onsdag 14. november 2012

ስደትና ስለላ በኖርዌ ከሀበሻ አበበ (ኖርዌ)



ባለፉት ወራት በተከታታይ የወጡ ጽሁፎችን ስንዳስስ ስለ ኖርዌ ስደተኞች ብዙ ነገሮችን ተገንዝበናል።
ስለስደት አስከፊነት ብዙ መረጃዎች አግኝተናል። የኖርዌ መንግስት ስደተኞችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ
ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያደረገው ስምምነት በብዙ መልኩ አነጋጋሪ ሆኖ መሰንበቱንም አይተናል።
ድርጊቱም ተተችቷል፣ በብርቱም ተቃውመውታል። ስደት የኩሩውን ኢትዮጵያውያን ማንነት ጥላሸት
መቀባቱ ብቻ ሳይሆን ከድህነቱና ከእርዛቱ በባሰ ሕዝባችንን የህፍረት ማቅ ያለበሰ መጠነ ሠፊ ችግር
ሆኗል።
በኖርዌ ውስጥ በርካታ የአፍሪቃ ቀንድ አህጉር ስደተኞች ይገኛሉ። ሀገሪቱን ካጥለቀለቁት የአፍሪካ ቀንድ
ስደተኞች መካከል ሶማልያና ኤርትራውያን ከፍተኛ ቁጥር ሲኖራቸው ኢትዮጵያውያን፣ ሱዳናውያን፣
ኬንያውያን፣ ኡጋንዳውያንና ሌሎችም ይገኛሉ። በአህጉሪቱ የተንሰራፋው ሁለገብ ችግር ሕዝቡን ለስደትና
ለስደቱ ሰለባነት ዳርጎታል። በመሆኑም የሕዝቡ ተስፋ ስደት ብቻ ሆኗል። ሠርቶ መክበር ተንቆ፣ ታግሎ
ማሸነፍ ተፈርቶ፣ ተሰዶ መንገላታት የደሀውም የሃብታሙም፣ የተማረውም ያልተማረውም፣ የገዥውም
የተገዥውም ዕጣ ፋንታ ሆኗል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ – "ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር
እምነትን ያገኝ ይሆንን?" – (ሉቃስ 18:8) ብሎ እንደጠየቀው ሁሉ - "እውን ዛሬ ከአፍሪካው ቀንድ አህጉር
መውጣት የማይፈልግ ዜጋ ይኖር ይሆን?" - የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ይሰነዘራል። በእርግጥ ጥቂቶች
ይኖራሉ።
ይህን ጽሁፍ እንድሞነጫጭር ትኩረቴን የሳበው በ ethiolion ና ethiomedia ድረ-ገጾች ላይ የተቀመጠው
Espionage on Ethiopians in Norway has TPLF backing - የሚለው መጣጥፍ ነው። ጽሑፉ በኖርዌ
ውስጥ የሚኖር ሱዳናዊ ዜጎቹን በመሰለል ተግባር ላይ መሰማራቱን ያወሳል። የሰባዓዊ ጥሰቱ አማሯቸው
ኖሪዌ የተጠለሉት ሱዳናውያን መሰለላቸው እጅግ አሳፋሪም አሳዛኝም ነው። ኢትዮጵያውያኖችም ሳይቀር
በዚሁ ሱዳናዊ ተሰለለን ማለታቸውንም ጸሃፊው ጨምረው ገልጸዋል። በእርግጥ ከሁኔታው አሳሳቢነት
አንጻር የኖርዌ መንግስት የራሱን እርምጃ ወስዶ ሁኔታውን ያጣራል፣ ያንገዋልላል፣ ይመዝናል
በመጨረሻም ውሳኔ ይቀርጻል።
ስለላ ብዙ መልኮች፣ በርካታ ተዋረዶችና ውስብስብ ሂደቶች አሉት። የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት
እንዳይናጋ ቅኝት፣ መረጃ ማሰባሰብ፣ ስለላና የስነ-አዕምሮ ውጊያ ሳይቀር ይተገበራል። አምባገነኖችም
የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ወታደራዊ የበላይና የበታች አለቆችን፣ ተቃዋሚዎችና ሕዝቡን ይሰልላሉ።
በራስ ንዝህላልነት ለስለላ ከመጋለጥ አንስቶ በስለላ ሙያ በሰለጠኑ ሰዎች ሀሳብን እስከመመዝበር፣ ቤትን
እስከማስበርበርና ዶኩሜንቶችን እስከማሰረቅ ያለውን ላይ ታችና ጠመዝማዛ ሁኔታ አቶ ማሞ ውድነህ
የእስራኤልን ስለላ ድርጅት አስታከው ተርጉመው ባቀረቡልን መጽሃፎቻቸው አስደምመውናል። በአፍሪቃ
ቀንድ ላይ ተራ ስለላ የሚጀምረው ከጎረቤት ወይም ከባልንጀራ ነው ይባላል። ይህም ከሱ ከተሻለ
ሊቀናበትና ሊያማው - ከሱ ካነሰ ደግሞ ሊንቀውና ስሙን ሊያጠፋ ፈልጎ ነው። ስለስለላ በዚህ ጹሁፍ
ብቻ ትምህርትን ሰጥቶ ማለፍ አይቻልምና ወደ ዋናው የጽሁፌ አላማ ልሸጋገር።
አንደኛ - ይህ ሱዳናዊ ሊሰልል ስለሚችልባቸውን መንገዶች እስኪ መላ እንምታ።
ወደ ኖሪዌ የመጣ ማንኛውም ጥገኝነት ጠያቂ እንክብካቤ አይጓደልበትም። እጁን ለፖሊስ ያስረከበ
ስደተኛ ወደ ማረፍያ ቤት እንዲሄድ ተደርጎ ከጥቂት ቀናት በኋላ ለቃለ መጠይቅ ይጠራል። የቃለ
መጠይቁ ሂደት ስደተኛው ትክክለኛውን መልስ እንዲያገኝ ወይንም የባለስልጣኑ መሥሪያ ቤት ጥያቄውን
ውድቅ ሊያደርጉት የሚያስችለው ቁልፍ ክንውን ነው። በቃለምልልሱ ወቅት እንደአስተርጓሚ ሆኖ
የተቀመጠው ሶስተኛ ሰው በባለስልጣኑ መሥሪያ ቤት ስልጠና የተሰጠው ወይንም በቋንቋ ችሎታው
ሥራውን ያገኘ ግለሰብ ሊሆን ይችላል። ከመረጃ ክንውን አንጻር ስንመረምረው እነዚህ አስተርጓሚዎች
ቀጥተና ተጽዕኖ ማድረግ አይችሉም። የባለስልጣኑ መሥሪያ ቤት ሊጠቅሙኝ ይችላሉ የሚላቸውን
ማንኛውንም ግለሰብ መቅጠርና መጠቀም መብቱ በመሆኑ - "እገሌ ይነሳልን" – በምትኩ - እገሌ
ይቀጠርላን" – ማለት አይቻልም። ሆኖም ግን ምዕራብያውያውኑ ሥራቸውን በንጹህ መስራት ስለሚፈልጉ
በትክክል የተበላሸ ነገር መኖሩን በማስረጃ አስደግፎ ከቀረበላቸው ለማሻሻል ፍቃደኞች ናቸው። ሱዳናዊው
ሰላይ ከነዚህ አስተርጓሚዎች መሀከል ጓደኛ ካበጀ አንዳንድ መረጃ ሊያገኝ ይችል ይሆናል። "እገሌ ምን
አለ?" – "እገሌ ምን ተናገረ?" – ብሎ ጠይቆ መረጃ ማግኘቱ ራሱ ቀላል አይደለም።
የምዕራቡ ኤሚግሬሽን ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች የውጭ ዜግነት ያላቸውን ባለሙያዎች በመቅጠር በብዙ
መልኩ ይገለገላሉ። ይህ ቁልፍ የደህንነት ሥራ ነው። እነዚህ ባለሙያዎች ለሀገሮቹ የደህንነት ሥራ በቂእገዛ በማድረግ፣ መሥሪያ ቤቶቹን በቋንቋና በስነልቦና፣ መረጃዎችን በመመዘንና በማንገዋለል እንዲሁም
ድብቅብቅ ያሉ ባህሎችንና አመለካከቶችን በመፍታት፣ አስፈላጊ ከሆነም በተለያዩ ምስጢራዊ ሥራና
በዲፕሎማሲው መስክ አገልግሎት ሊሰጡ ይችላሉ። እነዚህ እጅግ ከፍተኛ ሥራ ላይ የተመደቡት
ባለሙያዎች በዲሲፕሊን የታነጹ፣ በምግባራቸውና በጠባያቸው የተከበሩ፣ ቁጥብና ራሳቸውን የሚጠብቁ
ካልሆኑ የመረጃ ዝርክርክነት ይከሰታል። ይህ ከሆነ የስደት ጠያቂዎቹ ምስጢሮች፣ የፖለቲካ ወይም
የዕምነት አመለካከቶች ከዚህም አልፎ ተርፎ የየሀገሮቹ አለማቀፋዊ ግኑኝነት ምስጢሮች ወደ ሰላዮች
ቀልብ በቀላሉ ይደርሳሉ። በእርግጥ ይህ እንዳይከሰት የሃገሪቱ የመረጃ ሰዎች አስፈላጊውን ክትትል
ሊያደርጉ ይችላሉ። ቢሆንም ግን ይህ ሱዳናዊ ሰላይ ምናልባት ከአንድ ባለሙያ ጋር ተወዳጅቶ እጅግ
ከፍተኛ ምስጢራዊ መረጃ ለማግኘት የሚያስችለው እድል አጋጥሞት ይሆን?
አንዳንድ ሱዳናውያን ተጨቆንን፣ የአልበሽር መንግስት ሥጋዬን ዘለዘለው ወይም ደህንነቶቹ ቁም ስቃይ
አበሉኝ ብለው ዋሽተው ሊሆን ይችላል የመኖርያ ፈቃዱን ያገኙት። ፈቃዱን ባገኙ ማግስት ግን ከዚያው
ከአልበሽር መንግስት ባለስልጣናት ጋር ተዋውለው ወደ ካርቱም የሚያዘግሙም አይታጡም። ታድያ
መረጃ ሰጥቶ መቀበል ሊሆንም ስለሚችል የብዙ የትግል አጋሮቻቸውን ምስጢሮች፣ የድርጅቶቻቸውን
የትግል ስልትና ስትራተጂ ሳይደብቁ ለመናገር ጥቅም አስገድዷቸው እንደሆነስ? ይህ ዓይነቱ ተራ ክህደትና
ለጥቅም የመገዛት ባህል የሰላዮች ሲሳይ ነው።
ፈቃዱን የተከለከሉ አንዳንድ ሱዳናውያን ቆራጥ የአልበሽር መንግስት ተቃዋሚ ሆነው ሊታዩ ይችላሉ።
ነገር ግን ጠዋት ተቃዋሚ - ማታ የሰላዩ ጓደኛ በመሆን እጅግ ማፈርያ ሥራ ቢያከናውኑስ – ማን
ያያቸዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ የተቋሚዎቹ የፖለቲካ ድርጅት አባሎች ለይስሙላ ያህል በየስብሰባው
ይጮሃሉ፣ በጋዜጦችና በድረ-ገጾች ላይም የሱዳኑን አምባገነን መንግስት ይኮንናሉ። ፈቃዱን እንዳገኙ
ትዳራቸውን መሥርተው ኑራቸውን ለመኖር ወይንም በሀገራቸው ያሏቸውን ንብረቶች ለማስከበር
እየተዘጋጁ በመሆኑ ለሱዳኑ ሰላይ የየጓደኞቻቸውንም ሆነ የድርጅቶቻቸውን ምስጢር አሳልፈው ሲሰጡ
ይቆዩ ይሆናል። የዚህ ዓይነቱ መናኛ ግለሰብ - "ምን ላድርግ ብለህ ነው - ይህን ሁሉ ያደረኩት ለፍቃዱ
ስል ነው" - ብሎ መቅለስለስ ያበዛል። አጅሬው ሰላይ እንደ ድመት ለስለስ ብሎ ተጠግቶ መረጃውን
ቃርሞ እንደሆነስ? እግዚአብሄር ይወቀው።
አንዳንዱ የዋህ ከማን ጋር እንደሚውል ላያውቅ ይችላል። ያየውን፣ የበላውን፣ የሰማውን፣ የጎበኘውን፣
የወደቀውን የተኛውን ሳይቀር የሚያወራ ንዝህላል የጓደኛውንም ገበና ወይም ችግር ለሌላው ይዘከዝካል።
እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች የመረጃ ሰዎችን ትኩረት ይስባሉ። ምቀኝነት፣ ቅናትና ጥላቻ የተጠናወተው ሰው
ሃሚታ፣ አሉባልታና የስም ማጥፋት ያበዛል። በነዚህ አይነት ሰዎች የተነሳ ሰላዮች ሕብረትን ያላላሉ፣
ፍቅርን ያደበዝዛሉ፣ አባላትን ያጋጫሉ። የተቃዋሚው ፖለቲካ ድርጅቶች ዓላማ ግቡን እንዳይመታ
እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ማቅረብ የሰላዮች የመጀመርያው ምዕራፍ ነው።
ሁለተኛ – የሀርን ደህንነት ለመጠበቅ፣ ጉዳዮችን ለመከታተል፣ መረጃን ለመሰብሰብ እንዲሁም በተራ
ስለላ ሥራ ላይ የሚሰማሩት ተዋንያን ምን ይሻሉ?
የምዕራቡ ሀገሮች የኤሚግሬሽን መስሪያ ቤቶችና ፖሊሶቹ የሃገራቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ በሙያ
የታገዘ አድሏዊ ያልሆነና ሰባዓዊ መብትን የማይነካ ግልጽ፣ ስውር፣ ባህላዊ ወይንም በቴክኖሎጂ የተደገፈ
ክትትል ያደርጉ ይሆናል። ስደተኞች የሰጡት መረጃ ትክክለኛ ሆኖ ባይገኝ ወይንም አግባብ ያልሆነ
ሥራዎች መፈጸማቸውን ሲያረጋግጡ ያልተቋረጠ ክትትል ሊያደርጉ ይችላሉ። ሽብርተኝነትና ወንጀል
እንዳይስፋፋ ስለላ ያደርጋሉ።
የሱዳን መንግስት ለሕልውናዬ ያሰጉኛል የሚላቸውን ሰዎች አይሰልልም አይባልም። ሁሉም ግን ላይሰለሉ
ይችላሉ። ምክንያቱም ከማህበራዊ ዘርፍ እንቅስቃሴአቸው አኳያ ምንነታቸው ከተለየ ስለላ ላያስፈልግ
ይችላል። በሰላማዊ ሰልፍ ላይ የሚሳተፉት፣ ተቃውሟቸውን በጽሁፍ የሚያስረዱት እንዲሁም በአመራር
ቦታ ላይ በግልጽ የሚሰሩ ሰዎች ሊሰለሉም ላይሰለሉም ይችላሉ። በከፍተኛ ደረጃ ድርጊታቸውና
እንቅስቃሴአቸው የሚለካው የተቃዋሚ ድርጅቶችን የሚፈጥሩና የሚያጠናክሩ፤ ለትግሉ ማካሄጃ ገንዘብ
የሚያሰባስቡ፣ ተሰሚነትና ብቃት ያላቸውና ቆራጥ ሰዎች ብቻ ናቸው። የሚታገለው ለእውነት - በእውነት
የሆነ ግለሰብ ጥርስ ይነከስበታል። በጥቅም የማይያዝ የአልበሽር መንግስት እስከሚገረሰስ ድረስ ወደ
ካርቱም ዝር የማይሉት ብርቱዎች በሰላዮች ክትትል ይደረግባቸው ይሆናል። በምሳሌነታቸው የደረጁ
መሪዎች የብዙ ሰዎችን ቀልብ ስለሚስቡ እንደነዚህ ዓይነቶቹን ደፋር ታጋዮች ለማጨናገፍ ሰላዮች
ይራወጣሉ። የሱዳኑ መንግስት የሚያሰልለው ለሕልውናው አደገኛ የሚላቸውን ጥቂት ሰዎች እንጂ
ያወራውን፣ የዘፈነውን፣ የተሳደበውን፣ የጻፈውን፣ የጮኸውን ሁሉ አይፈልገውም።
የመኖርያ ፈቃዱን ለማግኘት ብቻ ሁሉም ተሰለልን ቢሉ የባለስልጣኑ መሥሪያ ቤት ሊታዘብ ይችላል፣በከንቱ ተሰለልን፣ ዛቻ ተደረገብን፣ አስፈራሩን የሚሉ እንደውሸታም ተቆጥረው ሌሎቹንም ጨዋ ስደተኞች
በውሸታምነት ያስፈርጃሉ። ጀግንነታቸው ሲለካ አንበሳንና ነብርን ያስራሉ የተባሉ ልሳን አሳማሪ ታጋዮች
ፈቃድ በተሰጣቸው ማግስት ሱዳን ካርቱም ውስጥ ከሰላዮች ጋር ሲሞዳሞዱ ታይተው እንደሆነ ደግሞ
የሌሎች ስደተኞች ጓደኞቻቸውን እድል ያበላሻሉ። የፕሮቴክሽን ፈቃዱን ካገኙ ቀን ጀምሮ ትግሉን እርግፍ
አድርገው ትተው የግል ሥራቸውን ብቻ የሚያቀላጥፉ ወደ ሀገራቸው የማይጓዙ ግለሰቦችም ቢሆኑ እንደ
ወስላቶች ሊቆጠሩ ይችላሉ። ልዩ ልዩ ልምዶችን የተካነው የኤሚግሬሽኑ መሥሪያ ቤት ጊዜ እንዲያጠፋ
የሚያደርጉት እንደ እነዚህ ዓይነት አስመሳዮች ናቸው። እነዚህ ራስ ወዳዶች በትክክል ከለላ
ለሚያስፈልገው ስደተኛ እንዲሁም የትውልድ ሀገሩ ከአምባገነኖች እንድትነጻ በጽኑ ለሚታገለው ሀቀኛ
ግለሰብ ግርዶሽ ይሆናሉ።
ሶስተኛ – ተጨባጭ ምሳሌ
በውጭ ሀገር ያሉ ዜጎቹን በመሰለል በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሳይቀር እያደር ዘግናኝ ሥራው
የተረጋገጠው ሙክሃባራት (MUKHABARAAT) የተባለው በፕሬዚዳንቱ የሚመራው የሶርያ የስለላ
ድርጅት ነው። ይህ የስለላ ድርጅት የሶርያን መንግስት በመቃወም በውጭ ሀገር የሚኖሩትን ሶርያውያን
አበሳ ከማሳያቱ በተጨማሪ በሶርያ የሚገኙትን የነዚሁ ታጋዮችን ዘመዶችና ጓደኞችን ያሰቃያል። በርካቶች
በካናዳ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ቺሊ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ስፔን፣ ስዊድንና እንግሊዝ ያሉ ደፋርና ቆራጥ የሶርያ
መንግስት ተቃዋሚዎች እየተሰለሉ ዘመዶቻቸው መታሰራቸውና ደብዛቸው መጥፋቱን ተናግረዋል። እስቲ
ከብዙ በጥቂቱ Amnesty 2011 October ስለ ሶርያው የስለላ ድርጅት በኖሪዌ ጎረቤት ሀገር ስዊድን
የተፈጸመውን አስመልክቶ የዘገበውን በራሴ ትርጉም ላቅርብላችሁ።
ኢማን አል-ባግዳዲ ትባላለች። ከሶርያ ወደ ስዊድን ከመጣች ሁለት ዓመት ገደማ ይሆናታል። ይህች
ስደተኛ ስለደረሰባት ችግር ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋር የተወያየች ስትሆን በስዊድኑ Dagens Nyheter
ጋዜጣ ላይ 30 july 2011 ዓ/ም ቃለ መጠይቅ ተደርጎላታል። እንደ እርሷ አባባል ሕዝባዊ አመጹ በሶርያ
ከተቀጣጠለ በኋላ ይህንኑ የሕዝብ ትግል ስቶክሆልም ከሚገኘው መኖርያ ቤቷ በተለያዩ ሜድያና ድረ-
ገጾች ስታሰራጭ ነበር። እሷና ባለቤትዋ በበርካታ ትዕይንተ ሕዝብ ላይም ተሳታፊ ሆነዋል። ይህ በእንዲህ
እንዳለ አንድ ቀን በጎረቤትዋ አማካኝነት በአረብኛ ቋንቋ የተጻፈ ደብዳቤ ደረሳት። ጽሁፉ - "አርፈሽ
ተቀመጭ አለበለዝያ አንቺም ሆንሽ ሶርያ የሚገኙት ዘመዶችሽ ደህንነታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል" –
ይላል። መለዕክቱን ስታስተላልፍ የቆየችው በቤት ስሟ ቢሆንም እንኳን ይሄው ስሟ ግን በሶርያው
የመረጃ ሰዎች ሊታወቅ ችሏል። ከጥቂት ቀናት በኋላ ሶርያ የሚገኘው የኢማን ወንድም ተይዞ ቁም
ስቅሉን አሳይተውት ሲያበቁ ሁለቱን እጆቹን ከሰበሩት በኋላ ይሄ ስቃይ ሊደርስበት የቻለው በእህቱ
ምክንያት መሆኑን አስገድደው ካስፈረሙት በኋላ ለቀቁት። ኢማን ይህንኑ ጉዳይ ስዊድን በሚገኘው
አንድ ሬዲዮ ጣብያ ተገኝታ ለአየር አብቅታዋለች። አሁንም አዲስ ደብዳቤ ደረሳት። "ድምጹ ያንቺ
መሆኑን አረጋግጠናል" – ይላል።
ወገኖቼ ምናልባት የለዋወጠችው ስም አብረዋት አምናቸው ከሚሰሩት ንዝህላሎች ወይንም ድብቅ ሰላዮች
ወደ ሶርያ የተላከ ይሆን? - ታድያ ማን ይታመናል? ስለላም ልጆቿን ትበላለች ማለት ነው?
አራተኛ - ማሳሰብያ
በዚህ አጋጣሚ ሁሉም ማህበሮች የአባላትን ስም፣ አድራሻ፣ የሴኩሪቲ መለያዎች የያዙ ሰነዶች፣
ደብዳቤዎች፣ ክሶች፣ ቃለጉባኤዎች ውሳኔዎች በምስጢር መያዝ እንዳለባቸው ምክሬን እለግሳለለሁ።
ዲያስፖራው በቂ የሰው ኃይል ያለው በመሆኑ ይህን ትልቅ አደራ ሊሸከሙ የሚችሉ ሞልተውታል።
በተቻለ መጠን ለዚህ ሥራ የሚታጩት በከፍተኛ ምስጢራዊ ሥራ ላይ ልምዱ ያላቸው ቢሆን መልካም
ነው። በመከላከያና ደህንነት፣ በውጭ ጉዳይ፣ በስደተኞች ጉዳይ ቢሮዎች ወይንም በከፍተኛ አስተዳደር
ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ፣ ምራቃቸውን ዋጥ ያደረጉ፣ የመኖርያ ፈቃዱ ያላቸውና የሀገሩን ልማድና
ወግ የተረዱ ሕግ አክባሪዎች ለዚህ ሥራ ከሞላ ጎደል ብቁ ናቸው። የሚሰሩ ወይም የሚመረጡ ጠፍተው
እምነት የማይጣልበትን ግለሰብ ለመርዳት ሲባል ብቻ ወደ ሲቪክ ማህበሩ ማስጠጋት ውድቀት ያመጣል።
"አለባብሰው ቢያርሱ - በአረም ይመለሱ" - ይህ ዓይነቱ የግብር ይውጣ ሥራ ነው።
ስለላና ስደት በቀኙም በግራውም በኩል ሲቃኝ በኔ ግምት ይህን መሰል ነው። በሙያው የደረጃችሁ ሰዎች
ልታክሉበት ትችላላችሁ።
እግዚአብሄር የአፍሪቃ ቀንዱን የስደት መከራ ይቀርፈው ዘንድ ከልብ እንለምናለን። እኛም ስደቱ
እንዳይስፋፋ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች። አሜን።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar