ኢትዮጵያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ምርት እድገት አሳየች!
አቤ ቶኪቻው
አቶ ሃይለማም ሲፈሩ ሲተቡ ቆይተው ዛሬ የካቢኔ ሹመት ለማደረግ ፓርላማ ብቅ ብለው ነበር አሉ። ይዘዋቸው ከመጡዋቸው ካቢኔዎቻቸው መካከል ሌላ ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ይገኙበታል።
አቶ ሃይለማሪያም ሲያስቡት ሲያስቡት ለአቶ ደመቀ ብቻ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መስጠት አይችሉትም ብለው ሰጉ መሰለኝ…(መሰለኝ ነው ያልኩት) ዛሬ አቶ ሙክታር ከድር እና አቶ ደብረ ፅዮን ገብረሚካኤልን ደጋፊ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው አሹመዋል። በጥቅሉ በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች አሏተው።
እኛ ሹመቱን ከላይ ከላይ የምናየው የመንግስታችን አድናቂዎች “እሰይ ሀገራችን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እድገት እመርታ አሳየች” ብለን ካገኘን ፅዋ ካጣን ደግሞ ግንባራችንን እያጋጨን ደስታችንን እንገልፃናል።
የምር ግን አቶ ሃይለማሪያም ያኔ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ይሰሩ የነበረ ጊዜ እንደው ሰውየው መለስ ሆነውባቸው “ተሸከሙ” ያሏቸውን ሁሉ “እሺ ጌታዬ” ይሏቸው ነበር እንጂ፤ የጫኑባቸው ሸክም በእጅጉ ከብዷቸው ነበር ማለት ነው!? አዎና ይኸው አቶ ደመቀ ሸክሙን አይችሉትም ብለው የጠረጠሯቸው ከራሳቸው ልምድ ተነስተው አይመስልዎትም!?
ሌላው ጥርጣሬ የኢህአዴግ “ፈላጭ ቆራጮች” (ይሄ “ፈላጭ ቆራጭ” የሚለው ቃል ኢህአዴግ ይፈልጣል ይቆርጣል ብሎ ለማሽሟጠጥ ታስቦ የገባ ቃል አለመሆኑን በቅንፍ አሰውቀን እንቀጥል) እና የኢህአዴግ ፈላጭ ቆራጮች አቶ ሃይለማሪያምን ለአንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ አምነው መተው ምቾት አልተሰማቸውም ይሆናል!
ለማንኛውም ዶክተር ቴውድሮስ አድሃኖምን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። ዶክተሩ ከጤና ጥበቃ የተነሱት ጤና ስለነሱ ይሁን ወይስ የውጭ ጉዳዩ ስራ ህክምና ስለሚያስፈልገው አልታወቀም። ሲታወቅ እናወጋዋለን!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar