አዲስ አበባ-የሱዳኖች ሥምምነት

የተቋረጠዉ የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ዘይት ምርት እና ሽያጭ በሁለት ሳምንት ዉስጥ እንዲቀጥል የሁለቱ ሱዳኖች ባለሥልጣናት ተስማሙ።የደቡብ ሱዳን  ባለሥልጣናት ሰሜን ሱዳን ነዳጅ ዘይት ሠርቃብናለች በሚል ሰበብ ባለፈዉ ዓመት ነዳጅ ዘይት ማምረትና በሰሜን ሱዳን ወደብ በኩል መሸጡን አቋርጠዉ ነበር።የሰሜን ሱዳኑ ዋነኛ ተደራዳሪ ኢድሪስ መሐመድ አብደል ጋዲር እና የደቡብ ሱዳኑ አቻቸዉ ፓጋን አሙም ዛሬ አዲስ አበባ ዉስጥ በተፈራረሙት ዉል መሠረት የነዳጅ ዘይቱ ምርትና ሽያጭ በሁለት ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ይጀመራል።ደቡብ ሱዳን በቀን 3 መቶ ሐምሳ ሺሕ በርሚል ነዳጅ ዘይት እያመረተች በሰሜን ሱዳን በኩል ወደ ዉጪ ትሸጣለች።ተደራዳሪዎቹ በየሐገሮቻቸዉ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ ቀጣና ለመመስረትም ተስማምተዋል።በአዲሱ ዉል መሠረት ሁለቱ ሐገራት አዋሳኝ ድንበር ያሳፈሩትን ጦራቸዉን እስከ መጋቢት ማብቂያ ድርስ ከየአካባቢዉ ያነሳሉ።የአወዛጋቢዋ የአብዬ ግዛት እጣ ፈንታ ግን ገና አልተወሰነም።

ዘ ሔግ-የዓለም ፍርድ ቤት ክስና ኬንያ

የዓለም የወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት (ICC) ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በኬንያ ፖለቲከኞች ላይ መሥርቶት የነበረዉ ክስ አሁንም እንደፀና መሆኑን አስታወቀ።ኬንያ ዉስጥ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2007 በተደረገዉ ምርጫ ዉጤት ዉዝግብና ግጭት ለጠፋዉ ሕይወትና ንብረት ተጠያቂ ናቸዉ የተባሉ አምስት የኬንያ ፖለቲከኞች ተከሰዉ ነበር።አቃቤ ሕግ ከተከሳሾቹ በአንዱ በፍራንሲስ ሙሳዋራ ላይ መሥርቶት የነበረዉን ክስ ግን ዋና ምስክሩ መረጃዎችን በማዛባቱ ትናንት ሠርዞታል። የአቃቤ ሕጉ ዉሳኔ የተሰማዉ ባለፈዉ ሳምንት ኬንያ ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ ከተከሳሾቹ መሐል ኡሑሩ ኬንያታ ማሸነፋቸዉ በታወጀ ማግሥት በመሆኑ ሌሎቹም ተከሳሾች ክሱ ይነሳላቸዉ ይሆናል የሚል ግምት አሳድሮ ነበር።ጠቅላይ አቃቢት ሕግ ፋቶ ቤኒሶዳ እንዳስታወቁት ግን ከሙሳዋራ በስተቀር በሌሎቹ ላይ የተመሠረተዉ ክስ አይንሳም።
«በሙሳዋራ ላይ የቀረበዉ ዋና ምሥክር ሊያቀርብ የሚገባዉን በጣም አስፈላጊ መረጃ በማዛባቱና ጉቦ መቀበሉን በማመኑ ምሥክርነቱን ዉድቅ አድርገነዋል።አንድ ነጥብ ግን ፍፁም ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ።ይሕ ዉሳኔ የሚመለከተዉ ሚስተር ሙሳዋራን ብቻ ነዉ።የሌሎቹን ክስ ጨርሶ አይመለከትም።»  ተመራጭ ፕሬዝዳት ኡሑሩ ኬንያታና ምክትል ፕሬዝዳት ዊሊያም ሩቶ ጨምሮ ቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች በሰዉ ልጅ ላይ በተፈፀመ አምስት የወንጀል ጭብጥ ተከሰዋል።ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ለመጪዉ ሐምሌ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቴና-የታገተችዉ መርከብና ሠራተኞቿ ተለቀቁ

የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ከአስር ወራት በፊት አግተዋት የነበረችዉን አንዲት የግሪክ ነዳጅ ዘይት አመላላሽ መርከብ ለቀቁ።የመርከቤቱ ኩባንያ ዛሬ እንዳስታወቀዉ ባለፈዉ ዓመት ግንቦት ላይ ታግታ የነበረችዉ መርከብ ከነሰራተኞችዋ ተለቀቅቃ  ከነበረችበት ሥፍራ ሥሙ ወዳልተገለፀ ወደብ መቅዘፍ ጀምራለች።ኩባንያዉ እንዳስታወቀዉ መርከቢቱ ያሳፍረቻቸዉ አስራ አራት የፊሊፒንስ፥ አስራ አንድ የሕንድ፥ ሁለት የግሪክ እና አንድ የሩሜንያ ዜጎች ሠራተኞችዋ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።አጋቾቹ መርከቢቱን የለቀቁት ገንዘብ ተቀብለዉ እንደሆነ በሰፊዉ ይታመናል። የመርከቢቱ ኩባንያ ግን ገንዘብ መክፈሉን አላረጋገጠም።አልካደምም።መርከቢቱ የታገተችዉ 135 ሺሕ ሜትርክ ቶን ነዳጅ ዘይት ጭና ከኦማን በሥተምሥራቅ አቅጣጫ መቅዘፍ ላይ እንዳለች ነበር።

ሽትራስቡርግ፥-የአረብ ሊግ ጦር ሶሪያን እንዲወጋ እስራል ጠየቀች።

የአረብ ሊግ አባል ሐገራት የሶሪያን መንግሥት ጦር የሚወጋ ጦር እንዲያዘምቱ የእስራኤሉ ፕሬዝዳት ሼሞን ፔሬዝ ጠየቁ።ፔሬዝ ዛሬ ሽትራስቡርግ-ፈረንሳይ ለተሰየመዉ ለአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት ስብሰባ እንደነገሩት የሶሪያዉ ፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ በራሳቸዉ ሕዝብ ላይ ይፈፅሙታል ያሉትን ጭፍጨፋ ለማስቆም አረቦች ጦር ማዝመት አለባቸዉ።በእስራኤሉ ፕሬዝዳት እምነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶሪያን መንግሥት ለመዉጋት የሚዘምተዉን የአረብ ጦር መርዳት አለበት።አንድ የእስራኤል ፕሬዝዳት ለአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት ንግግር ሲያደርግ በሰላሳ ዓመታት ዉስጥ ፔሬዝ የመጀመሪያዉ ናቸዉ።እዚያዉ ሶሪያ ዉስጥ የሶሪያ መንግሥትና አማፂያን የሐገሪቱን ትልቅ ከተማ የአሌፖን አዉሮፕላን ማረፊያ ላለ-ማስያዝና ለመያዝ የሚያደርጉት ዉጊያ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።አማፂያኑ አዉሮፕላን ማረፊያዉን በሚቆጣጠረዉ የመንግሥት ጦር ላይ ዛሬ መጠነ-ሠፊ ጥቃት ቢከፍቱም የመንግሥት ጦር ሰብሮ መግባት ግን አልቻሉም።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና የሶሪያ መንግሥት ጦር ከጦሩ የከዱ ሠላሳ ወታደሮችን መረሸኑን አማፂያኑ አስታወቀ።የሶሪያ መንግሥትን የሚወጉት አማፂያን ዛሬ እንዳስታወቁት የመንግሥት ታማኝ ወታደሮች ከጦሩ ከድተዉ ይጓዙ የነበሩ  ባልደረቦቻቸዉን ደማስቆ አዉሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ይዘዉ ገድለዋቸዋል።የአማፂያኑ መግለጫ በነፃ ምንጭ አልተረጋገጠም።

ለንደን-የፎክላድ ሕዝበ-ዉሳኔ፥ ብሪታንያና አርጀቲና

የፎክላንድ ተጫፋሪ ደሴቶች ነዋሪዎች ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ የሠጡት ድምፅ አመታት ያስቆጠረዉን የብሪታንያ እና የአርጀቲናን እሰጥ አገባ ዳግም ቀስቅሶታል።ነዋሪዎቹ በሰጡት ድምፅ አወዛጋቢዎቹ ደሴቶች በብሪታንያ አስተዳደር ሥር እንዲቀጥል ወስነዋል።ትናንት ማታ ይፋ የሆነዉ ዉጤት እንዳመለከተዉ ድምፁን ከሰጠዉ 1 ሺሕ ስድስት መቶ ሰባ ሁለት ሕዝብ ከሠወስቱ በስተቀር ማለት 99.8 ከመቶዉ ደሴቶቹ በብሪታንያ መገዛታቸዉን ደግፈዋል።የደሴቶቹ አገረ-ገዢ ኒግል ሐይዉድ አርጀቲና የሕቡን ዉሳኔ እንዳታከብር ጠይቀዋል።
«በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሕዝብ ተሳትፏል።የተሰጠዉ ድምፅ ለኔም ጭምር አስደናቂ ነዉ።ፍፁም አወንታዊ ነዉ።ለዓለም ሐገራት የሚያስተላልፈዉም መልዕክት አርጀቲና ወደናንተ መጥታ ደሴቶቹ ይገቡናል ሥትላቸዉ የእነዚያ ሐገራት መልስ የለም (ይሕን ጥያቄ) አቁሚ የሚል መሆን አለበት።»
አርጀቲና ግን የሕዝበ-ዉሳኔዉን ሒደትና ዉጤት አልተቀበለችዉም።በብሪታንያ የአርጀቲና አምባሳደር አሊሲያ ካስትሮ እንዳሉት ድምፃቸዉን የሰጡት ነዋሪዎች ብሪታንያዊ መሆናቸዉን የከደ የለም።የያዙት ግዛት ግን የአርጀቲና ነዉ።የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካምሩን ባንፃሩ «አርጀቲና የደሴቶቹ ነዋሪዎችን ዉሳኔ ማክበር አለባት» ብለዋል።አዲሱ ዉዝግብ የተነሳዉ ብሪታንያ እና አርጀቲና በደሴቲቱ ይገባኛል ሰበብ የተወጋቡት ሠላሳኛ ዓመት በታሰበ ማግሥት መሆኑ ነዉ። አርጀቲናዎች ላስ አይስላስ ማልቪነስ የሚሏቸዉን ተጫፋሪ ደሴቶች ብሪታንያ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ከ1833 ጀምሮ ትገዛቸዋለች።

ፓሪስ እና የተለያዩ-ሰሜን ምዕራብ አዉሮጳ በበረዶ ተመታች

የሠሜን ምዕራብ አዉሮጳ ሐገራትን የመታዉ ወቅቱን ያልጠበቀ የበረዶ ወዠቦ የበርካታ ሐገራትን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ አጉሎት ዋለ።ከትናንት ማታ ጀምሮ በተለያዩ ሐገራት ሲጥል አድሮ፥ ዛሬም ሲጥል የዋለዉ በረዶ የፍራክፈርቱን አዉሮፕላን ጣቢያን፥ፓሪስን ከለንደን የሚያገናኘዉን የባቡር መስመርን እና በርካታ የመኪና አዉራ መንገዶችን አዘግቷል።የፍራንክፈርቱ አዉሮፕላን ማረፊያ ከአዉሮጳ ሰወስተኛዉ ባተሌ አዉሮፕላን ማረፊያ ነዉ።የፓሪሶቹ ሻርልስ ደጎል እና ኦርሌይ አዉሮፕላን ማረፊያዎችም በረራዎችን በግማሽ ሠርዘዉ ነዉ የዋሉት።ፈረንሳይ፥ ጀርመን፥ ብሪታንያ፥ ቤልጂግ እና ኔዘርላንድስ ዉስጥ በርካታ የኤሌክትሪክ መስመሮች ተቋርጠዋል፥ የከተማ ዉስጥ የባቡርና የአዉቶብስ አገልግሎቶች ተዛብተዋል።በርካታ የምኪና አድጋ ድርሷልም።በልማዱ የሰሜኑ ንፍቀከ ክበብ ክረምት ካንድ ሳምንት በሕዋላ ማብቃት ነበረበት።አሁን ከመሸ የፍራንክፈርት አዉሮፕላን ማረፊያ በከፊል ሥራ መጀመሩ ተዘግቧል።