lørdag 5. januar 2013


የሃይለማሪያም ደሳለኝ የፓርላማ ውሎ አውዛጋቢና በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችም ያጣጣሉት እንደነበር ታወቀ

ወያኔዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለ ማሪያም ደሳለኝ ባለፈዉ ማክሰኞ ታህሳስ 23 ቀን 2005 ዓም አሻንጉሊት ፓርላማዉ ዉስጥ ተገኝቶ ከፓርላማዉ አባላት የቀረበለትን ጥየቄዎች ሲመልስ ብዙ ግራ የሚያጋቡና አወዛጋቢ መልሶች መስጠቱንና በምርጫ ዙሪያ የሰጠውን መልስ መሰረታዊ የሚባሉት የፖለቲካ መብቶች ካልተሟሉ በምርጫው አንሳተፍም በማለት አቋም የያዙት በሃገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉት 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማጣጣላቸውን የዕለቱን የፓርላማ ዉሎ የተከታተለው ዘጋቢያችን በላከልን ዜና ገለጸ።
በያዝነዉ ወር አጋማሽ ላይ በኤርትራ ጉዳይ ከአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረገዉ ቃለምልልስ ላይ በሰጣቸዉ የመላምት መልሶች ከፍተኛ ትችት የደረሰበት ሀይለማርያም ደሳለኝ ባለፈዉ ማክሰኞ በእነዚሁ በተተቸባቸዉ ጉዳዮች ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሲሰጥ ዉሏል። በተለይ ከኤርትራ መንግስት ጋር ለመደራደር አስመራን ጨምሮ ዬትም ቦታ ለመሄድ ፈቃደኞች ነን ብሎ የተናገረዉን ንግግር በተመለከተ የቀረበለትን ጥያቄ ሲመልስ አስመራ እሄዳለሁ ያልኩት በየትኛውም ቦታ እንደራደራለን የሚለውን የመንግስት አቋም አጽንኦት ለመስጠት ነዉ ሲል ተናግሯል።
ወያኔዎች እንደ ግል ቤታቸዉ በሚቆጣጠሩት የኢትዮጵያ አሻንጉሊት ፓርላማ ዉስጥ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አስመራ ድረስ በመሄድ ከኤርትራ ጋር ለመደራደር እንደሚፈልጉ ከገለጹ፣ ለእኛ ለተቃዋሚዎችም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመነጋጋር ቢሮውን ክፍት ያድርጉልን” የሚል ጥያቄ ለይለማርያም ደሳለኝ  ሲያቀርብ አብዛኛዉን ግዜዉን በሳቅና በቧልት የሚያጠፋዉ ፓርላማ እንደ ተለመደዉ ቢስቅም ሀይለማሪያም ደሳለኝ ግን ለዚህ የሀዝብ ጥያቄ ተገቢዉን ምላሽ ሳይሰጥ አልፏል።
ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ የተሾሙትን ሁለት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ሁለቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ህጋዊ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሳይሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ማእረግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የሚሰሩ ናቸው በማለት አገሪቱ ያላት አንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ መሆኑንና እሱም  ደመቀ መኮንን መሆኑን ተናግሯል። ቀድሞዉንም ቢሆን ሁለት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች መሾም ያሰፈለገዉ የኦህዴድን አፍ ለማስዘጋት ስለነበር ሀይለማርያም ደሳለኝ  አገሪቱ ያላት አንድ ህጋዊ አንድ ም/ል ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ መሆኑን በግልጽ መናገሩ በህወሀት እና በኦህዴድ ውስጥ ቀደም ብሎ የነበረው የጥላቻና ያለመግባባትና ያለመተማመን ስሜት እንደገና ሊያገረሽበት እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
ሀይለማርያም ደሳለኝ በአገሪቱ ዉስጥ ስለደረሰዉ ከፍተኛ የጤፍ እጥረት ሲያስረዳ በኢትዮጵያ የተፈጠረው የጤፍ እጥረት ጤፍ በልቶ የማያውቀው ህዝብ ጤፍ መብላት በመጀመሩ ነው በማለት ከጌታዉ ከመለስ ዜናዊ የተማረዉን መልስ ሰጥቷል። ከዚህ ቀደም መለስ ዜናዊ የስኳር ዋጋ የተወደደው አርሶ አደሩ ስኳር መብላት በመጀመሩ ነው የሚል የቅጥፈት ጥግግር ማድረጉ ይታወሳል። በመጨረሻም ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ  የለም የሚል አደናጋሪ ንግግር በማድረግ ክርስቲያን በመሆኔ አልዋሽም ሲል የነበረዉ ሀይለ ማሪያም ደሳለኝ ዉሸት ብቻ ሳይሆን ክህደት የሞላበት መልስ በመስጠት  የዕለቱን የፓርላማ ዉሎዉን ጨርሶ ወደ ቤተመንግስቱ ሄዷል።
ሃይለማሪያም ደሳለኝ እንደመለስ ዜናዊ “ተቃዋሚዎች በመጪው የአካባቢ ምርጫ የማይሳተፉት ከምርጫው በሁዋላ የሚያስገኘው ጥቅም ስለሌለ  ነው” በማለት ለአሻንጉሊቱ ፓርላማ ምክር ቤት አባላት የተናገረውን በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ተቃዋሚዎች አጣጥለውታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ መሰረታዊ የሚባሉት የፖለቲካ መብቶች ካልተሟሉ በምርጫው አንሳተፍም በማለት አቋም የያዙት 33 የፖለቲካ ድርጅቶች ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አስራት ጣሴ ተቃዋሚዎች በምርጫ የሚሳተፉት ለጥቅም ብለው ሳይሆን ምርጫ የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሂደት በመሆኑ ነው ማለታቸውን ተያይዞ የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። በአዲስ አበባ እና አካባቢ ምርጫ መሳተፍ ጥቅም ከሌለው የትኛው ምርጫ ነው ጥቅም ያለው በማለት የጠየቁት አቶ አስራት በምርጫ 2002 ምርጫ ቦርድ የሰጣቸውን ገንዘብ መልሰው መላካቸውን በምሳሌነት የጠቀሱ ሲሆን በአንጻሩ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ደግሞ ተቃዋሚዎች በምርጫው አብረውት ቢሮጡም ባይሮጡም ለውጥ እንደሌለው መናገሩን የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar