ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከቁራና ከዳዊት የቱን ይመርጣሉ? ከተከበሩ ግርማ ሠይፉ ማሩ
ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
አልፎ አልፎ ጠዋት የማገኛቸው የማኪያቶ ቡድን አለ፡፡ በፓርላማ ሰለነበረው ውሎ መሠረት አድርገው የግል አሰተያየት ይሰጣሉ በዚህ መሃል አንዱ ምሳሌያዊ ንግግር አደረገ ወደድኩትና ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ቁራ ታውቃላችሁ በተለይ መሬት ላይ በእግሯ ስትሄድ አታምርም ይህ ችግር እንዳለባት ታውቃለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእርግብ አካሄድ ይማለርካታል፡፡ አካሄዷን ለማሳመር እንደ እርግብ መሄድ ይኖርብኛል ብላ ወሰነችና ልምምድ ጀመረች፡፡ አስር ዓመት ሙሉ ቤት ዘግታ ስትለማመድ ቆይታ ሳይሳካላት ይቀርና ተስፋ በመቁረጥ አንድ ውሣኔ ላይ ትደርሳለች ቢያስጠላም በራሷ በቀድሞ አካሄድ እንደ ቁራ ለመሄድት ወስናለች፡፡የሚያሳዝነው ነገር ግን የእርግብንም ሳትለምድ የራሷም የቁራ አካሄድ ጠፋባት፡፡
የዚህ ምሳሌ መነሻ የሆኑት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ በምክር ቤት ውስጥ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ለመምሰል ሲያደርጉ የነበረውን ሙከራ የትዝብቱ አንድ አካል ነው፡፡ በዚህ ዕይታ ሙሉ በሙሉ ባልስማማም ፍፁም ውሽት ነው ራሳቸውን ነበር የነበሩት ብዬ ልከራከር አልችልም፡፡ እኔም የሆነ ነገር ታይቶኛል፡፡ ስለዚህ ይህ ማሳሰቢያው አቶ ሀይለማሪያም መለስን ላይሆኑ ሀይለማሪያምን እንዳያጡት የተሰጠ ምክር በመሆኑ በበጎ ወስጀዋለሁ፡፡
የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በደንብ በሚያውቁት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላስረዳ፡፡ መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ምዕራፍ 17 ዝርዝሩን ማየት ይቻላል በአጭሩ ታሪኩ የጎሊያድና የዳዊት ነው፡፡ ንጉስ ሳኦል ዳዊት ጎልያድን ለመግጠም ይመረጥና ይልከዋል ወደ ፍልሚያው ሊገባ ሲል፤ ሳኦል ለዳዊት እንዲጠቅመው በሚል የንጉሱን ካባና ንጉሱ በጦርነት ጊዜ የሚጠቀምበትን ዋነኛ መዋጊያ የሆነ የናስ ቁር ደፋለት፤ ጥሩርም አለበ ሰው፡፡ የንጉሱን ልብስ ለብሶ መንገድ ሲጀምር አልተመቸውም አውልቁልኝ ብሎ አወለቀው፤ በማስከተልም የተሰጠውን ትጥቅ ይቅርብኝ ብሎ ወንጭፌን አምጡ አለ፡፡ ከዚያም ብዙዎቹ በዚህ አለባበስና በወንጭፍ እንዴት ጎልያድን የሚያክል ግዙፍ ሰው ለማሸነፍ እንደሚችል ሲጠየቅ ጎልያድ እንደምታዩት ትልቅ ነው (የጎልያድ ቁመት ከስድስት ክንድ በላይ ነው) ለኔ ጎልያድን መምታት ሳይሆን መሳት ነው ከባድ ይላቸዋል፡፡ ግጥሚያው ሲጀመርም ዳዊት ጎልያድን በወንጭፍ ግንባሩን ብሎ ጣለው፡፡ እንዳለውም ጎልያድን መምታት ሳይሆን ከባድ መሳት ከባድ መሆኑን አስመሰከረ፡፡ ዳዊት ያደረገው ከንጉሱ ካባ ይልቅ የራሱ ደበሎ፤ ከንጉሱ ዘመናዊ መሳሪያ ይልቅ የራሱ የሚያውቀው ወንጭፍ እንደሚሻል አሰመሰከረ፡፡ እዚህ ጋ ለአቶ ሀይለማሪያም የተላለፈው መልዕክት የንጉሱ ሌጋሲ ማስጠበቅ በሚል ሳይሆን በራሳቸው ደበሎና ወንጭፍ እንዲጠቀሙ ለማሳሰብ ነው፡፡
እነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ለአቶ ሀይለማሪያም በጣም ጥሩምሳሌዎች ናቸው፡፡ ምርጫው እንደ ቁራዋ ሌላ ለመሆን ሞክሮ እራሳቸውንም መሆን አቅቶዋቸው ሳይሳከላቸው መቅረት ወይም እንደ ዳዊት የንጉሱን ትተው እራሳቸውን መሆን ነው፡፡ ምርጫው የግል ነው የኛ ጉዳይ መምከር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸውን እንዲሆኑ የምፈልግበት አንድ ሁለት ነጥብ ላንሳላችሁ አንድ የፕሬስ ህግ የመናገርና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የንግድ ህግ መሆኑን አናውቅም ነበር፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች በንግድ ህግ ብቻ የሚጠቀሱ ቢሆን ኖሮ በፍትሕ ብሔር ህግ እንጂ በህገመንግስት ውስጥ የሚጠቀሱ አይሆኑም ነበር፡፡ የህገ መንግሰቱን አንቀፅ 29/2 እና ሌሎችም ድንጋጌዎች እንዳይሸራረፉ መጠየቅ በንግድ ህግ እንዲታይ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡
ነጋዴዎች የያዙትን የንግድ ቤት በሽያጭ ይተላለፍ የሚል አስተያየት ሲሰጥ ይህ ዓላማው ድሃው እንዲኖርበት ነው ማለት የእውቀት ሳይሆን ጉዳዩ ሌላ ነው ፣ ድሃው የሚኖርበት ቤትም ቢሆን ለድሃ በይዞታነት ይተላለፍ ማለት ይቻላል፡፡ በጥያቄ የቀረበላቸው ግን ነጋዴዎች እየነገዱ ያሉበትን ቤት ባለቤትነት አዛውሩና ገንዘብ ተቀበሉ፡፡ የተቀበላችሁን ገንዘብ ደግሞ ለኢንቨስትመንት አውሉት ማለት ለወዳጅ የተሰጠ ምክር ነው፡፡ ልብ ብለው ያድምጡኝ ይህ ምክር ከተቀናቃኝም ቢሆን ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ ለነገሩ ዓላማው እራሱን ችሎ የሚኖር ነጋዴንም ቢሆን በጭሰኝነት መያዝ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ለነፃነት ስንል ጫካ ገባን የሚል ቡድን የዜጎቸን ነፃነትን ለመገደብ ምንም መንገድ እንደሚጠቀም ማሳያነው፡፡ ይህ ደግሞ ጫካ የመግባታቸው ሚስጥር ለነፃነት ነበር የሚለው ነጭ ውሽት እንደሆነ መረዳት ከበድ አይሆንም፡፡ ነፃነትን የሚያከብር ቡድን በምንም ዓይነት የሌሎችን ነፃነት በቁሳዊ ጉደይ ለመያዝ አይጥርም፡፡ ነፃነት የማያውቅ ነፃ አውጭ የሚለው የሚገልፃችሁ ይመስለኛል፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar