎ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የኢትዮጵያዊነትን ታላቅ ክብርና ብሔራዊ ኩራት ያደመነውን ለዘመናት የተጫነን የድህነት ቀንበር ለመሰበር ኢትዮጵያውያን በጋራ ለጋራ ጥቅም ክንዳቸውን በዓባይ ላይ የሚያሳዩበትን ታሪክ ሠርተው ለቀጣዩ ትውልድ ሕያው የሆነ አሻራ የሚያቆዩበት ታላቅ የታሪክ አጋጣሚ እንደሆነ ነበር በምሽቱ በመድረኩ ላይ የተነገረው፡፡
በዚህ በቅዳሜ ምሽት ላይ በሚሊንየም አዳራሽ በተደረገው ዝግጅት ላይ ለሁለት ተከታታይ ሰዓታት በላይ ከቀረቡት ዝግጀቶች መካከል በእጅጉ ልቤን የነካኝ በግምት ዕድሜዋ አስር ዓመት የሚሆናት ከመካኒሳ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ት/ቤት የመጣች ታዳጊ ህፃን ‹‹ዓባይ የት ነበረ›› በሚል እጅግ በሚመስጥ የድምፅ ቅላፄና የሰውነት እንቅስቃሴ ጋር ያቀረበችው ግጥም አንዱ ነበር፡፡ ለዚህ ጹሑፍ መነሻ ዋንኛ ምክንያት የሆነኝ ግን የዚህች ታዳጊ ሕጻን ከዓባይ የት ነበረ ግጥሟ አስከትላ ለክቡር ጠቅላይ ሚ/ሩ ያቀረበችው ስሜት ኮርኳሪና በእጅጉ አንጀትን የሚያላውስው ግጥሟ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ታዳጊዋ በቅድሚያ ባቀረበችው ግጥሟ በዓባይ ላይ የተጀመረውን የታላቁን የህዳሴውን ግድብ ለመፈጸም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነትና በፍቅር ክንዱን አስተባብሮ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ተባብረን መሥራት እንደሚያስፈልገን የገለጸችበትን ግጥም አቅርባ ከጨረሰች በኋላ አሁን ደግሞ አለች ያች ታናሽ ብላቴና በሚኮላተፍና በጣፋጭ አንደበቷ፤ አሁን ደግሞ… ይህን ግጥም የማቀርበው ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚ/ር ለተከበሩ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ነው፡፡ ይሄን ጊዜ አዳራሹ የሞላው ሕዝብ በግርምትና ምን ልትላቸው ይሆን በሚል ጉጉት ዓይኑን ወደ ልጅቱና ግጥም ሊበረከትላቸው ወዳሉት ወደ ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለ ማርያም አቅጣጫ የሁሉም ዓይኖች ተፈተለኩ፡፡
ግጥሙ አለች ያቺ እንደ ጎልያድ በገዘፈው መድረክ ላይ በዳዊት ብላቴናነት/ታናሽነት የተሰየመች ግን ደግሞ ዕድሜዋን ወይም ታናሽነቷን ፈፅሞ በማይመጥንና እጅግ በሚልቅ በእስራኤላዊው የዳዊት ጀግንነት፣ ታላቅ ወኔና በራስ የመተማመን መንፈስ፣ ከሕፃንነት ንፁህ ልብ ከሚመነጭ ፍቅር፣ ርኅራኄንና ምሕረትን በሚሹ ዓይኖቿ አንዴ ክቡር ጠቅላይ ሚ/ሩን አንዴ ደግሞ ሕዝቡን እየቃኘች በቦሌው የሚሊንየም መድረክ የምሕረት ያለህ! የይቅርታ ያለህ! አባቴን አስፍቱልኝ/ፍቱልኝ… እባክዎ ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር በሚል ተማህጽኖ መድረኩን የተቆጣጠረችው ሕፃን፡-
‹‹ይህ ግጥም እውነተኛ ታሪክ ነው፣ ግጥሙ ከእውነተኛ ታሪኬ በመነሳት የጻፍኩት ነው፡፡›› በማለት ምሽቱን ስለ ዓባይ ልማት ስናወራ በአንድነት የሚያስተሳሰረን የፍቅርና የእርቅ ልማት በኢትዮጵያችን ይቅደም፣ ይምጣ፣ አሁን ይሁን… በሚል ስሜት በአዳራሹ ውስጥ የፍቅርንና የእርቅን አዋጅ አወጀችበት፡፡ መድረኩ ለአፍታ ምሕረትን፣ ይቅርታን በሚሻው በብላቴናዋ ተማጽኖ ድባቡ የተቀየረ መሰለ፡፡
ይህ ድምፅ ከምሕረትና ከእርቅ ይልቅ ጥላቻና ጠላትነት ለነገሰበት የኢትዮጵያችን የፖለቲካው መድረክ፣ መለያየት፣ ጠብና መከፋፈል ላየለባቸው ለቤተ ክህነቱ መሪዎች፣ በጎሳና በዘር ፖለቲካ ቁም ስቅሏን ለምታየው እናት ምድራችን በዚህች ታናሽ ብላቴና የታወጀ የእርቅና የምሕረት አዋጅ መስሎ ተሰማኝ፡፡
በህፃኗ የአነጋገር ብስለት፣ አንደበተ ርእቱነትና ድፍረት የተመሰጡ በአዳራሹ በተሞሉ እንግዶች በአድናቆትና በግርምት ፈገግታ ጥቂት ቆየት ብሎም በሐዘኔታ መንፈስ የታጀበችው ሕጻን ከእሷ የሚወጣ በማይመስል አስገምጋሚ የፍቅር ነጎድጓድ ድምፅ ‹‹እባክዎ አባቴን ፍቱልኝ/አስፈቱልኝ›› ስትል ያቺ ትንሽ ብላቴና ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለ ማርያምን በግጥሟ መልእክትና በዓይኖቿ መማጸን፣ መሟገት ያዘች፡፡
ብላቴናዋ ልብን በሐዘን በሚሰብር ግጥሟ አባቷን፡- ‹‹አባባ ልጅህ አድጌልሃለሁ፣ በትምህርቴም ጎብዤያለሁ፣ ትልቅ ሰው ሆኜ ስምህን አሰጥረዋለሁ፡፡ አ…ባ…ባ… አ…ባ…ብ…ዬ…ዬ…ዬ… በጥፋትህ እንደተጸጸትህ አውቃለሁ፡፡ ነገ ከእስር ቤት ወጥተህ ጥፋትህን በሚልቅ ካሳ ለሕዝብና ለሀገር ባለውለታ እንደምትሆን አስባለሁ፣ አ…ባ…ባ…፣ አ…ባ…ብ…ዬ… ናፍቀኸኛል እኮ አባቢ! እንደሁሌው ሁሉ እስር ቤት መጭቼ አይሃለሁ… አንተም እንደምትናፍቀኝ አውቃለሁ፣ አባቢዬ…ዬ…ዬ…ዬ…!
እንደዚህ ባሉ እጅግ ስሜትን በሚነኩ፣ የዓይኖቻችንን የእንባ ምንጮች ሁሉ ለመንደል ኃይል ባላቸው፣ ጨካኝ የተባለን ሰው ልብ ቢሆን እንኳ ሊያርዱ በሚችሉና ነፍስ ድረስ ዘልቆ በሚሰማ ኃይለ ቃላቶች በተሞሉት ግጥሟ ብላቴናዋ ‹‹እባክዎ የተከበሩ ጠቅላይ ሚ/ር አባቴ ያስፈትሉኝ፣ አባቴን መንግሥትዎ ይቅርታ ያድርግለት!›› በሚለው ተማህጽኖዋ በዛች ቅዳሜ ምሽት በልቤ ውስጥና በሚሊንየሙ አዳራሽ መድረክ ላይ የነገሰች ብቸዋ እርቅን ሰባኪ፣ ምሕረትን የምትሻ ሕፃን መላው እኔነቴን ተቆጣጠረችው፡፡
ለወላጅ አባቷ መንግሥት ምሕረት ያደረግለት ዘንድ አጥብቃ የምትሻ ሚሚዬ፡- ክፋት፣ ጥላቻና ቂም በቀል ባየለባት ምድረ በዳ የበቀለችና ያበበች የእውነትና የፍትህ ምስክር ቡቃያ መስላ በዓይነ ኅሊናዬ እጅጉን ገዝፋ ታየችኝ፡፡ አዳራሹን ካስዋቡት የተለያዩ ሐምራዊ ቀለሞችን ከሚረጩት የመድረኩ አምፖሎች አስር እጅ ደምቃ፣ አብርታና ጎልታ ታየችኝ ይህች ታናሽ ብላቴና ግን ደግሞ ፍቅር ድፍረት፣ እውነት ኃይልና ብርታት የሆናት ‹‹ይቅርታንና ምሕረትን›› አጥብቃ የምትሻ የምሽቱ ታላቅ ጀግና ሕፃን፡፡
የዚህች ታናሽ ብላቴና ‹‹መንግሥት ለአባቴ ይቅርታ ያድርግለት!›› በሚል ለጠቅላይ ሚ/ሩ ያቀረበችው የተማጽኖ ግጥም የወላድን አንጀት የሚያንሰፈስፍ፣ ሁለተናን የሚያርድ፣ አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማና ውስጥን የሚበረብር ነበር፡፡ አባባና እማማ የሚሏቸው ልጆች ላላቸው ወላጆች ሁሉ ልብን በሐዘን በሚሰብር ቅላጼና ተማጽኖ የቀረበው የሚሚ ግጥም በእውነት ለመናገር በእጅጉ ነበር ውስጤን የነካው፡፡
እንዲህ ዓይነቱን የተማጽኖ ግጥም እየሰሙ ያሉት በአባትነት ፍቅር፣ በመልካም ስነ ምግባር ልጆቻቸውን አሳድገው በማሰተማር ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚ/ር በዛች ምሽት እንዲያ በመድረኩ ላይ ‹‹እባክዎ አባቴን በይቅርታ ይፍቱልኝ›› እያለች ፊት ለፊታቸው ቆማ በኮልታፋ አንደበቷ ዓይኗን እያንከራተተች ስትማፀናቸው ጠቅላይ ሚ/ሩ ምን ሊሉ እንደሚችሉ ባላውቅም የብላቴናዋ ግጥምና ተማጽኖ ግን ልባቸውን ሊነካቸው እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱስ ሲባል ጠቅላይ ሚ/ር በስስትና በፍቅር የሚመለከቷቸውና የሚሳሱላቸው አባባ፣ አባብዬ የሚሏቸው ልጆች አላቸውና፡፡
የቅዳሜዋ ምሽት የሚሊንየም አዳራሽ ዝግጅት በድንገት የተሰማው የምሕረት/የይቅርታ ጥያቄና የአባቴን ይፍቱልኝ ነፍስና አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማው የብላቴናይቱ የተማጽኖ ድምፅ ያለ ጥርጥር ፍትህንና እርቅን የተራቡ የብዙዎች ወገኖች ድምፅ እንደሆነ አስባለሁ፡፡
ይህ ድምፅ ከምሕረትና ከእርቅ ይልቅ ጥላቻና ጠላትነት ለነገሰበት የኢትዮጵያችን የፖለቲካው መድረክ፣ መለያየት፣ ጠብና መከፋፈል ላየለባቸው ለቤተ ክህነቱ መሪዎች፣ የጎሳና የዘር ፖለቲካ ቁም ስቅላቸውን ለሚያዩት የእናት ምድራችን ፖለቲከኞች በዚህች ታናሽ ብላቴና የዋህ ልብና ንጹህ መንፈስ የታወጀ የእርቅና የምሕረት አዋጅ መስሎ ቢሰማኝ ብዕሬን በማንሳት እንዲህ ስሜቴን ላጋራችሁ ወደድሁ፡፡
እናም የዛች ምሽት ጣፋጭና ተወዳጅ ብላቴና ግጥም ከወራት በፊት በሽብረተኝነት ወንጀል ተከሶ ወኅኒ የወረደውን እስክንድር ነጋ ብላቴና የሆነውን ሌላውን ምስኪን ሕፃን ናፍቆትን አስታወሰኝ፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በሽብረተኝነት ወንጀል ምክንያት ተጠርጥሮ በተያዘበት ጊዜ የነበረውን አሳዝኝ ትእይንትና በወቅቱ ሕፃን ናፍቆት የእውነት ያለህ፣ የፍትህ ያለህ ጩኸቱንና ዕንባውን እንዳስታውስ አስገደደኝ፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ሀገረ ሰላም ነው ብሎ ብላቴናውን ከት/ቤት አውጥቶ ወደ ቤታቸው በመውሰድ ላይ እያለ ነበር በመንግሥት የደህንነት ኃይሎች ገና ምንም በማያውቅ ብላቴናው ፊት እጁ በካቴና የፊጥኝ ታስሮ እንዲወስድ የተደረገው፡፡ በወቅቱ ብላቴናው ናፍቆት አ…ባ…ባ… አ…ባ…ዬ… አባቴን የት ልትወስዱት ነው የሚለውን የእስክንድር ብላቴና ጩኸት በወቅቱ ሰሚም ታዛቢም አላገኘም ነበር፡፡ በወቅቱ የእስክንድር ባለቤት እስክንድር በፖሊሶች ቁጥጥር ስር በዋለ ጊዜ የነበረውን አሳዛኝ ክስተት ስትገልጽ፡-
‹‹እኔ ሐዘን ነዉ የተሰማኝ። እስክንድር በመታሰሩ ሳይሆን እርሱን ሲወስዱት፣ ልጃችንን መጀመሪያ ሰጥተዉኝ፣ ከአባቱ አርቄዉ፣ በአባቱ ላይ ያደረጉትን ቢያደርጉ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ጨንቆት፣ እያለቀሰ፣ አባቱን እየቀረጹ፣ አባቱ እጅ ላይ ካቴና ሲያስገቡበት፣ የሚሆነዉን አጥቶ ሲጮህ በቃ ዉስጤ አዘነ። ሐዘኔ በሕጻኑ ነዉ፡፡ ሕጻኑ ነዉ ያሳዘነኝ፡፡›› ስትል የእስክንድር መታሰር በልጃቸዉ በናፍቆት እስክንድር ላይ ያሳደረዉን ትልቅ የስነ-ልቦና ችግር በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ እንዲህ ገልጻው ነበር፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ሰብአዊነትና ርኅራኄ የጎደለውን እርምጃ በምን ዓይነት መልኩ ፍትሐዊነቱና ሕጋዊነቱ ሊገለጽ እንደሚችል ሕግን እናስከብራለን፣ ለፍትህ፣ ለእውነትና ለሰው ልጆች መብት ቆመናል በማለት ነጋ ጠባ የሚነግሩን የፍትህ ተቋማትና ሰዎቻቸው ቢያስረዱን መልካም ነበር፡፡
በሰብአዊ መብቶች መከበርና ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አመነስቲ ኢንተርናሽናልና በሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ሀገራችን ያለው የሰብአዊ መብት አያያዝ እስከፊ ሁኔታ ላይ እንዳሉ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የመፃፍና የመናገር መብቶች የተጠበቁ ናቸው የሚለውን የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በሚቃረን መልኩ መንግሥት የተቃዋሚ ኃይሎችን፣ ጋዜጠኞችንና የመንግስትን አቋም አብዝተው የሚተቹና የሚጽፉ ሰዎችን ባሻው ጊዜ ያስፈራራል፣ያስራል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው አስከፊ የሆነ የመብት ጥሰት በተመለከተም የሂዩማን ራይትስ ዎች በ2012 ሪፖርቱ ሲገልጽና ሲተች፡-
Ethiopian authorities continued to severely restrict basic rights of freedom of expression, association, and assembly. Hundreds of Ethiopians in 2011 were arbitrarily arrested and detained and remain at risk of torture and ill-treatment.
እንዲህ በነጋ ጠባ ሀገር ውስጥና በውጭ በሚገኙ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ክፉኛ የሚብጠለጠለው የኢትዮጵያ መንግሥት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ከሙስናና ከአድሎዎ የጸዱ ለፍትህና ለእውነት የቆሙ የፍትህ ተቋማትን እናስፋፋለን ቢልም በተግባር እየታየ ያለው ግን ባለሥልጣናቱ ከሚነግሩን ጋር እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ አሳዛኝ እውነቶችን ነው፡፡ ዛሬም የመንግሥትን ፖሊሲዎችና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የሚተቹ ሰዎችና ድርጅቶች በአብዛኛው ዕጣ ፈንታቸው አንድም ዘብጥያ ነው አሊያም ከሀገር መሰደድ ነው፡፡
መንግሥት የሚቃወመውንና ከእኔ ወገን ካልሆንክ ከጠላቴ ወገን ነህ በሚል ጭፍን አካሄድ የገዛ ሕዝቡን በማሸማቀቅና የሽብረተኝነት ታርጋ በመለጠፍ ሊያሳቅቅ የሚገባው አይመስለኝም፡፡ ከሕዝብ ጋር ተኳረፎና ተራርቆ፣ የገዛ ወገንን አስጠብቦና አስጨንቆ በመያዝ ፈጣን የሆነ ልማት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያችን ለዘመናት ካስነከሳትና ስሟን ከለወጠባት የራብና የእርስ በርስ እልቂት አዙሪት ወጥታ፣ ቁስሏ ሽሮ ስብራቷም ተጠግኖ፣ አገራችን አንገቷን ከደፋችበት አሳፋሪ ታሪኳ ወጥታ ቀና ትል ዘንድና በልማትና በእድገት ጎዳና ላይ ተራምዳ እንድናያት ይህ ትውልድ አጥብቆ ይሻል፡፡
ይህ ይሆን ዘንድ ለእውነትና ለፍትህ የሚሟገት፣ ልበ ሰፊ፣ ታጋሽ፣ ሕዝቡን የሚሰማ፣ የሚወድና የሚያከብር መንግሥት ለኢትዮጵያችን በእጅጉ ያስፈልጋታል፡፡ አለበለዚያ ግን አቀንቃኙ እንዳለው ‹‹አዲስ ንጉሥ እንጂ መቼ ለውጥ መጣ!?›› ይሆናል ነገሩ፡፡ በተባበረ ክንድ ድህነትን እንበቀለው ዘንድ ጽኑ በሆነ መሠረት ላይ ሊያቆመንና ሊያስተሳስረን የሚችልበት ሕዝባዊ የሆነ የፍቅር ገመድ በልቡና ውስጥ እንዲያብብ የማይፈልግ መንግሥት ሰላሟን፣ እድገቷንና ብልጽግናዋን የምንመኝላት ኢትዮጵያችን ትንሣኤዋን ሊያሳየን ብቃት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ በእጅጉ አዳጋች ነው፡፡
በቅዳሜዋ ምሽት በሚሊንየም አዳራሽ የቀረበው የአባቴን ፍቱልኝ፣ መንግሥት ለአባቴ ይቅርታ አድርጎለት ይፈታ ዘንድ አማጸናለሁ በሚል መንፈስ በሕፃን መዓዛ ለጠቅላይ ሚ/ር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የቀረበው የአቤቱታና ተማህጽኖ ግጥም የእነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የእነ አንዱ ዓለም አራጌ እምቦቃቅላ ሕጻናትና ብላቴናዎች እንዲሁም የሌሎች በርካታ ፍትህን የሚሹ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችና ልጆቻቸው ጭምር ድምፅ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
እንደ ትላንትናው ዛሬም ፍትህንና ፍርድን የሚሹ የበርካታ ኢትዮጵያን እናቶች እንባ እንደ ራሄል እንባ የእውነት፣ የምሕረት፣ የፍትህ ያለህ በሚል ታላቅ ጩኸት ወደ ጸባኦት፣ ወደ አርያም እየተረጨ ነው፣ ይህ የብዙዎች እንባ፣ ለኢትዮጵያ ትንሣኤ የተገበረ የእልፍ ጀግኖቻችን ላብና ደም ከጭንገፋና ከመመከን ተርፎ ፍሬ አፍርቶና ጎምርቶ የምናይበትን ዘመን ልዑል እግዚአብሔር ያቀርብልን ዘንድ በመመኘት ልሰናበት፡፡
ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት፣ ፍትህና ልማት ለኢትዮጵያችን ይሁን!
ሰላም! ሻሎም!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar