mandag 26. november 2012

ዛሬ የመሪዎቻችንና ሌሎች ወንድሞቻችን ችሎት ተሰይሞ ውሏል፡፡


መሪዎቻችን ከቃሊቲ ልደታ ፍ/ቤት የገቡት ከሌሊቱ 10፡30 ነው፡፡
በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ተሰይሞ የዋለው ችሎት ስራውን የጀመረው ከጠዋቱ 3፡30 አካባቢ ነበር፡፡ ፖሊስ መሪዎቻችንን ማንም እንዳያገኛቸው ከሌሊቱ አስር ሰዓት ላይ ነበር ከቃሊቲ ጭኖ ልደታ ፍ/ቤት ያደረሳቸው፡፡ ከሌሊቱ 10፡40 የደረሱት ወንድሞች የችሎት መሰየምያ ጊዜው እስኪደርስ ልደታ ፍ/ቤት በሚገኘው ጊዜያዊ መቆያ እንዲጠባበቁ ተደርገው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በአካባቢው የሚገኘው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ወደ ፍ/ቤት ጊቢ ሲገቡ ሊየያቸው ሳይችል ቀርቷል፡፡ በዛሬ የችሎቱ ቀጠሮ የመሪዎቻችንና ወንድሞቻችን ጠበቆች አቃቤ ህግ ባለፈው ወር ባቀረበው ክስ ላይ የመቃወሚያ ምላሻቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቅ የነበረ ሲሆን፤ ጠበቆቹም 28 ገጽ የሚሆነውን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያቸውን በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ጭብጣቸውንም ለፍርድ ቤቱ በቃል አሰምተዋል፡፡ዛሬ የመሪዎቻችንና ሌሎች ወንድሞቻችን ችሎት ተሰይሞ ውሏል፡፡
ጠበቆቹ በዋነኝነት አቃቤ ሕግ የመሰረተው ክስ የኢትዮጵያን ሕገ መንግስትና አገሪቷ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ህግጋት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ቃል ኪዳንን የሚጥስ እንዲሁም ክሱ የሕግ ትርጓሜን የሚያስነሳ በመሆኑ ጭምር ጉዳዩ መታየት ያለበት ይህን ጉዳይ ለማየት ስልጣን ባልተሰጠው ከፍተኛው ፍ/ቤት ሳይሆን ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችን በሚያየው የፌዴሬሽን ም/ቤት መሆን እንዳለበት በመቃወሚያቸው ላይ አመልክተዋል፡፡ አስር አባላት ያሉት የመሪዎቻችን ጠበቆች ቡድን በጋራ ያዘጋጀውና ተራ በተራም ባቀረበው መቃወሚያ ክሱ መሠረታዊ የህግ ስህተቶች ያቀፈ፣ የተብራራ አለመሆኑን እና የቀን ግድፈትም ያለበት መሆኑን በተጨባጭ ማስረጃዎች አቅርቧል፡፡ ችሎቱ የጠበቆችን ምላሽ ካደመጠ በኋላ አቃቤ ሕግ ምላሹን እንዲያቀርብ የተጠየቀ ሲሆን አቃቤ ሕግም ምላሹን ለማቅረብ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ጠይቆ፤ ችሎቱ የአቃቤ ህግን ምላሽ ለማድመጥ ለመጪው አርብ ኅዳር 21/2005 ቀነ ቀጠሮ ሰጥቶ ተነስቷል፡፡ በችሎቱ ጋዜጠኞችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተው ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለዛሬ ኅዳር 13/2005 ተቀጥሮ የነበረውን ችሎት ለመታደም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአዲስ አበባና የአካባቢው ሕዝብ በልደታ ፍ/ቤትና አካባቢው ተገኝቶ ነበር፡፡ ከማለዳው አንድ ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በአካባቢው መከማቸት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም አብዛኛው ሰው ወደ ፍ/ቤቱ ቅጽር እንዳይገባ በፌዴራል ፖሊስ አባላት ተከልክሎ ነበር፡፡ እስከ ጠዋቱ 3 ሰዓት ድረስ ወደ ጊቢው መግባት ይፈቀድ የነበረ ቢሆንም ከዚያች ሰዓት በኋላ ግን የፍ/ቤት ጉዳይ ያላቸው ሰዎች ብቻ እንዲገቡናሌሎች ሰዎች ከአካባቢው እንዲርቁ ፖሊስ ድብደባ በመፈጸም ጭምር መከላለከል አድርጓል፡፡
ከፍርድ ቤቱ በታችኛው አቅጣጫ በሚገኘው ክልል በርካታ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞች እስከ መከላከያ መኮንኖች ክበብ ድረስ ተኮልኩለው ቆመው የነበረ ሲሆን፣ በሜክሲኮና ሞላማሩም አቅጣጫ እንዲሁም የፍርድ ቤቱን ዙሪያ ጨምሮ ያሉ መንገዶች በሰው ተሞልተው ነበር፡፡ የፌዴራል ፖሊሶች እንደተለመደው በሰላም የቆመውን ሕዝብ በማስፈራራትና በመደብደብ፣ በአካባቢው ያሉትን የንግድ ሱቆችና ካፍቴሪያዎች በማዘጋትም ጭምር አየሩን በስጋት ሊሞሉት ሲሞክሩ ታይቷል፡፡ ፖሊስ በዚህ ድርጊቱ ገፍቶበት በአካባቢው ያሉትን የተሸከርካሪ መንገዶች በሙሉ የዘጋ ሲሆን ኢስላማዊ ምልክት ያላቸውን ሰዎች ከርቀት አካባቢዎች ጭምር ወደ ልደታ አቅጣጫ እንዳይሄዱ ሲያቅብ ነበር፡፡ በሞባይል ፎቶ ግራፍ አንስታቹሀል በሚልና በሌሎችም ጥቃቅን ሰበብ አስባቦች ፌዴራል ፖሊስ ከ25 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን አስሯል፡፡ ብዙዎቹ አመሻሽ ላይ ቢፈቱም አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ አሉ፡፡ ሙስሊሙ ሕዝብ በየእለቱ እና በየሰዓቱ በፖሊስ ከፍ ያለ በደል እየተፈጸመበትም በሰላማዊነቱና ትእግስቱ ዘልቋል፡፡ የሚያኮራ ትውልድ!
አላሁ አክበር!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *
*
You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar