የመልስ ምት ለመለስ ሌጋሲባለ አደራ
የኢትዮጵያ ገበሬ በማዳበሪያ እዳ ምክንያት ዘሩን ቆልቶ በበላበት ፣ መሬቱ ለውጭ ዜጎች በተሸጠበት ማግስት እና ለፖለቲካ መጠቀሚያ ያደረገውን የውጭ እርዳታ ስንዴ ጠባቂ በሆነበት ወቅት የመለስ ሌጋሲን ለማስቀጠል የተመደቡት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በሳቂታው ህዝብ ተወካዮች ተብየው ፓርላማ ውስጥ በ 23-ታህሳስ -2005 የኢትዮጵያን ህዝብ በአደባባይ ‘ጤፍ በልቶ የማያውቀው ህዝብ ጤፍ መብላት ስለጀመረ ‘ የጤፍ ዋጋ መናር እንዲሁም የጤፍ ምርት እጥረት ተከሰተ ብለው ሲሳደቡ፤ የህዝብ ተወካይ የሚባለው የሻንጉሊት ስብስብ የህዝቡ እና የታሪክ ባይተዋር እንደሆኑ በዝምታችው አስመሰከሩ ።
በጣም የሚያሳዝነው የሃገራችን ህዝብ በአደባባይ በጠራራ ፀሃይ በተሰደበበት ወቅት ማልቀስ የሚገባቸው አሻንጉሊቶች አንድ ለእናቱ የሆኑትን የተቃዋሚ ተወካይ አግባብ ያለው ጥያቄ ሲጠይ እንደለመዱት የጣር ሳቅ አሰሙ ።
ኧረ ለመሆኑ አቶ ሃይለማርያም ከቀድሞው ሟች ጠቅላይ ሚንስቲር ታሪክን የማበላሸት ብሎም በአደባባይ የኢትዮጵያን ህዝብ መዋሸት እና መሳድብ ወርሰው እንጂ በአደባባይ ህዝቡን በንቀት የሚሳደቡት የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም በላይ እየተሰቃየ እየታረዘ የሚገኝበት ወቅት ነው ፤ አምናለሁ ባለ ሌጋሲው ጠቅላይ ሚንስቲር እንዳሉት ፤ ይህ አፋኝ መንግስት ወደ ስልጣን ከወጣ በኋላ የሕወሃት አባል ብሎም ቤተሰቦች ጠግበው ጤፍ እንጀራ አማርጠው ከመብላት አልፈው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጉሮሮ በመቀማት ወደ የተለያየ የአለማችን ክፍል ጤፍን በጥሬው ወይም በእንጀራ መልክ በማላክ ሚሊየነሮች እንደሆኑ ።
ለሌጋሲው ባለ አደራ አንድ ጥያቄ አለኝ ። ኧረ ለመሆኑ አንድ ኮንታል ጤፍ ከ400 ብር በታች እያለ ጤፍ መብላት ያቃተው በጡረታ የሚተዳደረው ሚስኪን ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ፣ በዝቅተኛ ደመወዝ የሚተዳደረው የመንግስት ሰራተኛ ሌላው ምንም ገቢ የሌለው የኢትዮጵያ ህዝብ ገቢው ሳይጨምር ጤፍ መብላት አቃተው ነው ወይስ መብላት ጀመረ ነው የሚባለው ? ይህን ሁሉ ብስለት የሌለው ንግግር እንዲናገሩ ያነሳሳቸው በቤተ መንግስት እና በህወሃት ቤተሰቦች ዘንድ ያለ አግባብ የተገኘውን ስር ነቀል የኢኮኖሚ እድገት የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስመሰል ሲሞክሩ ነው ። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ስቃይ ማየት እንዳይችሉ ፤ እውነታውን ቢያውቁም ፣ መናገር እንዳይችሉ በቀድሞው ሟች ጠቅላይ ሚንስቲር ስም ያስማላቸው ሃይል አለ እንዴ ?
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት ጤፍ መብላት የጀመረው በአምባገነኑ የወያኔ ጨቛኝ መንግስት እየተሰቃየ ያለው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ፤ ለሆዳችው ያደሩ ሆድ አደሮች ፣ባንዳ የባንዳ ልጆች ፣ ጥቂት ዘረኛ የአንድ ብሄር ተወላጆች እና ከዚህ ድርጅት ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ግለሰቦች ጤፍ እንደልባችው ያልበሉበትን ያንን ጊዜ ለማካካስ በሚመስል ሁኔታ እያማረጡ መብላት ጀመሩ ማለት ይቻላል ።
ለነገሩ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስቲር ቀደም ብለን ብዙ ኢትዮጵያዊያኖች እንደተናገርነው ከእባብ እንቁላል እርግብ እንደማይገኘው ሁሉ ከኚህ ግለሰብ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስቲር የተለየ ነገር መጠበቅ የዋህነት ብቻ ሳይሆን ጅልነትም ነው። የገዡ አምባገነን መንግስት ተቃዋሚዎች በሙሉ ስለ ሃገራችን ጉዳይ እንደራደር ፣ብሔራዊ እርቅ ይኑር እያሉ በሚጠይቁበት በዚህ ሰኣት በንቀት ጀርባ የሰጠው ዘረኛ አምባገነን ፤ ከኤርትራ መንግስት ጋር አስመራ ድረስ በመሄድ ለመደራደር ዝግጁ እንደሆነ ሲናገሩ ሰምተናል ።
ልብ ያለው ልብ ይበል ይህ ቡድን በማይገባው እና ህዝቡን ያላሳተፈ ሰላማዊ ትግል ውጤታማ እሆናለሁ ብሎ ከመጠበቅ ይልቅ ፤በሚገባው ቛንቛ ማናገር ወይም ለድርድር እንዲበረከክ ማድረግ አማራጭ የሌለው አማራጭ ይመስለኛል። በማንኛውም ሁኔታ ለሚደረገው ሰላምዊ ትግል ለገፈት ቀማሹ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ ማቅረብ እና በህዝብ የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል ውጤታማ እንዲሆን ማታገል ከተቃዋሚ መሪዎች የሚጠበቅ ይሆናል ። በጣም የሚገርመው በሃገርቤት የሚገኙ ተቃዋሚዎች ህዝቡን ሰብስበው ማወያየት እንኳን አይችሉም ። ድንቄም ዲሞክራሲ ።
አንድ ቀልደኛ ጓደኛዬ በመለሰልኝ መልስ ልሰናበታችሁ የእኔ ጥያቄ የነበረው የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ህዝብን ሰብስበው ማወያየት በገዡ ቡድን የማይፈቀድላቸው ከሆነ ፣ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥ ስለ ፓርቲያቸው ማስተዋወቅ የማይችሉ ከሆነ ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ተቃዋሚዎች መቼ እና የት ይሰማል ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ የሚከተለው ነበር
1. ለወያኔ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሆነው ‘የምርጫ ቦርድ ‘ስለ ምርጫ ሁኔታ እንደ ገለልተኛ አካል በገዡ መደብ ላይ ክስ ሲመስርቱ
2. የተቃዋሚ መሪዎቻቸው በሃሰት ተከሰው እና በሃሰት ተመስክሮባችው በካንጋሮው ፍርድ ቤት ተፈርዶባችው እንዲሁም የሸባሪነት ታርጋ ተለጥፎባቸው ከርችሌ ሲወረወሩ ብሎ አስደምሞኛል ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar