torsdag 10. januar 2013

የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች የተግባር ድክመት ወይንስ የግብና እቅድ ልዩነት

የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች የተግባር ድክመት ወይንስ የግብና እቅድ ልዩነ


(አንዱ ዓለም ተፈራ)
January 10, 2013 08:51 am By Editor Leave a Comment
“የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በድረ-መለስ ኢትዮጵያ፣ ርዕዩተ ዓለምና የትግል ግብና ዕቅድ ሁኔታዎች” በሚል ርዕስ አቶ ጋሻው ዓለሙ ጥሩ የመወያያ ሃሳብ አቅርበውልናል። ማለፊያና ብዙ የምስማማባቸውን ነጥቦች የያዘ በመሆኑ፤ ላመሰግንና ድጋፌን መስጠት እፈልጋለሁ። መቼም ብዕሬን ያነሣሁ ተስማምቻለሁ ለማለት ብቻ አይደለም። የተስማማሁባቸውን መደረቱም አንባቢን ማድከም ነው። የማቀርበው ለየት ያለ አቀራረብ ሊኖረው ይገባ ነበር ያልኳቸውን ላመላክት ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ በኔ በኩል ድክመት ሳይሆን ልዩነት ነው ያለው። በርግጥ በተለያዬ መልክና ቦታ ይኼ ጉዳይ በጽሑፉ ውስጥ ተጠቅሷል። ነገር ግን ማዕከላዊ ቦታ መያዝ የሚገባው ጉዳይ ተለጣፊ በመሆን ቀርቧል ባይ ነኝ።
እንዲህ ነው።
የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎችን አንድ ተግባር እንዲፈፅሙ እንፈልጋለን። ይኼም ተግባር የዘረኛውን አምባገነን የወያኔ ቡድን አስተዳደር አውርደው በቦታው ለሕዝብ ተጠሪ የሆነ መንግሥት እንዲያቋቁሙ ነው። ይህ ተግባር እንግዲህ፤ ተግባሩ ምን እንደሆነ፤ ለምን መፈፀም እንዳለበትና እንዴት መፈፀም እንዳለበት የተስማሙ አካላት እንዳሉና እንደተነሱ መቀበልን ግድ ይላል። ከዚህ በኋላ ሳይፈፅሙት ሲቀሩ፤ ድክመት አለ ብለን መናገር እንችላለን። አለበለዚያ ሌላ ጉዳይ አለ ማለት ነው። ለኔ ሌላው ጉዳይ ልዩነት ነው።
ልዩነት፤ በተግባሩ ላይ ልዩነት ካለ፤ ያልተፈፀመው በልዩነቱ ምክንያት እንጂ፤ በድክመት አይደለም።
ልዩነት – ሀ፤ ወያኔ፤ ለዘመናት በሀገራችን በገዥዎችና በሕዝቡ መካከል የነበረውን መሠረታዊ የፖለቲካ ቅራኔ አሽቀንጥሮ ጥሎ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ሕዝቡን በትውልድ ከፋፍሎ፣ አንዱን ጠላት አድርጎ በማስቀመጥ፤ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሂደት መሥርቷል። ከዚህም ተነስቶ አስተዳደሩን በክፍፍሉ መሠረት ጠንስሶ፤ አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን የበይ ተመልካች አድርጓል። ይህ ደግሞ የሚከተሉንን ትውልዶች ለማያባራ አይቀሬ የርስ በርስ ትልቅልቅ አመቻችቷቸዋል።
ይኼን ሀቅ ለመቀልበስና ቀጣይ ትውልዶችን ከዚህ አይቀሬ መተላለቅ ለማዳን፤ ወያኔ ከነሥርዓቱ መወገድ አለበት። የሚያስወግደው ኃይል፤ ይኼን መሠረታዊ መነሻ በትግሉ ያዋኻደ መሆን ይገባዋል። ስንቱ ነው ከተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች መካከል ይኼን የተቀበለ? ስንቱስ ነው የማይቀበል? የሚቀበሉና የማይቀበሉ ካሉ፤ ታዲያ እንዴት እኒህ ተቃራኒዎች ባንድነት ሊቆሙ ይችላሉ?
ልዩነት – ለ፤ ወያኔ ተወግዶ የሚተካው የሕዝብ ተጠሪ መንግሥት፤ ወያኔን ከነሥርዓቱና ከነመመሪያው የሚያስወግድና የሕዝቡን ፈቃድ በማንኛውም ተግባር ጠያቂ መሆን አለበት። ይኼን የሚያደርግ ክፍል፤ በድርጅታዊ መርኀ ግብሩ ላሠፈረው አጀንዳ ሳይሆን፤ ሕዝቡ ለሚጠይቃቸው ጉዳዮች ተገዢ መሆን አለበት። ባሁኑ ሰዓት፤ ያሉት የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በየአጀንዳዎቻቸው ተጠቅልለው በመሠረታዊ ሀገር አቀፍ ጉዳዮች ላይ ስምምነት መድረስ ያቃታቸው ናቸው። ታዲያ እንዴት እነኚህ ክፍሎች የሕዝብ ተጠሪ መንግሥት ሊያቋቁሙ ይችላሉ?
መወንጀል ብቻና እጅን መተጣጠቡ ከታጋይ ወገን ነኝ ከሚል አይጠበቅም። መንገድ ማሳየት ግዴታ አለብኝ። እስኪ እነኝህን የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በሚከተሉት አምስት ጉዳዮች ላይ እያንዳንዳቸው መልስ ይስጡባቸው። እኒህ አምስት እሴቶች፤ ከግለሰብና ከድርጅት በላይ ሀገራዊ ናቸው። መልሳቸው አብረው መሥራት ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ይነግረናል። ልዩነት ከሌላቸው፤ ስህተቴን ተቀብዬ ልክ ልገባ ቃል እገባለሁ።
፩ኛ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብን አንድነት በተመለከተ፤ አንድ ሕዝብ ነን ወይንስ አይደለንም?
፪ኛ፤ ሀገራችንን በተመለከተ፤ ኢትዮጵያ፤ የቆዳ ስፋቷና ክልሏ ተጠብቆላት፤ አንድ ሀገር ናት ወይንስ አይደለችም?
፫ኛ፤ የዴሞክራሲያዊ መብትን በተመለከተ፤ እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት፤ የግለሰብ መብቷ ተከብሮላት፣ በየትኛውም የሀገሪቱ ክልል ሠርታ የመጠቀም፣ መኖሪያ የማበጀት፣ ሀብት የማፍራት፣ በኢትዮጵያዊነቷ (ከሃይማኖትና የዘር ትውልድ ባልተዛመደና ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ በማያገልል መንገድ) ከመሰል የአስተሳሰብ አንድነት ካላቸው ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች ጋር የፖለቲካ ተሳትፎዋን ማድረግ የምትችልበት እንድትሆን ነው ወይ ትግሉ?
፬ኛ፤ የሕግ የበላይነትን በተመለከተ፤ ከግለሰቦችና ድርጅቶች ውጪ፤ በሕገ ደንብና አሠራር ለመገዛትና ለመተማመን ነው ወይ የምንታገለው?
፭ኛ፤ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በተመለከተ፤ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ጠላት ዘረኛው አምባገነን የወያኔ አስተዳደር ነው። ይህ መንግሥት ሊታረም የማይፈልግና የማይችል ነው። ይህን መንግሥት መወገድ አለበት ወይስ የለበትም?
በሌላ በኩል፤ የተቃዋሚ ኃይሎች ልሂቃን ያቀረቡት፤ “አሁን ያለውን ሥርዓት ለመታገል፤ የአሁኑ ትውልድ ሀገራዊ ፍቅርም ሆነ ወኔ ያንሰዋል።” ማለታቸው በጣም አሳዝኖኛል። የተለመደ አባባል አለ። “በኛ ጊዜ ሁሉ ወርቅ ነበር። ያሁኖች ልጆችማ አይረቡም።” የሚለው። ይኼ ከትውልድ ትውልድ እንደቅርስ የሚተላለፍ ነበር፤ ነውም። እኒህ ልሂቃን የመከራከሪያ ሃሳባቸው መሠረተ ቢስና ቁንፅል፤ ባጠቃላይም ደካማ አስተሳሰብ ነው።
በመጀመሪያ ነገር፤ ትውልድ ሲባል የወቅቱን ጠቅላላ የሀገሪቱ ተወላጆች ያጠቃልላል። እናም የትናንቱ ትውልድ ሲሉ፤ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ መላኩ ተፈራ፣ አሊ ሙሳ፣ ግርማ ከበደ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ንግሥት አዳነ፣ ኃይሌ ፊዳ፣ መለስ ዜናዊና አረጋዊ በርሄን ባንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጥላሁን ግዛው፣ ሻምበል ሞገስ ወልደሚካኤል፣ ማርታ መብራቱ፣ ባቢሌ፣ ይካተቱበታል። እናም ገዳይም ተገዳይም፣ ተራማጅም አድሃሪም፤ ሁሉንም ያካተተ ነበር። እኔም የዚሁ ተጠቃሽ ትውልድ አባል ነኝ። መቼም ዘመኑን የመከለል እንጂ፤ መርጠን ይኼ ነው የዚያ ትውልድ የሚባለው ይኼኛውን አንፈልገውም የሚባልበት ትውልድ አመካከል አይፈቀድልንም። ታዲያ በምን መንገድ ነው የትናንቱ ትውልድ ከዛሬውና ከነገው ትውልድ የሚለየው?
ማንም ትውልድ የወቅቱን የኅብረተሰብ ሀቆች ተከትሎ፤ ወግኖ የወቅቱን መፍትሔ ከወንዝ ወዲያና ወዲህ በመሆን ይጋፈጣል። ለትውልዱ መፈራጃ የሚሆኑት፤ የወቅታቸው የኅብረተሰብ ክንውኖች እንጂ፤ በዘመናቸው ያልተከሰተ ኩነቶች አይደሉም። ትናንት ከወያኔ ጋር ተጋፍጣ ሕይወቷን የሰጠችው ሽብሬ ደሳለኝ ቁጥሯ ከነበላይ ዘለቀ ነው። ለምን ቢባል፤ በነበረችበት የታሪክ ወቅት፤ የኅብረተሰቡ ችግር የሆነውን ተጋፍጣ ሕይወቷን ሰጥታለችና። ታዲያ የሽብሬ ደሳለኝን ትውልድ ነው ወኔ የለውም የምንለው? በጣሊያን ጊዜ የታገሉት እነበላይ ዘለቀ፤ ታሪክ በወቅታቸው ያጋፈጣቸውን ግዴታ ፈፅመዋል። በዘመናቸው ባንዳዎች እንደነበሩ ሁሉ፤ ዛሬም ጫማ ላሾች አሉ። ሀቁ ግን፤ ወጣቱ ከማናቸውም ባላነሰ መልኩ እየታገለ፤ መሪ በማጣቱ ነው፤ ትግሉ በምንወደው ፍጥነት ወደፊት መሄድ ያልቻለው። ትግሉ እየተካሄደ ነው። የዛሬው ትውልድ ታሪካዊና ትውልዳዊ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው። የጎደለው ተመክሮ ያላቸው አዛውንቱ መምራት ስላልቻልን ነው። ተጠያቂ ከተፈለገ፤ አሁንም ለማስመር ያህል፤ ተጠያቂው የአሁኑ ትውልድ ሳይሆን፤ አንድም ባለማውረስ፤ ሌላም የራስን ድርሻ ባለመወጣት አዛውንቶቹ ነን።
አንድ ሌላ ያልተቀበልኩት ነጥብ አለ። “መሠረታዊ የትግል ስልት ሊመራ የሚገባው በሰላማዊና ህጋዊ ማዕቀፍ ሊሆን ይገባዋል።” ይላል ጽሑፉ። የትኛውና የማን ህግ ተጠቅሶ ነው? በዝርዝርም የትግሉ ትጥቅን ማካተት አፍራሽነት ሠፍሯል። ትግል እኮ በጠላትነት ፈርጀውት በሚታገሉት ኃይልና ሊያቸንፉ በሚፈጉት ክፍሎች ጥንካሬ የሚተረጎም እንጂ በቀኖና ቋሚ የሆነ ቅፅ የሚከናወን አይደለም። እያንዳንዱ ትግል የራሱ የሆኑና ሁሉን አቀፍ የሆኑ ባህርይ አሉት። ሁሉን አቀፍ ባህሪዎቹ አጠቃላይ አቅጣጫውን ሲያመለክቱ፤ የራሱ የሆኑት ባህሪዎቹ ደግሞ፤ የራሱን የመፍትሔ መንገድ ይወስናሉ። ጠመንጃ ያነሳ ሁሉ አይወገዝም። ለወረራ፣ ለቅኝ ገዥዎች፣ ለፍፁም አምባገነኖች የሚደረጉ ትግሎች፤ የአመጻቸው መንገድ ግዴታ ትጥቅን ይላል። እንደኛ ባለው ሀገር የሚካሄዱ ትግሎች ችግራቸው፤ ትጥቅ ማንሳታቸው ሳይሆን፤ ትጥቁን ያነሳው ክፍል ምን ያህል ሕዝቡን ያቀፈና ብዙኀኑን ያካተተ መሆኑ ላይ ነው። አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ ማንም አንድ ድርጅት ትጥቅ ቢያነሳ፤ ጉልቻ መቀያየር መሆኑን እጋራለሁ። ነገር ግን፤ ብዙኀኑ ሀገራዊ የሆኑት ክፍሎች ተሰባስበው የሚመሩትን የትጥቅ ትግል፤ የማልኮንነው ነው።
ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ፤ “ስለዚህ የተቃዋሚዎች ውስጣዊ ድክመቶችና የገዥው ቡድን ሁለንተናዊ የበላይነት ጋር ተዳምሮ ተቃዋሚዎች በመርህ ላይ የተመሠረተ ያጋራ ትብብር መፍጠር እንዲችሉ አግዷቸዋል።” የሚለው ሠፍሯል። ለኔ ያገዳቸው ጉዳይ፤ ያላቸው አቋም የተለያየ መሆኑ ብቻ ነው። ወያኔን ለማውረድ የሚፈልጉት ለተለያየ ግብ ስለሆነ፤ በምንም መንገድ አንድ ላይ ሊሰባሰቡ አይችሉም። ባንድ ላይ ካልተሰባሰቡና ላንድ ዓላማ፤ ባንድ ካልቆሙ፤ የውጩ ኃይል ሳይሆን፤ የውስጣቸው ጉዳይ ብቻ ነው ተጠያቂ እላለሁ።
(ይህ ጽሁፍ አቶ ጋሻው ዓለሙ፡ “የተቃዋሚፖለቲካኃይሎችበድረ-መለስኢትዮጵያ፣ርዕዩተ ዓለምና የትግል ግብና ዕቅድ ሁኔታዎች” በሚል ለጻፉት መልስ ነው)
ታህሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፭ ዓመተ ምህረት

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar